የእለት ዜና

ትኩረት የሚሻው የወንዶች አጋርነት

ሰው መሆን ሁሉን ይበልጣል፤ ሰው መሆን ይቀድማል። ጾታ፣ ሀይማኖት፣ ብሔርና ዘር ወዘተ ሰውነትን መሠረት ያደረጉ እንጂ ከሰውነት በላይ የሆኑ አይደሉም። ስለስርዓተ ጾታ ጉዳይ ተነስቶ የሴቶችና የወንዶች እኩልነት ሲባልም ስለሰዎች እኩልነት እየተነገረ መሆኑ እሙን ነው። የሰው ልጅ ሁሉ እኩል ነው በሚለው ሐሳብ የሚስማማ ሰው፣ ይህ እኩልነት የትኛውም ዓይነት ልዩነትና ብዝኀነት ተጽእኖ የማያሳድርበት መሆኑን ያውቃል፤ ይረዳል።

እንግዲህ በጠቅላላው ስለ ሴቶች መብት እንዲሁም እኩልነት ስናነሳ የሰው ልጆችን እኩልነት ጉዳይ እያነሳን ነው ማለት ነው። በዚህ መሠረት ታድያ ይህ የእኩልነት ጉዳይ የሁሉንም ሰው አጋርነት የሚፈልግ መሆኑ ለክርክር አይቀመጥም።
የሴቶች መብት በሴቶች ብቻ የሚመጣ የሚመስላቸው ይኖራሉ። ሴቶች በማኅበር መደራጀታቸው፣ ንቅናቄ መፍጠራቸው፣ መታገላቸው ወዘተ ብቻውን ለውጥ ያመጣል ብሎ ማሰብ ከባድ ነው። እኩልነትን አጀንዳ ያደረገ የሴቶች እንቅስቃሴም ወንዶችን በማሳነስና በማውረድ ወይም በማቃለል ውጤት ለማምጣት ቢሞክር ዋጋ አይኖረውም።

የእኩልነት ጥያቄ ሌላ የእኩልነት ጥያቄን እንዲፈጥር አይገባም። የወንዶች የበላይነትን በሴቶች የበላይነት መተካት ወይም በወንዶች ታይተው የተነቀፉ ምግባራትን ወደ ሴቶች ማዞርና መድገም የእኩልነት ማሳያዎች አይደሉም። ግን ሴትም ወንድም በማንኛውም ጉዳይ ላይ እንደ ሰው ማሰብ፣ ማስተዋል፣ ማመዛዘንና መወሰን የሚችል አእምሮ የታደሉ መሆኑን መገንዘብ እኩልነትን በሚገባ ይገልጻል።

ይህ ታድያ ከወንዶች በተቃራኒ አቅጣጫ ላይ በመቆም ሳይሆን አብሮ በመሰለፍ ሊመጣ የሚችል ነው። ሴቶች ፖለቲካውን ጨምሮ በተለያዩ አገራዊ ጉዳዮች እንዲሁም ባላቸው ፍላጎት እና ተሰጥኦ መሠረት መሳተፍ በሚችሉባቸው መስኮች ተሳታፊ እንዲሆኑ ከራሳቸው ጥረት በተጓዳኝ የወንዶች አጋርነት ያስፈልጋቸዋል። አጋር መሆን የመብለጥ ወይም አጋርነትን መጠየቅ የማነስ መገለጫ አይደለም፤ የተፈጥሮና በብዝኀነትና በልዩነት የመፈጠር ውጤት የሆነ የሙላት ኃይልና አቅም ነው።

ጥናቶችና ዓለማቀፍ ልምዶች እንደሚነግሩን የፖለቲካ ውሳኔ ሰጪነት የተሻለ ውጤት እንዲያመጣ የጾታ ተዋጽኦ ከፍተኛ ድርሻ አለው። ሴቶች በአካባቢያዊ እንዲሁም አገራዊ ጉዳዮች ላይ የሚኖራቸው ሱታፌም የዴሞክራሲ ግብረ መልስን እንደሚያሻሽለው ይታመናል። ሆኖም እንደሚታወቀው አሁንም የሴቶች የፖለቲካ ተሳትፎ አጥጋቢ ደረጃ ላይ አልደረሰም።

ይህን ማሳከት የሚቻለው ወንዶች ከሴቶች ጋር ጎን ለጎን ሆነው የሴቶችን እኩል ተሳትፎ የሚጻረሩ አጉል ባህላዊ አመለካከቶችን በማስወገድ፣ ጉዳዩ የሰው ልጅ የእኩልነት ጉዳይ መሆኑን በማመን በጋራ መሥራት ሲችሉ ነው። ተጽእኖ መፍጠር የሚችሉ በየኃላፊነቱ ያሉ ወንዶች አጋርነትም እጅግ አስፈላጊ ነው።

በከፍተኛ የትምህርት ተቋማት ‹የወንዶች አጋርነት› ከሴቶች እንቅስቃሴ ጋር እንደ አንድ ዐቢይ ክፍል ሆኖ ሲንቀሳቀስ ይታያል። ይህም ሴቶችን ከጥቃት የመጠበቅ፣ ‹የእህቴ ጠባቂ ነኝ› የሚለውን ጉዳይ በተግባር የመግለጥ እንዲሁም ከምንም በላይ ደግሞ የሰውን ልጅ እኩልነትና ሰብአዊ መብት የማክበርና የማስከበር ዓላማ ያለው ነው።

እናም የሴቶች የእኩልነት ጥያቄና መብትን የማስከበር ትግል የሚደረገው ከወንዶች ጋር እንዳይደለ ልብ ማለት ያሻል። የወንዶች አጋርነት የሚያስፈልገውም ለዚህ ነው። ትግሉ ዘመናት ከኖረ ትክክል ካልሆነ ስርዓት፣ ከአጉል አመለካከት፣ ከተንሻፈፈ አግላይ አሠራርና ሴትን ዝቅ አድርጎ ከመመልከት አባዜና አለማወቅ ጋር ነው። እንደሚታወቀው ደግሞ ሴቶችን ዝቅ አድርጎ ማየት የወንዶች ብቻ ሳይሆን የሴቶችም አስተሳሰብ ሆኖ ይገኛል።

የወንዶች አጋርነት በምን ይገለጥ ለሚለው፣ ከቤት ውስጥ የሚጀምር እንደሆነ እሙን ነው። ባል፣ ወንድም ወይም አባት አጋርነታቸውን በማሳየት በቤታቸው ድርሻቸውን ሊወጡ ይገባል። ‹ከስኬታማ ወንድ ጀርባ ጠንካራ ሴት አለች› እንደሚባለው፣ ከሴቶቻቸው ስኬት ጀርባ ወይም አጠገብ የሚቆሙ ብርቱ ወንዶች ሊሆኑ ይገባል።

ከዚህ በተጓዳኝ በኃላፊነት ደረጃ ላይ ያሉ ወንዶች የሴቶችን መብት የሚያስከብሩ የሕግ አፈጻጸሞች እንዲጸኑ በማድረግና በአንጻሩ የሚሠሩ የሴቶችን እድል የሚነፍጉ አግላይ አሠራሮችን በመቃወም አጋርነታቸውን ሊያሳዩ ይችላሉ። እንዲሁም ባሉበት የሥልጣን ደረጃ ላይ በሚኖሩበት ጊዜ ብቃትና አቅም ያላቸውን ሴቶች በእጩነት በማሳተፍና በማቅረብ፣ እድል በመስጠትና እድል የሚዘጉ አጋጣሚዎችን በመከላከል ጭምር አጋርነትን ማሳየት ያስፈልጋል።

የሴቶች የፖለቲካ ተሳትፎ የሚያስገኘውን ጥቅም በማወቅና በማመን እንዲሁም ለሌሎች በመግለጽና በማስረዳት፣ አቅም ያላቸው ሴቶችን በማበረታታት እንደውም ‹ምነው ትግሉን የሴቶች ብቻ አደረጋችሁት? ሴት እናት፣ እህት ወይም ሚስት ስለሆነች ሳይሆን በሰውነቷ እኩል መብትና እድል ሊኖራት ስለሚገባ እኔም የትግሉ አካል ነኝ› በማለት ጭምር አጋርነታቸውን የሚያሳዩ ወንዶች ያስፈልጋሉ።

ዓለማችን እንደ ሩዋንዳው ፕሬዝዳንት ፖል ካጋሜ ዓይነት መሪዎች በብዛት ያስፈልጓታል። እንዲህ ያለ አጋርነት ለመጠቀምና እድሉን የተሻለ ለውጥ በማምጣት አዎንታዊ አመለካከቶችን ለመፍጠርና ለማጽናት ደግሞ እንደ ፕሬዝዳንት ሳህለወርቅ ዘውዴ እና እንደ ብርቱካን ሚደቅሳ ያሉ ሴቶች ያሻሉ። እንዲያ ያሉ መሪዎች እንዲኖሩ እንዲህ ያሉ ሴቶች በብዛት ሊኖሩ ይገባልና፣ ለወንዶች አጋርነት ትኩረት መስጠት ተገቢ ነው።


ቅጽ 3 ቁጥር 146 ነሐሴ 15 2013

Comments: 0

Your email address will not be published. Required fields are marked with *

This site is protected by wp-copyrightpro.com