የእለት ዜና

በቤንሻንጉል ጉምዝ ክልል የጸጥታ ችግር በፈጠረው ስጋት የዋጋ ግሽበት መባባሱ ተገለጸ

የዋግ ግሽበቱ ቀድሞ ከነበረበት በዕጥፍ ጨምሯል ተብሏል

በቤንሻንጉል፣አሶሳ ዞን፣ ቡሊጊ ሊጉ ወረዳ ዳለቲ እና አጎራባች ቀበሌዎች ላይ የጸጥታ ችግር በፈጠረው ስጋት ምክንያት የዋጋ ግሽበት መባባሱን የአከባቢው ነዋሪዎች አስታውቀዋል።
በክልሉ በተደጋጋሚ በሚፈጥረው የጸጥታ ችግር ስጋት ምክንያት ከዚህ ቀደም ከተለያዩ ቦታዎች ወደ ክልሉ መንገደኞችንና እና የምግብ እህልን ያጓጉዙ የነበሩ መኪኖች መግባት በማቆማቸው በገበያው ላይ የዋጋ ግሽበት እንዲከሰት(እንዲባባስ) እያደረገ እንደሚገኝ የአከባቢው ነዋሪዎች ለአዲስ ማለዳ ተናግረዋል።

የጸጥታ ስጋት ባልነበረበት ወቅት መኪኖች ከመሀል አገር እና ከተለያዩ አጎራባች ክልሎች ወደ ክልልሉ የተለያዩ ምርቶችን እና ሸቀጣ ሸቀጦችን ይዘው ይመጡ እንደነበር ነዋሪዎቹ አንስተዋል። ቀደም ብሎ የኑሮ ውድነቱ በአካባቢያቸው መስተዋል የጀመረ ቢሆንም፣ አሁን ያለበት ከፍተኛ ሁኔታ ላይ የደረሰው በአከባቢው ባለው የጸጥታ ስጋት ምክንያት ምርት ያቀርቡ የነበሩ ነጋዴዎች ሥራ ያቆሙበት ሁኔታ በመፈጠሩ ነው ብለዋል።

በዚህም እየተባባሰ የመጣው የዋጋ ንረት ከአቅማቸው በላይ እየሆነ መሄዱን እና ከፍተኛ የኑሮ ጫና ውስጥ እንዲገቡ እንዳደረጋቸው ነዋሪዎቹ ገልጸዋል። በክልሉ በሚገኙ አንዳንድ አካባቢዎች ላይ የትራንስፖርት እንቅስቃሴ እንደ ከዚህ ቀደሙ አለመኖሩን ተከትሎ ነጋዴዎች በመጋዘናቸው ያከማቹትን እህል፣ ሸቀጣ ሸቀጥ እና ለምግብ ፍጆታነት የሚውል ዕቃ በውድ ዋጋ ለማኅበረሰቡ በመሸጥ ላይ እንደሚገኙ የአዲስ ማለዳ ምንጮች ገልጸዋል።

ባለው የጸጥታ ችግር ምክንያት ነጋዴዎች ወደ ተለያዩ አጎራባች አካባቢውች ተጉዘው ምርቶችን በማምጣት ለሕብረተሰቡ የሚያቀርቡበት ሥራ እየተሠራ እንዳልሆነ የተገለጸ ሲሆን፣ የአካባቢው ነዋሪዎችም እንደፈለጉት ተዘዋውረው የሚያስፈልጋቸውን ለመሸመት እንዳልቻሉም ለማወቅ ተችሏል።

ይህ ዘገባ እስከተዘጋጀበት ድረስ የአካባቢው ነዋሪዎች ጨው በኪሎ ከ30 እስከ 35 ብር፣ ሽንኩርት በኪሎ ከ50 እስከ 60 ብር፣ ዳቦ በሦስት ብር እየተገበያዩ እንደሚኙ ተናግረዋል። አያይዘውም ዘይት ከገበያ ላይ መጥፋቱን እና ጤፍ በኪሎ ሀምሳ ብር የነበረ ሲሆን አሁን ግን በገበያ ላይ ማግኘት እንዳልቻሉ አስተያየት ሰጪዎቹ ጠቁመዋል።

አብዛኞቹ የአካባቢው ነዋሪዎች በቀን ሥራ የሚተዳደሩት እና የወር ደሞዝተኛ በመሆናቸው አሁን ያለውን ከፍተኛ የዋጋ ግሽበት ለመቋቋም ምንም አይነት አቅም እንደሌላቸው አመልክተዋል። ክልሉ ከተለያዩ አቅጣጫዎች በሚነሱ ግጭቶች ምክንያት በከፍተኛ ውጥረት ላይ በመገኘቱ የኑሮ ውድነቱን ማረጋጋት እንዳልተቻለም አስታውሰዋል። በዚህም ምክንያት ነዋሪዎች ለመንግሥት ቅሬታ ለማቅረብ እንኳ እንደተቸገሩ ገልጸዋል።

የጸጥታ ስጋት ባሉባቸው የክልሉ አካባቢዎች ያሉት ነዋሪዎች ስጋቱ በምግብ ፍጆታዎች እና ሸቀጣ ሸቀጦች ላይ የፈጠረው ከፍተኛ የሆነ የዋጋ ንረት በዚህ ሁኔታ ከቀጠለ ሊያስከትለው የሚችለው የኢኮኖሚ መቃወስና የምግብ ፍጆታ ማሟላት አለመቻል ትልቅ ውጥረት ውስጥ እንዲገቡ እያደረጋቸው መሆኑን አንስተዋል። ስለሆነም ማኅበረሰቡ የተጋረጠበትን ችግር መንግሥት በጥልቀ ተመልከቶ ለውጥ ለማምጣት ሊሠራ እንደሚገባው አሳስበዋል።


ቅጽ 3 ቁጥር 146 ነሐሴ 15 2013

Comments: 0

Your email address will not be published. Required fields are marked with *

error: Content is protected !!