የእለት ዜና

የጀማሪ የቢዝነስ ሐሳቦችን የሚመራ አዋጅ መዘጋጀቱ ተገለጸ

የሳይንስ ቴክኖሎጂ እና ኢኖቬሽን ሚኒስቴር የጀማሪ ቢዝነስ ሐሳቦችን የሚመራ አዋጅ ማዘጋጀቱን አስታወቀ።
የሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ ሚኒስትር ዲኤታ አህመድ መሐመድ (ዶ/ር) ለአዲስ ማለዳ እንደገለጹት፣ ይህ አዋጅ የጀማሪ ቢዝነስ ፈጣሪዎችን የሚያበረታታ ነው ብለዋል።
በአሁኑ ሰዓት የተለያዩ ባለድርሻ አካላት ተወያይተውበት የመጨረሻ ደረጃ ላይ የሚገኝ ረቂቅ አዋጅ ሲሆን፣ በቅርቡ ይጸድቃል ተብሎ እንደሚጠበቅ ገልጸዋል።

በዚህ አዋጅ አተገባበር ቢያንስ ለአምስት ዓመታት ሥራ ላይ የዋሉ የፈጠራ ሥራዎች የፈጠራውን የንግድ መለያ የሚያገኙ ሲሆን፣ አዋጁ የኢኮ-ሲስተም አስተባባሪዎች እና በዚህ እውቅና ያገኙ ባለሀብቶችን ያጠቃልላል ተብሏል።
በዚህም ብሔራዊ የጀማሪ ቢዝነስ ካውንስል ምክር ቤት የሚቋቋም ሲሆን፣ ምክር ቤቱ ከዘጠኝ የማይበልጡ አባላት እንደሚኖሩት ታውቋል።

የምክር ቤቱ ዓላማዎች ኢኮ-ሲስተም በመፍጠር የኢኮኖሚ ዕድገትን ማሳደግ ሲሆን፣ ለፈጠራ ቴክኖሎጂ እድገት፣ የፈጠራ ሥነ ምህዳራዊ ሥርዓት ለመፍጠር፣ የሚያስፈልጉ ሀብቶችን ለማንቀሳቀስ እና ለሥራ ፈጣሪዎች ፣ ለጀማሪዎች እና ለፈጠራ ንግዶች የተለያዩ ድጋፎችን ማቅረብ መሆኑን የአዋጁ ረቂቅ ጠቅሷል።

ለድርጅት ኃላፊዎች አስፈላጊውን ድርጅታዊ ክፍል በመፍጠር፣ የመነሻ እና የፈጠራ ሥነ ምህዳራዊ ሥርዓት ልማት እና ኢኖቬሽን ፈንድ በማዘጋጀት በሚኒስቴሩ የሚተዳደር እንደሚሆንም ተገለጿል።
ንግዱን ለሚደግፉ ባለሀብቶች በካፒታል ትርፍ ላይ የግብር ቅነሳ በማድረግ፣ ለውጭ ባለሀብቶች የካፒታል ትርፍ ወደ ውጭ ለመላክ ማመቻቸት ፣ የዕዳ ኢንቨስትመንትን መፍቀድ እና ከሚያገኙት ዋጋ በታች ያለውን ድርሻ እንዲሸጡ መፍቀድ ለባለሀብቶች የሚደረግ ማበረታቻ መሆኑን የአዋጁ ረቂቅ ይጠቅሳል።

ከአነስተኛ የውጭ ባለአክሲዮኖች ጋር የአገር ውስጥ ኩባንያዎች አብረው እንደሚቆጠሩ የገለጸው መመሪያው፣ የኢትዮጵያ ኢንቨስትመንት ኮሚሽን ከኢንቨስትመንት ቦርድ ጋር በመተባበር ተግባራዊ የሚያደርገው ሲሆን፣ ለውጭ ቀጥታ የተቀመጠውን አነስተኛ የኢንቨስትመንት ካፒታል እንደሚቀንስም ይገልጻል።

የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ በልማት መመሪያ ላይ የሚተዳደር ሲሆን፣ ኢንቨስትመንት ፣ የድርጅት ካፒታሎች እና የግል አክሲዮን ፈንድ በሚተገበርበት ወቅት መመሪያው የሚመለከታቸው አካላት ናቸው።
ደንቦችን እና መመሪያዎችን የማውጣት ሥልጣን ያለው የሚኒስትሮች ምክር ቤት ሲሆን፣ ይህን ተግባራዊ ለማድረግ ደንቦችን በማውጣት ለሚነሱ ጉዳዮች አፈጻጸም መመሪያ እንደሚያወጣም ተጠቅሷል።

የጀማሪ ቢዝነስ ስያሜን ለማግኘት፣ ኩባንያው ወደ ገበያው ሊያመጣ የፈለገው ምርትም ሆነ ሂደቱ ከጊዜ ወደ ጊዜ እየፈጠረ ያለውን ወይም አሁን ያለውን ምርት አገልግሎት ወይም ገበያ ማደናቀፍ እንደሌለበትም የአዋጁ ረቂቅ ይጠቅሳል።
የጅምር ሥራው የዕድገት አቅም ሊኖረው እና ሊለዋወጥ የሚችል ንግድ ሲሆን፣ ካፒታሉ ከአንድ አራተኛ (1/4) ያላነሰ ሥራ ፈጣሪው ይይዛል።

ፈጠራን እና የሥራ ፈጠራን በብቃት ለማስተዋወቅ የሚችል የፈጠራ ሥነ ምህዳራዊ ሥርዓት በኢትዮጵያ ውስጥ መፍጠር አስፈላጊ መሆኑን ያነሱት አህመዲን፣ የንግድ ሥራን የማቋቋም ፣ የማስፋፋት እና የመዝጋት ሒደቶችን በማቅለል ለሥራ ፈጣሪነት እንቅፋቶችን ለማስወገድ አዋጁ የሚጠቅም ነው ብለዋል።


ቅጽ 3 ቁጥር 146 ነሐሴ 15 2013

Comments: 0

Your email address will not be published. Required fields are marked with *

This site is protected by wp-copyrightpro.com