የእለት ዜና

የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል የ40 ቢሊዮን ዶላር ፕሮጀክቶች ሊሠራ መሆኑን ገለጸ

በከፍተኛ ደረጃ እያደገ የመጣውን የኃይል ፍላጎት ለማሟላት የውኃ፣ የሶላር፣ የንፋስና የጂኦተርማል ማመንጫዎችን በ40 ቢሊዮን ዶላር ለመገንባት መታቀዱን የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል የኮርፖሬሽን ፕላኒንግ ሥራ አስፈጻሚ አንዱአለም ሲዓ ገልጸዋል።
እነዚህ አዳዲስ የሚገነቡ ፕሮጀክቶች የኮይሻ እና የታላቁ ሕዳሴ ግድብ ማሟላት ያልቻሉትን ኃይል ለማሟላት የሚረዱ መሆናቸውን አንዱአለም ጠቅሰዋል።
ከውኃ 16፣ ከጂኦተርማል 12፣ ከንፋስ 24 እና ከሶላር 14 በአጠቃላይ 66 የማመንጫ ፕሮጀክቶችን ለመሠራት ታቅዷል።

ተቋሙ ባለው የሶፍትዌር መሣሪያ በመጠቀም አነስተኛ ወጪ የሚጠይቁ የኃይል ማመንጫዎችን በቅድሚያ በመገንባት የኤሌክትሪክ ፍላጎትን ለማሟላት እየሠራ እንደሚገኝ አንዱአለም ተናግረዋል።
እነዚህ የተለያዩ ፕሮጀክቶች በግልና በመንግሥት ሽርክና ወይንም በግል ብቻ እንዲተገበሩ የማድረግ አሠራር ያለ ሲሆን፣ አሁን ላይ ኹለት የሶላር ማመንጫ ለመገንባት የሚያስችል ስምምነት በመፈረም ወደ ሥራ ለመግባት ታቅዷል።
ይህ ስምምነት የተፈጸመው አኳ ፓወር ከተሰኘ የሳዑዲ አረቢያ ድርጅት ጋር መሆኑን የጠቆሙት ሥራ አስፈጻሚው፣ ቱሉ ሞዬ እና ኮርፔቲ የተባሉ የጂኦተርማል ማመንጫ ግንባታዎችም መጀመራቸውን ጠቅሰዋል።

በቀጣይ በንፋስ ኃይል ማመንጫ ግንባታ ለማካሄድ የጨረታ ሒደት ላይ የሚገኙ ተቋማት መኖራቸውንም አዲስ ማለዳ ሰምታለች። የአይሻ1 የንፋስ ኃይል ማመንጫን ለማስገንባት ተቋሙ ከዱባይ አሚያ ፓወር ድርጅት ጋር ድርድር ላይ እንደሚገኝ አዲስ ማለዳ ሰምታለች።
የኤሌክትሪክ ዘርፉ ያለበትን ደረጃ ጥናት በማድረግ መሻሻል የሚገባቸው ተግባራት ላይ በማሻሻል ከፍተኛ የኤሌክትክ ፍጆታን ለመሸፈን በአስር ዓመት የልማት ዕቅድ መያዙን አንዱአለም ጠቅሰዋል።

ለእያንዳንዱ ደንበኛ፣ ለኢንዱስትሪዎች እና ለጎረቤት አገራት በሚፈለገው ደረጃ የኤሌክትሪክ አቅርቦት እንዲኖር ለማድረግ እየሠራ መሆኑንም አንስተዋል። ለዚህ ፍላጎት ማስፈጸሚያ ደግሞ ከኃይል ማመንጫ ጀምሮ እስከ ግለሰቦች የሚደርስ መሠረተ ልማት ለማሟላት ማቀዱን ተቋሙ አስታውቋል።

የአገሪቱን የውስጥ ምርት (ጂዲፒ) ዕድገት፣ የኤክስፖርት መጠን እና የኢንዱስትሪዎች መስፋፋት ታሳቢ በማድረግ በሚቀጥሉት አስር ዓመታት የአገሪቱን ኃይል የማመንጨት አቅም አሁን ካለው አራት እጥፍ እና በኢነርጂ ደግሞ ሰባት እጥፍ ለማሳደግ ታቅዷል። ይህም ማለት የነበረውን 4515 ሜጋዋት የማመንጨት አቅም ወደ 17ሺሕ ሜጋዋት ማሳደግ ሲሆን ከ15ሺሕ ጌጋዋት ኃይል ወደ 65 ሺሕ ጌጋዋት የኃይል ፍላጎት እንደሚኖር ተገምቷል።

የአገሪቱ ኢንዱስትሪዎች የጀርባ አጥንት የሆነው የኤሌክትሪክ አገልግሎት ለማስፋት ከአሜሪካ መንግሥት USAID በተገኘ የአምስት ሚሊዮን ዶላር እርዳታ WSP በተባለ የእንግሊዝ የአማካሪ ድርጅት የ25 ዓመት ዕቅድ እንደተዘጋጀ አንዱአለም ገልጸዋል።
ይህ አማካሪ ድርጅት በኤሌክትሪክ ዘርፉ ያለውን የፍላጎት መጠን እና አቅርቦት ምን ያህል መሆን እንደሚገባው የማጥናት ሥራ እንዳከናውን አብራርተዋል። አያይዘውም ይህን የዕቅድ በ2014 ለመተግበር ተቋሙ መዘጋጀቱን ሥራ አስፈጻሚው ጠቁመዋል።
ተቋሙ በ2013 በጀት ዓመት የኤሌክትሪክ ኃይል በመሸጥ 90 ሚሊዮን ዶላር ገቢ ማግኘቱ ይታወሳል።

ተቋሙ በተጠናቀቀው በጀት ዓመት ከውጭ አገራት የኃይል ሽያጭ የሰበሰበው ገቢ ከ2012 በጀት ዓመት ተመሳሳይ ወቅት ከሰበሰበው ጋር ሲነፃፀር የ24 ነጥብ 1 ሚሊዮን የአሜሪካ ዶላር ወይም የ36 ነጥብ 2 በመቶ ብልጫ እንዳለው ታውቋል።


ቅጽ 3 ቁጥር 146 ነሐሴ 15 2013

Comments: 0

Your email address will not be published. Required fields are marked with *

This site is protected by wp-copyrightpro.com