የእለት ዜና

በከተሞች ያለው የኤች አይ ቪ ሥርጭት መጠን በገጠር ካለው በሰባት እጥፍ እንደሚልቅ ተገለጸ

በ2013 ከ11 ሺሕ በላይ ሰዎች በቫይረሱ ተይዘዋል

የኤች አይ ቪ ቫይረስ በአገሪቱ በተለይም በከተሞች ያለው የሥርጭት መጠን በከፍተኛ ሁኔታ ላይ እንደሚገኝ ተገለጸ። በከተሞች ያለው የቫይረሱ ሥርጭት ገጠር ካለው ጋር ሲነጻጸር በሰባት እጥፍ ብልጫ ያለው መሆኑ ታውቋል።
በአዲስ አበባ፣ በጋምቤላ እና ከተሜነት እየተስፋፋባቸው ባሉ አካባቢዎች ላይ ሥርጭቱ ከፍተኛ ደረጃ ላይ መድረሱ የታወቀ ሲሆን፣ የኤች አይ ቪ ኤድስ ሥርጭት በኢትዮጵያ የጤና ስጋት ሆኖ በመቀጠል ላይ እንዳለ የጤና ሚኒስትር የሆኑት ዶ/ር ሊያ ታደሰ ለ33ኛ ጊዜ በአገራችን በተከበረው የዓለም ዐቀፉ የኤች አይ ቪ ኤድስ ቀን ላይ መናገራቸውም ይታወሳል።

ለቫይረሱ ተጋላጭ ከሆኑ የሕብረተሰብ አካላት መካከል በከፍተኛ አገር አቀፍ የትራንስፖርት አገልግሎት የተሰማሩ ግለሰበች፣ ሴተኛ አዳሪዎች፣ ትዳር የፈቱ ሰዎች፣ የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ተማሪዎች ላይ የኤች አይ ቪ ኤድስ ቫይረስ በከፍተኛ ሁኔታ ሥርጭቱ ከፍ ያለ ነው ተብሏል። ከነዚህም በተጨማሪ በአሁን ሰዓት ከፍተኛ የሰው ኃይል በማንቀሳቀስ ላይ በሚገኙት የኢንዱስትሪ ፓርኮች አካባቢ ሥርጭቱ ከፍ እያለ እንደሆነም ታውቋል።

የሥርጭት ምጣኔው ከጾታ አንጻር ሲታይ፣ ሴቶች ከወንዶች በኹለት እጥፍ በቫይረሱ የመያዝ ዕድላቸው ከፍ ያለ ነው ተብሏል።

በአገራችን ያለው የኤች አይ ቪ ኤድስ ሥርጭት 0.86 በመቶ ላይ እንዳለ የተገለጸ ሲሆን፣ በዓለም ዐቀፍ የጤና ድርጅት መሠረት አንድ አገር ካላት የሕዝብ ብዛት ውስጥ ከአንድ ከመቶ በላይ የሆነው በቫይረሱ የተጠቃ ከሆነ በወረርሽኝ ደረጃ የሚገለጽ ሲሆን፣ እስካሁን በኢትዮጵያ ሥርጭቱ ወደ ወረርሽኝ ደረጃ አልደረሰም።

በኢትዮጵያ በ2013 ዓመት ብቻ 11 ሺሕ 715 አዲስ በቫይረሱ የተያዙ ሰዎች የተገኙ ሲሆን፣ በዚሁ ዓመት 12 ሺሕ 685 ወገኖች በኤች አይ ቪ ኤድስ ቫይረስ እና ተያያዥ ምክንያቶች ሕይወታቸውን አጥተዋል። በአሁን ወቅት በአጠቃላይ 622 ሺሕ 326 ሰዎች ከቫይረሱ ጋር እንደሚኖሩ በፌደራል ኤች አይ ቪ ኤድስ መከላከያ እና መቆጣጠሪያ ጽሕፈት ቤት የዕቅድ፣ ክትትልና ግምገማ ዳይሬክተር ነጻነት ሀኒኮ ለአዲስ ማለዳ ተናግረዋል።

በአገር ዐቀፍ ደረጃ አዲስ የሚያዙ ሰዎችን ቁጥር ዝቅ ለማድረግ ዕቅድ ተይዞ ቢሠራም ማሳካት እንዳልተቻለ የተገለጸ ሲሆን፣ ዕቅዱ በቫይረሱ የሚያዙ ሰዎችን ቁጥር በ75 በመቶ ለመቀንስ የተያዘ ቢሆንም ማሳከት የተቻለው ግን 52 በመቶውን ብቻ ነው።
ከኮቪድ-19 ወረርሽኝ ጋር በተያያዘ ሰፊ ሥራ መሠራቱን አንስተው፣ ኮቪድ ተጓዳኝ በሽታዎች ያሉባቸውን ሰዎች በስፋት ለሞት ከመዳረጉ የተነሳ የኤች አይ ቪ ኤድስ ቫይረስ በደማቸው ውስጥ ያለ ሰዎች ደግሞ በተጓዳኝ በሽታ የመያዝ ሰፊ ዕድል ያላቸው በመሆኑ ከመከላከል አንጻር ትልቅ ሥራ ተሠርቷል።

ከዚህም መካከል መደኃኒት ለመውስድ የሚደረግን ምልልስ ለመቀነስ ታስቦ በየወሩ የነበረውን ከሦስት ወር እስከ ስድሰት ወር ድረስ ከፍ እንዲል በማድረግ፣ ቫይረሱ ያለባቸው ዜጎች በኮቪድ-19 የመያዝ ዕድላቸውን ዝቅ ለማድረግ መሠራቱንና ይህም ትልቅ ውጤት እንዳስገኘ ዳይሬክተሩ ለአዲስ ማለዳ ተናግረዋል።


ቅጽ 3 ቁጥር 146 ነሐሴ 15 2013

Comments: 0

Your email address will not be published. Required fields are marked with *

error: Content is protected !!