የእለት ዜና

የ45 ዩኒቨርሲቲዎች የመሠረተ ልማት ግንባታ በባለድርሻ አካላት አለመናበብ መዘግየቱ ተገለጸ

በ92 ቢሊዮን ብር በጀት የሚገነቡ የ45 ዩኒቨርሲቲዎች የመሠረተ ልማት ግንባታዎች፣ ባለድርሻ አካላት ተናበው ሥራቸውን ባለመሥራታቸው የተነሳ በታቀደው የጊዜ ገደብ መጠናቀቅ እንዳልቻሉ ተገለጸ።
በመንግስት 92 ቢሊዮን ብር በጀት ተመድቦ በ45 ከፍተኛ የትምህርት ተቋማት ውስጥ የመሠረተ ልማት ግንባት የተጀመረ ቢሆንም፣ በግንባታ ገንቢዎቹ፣ አስገንቢዎቹ እና አማካሪዎቹ በጋራ ተናበው የመሥራት ሁኔታ ባለመኖሩ በተያዘላቸው የጊዜ ገደብ ማጠናቀቅ እንዳልተቻለ የተናገረው የኮንስትራክሽን ሥራዎች ተቆጣጣሪ ባለሥልጣን ነው።

በከፍተኛ የትምህርት ተቋማት ውስጥ ለተማሪዎች የመማሪያ ክፍል፣ የመኖሪያ ቤት፣ የመሰብሰቢያ አዳራሾች፣ ለጥናትና ምርምር የሚያገለግሉ እና ሌሎች የትምህርት ማስተማር ሒደቱን ስኬታማ ሊያደርጉ የሚችሉ በድምሩ 754 የግንባታ ብሮጀክቶች ተጀምረው እንደነበር የኮንስትራክሽን ሥራዎች ተቆጣጣሪ ባለሥልጣን ሕዝብ ግንኙነት ኃላፊ ሲሳይ ደርቤ ለአዲስ ማለዳ ተናግረዋል።

የተጀመሩት የመሠረት ልማት ግንባታዎች የመማር ማስተማር ሂደቱ ቀልጣፋና ውጤታማ ለማድረግ ወሳኝ ሚና እንዳላቸው ኃላፊው አንስተዋል። በተቋሞቹ መሠረት ልማት ግንባታዎችን የሚያከናውኑ አንዳንድ አስገንቢዎች በሚፈጠር ክፍተት፣ ገንቢዎች ገንዘብ ተቀብለው ቦታ የሚቀይሩበት ሁኔታ በመኖሩ እና ከአማካሪዎች ጋር ተናበው በቅንጅት የመሥራት ሒደት በስፋት ባለመኖሩ ለግንባታ ሥራዎቹ መጓተት ዋነኛው ምክንያት መሆኑን አስታውቀዋል።

በአገራችን ብሎም በዓለም ዐቀፍ ደረጃ የተከሰተው የኮቪድ 19 ወረርሽን እና የኮንስትራክሽን ግብዓት የዋጋ ንረት፣ ተቋማቱ ለግንባታዎቹ መጓተት እንደ አንድ ተጽዕኖ የሚያነሱት ቢሆንም፣ ከዓመታት በፊት ለተጀመረ የመሠረት ልማት ግንባታ ምክንያት እንደማይሆን ጠቁመዋል።
ሲሳይ አክለውም፣ በከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ላይ የተጀመሩት መሠረተ ልማቶች አለመጠናቀቃቸው በትምህርት ጥራት ላይ፣ በተማሪዎች ቅበላ ላይ ሰፊ የሆነ ተጽዕኖ እንደሚኖረው፣ እንዲሁም በአገር በጀት ላይ ከፍተኛ ጫና እንደሚያሳድር ተናግረዋል።

ተጀምረው ያልተጠናቀቁ ግንባታዎችን በፍጥነት አጠናቆ ለአገልግሎች ምቹ ለማድረግ ከኹሉም የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት የተውጣጣ ኮሚቴ እንደተቋቋመና እስከ ነሐሴ 30 ድረስ የግንባታዎቹን መጓተት መሠረታዊ ችግሮች አጥንቶ ይፋ እንደሚያደርግ ገልጸዋል።
የተጀመሩት የመሠረት ልማት ግንባታዎች ከፍተኛ የመንግሥት በጀት ወጪ የተደረገባቸው እና ዜጎች የሚጠቀሙባቸው በመሆናቸው በቁጭት እና በአገራዊ ስሜት መጠናቀቅ አለባቸው ብለዋል። በከፍተኛ ትምህርት ተቋማት የመሠረተ ልማት ግንባታዎች ላይ የታየውን ችግር ለመፍታት ኮሚቴው እና ተቋማቶች በጥልቀት እንደሚሠሩም ገልፀዋል።

ኃላፊው አያይዘውም እንደ አገር በብዙ ነገሮች የከሰርንበት ኹኔታ በመኖሩ ከዛ ኪሳራ ለመዳን የማስተባበር ሥራ እየተሠራ ቢሆንም፣ በቀጣይ ዕርምጃ ሊወሰድ እንደሚገባም አንስተዋል። በከፍተኛ የትምህርት ተቋማት የተስተዋለው የመሠረተ ልማት ግንባታዎች መጓተት ትምህርት ተወስዶበት በሌሎች መሰል ግንባታዎች ላይ መደገም እንደሌለበት ሲሳይ ከአዲስ ማለዳ ጋር በነበራቸው ቆይታ ተናግረዋል።

አክለውም፣ በቀጣይ በአገሪቱ ላይ የሚገነቡ የመሠረተ ልማት ግንባታዎች በጥራት እና መንግሥት በበጀተው በጀት በታቀደለት የጊዜ ገደብ የማጠናቀቅ ሥራ በሰፊው መሠራት እንዳለበት ገልጸዋል።


ቅጽ 3 ቁጥር 146 ነሐሴ 15 2013

Comments: 0

Your email address will not be published. Required fields are marked with *

error: Content is protected !!