የእለት ዜና

የጨርቃ ጨርቅ ኢንዱስትሪው በጸጥታ ችግርና በውጭ ምንዛሬ እጥረት መፈተኑ ተገለጸ

በ2013 በጀት ዓመት የጨርቃ ጨርቅ ኢንዱስትሪው በጸጥታ ችግር ምክንያት በከፍተኛ ሁኔታ መፈተኑን የኢትዮጵያ ጨርቃ ጨርቅ ኢንዱስትሪ ልማት ኢንስትቲዩት ገለጸ።
አሁን ላይ የጸጥታ ችግር በኹሉም አካባቢ በሚባል ደረጃ ላይ መከሰቱ ለኢንቨስትመንት፣ ኢንዱስትሪውን ለማስፋፋት እና ለማሳደግ በሚደረገው ሒደት ላይ አሉታዊ ተጽዕኖ እያሳደረ ነው። በአገሪቱ ውስጥ ያለው የጸጥታ ችግር ባለሀብቶችን ወደ ዘርፉ እንዳይገቡ ከማድረግ ባለፈ የገቡትም በሥጋት ምክንያት ለመውጣት እንዲያስቡ ሊያደርጋቸው እንደሚችልም ተሰግቷል።

በሰሜኑ የአገራችን ክፍል ከጥቅምት 2013 ጀምሮ እየተካሄደ ባለው ጦርነት ምክንያት በትግራይ የሚገኙ፣ “ማ ጋርመንትን” ጨምሮ፣ ትላልቅ የጨርቃ ጨርቅ ፋብሪካዎች ሙሉ በሙሉ ሥራ ማቆማቸውን ኢንስትቲዩቱ ገልጿል።
በዓመቱ የጥጥ ምርት በከፍተኛ ሁኔታ ከሚመረትባቸው አካባቢዎች አንዱ በሆነው የቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል ከፍተኛ የጥጥ ምርት ቢመረትም፣ በነበረው የጸጥታ ችግር ምክንያት ሠራተኛ ወደ አካባቢው ተጉዞ ምርቱን ለመልቀምና በጊዜ ለመሰብሰብ ከፍተኛ ስጋት እንደነበርም የኢትዮጵያ ጨርቃ ጨርቅ ኢንዱስትሪ ልማት ኢንስትቲዩት ኮሚዩኒኬሽን ጉዳዮች ዳይሬክተር የሆኑት ባንትይሁን ገሰሰ ተናግረዋል።

በአገሪቱ ባለው የጸጥታ ችግር ምክንያት የጨርቃ ጨርቅ ኢንዱስትሪዎች ምርታማነት በሚፈለገው ደረጃ እንዳላደገ የሚያነሱት ዳይሬክተሩ፣ በወር በትንሹ እስከ አንድ ሚሊዮን ዶላር ድረስ ያስገቡ የነበሩ የጨርቃ ጨርቅ ኢንዱስትሪዎች አሁን ላይ ቀድሞ የሚያስገኙትን ገቢ ማስገኘት እንዳልቻሉ ተመላክቷል። በዚህም ምክንያት በጥሩ ዕድገት ላይ በነበረው ኢንዱስትሪ ላይ ጠባሣ እንዳያሳርፍ ተሰግቷል።

የጨርቃ ጨርቅ ኢንዱስትሪው በብዙ ችግሮች ውስጥ እያለፈ እንደሚገኝና ከነዚህ ውስጥ እንደ አገርም ጭምር መፍትሔ ያጣ ሁኖ የቀጠለው የውጭ ምንዛሬ ችግር ኢንዱስትሪውንም እየተፈታተነው ይገኛል። በጥጥ ልማት ላይ የሚገኙ እርሻዎች ኬሚካል በወቅቱ ካላገኙ በምርት ሒደቱም ሆነ ጥራቱ ላይ ከፍተኛ ችግር የሚያስከትል ጉዳይ ነው። “እነዚህ አስፈላጊ የሆኑ ኬሚካሎች በውጭ ምንዛሬ ዕጥረት ምክንያት በጊዜ አገር ውስጥ መግባት ካልቻሉ የጥጥ ምርቱ ላይ የሚያስከትለው ማሽቆልቆል ከፍተኛ ነው” ሲሉ ባንትይሁን ገሰሰ ይናገራሉ።

በ2012 ላይ ተከስቶ በመላው ዓለም ላይ ከፍተኛ ኢኮኖሚያዊ ተጽዕኖውን ያሳረፈው የኮቪድ-19 ወረርሽኝ ምክንያት ሠራተኞችን በፈረቃ በማሠራት፣ የደህንነት መጠበቂያ በማቅረብ፣ የግንዛቤ ማስጨበጫ ትምህርቶችን በመስጠት ወረርሽኙ በኢንዱስትሪው ላይ የከፋ ችግር ሳያስከትል ማለፍ የተቻለ ቢሆንም፣ አሁን ላይ ያለው የጸጥታ ችግር የጨርቃ ጨርቅ ኢንዱስትሪውን በከፍተኛ ደረጃ እየፈተነው መሆኑ ተመላክቷል።

ከዚህም በተጨማሪ ባለፈው የክረምት ወቅት ላይ ሰፊ የጥጥ ማምረት እየተከናወነ በሚገኝበት በአፋር ክልል፣ የአዋሽ ወንዝ ከመጠን በላይ ሞልቶ በደረሰው የጎርፍ መጥለቅለቅ በከፍተኛ ሁኔታ ተስፋ ተደርጎበት የነበረው የጥጥ እርሻ ሙሉ በሙሉ መጥፋቱን ዳይሬክተሩ የተናገሩ ሲሆን፣ ይሔም በፍላጎት ላይ ክፍተት እንዲፈጠር ማድረጉን ያክላሉ።

በ2013 ዓመት ላይ 55 ሺሕ ቶን የተዳመጠ ጥጥ ተፈልጎ የነበረ ቢሆንም፣ በአገር ውስጥ ምርት ማግኘት የተቻለው ግን 33 ሺሕ ቶን ብቻ ነው። በፍላጎት እና በምርት ላይ የተፈጠረውን ክፍተት ለመሙላት ከውጭ ማስገባት ለሚችሉ ፋብሪካዎች ማስገባት እንዲችሉ ዕድሉ መሰጠቱንም ባንቲሁን ተናግረዋል።

ኢትዮጵያ ለጥጥ ምርት የተመቸች እና ከፍተኛ አቅም ያላት አገር መሆኗ ቢታወቅም፣ ያለውን አቅም ከፍ ባለ ደረጃ ከመጠቀም አንጻር ክፍተት ያለ በመሆኑ ይሔን ለማስተካከል የሚያስችል የ15 ዓመት የስትራቴጂክ ዕቅድ ተዘጋጅቶ ወደ ሥራ ለማስገባት የኢትዮጵያ ጨርቃ ጨርቅ ኢንዱስትሪ ልማት ኢንስትቲዩት በሒደት ላይ መሆኑን ዳይሬክተሩ ለአዲስ ማለዳ አስታውቀዋል።


ቅጽ 3 ቁጥር 146 ነሐሴ 15 2013

Comments: 0

Your email address will not be published. Required fields are marked with *

This site is protected by wp-copyrightpro.com