የእለት ዜና

የአፋር እና ሱማሌ ክልል የድንበር ውዝግብ የተባባሰ ችግር እንዳይፈጥር ተሰግቷል

በአፋር እና በሱማሌ ክልል መካከል ያለው የድንበር ውዝግብ የተባባሰ ችግር እንዳይፈጠር ስጋት መሆኑን የሱማሌ ክልል መንግሥት ለአዲስ ማለዳ ጋዜጣ ገለጸ።
ውዝግብ ከተፈጠረበት ድንበር አከባቢ የተፈናቀሉት የሱማሌ ክልል ማኅበረሰቦች እስካሁን ወደየመኖሪያ ቦታቸው አለመመለሳቸው የተገለጸ ሲሆን፣ ተፈናቃዮች ወደ ቦታቸው መመለስ ያልቻሉት ችግሩ መፍትሔ ባለማግኘቱ ነው ተብሏል። “አፋሮች ቦታውን አንለቅላችሁም በማለታቸውና ተፈናቃዮቹ ቦታችንን በኃይል እንመልሳለን የሚል አስተሳሰብን ስለሚያንጸባርቁ ብጥብጥ ይነሳል የሚል ስጋት ፈጥሯል” ሲሉ የሱማሌ ክልል የኮሚዩኒኬሽን ቢሮ ዳይሬክተር መሐመድ ሮብሌ ገልፀዋል።

ዳይሬክተሩ እንዳሉት፣ ከአሁን በፊት በተፈጠረው ግጭት ምክንያት ሰዎች ለሕልፈተ ሕይወት እንደተዳረጉና በዚህም ክስተት ሴቶችና ሕጻናትን ጨምሮ በርካቶች የችግሩን ገፈት የቀመሱ ሲሆን፣ ከአካባቢያቸው ተፈናቅለው በተለያዩ መጠለያዎች ተጠግተው የሚገኙ የሱማሌ ማኅበረሶቦችም ከ30 ሺሕ በላይ ናቸው።

የሱማሌ ክልል መንግሥት እና ማኅበረሰቡ ችግሩን ለመቅረፍ የተፈናቀሉትን ለማግባባት እየሞከሩ ቢሆንም፣ በክልሎቹ መካከል ብጥብጥ ያስነሱ ድንበሮችን በተመለከተ ምንም አይነት መፍትሔ ላይ አልተደረሰም ተብሏል። “ክረምቱን በስደት መቋቋም አልቻልንም ሲሉ የሚሰሙት ማኅበረሰቦች ትዕግስታቸው ያለቀ ይመስላልና ለዳግም ብጥብጥ እንዳይነሳሱ የሚል ስጋት ተፈጥሯል” ሲሉ ዳይሬክተሩ አክለዋል።

ቀድሞ በነበረው ብጥብጥ ምክንያት የኹለቱ ክልል ማኅበረሰቦች በምርጫ አለመሳተፋቸውን የገለጹት ዳይሬክተሩ፣ አክለውም መንግሥት በአካባቢዎቹ ጳጉሜን 1/2013 ምርጫ እንዲካሄድ ዕቅድ የያዘ ቢሆንም፣ በአካባቢው ያለው የፖለቲካ አለመረጋጋት የማኅበረሰቡ አባላት በምርጫ መሳተፍ እንዳይችሉ አንቅፋት እንዳይሆን ስለሚያሰጋ በመጀመሪያ የማረጋጋቱ ሥራ ቅድሚያ ሊሰጠው እንደሚገባ ጠቁመዋል።

በተጨማሪም፣ ምርጫ ከመካሄዱ በፊት ምርጫ ቦርዱ የሱማሌ እና የአፋር ክልል በምርጫው እንዳማይሳተፉ ያስተላለፈው ውሳኔ ብዙዎቹ ላይ የመበሳጨትና የመናደድ ስሜት ስላሳደረ የመምረጣቸውን ጉዳይ እርግጠኛ ሆኖ መናገር ባይቻልም፣ እስካሁን ባለው መረጃ መሠረት ምርጫው እንደሚካሄድ ነው የሚታመነው ብለዋል።

አዲስ ማለዳ ጋዜጣ ጉዳዩን በማስመልከት ተፈናቅለው ከሚገኙት የሱማሌ ክልል ነዋሪዎች መካከል የተወሰኑትን በስልክ አነጋግራለች። ባገኘችውም መረጃ መሠረት ከኹለቱ ቦታዎች የተፈናቀሉት ዜጎች በዚህ ወቅት በአጎራባች ቦታዎች በሚገኙ ማኅበረሰቦች ተጠግተውና በተዘጋጀላቸው ጊዜያዊ መጠለያ እንደሚኖሩ ማረጋገጥ ችላለች።

በአፋርና በሱማሌ ክልል በተፈጠረው የድንበር አለመግባባት ምክንያት በነበረው ብጥብጥ ከተፈናቀሉት ዜጎች መካከልም ሰይድ ያሲን የተባሉ ግለሰብ “የአፋር ክልል የምንኖርባችውን ከተሞች በኃይል ስለተቆጣጠረብን ቀያችንን ለቀን ሜዳ ላይ ነው ያለነው” ብለዋል።
ተፈናቃዮች ያሉበት ኹኔታ ምቹ አለመሆኑን የጠቆሙት ሰይድ፣ “ክረምቱንም መቋቋም አልቻልንም፤ በግፍ የተወሰዱብን ቦታዎች መንግሥት አስፈላጊውን ዕርምጃ በመውሰድ እንዲያስመልስልን እና ወደ ቦታችን እንዲመልሰን እናሳስባለን” በማለት ተናግረዋል።

በአፋር እና በሱማሌ ክልል አዋሳኝ ቦታ ላይ በሚገኙ አደይቱ እና ገርበኢሴ በተባሉት ኹለት የድንበር አካባቢዎች በተከሰተ አለመግባባት ምክንያት የሰዎች ሕይወት ያለፈ ሲሆን፣ ችግሩ በኹለቱ ክልሎች መካከል ከፍተኛ ውዝግብ አስከትሎ እንደነበር የሚታወስ ነው።
አዲስ ማለዳ በጉዳዩ ላይ የአፋር ክልል መንግሥትን አስተያየት ለማግኘት በተደጋጋሚ ስልክ ብትደውልም ያደረገችው ጥረት አልተሳካም።


ቅጽ 3 ቁጥር 146 ነሐሴ 15 2013

Comments: 0

Your email address will not be published. Required fields are marked with *

error: Content is protected !!