የእለት ዜና

የደሴ ከተማ አስተዳደር ለተፈናቃዮች ድጋፍ ለማድረግ መቸገሩን ገለጸ

ወደ ከተማው በቀን እስከ ኹለት መቶ የሚደርሱ ተፈናቃዮች ይገባሉ

ከአዲስ አበባ በ400 ኪ.ሜ ርቀት ላይ ወደምትገኘው ደሴ ከተማ የሚገቡ የተፈናቃዮች ቁጥር እየጨመረ በመምጣቱ የሰብዓዊ ድጋፎች ለማድረግ ተችግሬያለሁ ሲል የከተማው አስተዳደር ለአዲስ ማለዳ አስታወቀ።
የደሴ ከተማ መንግሥት ኮሚዩኒኬሽን ጉዳዮች መምሪያ ኃላፊ ምሳዬ ከድር ለአዲስ ማለዳ እንደገለጹት፣ የቀይ መስቀል፣ የአደጋ መከላከያ እና ምግብ ዋስትና ጽሕፈት ቤት የተለያዩ አካላት ድጋፍ እያደረጉ ቢሆንም፣ ከቀን ወደቀን እየጨመረ ለመጣው የተፈናቃዮች ቁጥር የተሰጡ የሰብዓዊ ድጋፎች አነስተኛ ናቸው ብለዋል።

አያይዘውም በየቀኑ የሚገቡትን ተፈናቃዮች ለማስተናገድ ተከታታይ የሆነ ድጋፍ ያስፈልጋል ሲሉ ነው የገለጹት። ጉዳዩ በመንግሥት በኩል ለጥቂት ጊዜ ብቻ ትኩረት ተሰጥቶት የነበረ ቢሆንም፣ በአሁኑ ሰዓት ጉዳዩ እየተረሳ በመምጣቱ የሚሰጡ ድጋፎች መቀነሳቸውን ጠቅሰዋል። በዚህም ተፈናቃዮችን ለማስተናገድ ከፍተኛ ችግር ገጥሞናል ሲሉ አንስተዋል። በአሁኑ ሰዓት የከተማው ማኅበረሰብ ከሚያደርገው ድጋፍ ውጭ በመንግሥት በኩል ተከታታይ ዕርዳታዎች ባለመምጣታቸው ችግር ላይ እንገኛለን ብለዋል።
የከተማዋ ደሕንነት ከገዜ ወደጊዜ እየተሻሻለ የመጣ ሲሆን፣ ከተለያዩ አካባቢዎች እየተፈናቀሉ ወደከተማው የሚገቡ ሰዎች ቁጥር በመጨመሩ ምክንያት የአስቸኳይ ጊዜ ዐዋጅ መውጣቱን ኃላፊዋ አስታውሰዋል።

በዚህም መሰረት የታክሲ ተሽከርካሪ እና የነዋሪዎች እንቅስቃሴ እስከ ምሽቱ ኹለት ሰዓት፣ እንዲሁም ባጃጆች 12 ሰዓት ድረስ ብቻ እንዲሠሩ የሰዓት ዕላፊ ገድብ ተጥሏል።
ከነሐሴ 4/2013 ጀምሮ ተግባራዊ የሆነው የሰዓት ዕላፊ ገደብ ወደ ከተማው የሚገቡ ተፈናቃይ ሰዎች ቁጥር እስከሚቀንስ የሚቀጥል ነው ተብሏል።

ይህ መረጃ እስከተጠናከረበት ቀን ድረስ ወደ ከተማዋ የሚገቡ ተፈናቃዮች ቁጥር እየጨመረ ሲሆን፣ በቀን እስከ 200 ሰዎች ከተለያዩ አካባቢዎች እየገቡ ነው ብለዋል። በዚህም ከ300 ሺሕ በላይ ተፈናቃዮች በአካባቢው እንደሚገኙ ነው የጠቆሙት።
ወደ ደሴ ከተማ እየገቡ ያሉ ተፈናቃዮች በሽብርኝነት የተፈረጀው ህወሓት ወረራ ከፈጸመባቸው የሰሜን ወሎ አካባቢዎች እና የአፋር ክልል መሆኑን ምሳዬ ይናገራሉ። በዚህም የሰሜን ወሎ ዞን አጠቃላይ ነዋሪዎች፣ ከአፋር ክልል የአንድ ወረዳ ነዋሪዎች፣ እንዲሁም የሌሎች አካባቢ ተፈናቃዮች ወደከተማው መግባታቸው ነው የተገለጸው።

በደሴ ከተማ የሚገኙ ተፈናቃዮች ሲጠቀሙባቸው የቆዩትን አምስት መጠለያ ጣቢያዎች ባሳለፍነው ሰኞ ወደ ዘጠኝ እንዳሳደጉት የገለጹት የመምሪያ ኃላፊዋ፣ መጠለያዎቹን የማይጠቀሙና ቤት ተከራይተው እንዲሁም ዘመድ ጋር ተጠግተው የሚኖሩ እንዳሉ ጠቅሰዋል።
በመጠለያ ለሚገኙት የሕብረተሰብ ክፍሎች የከተማው ነዋሪዎች ምግብ እና አልባሳት በማሟላት የሰብዓዊ ድጋፍ እያደረጉ እንደሆነ ነው የገለጹት። በከተማዋ የሚገኙ የጤና ተቋማት የጤና አገልግሎትን በመስጠት እንዲሁም ገንዘብ ያላቸው ገንዘብ በመስጠት ተፈናቃዮችን እያገዙ ይገኛሉ ተብሏል።

የደሴ ከተማ ነዋሪዎች በየሠፈሩ የራሳቸውን አደረጃጀት ፈጥረው አካባቢያቸውን እየጠበቁ እንደሚገኙም ምሳዬ ጠቁመዋል።
የበጎ ፍቃደኛ ወጣቶች እና የፀጥታ አካላት በጋራ በመሆን በፈጠሩት አደረጃጀት የተለያዩ ሠርጎ ገቦች ወደ ከተማዋ እንዳይገቡ የማድረግ ሥራ እየሠሩ ነውም ተብሏል።
ይህ አደረጃጀት በተለያዩ የኬላ ጣቢያዎች ላይ በመሰማራት የሚያደርገው ጥበቃ መጠናከሩን ገልጸዋል።

አካባቢውን የህወሓት ታጣቂዎች ተቆጣጥረውታል እየተባለ የሚወራው መረጃ ፍጹም ስህተት ነው ሲሉም አንስተዋል። እንደዚህ አይነት የተሳሳቱ መረጃዎችን በመልቀቅ ሕብረተሰቡን እያደናገሩና ፍርሐት ለመፍጠር እየሞከሩ እንዳሉነው ኃላፊዋ የጠቆሙት።
አዲስ ማለዳ ከዚህ በፊት ከተለያዩ ከሰሜን ወሎ ዞን አካባቢዎች ተፈናቅለው ወደ ደሴ እና ኮምቦልቻ የገቡ ተፈናቃዮች መሠረታዊ የምግብ ፍጆታ እና የመጠለያ ችግር እንደገጠማቸው መዘገቧ የሚታወስ ነው።


ቅጽ 3 ቁጥር 147 ነሐሴ 22 2013

Comments: 0

Your email address will not be published. Required fields are marked with *

error: Content is protected !!