የእለት ዜና

በቤንሻንጉል ጉምዝ ክልል መተከል ዞን ቡለን ወረዳ 10 ሰዎች በታጠቁ ኃይሎች መገደላቸው ተገለጸ

በቤንሻንጉል ጉምዝ ክልል መተከል ዞን ቡለን ወረደ 10 ንጹኃን ዜጎቸ ባሳለፍነው ነሐሴ 20/2013 በታጠቁ ኃይሎች መገደላቸውን የአካባቢው ነዋሪዎች ለአዲስ ማለዳ ገለጹ።
ታጣቂዎቹ ከቻግኒ ወደ ግልገል በለስ ከተማ 14 ሰዎችን ጭነው ሲጓዙ የነበሩ ኹለት አነስተኛ የሕዝብ ማመላለሻ መኪኖችን በማገት በቡለን ወረዳ 10 ንጹኃን ዜጎችን መግደላቸውን አዲስ ማለዳ ከአካባቢው ምንጮቿ አረጋግጣለች።
ከአዲስ ማለዳ ምንጮች መረዳት እንደተቻለው፣ ከታገቱት 14 ንጹኃን መካከል ሰባት ወንዶችና ሦስት ሴቶች የተገደሉ ሲሆን፣ ቀሪዎቹ አራት ሰዎች ይህ ዘገባ እስከተዘጋጀበት ስዓት ድረስ ያሉበት ሁኔታ አይታወቅም።

ነዋሪዎቹ አክለውም ግልገል በለስ በተባለችው የዞኑ ዋና ከተማ ሦስት የመከላከያ አባላት በታጣቂ ኃይሉ እንደተገደሉ በመጠቆም፣ በተለይ በአንደኛው አባል ላይ አሰቃቂ ግድያ ፈጽመውበታል በማለት የዓይን ዕማኝነታውን ሰጥተዋል። ከንጹኃን ዜጎች ሞት በተጨማሪ ታጣቂ ኃይሉ ኹለት የመከላከያ አባላትን ማቁሰሉን የአዲስ ማለዳ ምንጮች ተናግረዋል።

ግድያዉ ሲፈጸም ከመከላከያ አባላቱ በኩል ተኩስ ባለመኖሩ ጥቃቱን ከሰነዝሩት ተቃራኒ ኃይሎች ውስጥ የሞተ ሰው እንደሌለም የአዲስ ማለዳ ምንጮች አብራርተዋል። የአካበባው ነዋሪዎች እንደሚሉት “ጥቃቱን የፈጸሙት በቡለን ወረዳ ጥበቃ እንዲያደርጉ ኃላፊነት የተሰጣቸው፣ ነገር ግን አደራቸውን ቅርጥፍ አድርገው የበሉ የጉምዝ ሽፍታዎች ናቸው።”

ነዋሪዎች እንደሚሉት ከሆነ ታጣቂዎች የሚሰነዝሩት ጥቃት በየወቅቱ እየጨመረ በመሆኑ፣ የሞቱ ሰዎችን በግልጽ ማወቅ ባይቻልም በየቀኑ ሰዎች እንደሚገደሉ ተናግረዋል። ነዋሪዎቹ አክለውም በሞትና በሕይወትና መካከል የሚገኙ ቁስለኛ ዜጎችን የከተማው ወጣቶች ተሰባስበው በማንሳት ለማሳከም ቢሞክሩም የጤና ተቋማት በግጭት ምክንያት ስለተዘጉ ሕይወታቸውን ማትረፍ አስቸጋሪ ሁኗል ብለዋል።

አዲስ ማለዳ ካነጋገረቻቸው ምንጮች መካከልም ስማቸው እንዳይጠቀስ የፈለጉ የአከባቢው ነዋሪ “ግድያውን የፈጸሙት አካባቢውን ከጥቃት እንዲጠብቁ ኃላፊነት ተሰጥቷቸው መሣሪያ ይዘው ቆመው የነበሩ ታጣቂዎች እንደሆኑ በዓይኔ አይቻለሁ’’ ሲሉ ገልጸዋል።
እኒህ ነዋሪ ’’ምንም አይነት የሚታመን ባህሪ የላቸውም፤ ሲርባቸውና ሲጠማቸው ከማኅበረሰቡ ዘንድ እየተመላለሱ በማስገደድ ይመገባሉ፤ ዙረው የመገባቸውን ማኀበረሰብ ይገድላሉ፤ በተደጋጋሚ የሲቃ ድምጻችንን ብናሰማም ካለንበት ከባድ ሁኔታ የሚከልለን አካል ማግኘት አልቻልንም’’ ብለዋል።

አክለውም “ይህ ጥቃት ሲደርስብን መከላከያ ሠራዊቱ ቆሞ የሚመለከተው ለምን እንደሆነ መንግሥት ማብራሪያ ሊሰጠን ይገባል፤ ሁኔታው የመንግሥት ፍቃድ ያለበት ይመስላል” በማለት ነው ለአዲስ ማለዳ የገለጹት።
ነዋሪዎቹ እንደተናገሩት ከሆነ “ጥቃቱን ይከላከላሉ ተብለው የተመደቡ የመከላከያ ኃይሎች ግድያዉን ዝም ብለው ከመመልከት ውጪ ምንም አይነት ከለላ እያደረጉ” አይደለም ብለዋል። ይህን ተከትሎም ታጣቂዎቹ በማናለብኝነት በዜጎች ላይ “የግፍ ግፍ’’ እያከናወኑ መሆናቸውን ነው የአካባቢው ነዋሪዎች የተናገሩት።

በዞኑ የሚገኙ ዜጎች በተደጋጋሚ ለመንግሥት ቢያመለክቱም ምንም መፍትሔ ባለመሰጠቱ ምክንያት ችግሩ ተባብሶ በመቀጠሉ በአካባቢው በነጻነት ተንቀሳቅሶ አገልግሎት ማግኘት አስቸጋሪ መሆኑ ተመላክቷል።
ነዋሪዎቹ እንደገለጹት ከሆነ አዛዉንቶች፣ ነፍሰ ጡሮችና ሕፃናትን የሚያጠቡ እናቶች ሸሽተው የማምለጥ አቅማቸው ትንሽ በመሆኑ መንግሥት በአትኩሮት ይጎበኛቸው ዘንድ በተስፋ እየጠበቁ እንደሆነ ተናግረዋል።

ነዋሪዎቹ አያይዘዉም በመተከል ዞን የሚገኙ ዜጎች በየቤታቸው ተዘግተው እንዳሉና ከሚሰነዘረው ጥቃት ለማምለጥ የሚያስችል ምንም አይነት ዋስትና እንደሌላቸው የተናገሩ ሲሆን፣ የገፈቱ ቀማሽ የሆኑት ግለሰቦች የደረሰባቸው ተመሳሳይ ችግር ሳይደርስብን የሚመለከተው አካል በአፋጣኝ ሊደርስልን ይገባል ነው ያሉት።

አዲስ ማለዳ ጉዳዩን በማስመልከት ከቤንሻንጉል ጉምዝ ክልል እና ከመተከል ዞን የሥራ ኃላፊዎች ምላሽ ለማግኘት በተደጋጋሚ ስልክ ብትደውልም መረጃ ለመስጠት ፈቃደኛ ባለመሆናቸው ምላሻቸውን ማካተት አልቻለችም።


ቅጽ 3 ቁጥር 147 ነሐሴ 22 2013

Comments: 0

Your email address will not be published. Required fields are marked with *

error: Content is protected !!