የእለት ዜና

የኦሮሚያ ክልል የነጠቀውን የነዳጅ ዴፖ ማስገንቢያ ቦታን ለመመለስ ተስማማ

በኦሮሚያ ብሔራዊ ክልላዊ መንግሥትና በኢትዮጵያ ነዳጅ አቅራቢ ድርጅት መካከል በነበረውና ተቋርጦ በቆየ ውል መሠረት ከድርጅቱ ተነጥቆ የነበረውን የዱከም የነዳጅ ማጠራቀሚያ ዴፖ ማስገንቢያ ቦታ ለመመለስ የክልሉ መንግሥት መስማማቱ ተነገረ።
የኢትዮጵያ ነዳጅ አቅራቢ ድርጅት ከፍተኛ ነዳጅ የማከማቸት አቅም ያለው የነዳጅ ማከማቻ ዴፖ ለማስገንባት በዱከም ከተማ ወስዶት በነበረው መሬት ላይ ግንባታ ባለማከናወኑ ውሉ ተቋርጦበት የነበረውን መሬት፣ የኦሮሚያ ክልል መልሶ ለመስጠት ከሥምምነት ላይ መድረሳቸውን የኢትዮጵያ ነዳጅ አቅራቢ ድርጅት የሕዝብ ግንኙነት ባለሙያ አለማየሁ ጸጋዬ ለአዲስ ማለዳ ተናግረዋል።

የኢትዮጵያ ነዳጅ አቅራቢ ድርጅት ከሦስት ዓመት በፊት በ2.5 ቢሊዮን ብር ወጪ በዱከም ከተማ ላይ ለማስገንባት አቅዶ ዓለም ዐቀፍ ጨረታ በማውጣት የዲዛይን ግምገማ ተደርጎ የነበረ ቢሆንም፣ በታቀደው ልክ ግንባታውን ማስጀመር አለመቻሉ ታውቋል።
ከተሰጠበት ጊዜ ጀምሮ ምንም አይነት ግንባታ ያልተከናወነበትን መሬት የክልሉ መንግሥት ከድርጅቱ ጋር አስሮት የነበረውን ውል በማቋረጥ ለመውሰድ መገደዱ የሚታወስ ሲሆን፣ አሁን ላይ ግን ከኹለቱም ወገን በኩል በከፍተኛ የመንግሥት ኃላፊዎች መካከል በተደረገ ውይይት መሬቱን ዳግም ለግንባታው ለመመለስ ከሥምምነት መደረሱን የሕዝብ ግንኙነት ባለሙያው ተናግረዋል።

ይህን አይነት ግዙፍ የነዳጅ ማከማቻ ዴፖ ከፍተኛ የሆነ የቴክኖሎጂ ግብዐት የሚያስፈልገው ነው የሚሉት አለማየሁ ጸጋዬ፣ እንደዚህ ያለን ግንባታን ለመገንባት ደግሞ ዓለም ዐቀፍ ጨረታ ማውጣት የሚያስፈልግ መሆኑን ያክላሉ።
ግንባታውን ለማከናወን ከፍተኛ የሆነ የውጭ ምንዛሬ የሚያስፈልገው መሆኑ የተጠቀሰ ሲሆን፣ ይህንንም ለማሟላት ከሦስት ዓመት በፊት ሥራውን በሽርክና ለመስራት ታቅዶ ወደ እንቅስቃሴ ቢገባም፣ ሒደቱ ረጅም ጊዜ በመውሰዱ ምክንያት የግንባታው ሒደት የሚፈለገውን ቅድመ ኹኔታ አሟልቶ ወደ ተግባር መገባት ባለመቻሉ በኦሮሚያ ክልል በኩል ውሉ መቋረጡ ተጠቅሷል።

በቀጣይ ግንባታው በምን አይነት መንገድ ይከወን የሚለው ጉዳይ የመንግሥትን ውሳኔ የሚጠብቅ መሆኑን የሕዝብ ግንኙነት ባለሙያው ገልጸዋል።
በዱከም ከተማ ሊገነባ የታቀደው ግዙፍ የሆነው የነዳጅ ማከማቻ ዴፖ 300 ሚሊዮን ሊትር የተለያዩ አይነት ነዳጆችን ለማጠራቀም እና የአገሪቱን መጠባበቂያ የነዳጅ ክምችት በከፍተኛ መጠን ከፍ ለማድረግ የሚያስችል ፕሮጀክት መሆኑ ተጠቅሷል።

ኢትዮጵያ የሚያስፈልጋትን የነዳጅ ፍላጎት በአብዛኛው በጅቡቲ ወደብ በኩል በመኪና ተጓጉዞ ወደ ተፈለገበት ቦታ የሚከፋፈል መሆኑ ይታወቃል። በዱከም ከተማ ይገነባል ተብሎ የሚጠበቀው የነዳጅ ማከማቻ ዴፖ፣ ቀጥታ አገሪቱ የሚያስፈልጋትን ነዳጅ ከጅቡቲ ወደብ በባቡር በማጓጓዝ ወደ ማከማቻ በማድረስ በመኪና ሲጓጓዝ ይወስድበት የነበረውን ጊዜና ወጪ ያሳጥረዋል ተብሎም ይታሰባል።

በተያየዘ፣ የኢትዮጵያ ነዳጅ አቅራቢ ድርጅት በ2013 በጀት አመት ከሦስት ሚሊዮን ሜትሪክ ቶን በላይ መጠን ያለው ነዳጅ ያቀረበ ሲሆን፣ ለዚህም ከ118 ቢሊዮን ብር በላይ ወጪ ማድረጉ ተነግሯል። ቤንዚን፣ ነጭ ናፍጣ፣ የአውሮፕላን ነዳጅ፣ ቀላል ጥቁር ናፍጣ እና ከባድ ጥቁር ናፍጣ ለአገር ውስጥ ፍጆታ የቀረቡ ዋነኛ የነዳጅ አይነቶች መሆናቸውን አለማየሁ ጸጋዬ ለአዲስ ማለዳ ተናግረዋል።


ቅጽ 3 ቁጥር 147 ነሐሴ 22 2013

Comments: 0

Your email address will not be published. Required fields are marked with *

error: Content is protected !!