የእለት ዜና

በአፋር የተፈናቃዮች ቁጥር ከ 112 ሺሕ በላይ መድረሱ ተገለጸ

በአፋር ክልል በግጭት ምክንያት አካባቢያቸውና እና ቀዬያቸውን ጥለው የተሰደዱ ሰዎች ቁጥር ከ112 ሺሕ በላይ መድረሱ ተገለጸ፡፡
በአፋር ክልል ጦርነቱ በፈጠረባቸው ስጋት ምክንያት ወደ ተለያዩ የክልሉ ከተሞች የተፈናቀሉ ሰዎች ቁጥር ከሳምንት በፊት 76 ሺሕ መሆኑ ተገልጾ የነበረ ሲሆን፣ አሁን ላይ ቁጥሩ አሻቅቦ ከ112 ሺሕ በላይ መድረሱ ታውቋል፡፡

በሰኔ ወር ላይ የፌደራል መንግስቱ የተናጠል የተኩስ አቁም አውጆ የትግራይን ክልል ለቆ ከወጣበት ጊዜ ጀምሮ በአጎራባች ክልሎች ላይ በሽብርተኝነት የተፈረጀው ሕወሓት የከፈተውን ጥቃት በመሸሽ ዜጎች አካባቢያቸውን ጥለው መሰደዳቸው ይታወቃል፡፡
በአፋር ክልል አካባቢያቸውን ጥለው የተሰደዱ ሰዎች ቁጥር ከጊዜ ወደ ጊዜ በመጨመር አሁን ላይ በከፍተኛ መጠን ማሻቀቡን የክልሉ መንግሥት የቅድመ ማስጠንቀቂያ እና ምላሽ ባለሙያ የሆኑት ማሃር አሊ ለአዲስ ማለዳ ተናግረዋል፡፡

ተፈናቃዮቹ ከተለያዩ የክልሉ ክፍሎች የመጡ እንደሆኑ የተጠቀሰ ሲሆን፣ በተለይ ለትግራይ ክልል አጎራባች ከሆኑ አካባቢዎች የሚመጡ ስደተኞች ቁጥር ከፍ ያለ እንደሆነ አንስተዋል፡፡
ስደተኞቹ ያሎ፣ ጉሊና፣ አውራ እና እዋ ከተባሉ አካባቢዎች የመጡ መሆናቸውን የሚገልጹት ባለሙያው፣ ጭፍራ ከተባለም አካባቢ የተፈናቀሉ ወገኖች መኖራቸውንም ተናግረዋል፡፡

እነዚህን ከአካባቢያቸው የተፈናቀሉ ዜጎችን ለመቀበል ይረዳ ዘንድም በክልሉ ስምንት የስደተኛ መጠለያዎች መቋቋማቸውን ገልጸዋል፡፡ በነዚህም የስደተኛ መጠለያ የሚገኙ ስደተኞችን ለመርዳት ክልሉ ከፍተኛ እንቅስቃሴ ላይ እንደሚገኝ ጠመቁመው፣ ይሁን እንጂ የአፋር ብሔራዊ ክልላዊ መንግሥት ብቻውን የሚወጣው ነገር ባለመሆኑ የበጎ ፍቃደኞችን ዕርዳታ ያስፈልጋል ተብሏል፡፡

ተፈናቃዮቹ የሚያስፈልጋቸውን መሠረታዊ የሆኑ እንደ ምግብ፣ መጠለያ እና የጤና አገልግሎት ለማቅረብ ቀይ መስቀልን ጨምር የተለያዩ የረድዔት ድርጅቶች ጋር በጋራ ለመስራት በእንቅስቃሴ ላይ መሆናቸው ታውቋል፡፡
የአፋር ብሔራዊ ክልላዊ መንግሥት ባለው አቅም ለመርዳት ባደረገው እንቅስቃሴ 11 ሺሕ 600 ኩንታል እህል ለተፈናቃዮች ማከፋፈሉን ባለሙያው ተናግረዋል፡፡

የዓለም ምግብ ፕሮግራም (WFP) እና የስደተኞች ተቋም ጋር በመሆን ለተፈናቃዮች የዕለት ዕርዳታ በመደረግ ላይ ይገኛል፡፡ በዚህ ሂደት ለሦስት ወር ያክል የሚሆነውን የምግብ አቅርቦት የዓለም ምግብ ድርጅት ለማቅረብ ከስምምነት ላይ ደርሶ ወደሥራ መግባቱን ማሃር አሊ ለአዲስ ማለዳ ተናግረዋል፡፡

“አፋር ክልል የተወሰነ አቅም ነው ያለው” ያሉት ባለሙያው፣ ከዓለም ዐቀፍ ተቋማት ጋር ለስደተኞች ምግብን ለማቅረብ እየተሄደበት ያለው መንገድ ጥሩ መሆኑን ያነሱ ሲሆን፣ ነገር ግን አሁንም ቢሆን ቁጥሩ ከቀን ወደ ቀን እየጨመረ የመጣውን የተፈናቃዮች መጠን በአግባቡ ለማስተናገድ ይቻል ዘንድ ከፌደራሉም መንግሥት ሆነ ከበጎ አድራጊ ድረጅቶች በኩል ከፍተኛ ጥረት የሚያስፈልግ መሆኑ ገልጸዋል፡፡

በአሁን ወቅት ተፈናቃዮቹ ምንም አይነት የደህንነት ስጋት ሊያጋጥማቸው በማይችልበት ቦታ ላይ ስምንት መጠለያዎች ተሠርተው የገቡ ሲሆን፣ ወደ ፊት ግን የሚፈጠረው ነገር ስለማይታወቅ ከአሁኑ ትልቅ ጥንቃቄ ማድረግ ያስፈልጋል የሚሉት ማሃር አሊ፣ “ከተለያዩ አካባቢዎች ተፈናቅለው የሚመጡት ሰዎች ቁጥር አሁን ባለበት ፍጥነት የሚቀጥል ከሆነ የተፈናቃዮች ቁጥርም በቀናት ውስጥ ከፍ ሊል ይችላል” ሲሉ ሥጋታቸውን ለአዲስ ማለዳ ተናግረዋል፡፡


ቅጽ 3 ቁጥር 147 ነሐሴ 22 2013

Comments: 0

Your email address will not be published. Required fields are marked with *

error: Content is protected !!