የእለት ዜና

ሁዋዌይ በአይሲቲ የፈጠራ ዘርፍ አሸናፊ የሆኑ የአገራችንን ወጣት ተወዳዳሪዎች ሸለመ

ሁዋዌይ ኩባንያ “Connection, Glory, Future” በሚል ርዕስ ሲያካሂድው በቆየው የአይሲቲ ኢትዮጵያ 2013 ውድድር ላይ አሸናፊ የሆኑትን ተወዳዳሪዎች ባሳለፍነው ሀሙስ ነሀሴ 20/2013 በኢንተር ሌግዠሪ ሆቴል ባዘጋጀው መርሃ ግብር ላይ ሸልሟል።
“የኢትዮጵያን የአይሲቲ ተሰጥኦ እና የፈጠራ ሥነ ምህዳር ማልማት” በሚል መሪ ሀሳብ ሁዋዌይ ግንቦት 18 ቀን 2013 በይፋ የተጀመረውን ይህን የፈጠራ ሀሳብ ውድድር፤ ከመላ የአገራችን ክፍሎች የተውጣጡ ከ 1 ሺህ በላይ ተሳታፊዎች የተሳተፋበት እንደነበረ በሽልማት መድረኩ ላይ ተገልጿል።

ተወዳዳሪዎቹ በሰው ሠራሽ አስተውሎት (አርቴፊሻል ኢንተለጀንስ)፣ በቢግ ዴታ፣ በኢንተርኔት ኦፍ ቲንግስ እና በ5Gን በመሰሉ የቅርብ ጊዜ ቴክኖሎጂዎች ላይ ያላቸውን ግንዛቤ በሚፈትን መልኩ በተዘጋጀው በዚህ ውድድር ላይ፤ ከሰባት ዩኒቨርሲቲዎች የተውጣጡ 20 የላቀ ውጤት ያመጡ ተወዳዳሪዎች እና ስድስት ከፍተኛ ፉክክር ያሳዩ ቡድኖች ለፍፃሜ ተወዳድረውበታል።

በግለሰብ ደረጃ ከተወዳደሩትና በተግባራዊ ውድድር የፈጠራ ሃሳባቸውን ካቀረቡት ተማሪዎች መካከል ተማሪ ብስራት ያለው ከአልፋ ዩኒቨርሲቲ በNetwork Track Practical Competition እንዲሁም ተማሪ ስለሺ ንብረት ከአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ በCloud Track Practical Competition ዘርፍ በማሸነፍ በአንደኝነት ውድድሩን አጠናቀዋል።

በሌላኛው የቡድን የፈጠራ ሃሳብ ውድድር ዘርፍ “Innovation Competition” ተወዳዳሪዎች የዕለት ተዕለት የኑሮ ችግሮች የሚፈቱ የፈጠራ ሀሳቦችን በማቅረብ ከፍተኛ ፉክክርን ያሳዩበት ሲሆን፤ ተማሪ እዮቤድ ጥላዬ፣ እዮኤል ጥበቡ እና ኢዘዲን አሊ የተጣመሩበትና ‘ስማርት ሲቲ’ የሚል ስያሜ የተሰጠው የአዲስ አበባ ሳይንስ እና ቴክኖሎጂ ተማሪዎች ቡድን አንደኛ በመውጣት ውድድሩን አሸንፏል፡፡

ቡድኑ በአገራችን የሚስተዋለውን የትራንስፖርት ሥርዓት ችግር ለመቅረፍ የሚረዳና፤ ነገሮች እንዴት እና የት እንደተከሰቱ ለኢትዮጵያ መንገዶች ባለስልጣንና ለሚመለከታቸው አካላት በፍጥነት ማሳወቅ የሚችል ቴክኖሎጂን በመንደፍ ማቅረቡን የሚናገረው ከአሸናፊው የ’ስማርት ሲቲ’ ቡድን አባላት ውስጥ አንዱ የሆነው እዮቤድ ጥላዬ፣ ውድድሩን በማሸነፋቸው የተሰማውን በደስታ በመግለፅ፤ ቀጣይ ለሚመጡ ውድድሮች ከፍተኛ ዝግጅት እንደሚያስፈልግ ታሳቢ በማድረግ ሽልማቱ እንደ ቡድን ጠንክረው የመስራት ተነሳሽነታቸው እንደሚጨምር ለአዲስ ማለዳ አስረድቷል።


ቅጽ 3 ቁጥር 147 ነሐሴ 22 2013

Comments: 0

Your email address will not be published. Required fields are marked with *

error: Content is protected !!