የእለት ዜና

የቲያትር ቤቶች መነቃቃት

ብርሃኑ ተስፉማርያም ይባላል። የአዲስ አበባ ከተማ ነዋሪ የሆነ በንግድ ሥራ ላይ የሚተዳደር ወጣት ነው። የሥራው ሁኔታ ዕረፍት እንደማይሰጠው እና ብዙ ጊዜውን በሥራ ላይ እንደሚያሳልፍ ያስረዳል።
ብርሃኑ በሚኖረው አጭር ጊዜ የተለያዩ ቦታዎች በመሄድ እራሱን ለማዝናናት እንደሚሞክር ለአዲስ ማለዳ ተናግሯል። በዕረፍት ጊዜው የመድረክ ላይ ተውኔቶችን መመልከት እንደሚያስደስተው ይናገራል።
ብርሃኑ የመድረክ ላይ ተውኔቶችን እንዲያዘወተር ከሚያደርጉት ምክንያቶች መካከል አንዱ የሚያደንቃቸውን ተዋንያኖች በቀጥታ ሊመለከት መቻሉን ነው፡፡

በፊልሞች ላይ በሚስተዋለው ከኮፒ ራይት ጉዳይ ጋር የተያያዘ ችግር ምክንያት የመድረክ ላይ ተውኔቶችን መመልከት እንደሚመርጥ ይናገራል።
በአሁኑ ጊዜ የሚሠሩት ፊልሞች በፍጥነት እየተሰረቁ የፊልም አዘጋጆች የሚገባቸውን ሳያገኙ ለኪሳራ እንደሚዳረጉ ያነሳ ሲሆን፣ ይህን እኩይ ተግባር ለማስቀረት እሱም የተሰረቁ ፊልሞችን ባለማየት የድርሻውን እንደሚወጣም አንስቷል።
እንደእሱ ገለፃ ሲኒማ ቤቶች ሒዶ ፊልም ከማየት ይልቅ የመድረክ ላይ ተውኔቶች መመልከት ጥሩ ስሜት እንደሚሰጠው ያስረዳል።

የመድረክ ላይ ተውኔቶች በቀጥታ የሚከናወኑ በመሆናቸው እንደ ፊልሞች በቀላሉ ቤት ተቀምጦ የሚያይበት መንገድ ባይኖርም፣ ሁሌም አዲስ ተውኔት በወጣ ቁጥር ለመታደም እንደሚቸኩል ይጠቁማል። በኮሮና ቫይረስ ወረርሽኝ ምክንያት ተጥሎ የነበረው ክልከላ ከቀረ በኋላ በተለያዩ ማኅበራዊ ገፆች ላይ ማስታወቂያዎች ተመልክቶ ቲአትር እንደሚመለከት ይናገራል።

ሌላዋ ሐሳቧን ያካፈለችን ተማሪ ዮርዳኖስ ትዕግስቱ ነች። ያላትን ጊዜ በትምህርት እንደምታሳልፍ እና የዕረፍት ቀኗ የሆኑትን ቅዳሜ ወይም እሁድን ግን የተለያዩ የመድረክ ላይ ተውኔቶች በመመልከት ስታሳልፍ ደስታ እንደሚፈጥርላት ታነሳለች።
እንደ አሷ አተያይ የመድረክ ላይ ተውኔቶች ምንም አይነት ማስተካከያ ሳይደረግባቸው በቀጥታ ለተመልካች የሚቀርቡ በመሆናቸው የተዋንያኖቹን ልዩ ችሎታ ለመቃኘት እና የመድረክ ላይ ብቃታቸውን ለማድነቅ እንደሚያስችላት ትናገራለች።

የመድረክ ላይ ተውኔቶች በምትመለከትበት ጊዜ በቦታው የሚገኙ ታዳሚያን የሚሰጡት አስተያየት እና የሚኖረው ድባብ ስለሚያስደስታት በሚኖራት የዕረፍት ቀን ቴአትር እንድትመለከት ምክንያት ሆኗታል።
እሷ ለመመልከት ከምትመርጣቸው የመድረክ ላይ ተውኔቶች መካከል በዋነኛነት ቀልቧን የሚገዟት ሙዚቃዊ ተውኔቶች ናቸው።

መዚቃዊ ተውኔቶች ተመልካች ሳይሰለች ለረጅም ሰዓታት እንዲታደም ያደርጉታል ብላ ታምናለች።
ብዙ ጊዜ ቴአትር ቤት የምትሄደው ከጓደኞቿ ጋር ሲሆን፣ አሁን ቴአትር ቤቶች ሙሉ በሙሉ ሥራ ጀመረው የቴአትር ዘርፉ እንዲነቃቃ በመድረጉ እንዳስደሰታት አንስታለች።
በአገራችን ብሎም በዓለማችን ላይ የተከሰተው የኮቪድ ወረርሽኝ በኪነጥበቡ የሥራ ዘርፍ ላይ እጅግ ከፍተኛ የሚባል ጫና አሳድሮበት ነበር።

የመድረክ ላይ ተውኔቶች ከኮቪድ 19 መከሰት በፊትም መቀዛቀዝ የነበረባቸው ቢሆንም፣ ከወረርሽኙ በስፋት መሰራጨት ጋር በተያያዘ ቴአትር ቤቶች ሙሉ በሙሉ እንዲዘጉ በመደረጋቸው ምክንያት ገቢ ማስገባት አቁመው ነበር። የቴአትር ቤቶች ለተመልካች ዝግ በመሆናቸው እና ገቢ ባለመገኘቱ ምክንያት የዘርፉ ባለሙያዎችም ትልቅ ኪሳራ ውስጥ የገቡበት እና በፈተና ውስጥ የቆዩበት ሁኔታ ተፈጥሮ እንደነበር ይታወሳል።

ወረርሽኙ በአገር ውስጥ ከመከሰቱም በፊት በቴአትር ቤቶች ላይ ከፍተኛ የሆነ መቀዛቀዝ እንደነበር የሚታወቅ ሲሆን፣ በተለያዩ ችግሮች ምክንያት የመድረክ ላይ ትዕይንት እንደ ሌሎች የኪነጥበብ ሥራዎች በስፋት ሳይሠራበት ቀርቶ ነበር።
ቴአትር መቀዛቀዙ፣ እንዲሁም የኮቪድ 19 ወረርሽኝ በቴአትር ቤቶችና በባለሙያዎቹ የገቢ ምንጭ ላይ ባሳደረው ተፅዕኖ ምክንያት፣ የዘርፉ ባለሙያዎች የቴአትር ንቅናቄ እንዲጀምሩ ምክንያት ሆኗቸዋል።

“ስለ ቴአትር” ዓላማው ቴአትርን በማኅበረሰቡ ላይ ርዕሰ ጉዳይ አድርጎ በኮቪድ ምክንያት የተዘጉ የቴአትር ቤቶች እንዲከፈቱ እና ሙያው እንዳይጠፋ ማድረግ እንደሆነ የስለ ቴአትር ንቅናቄ አስተባባሪ የሆኑት የቴአትር ባለሙያና የፊልም ደራሲ መአዛ ወርቁ ለአዲስ ማለዳ ተናግረዋል።

እንደ መአዛ ገለፃ በኮሮና ቫይረስ ወረርሽኝ ምክንያት የተቋረጡ የቴአትር መድረኮች ዳግም መነቃቃት እየታየባቸው እንደሚገኝ አስታውቀዋል። የኮቪድ 19 ወረርሽኝ በአገራችን በመከሰቱ ምክንያት በወጣው አስቸኳይ ጊዜ ዐዋጅ የቴአትር ቤቶች ሙሉ በሙሉ ተዘግተው እንደነበር አስታውሰዋል።

የቴአትር ቤቶች በኮቪድ 19 ወረርሽኝ ምክንያት ለተመልካች ዝግ በመሆናቸው እና ገቢ ማግኘት ባለመቻሉ የዘርፉ ባለሙያዎች ከፍተኛ ጫና ውስጥ የገቡበት ሁኔታ እንደነበርም ተናግረዋል።
እንደ መአዛ ገለፃ፣ በወረርሽኙ ምክንያት የወጣው አስቸኳይ አዋጅ በመንግሥት ማሻሻያ ከተደረገበት በኋላ በኪነጥበብ ዘርፍ ላይ ግን ምንም አይነት ለውጥ እንዳልነበር አንስተዋል።

ሆኖም ግን በቴአትር ቤቶች ላይ ወረርሽኙ ያስከተለውን ችግር ለመፍታት ከሌሎች በጎ ፈቃድኛ የጥበብ ባለሙያዎች ጋር በመሆን “ስለ ቴአትር” የተሰኘ የንቅናቄ መድረክን ለማዘጋጀት እንደቻሉ አስረድተዋል። ንቅናቄው ማኅበራዊ ሚዲያዎችን በመጠቀም የተጀመረ ሲሆን፣ አሁንም ተጠናክሮ እየቀጠለ እንደሆነ ጠቅሰዋል።

በወረርሽኙ ምክንያት ሙሉ በሙሉ ተዘግተው የነበሩት የቴአትር ቤቶች ዳግም ሲከፈቱ የተመልካች መነቃቃት በመታየቱ የተጀመረው እንቅስቃሴ ውጤታማ መፍትሄ ማምጣት መቻሉን ማሳያ ሊሆን እንደሚችል ተናግረዋል።
መዓዛ አክለውም ከነሐሴ 21 እስከ 25 ድረስ የኢትዮጵያን የቴአትር እንድ መቶኛ ዓመት በማስመልከት የተለያዪ ይዘት ያላቸውን 50 ቴአትሮችን ለተመልካች የማቅረብ ዕቅድ ይዘው እየሠሩ እንደሚገኙ አስታውቀዋል።

ከዚህ ጋር በተያያዘ የኢትዮጵያን ቴአትር መቶኛ ዓመት አስመልክቶ እንዲሁም የኮቪድ ወረርሽኝ በዘርፉ ላይ ያሳደረውን ጫና ለመቅረፍ በታሰበው የቴአትር ፌስቲቫል ላይ የሚሳተፉ ተመልካቾች ወረርሽኙን ለመቆጣጠር እና ለመከላከል በጤና ሚኒስቴር የወጣውን መመሪያ ተግባራዊ ባደረገ መልኩ እንደሚታደሙ ጠቁመዋል።

ስለ ቴአትር የተሰኘው ንቅናቄ በበጎ ፍቃደኞች በአገሪቷን ላይ የሚስተዋለውን የቴአትር ችግር ለመፍታት የተመሠረተ ነው፡፡ ለዚህም ሲባል ባለሙያዎቹ የሚጠበቅባቸውን እየተወጡ እንደሚገኙ ለአዲስ ማለዳ ተናግረዋል። መአዛ ቴአትርን ጉዳያቸው ካደረጉ ሰዎች እና ተቋማት ጋር በኅብረት እየሠሩ እንደሚገኙም ጠቅሰዋል። በአሁኑ ወቅት የሚስተዋለው የቴአትር መነቃቃት ዳግም እንዳይቀዛቀዝ የኢትዮጵያ የቴአትር ማኅበር ከክልል ዩንቨርስቲዎች ጋር ጠንካራ የሆነ ግንኙነት ፈጥሮ እየተንቀሳቀሰ እንደሚገኝ ማንሳት ችለዋል።

መአዛ፣ የኢትዮጵያ ቴአትርን መቶኛ ዓመት ምክንያት በማድረግ ከነሐሴ 21 እስከ ነሐሴ 25 በሚቆየው ዝግጅት ከተለያዩ የአገሪቷ ክፍሎች የተውጣጡ፣ እንዲሁም በተለያዩ የአገሪቷ ቋንቋዎች የተዘጋጁ 50 የሚደርሱ የመድረክ ላይ ተውኔቶች ለተመልካች የሚቀርቡበት ሁኔታ መኖሩን አስታውቀዋል።

ከወራት በፊት በተመልካች ይታዩ ከነበሩ የመድረክ ላይ ተውኔቶች አንፃር፣ ስለ ቴአትር የተሰኘው ንቅናቄ በበጎ ፍቃደኛ ባለሙያዎች መጀመሩ አሁን ለሚስተዋለው የቴአትር መነቃቃት ምክንያት ሆኗል ብለዋል።
የቴአትር መነቃቃትን ተከትሎ የመድረክ ላይ ትርኢት የሚያሳዩ ቦታዎች እየበዙ መምጣታቸውን የጠቀሱት መአዛ፣ በዚህ ጊዜ ሥራ ያልጀመሩ የቴአትር ቤቶች በፍጥነት እድሳታቸውን አጠናቀው ቢገቡና ትርኢቶችን ለተመልካች ማሳየት ቢጀምሩ ከፍተኛ ጥቅም ማግኘት እንደሚችሉ ተናግረዋል።

የመድረክ ላይ ትርኢቶችን በ7 ማሳያ ቦታዎች ላይ ለተመልካች እየቀረቡ እንደሚገኙ አስታውቀዋል። ከነዚህም መካከል ብሔራዊ ቴአትር፣ ሀገር ፍቅር ቴአትር፣ ኦሮሚያ የባህል ማዕከል፣ አምባሳደር ሲኒማ፣ ሴንቼሪ ሞል፣ ኤድናሞል፣ አለም ሲኒማ፣ እንዲሁም አዶት ሲኒማ የመድረክ ላይ ትርኢት ለተመልካች እንደሚያቀርቡ የስለ ቴአትር ንቅናቄ አስተባባሪ የሆኑት የቴአትር ባለሙያና የፊልም ደራሲ መአዛ ወርቁ ለአዲስ ማለዳ ተናግረዋል።

የኢትዮጵያ ዘመናዊ ቲያትር በኢትዮጵያ የተጀመረበትን 100ኛ ዓመት በማስመልከት ሰፊ ሃገር አቅፍ ፌስቲቫል እንደሚካሄድ ነሐሴ 18/2013 በተጠራው ጋዜጣዊ መግለጫ ላይ የኢትዮጵያ ቲያትር በጎ ፈቃደኛ ባለሞያ እና የሀገር ፍቅር ቲያትር ስራ አስኪያጅ አብዱከሪም ጀማል አስታውቀዋል።

የስለ ቲያትር በጎ ፈቃደኛ አስተባባሪ እንደሆኑት መዓዛ ወርቁ ገለፃ፣ በስለ ቲያትር የበጎ ፈቃድ ባለሙያዎች በተጀመረው የቲያትር መነቃቃት ላይ ያጋጠሙ ችግሮች እንደነበሩም አንስተዋል፡፡ ከነዚህም መካከል የአመለካከት ችግር መፈጠሩን፣ በቲያትር ባለሞያዎች በጎ ፍቃደኝነት ላይ የተመሰረተ በመሆኑ የገንዘብ እጥረት እንደተፈጠረ፣ እንዲሁም በመንግስት መስሪያ ቤቶች ስር ያሉ ተቋማት የድጋፍ ችግር ተፈጥሮባቸው እንደነበር ተናግረዋል።

ዘመናዊ የኢትዮጵያ ቲያትር መጀመር መቶኛ ዓመት በማስመልከት አንድ መቶ ቲያትሮችን ለተመልካች ዕይታ የማቅረብ ዕቅድ ይዘው የነበር ሲሆን፣ 48 የተለያየ ይዘት ያላቸውን አጫጭር እና የሙሉ ጊዜ ቲያትሮችን ብቻ ለተመልካች ዕይታ ማቅረብ እንደቻሉም ጠቅሰዋል።


ቅጽ 3 ቁጥር 147 ነሐሴ 22 2013

Comments: 0

Your email address will not be published. Required fields are marked with *

error: Content is protected !!