የእለት ዜና

የኮቪድ ክትባት በኢትዮጵያ

ክትባት በሽታን የማስቀረት የቅድመ መከላከል ተግባር ያለው ሲሆን፣ የኮቪድ 19 ወረርሽኝ ከገባ በኋላ ክትባቶቹን ለማግኘት ከፍተኛ ጥረት ሲደረግ ነበር።
ክትባቶቹ ከተገኙ በኋላም ሰዎች ላይ ተግባራዊ ለማድረግ የሚመለከታቸው ተቋማት እንደ ምግብና መድኃኒት ቁጥጥር ባለሥልጣንና የዓለም የጤና ድርጅት ፈቃድ መስጠት አለባቸው የሚሉት በጤና ሚኒስቴር የኮቪድ ወረርሽኝ ምላሽ ግብረ-ኃይል አስተባባሪ መብራቱ ማሴቦ ናቸው።

እስከአሁን ሙሉ በሙሉ ፍቃድ ያገኘው ፋይዘር የተሰኘው አሜሪካ አገር የተመረተው ክትባት መሆኑን የገለፁት መብራቱ፣ በዓለም ምርምር ላይ የሚገኙ 68 የሚጠጉ ክትባቶች መኖራቸዎን ይናገራሉ።
ከነዚህ የዓለም ጤና ድርጅት ፈቃድ ከሰጣቸው ውስጥ 6 ወደ አገራችን ገብተው አገልግሎት ላይ እየዋሉ መሆኑን ነው መብራቱ ያነሱት። የምግብና መድኃኒት ቁጥጥር ባለሥልጣን፣ በጤና ሚኒስቴር ስር የሚገኙ አማካሪዎች እና ገለልተኛ ባለሙያዎች ባደረጉት ጥናት ክትባቶቹ ወደ ኢትዮጵያ ቢገቡ ችግር አያመጡም ተብሏል።

ከእነዚህም ውስጥ ወደ ኢትዮጵያ የገቡት ሦስት ሲሆኑ ሲኖቫክ፣ አስትራዘኒካ እና ጆንሰን ኤንድ ጆንሰን መሆናቸው ታውቋል።
ሲኖቫክ የቻይና ምርት ሲሆን፣ የዓለም ጤና ድርጅትን መሥፈርት አሟልቶ ፍቃድ ያገኘ ክትባት ነው። በአገራችንም ወደ አንድ ሚሊዮን የሚደርስ ብዛት ገብቷል። በመጀመሪያ 2.2 ሚሊዮን ክትባት የገባውና ሥራ ላይ የዋለው አስትራዘኒካ ይባላል። የአስትራዘኒካ ክትባት ባለቤት ኦክስፎርድ ዩኒቨርስቲ ሲሆን፣ በኢትዮጵያ ውስጥ በብዛት የገባ የክትባት አይነት ነው። አስትራዘኒካ እና ሲኖቫክ ኹለት ዙር የሚሰጡ ሲሆን፣ አስትራዘኒካ በሦሰት ወር የጊዜ ልዩነት ውስጥ እንደሚወሰድ ተጠቅሷል።

ሲኖቫክ ደግሞ የመጀመሪያው ከተሰጠ በ28 ቀን ውስጥ የሚሰጥ ነው። የመጀመሪያው ዙር የተወሰነ የመከላከል አቅም ካዳበረ በኋላ ኹለተኛው ዙር ላይ ከፍተኛ ደረጃ ለማድረስ ያስችላል ሲሉም መብራቱ ገልጸዋል። ከተከተቡ በኋላ ቢያዙ እንኳን በፍጥነት ወደ ጽኑ ሕሙማን እንዳይገቡ እና ለሞት እንዳይደረጉ ይረዳሉ ብለዋል።

ክትባቶቹ፣ አምራቹ በሚያዘጋጀው ኹኔታ እና ባላቸው የቴክኒካል አተገባበር በመረዳት እንዳመራረታቸው የሚሰጡ ናቸው። ሌላኛው ወደኢትዮጵያ የገባው ክትባት ጆንሰን ኤንድ ጆንሰን ይባላል። ባለቤትነቱ በአሜሪካ የሆነው ይህ ክትባት በመጀመሪያ ዙር ወደ 413 ሺሕ እና በቀጣይ ዙር ወደ 1.6 ሚሊዮን ክትባቶች ማስገባት ተችሏል። ጆንሰን ኤንድ ጆንሰን ባህሪው አንድ ጊዜ ብቻ የሚሰጥ ሲሆን፣ በአገራችን እየተተገበሩ ከሚገኙ የክትባት አይነቶች አንዱ ነው ሲሉ መብራቱ ለአዲስ ማለዳ ገልጸዋል።

በጤና ሚኒስቴር በተያዘው የክትባት ተደራሽነት መሠረት በአንድ ዓመት ውስጥ ማለትም በፈረንጆቹ 2021 ከኢትዮጵያን ሕዝብ ብዛት 20 በመቶውን ተደራሽ ለማድረግ የታቀደ ሲሆን፣ ቅድሚያ የሚሰጣቸው አቅመ ደካሞች፣ ተጓዳኝ በሽታ ያለባቸው እና ለበሽታው ተጋላጭ የሚያደርግ ሥራ የሚሠሩ ግለሰቦችን ይሆናሉ ተብሏል።

በኢትዮጵያ ከ18 ዓመት ዕድሜ በላይ የሆነ ኹሉንም የማኅበረሰብ ክፍል ለመከተብ የታሰበ ሲሆን፣ ክትባቱ በባህሪው በዓለም ዐቀፍ ደረጃ ከ12 ዓመት በታች ላሉ ዜጎች የማይሰጥ መሆኑ ተቀምጧል።
ከ12 ዓመት ዕድሜ በታች ሕፃናት የክትባቱ ፈዋሽነት ስላልተረጋገጠ ክትባቱን እንደማይወስዱ መብራቱ አረጋግጠዋል። በአዲስ አበባ የሦስተኛው ዙር ቫይረስ ስለተከሰተ፣ እስከ አንድ ሚሊዮን የአዲስ አበባ ነዋሪን ለመከተብ ታቅዷል። ከተማዋ ላይ በከፍተኛ ኹኔታ የበሽታው ሥርጭት ሊስፋፋ የሚችልባቸውን ቦታዎች በመለየትም ነው ለመከተብ የታቀደው። የተገኘውን ክትባት ለአብዛኘው ማኅበረሰብ ተደራሽ በማድረግ የመከላከል አቅምን መጨመር በጤና ሚኒስቴር ከተያዘ ዕቅድ ውስጥ አንዱ ነው ብለዋል።

93 አገራት በአንድ ላይ በመሆን ኮቫክስ የተባለ ቡድን መሥርተው ክትባቶች ወደየአገራቱ እንዲገቡ ያደርጋሉ። ይህ ቡድን ከዓለም የጤና ድርጅት እና ከ93 አገራት በተውጣጡ ሊቃነመናብርት የሚመራ ሲሆን፣ ክትባቶች በስጦታ፣ በብድር እና በተለያዩ ዓለም ዐቀፍ የገንዘብ ማግኛ መንገዶች ወደ ተለያዩ አገራት እንዲገቡ የሚያደርጉ ናቸው።

ክትባት የተከተቡ ሰዎች ኮቪድ የሚይዛቸው አዲስ የቫይረስ ዝርያ ስለሆነ ነው። አዲስ የመጣ መሆኑ ብቻ ሳይሆን ክትባቶች መቶ በመቶ ከበሽታ አይከላከሉም። የኮቪድ 19 ክትባት ዋና ዓላማ በቫይረሱ የሚሞቱ እና ጽኑ ሕሙማንን ቁጥር መቀነስን ያለመ ነው።
ክትባቱ የመከላከል አቅሙ ከሰው ሰው የሚለያይ ሲሆን፣ አንዳንድ ሰዎች ላይ መሉ ለሙሉ በሽታው እንዳይዛቸው የሚያደርግ ነው። ኮቪድ አንዳንድ ጊዜ የተያዘው ሰው ላይ ሳይበረታ ወደ ሌላ ሰው በማስተላለፍ ሌላ ሰው እንዲጎዳ ያደርጋል። ስለዚህ ክትባት ደግሞ የበሽታ የመከላከል አቅምን ለማሳደግ ስለሚረዳ ሰውዬው የሚያመርተው የበሽታ መከላከል አቅም ክትባቱ ሲጨመረበት ይዳብርለታል። ከዚህ በተጨማሪ አንድ ሰው በአቅራቢያው ያሉ በሙሉ ካልተከተቡ ያሰው ስለተከተበ ብቻ አይድንም ሲሉ መብራቱ በስፋት አስረድተዋል።
አብዛኛው ሰው የመከተብ ዕድል እያገኘ ቢሆንም፣ ኹሉም ሰው በጠቅላላ ካልተከተበ በስተቀር ወረርሽኙ ማቆም አይቻልም ብለዋል።

ማንኛውም ክትባት የራሱ የሆነ የጎንዮሽ ጉዳት አለው። በተለይ ደግሞ አንዳንድ ሰዎች ላይ ክትባቱ አለርጂክ ሆኖባቸው ከፍተኛ ሕመም ሊሰማቸው ይችላል። በዚህ ጊዜ ማስታገሻ ተዘጋጅቶ እሱን እንዲወስዱ ይደረጋል። መቋቋም የሚቻሉ እንደ ትኩሳት፣ የሰውነት መድከም የመሳሰሉት ምልክቶች ካጋጠሙ ግን፣ ክትባቱ ወደ ሰውነታችን እየተሰራጨ መሆኑን ማሳያ ስለሆነ የመከላከል አቅማችንን እየጨመረ መሆኑን መገንዘብ ያስፈልጋል። እንደዚህ አይነት ቀላል ምልክቶች ሲኖሩ እረፍት በማድረግና ፈሳሸ በመውሰድ መከላከል ይቻላል። ክትባቱ እንደዚህ አይነት ባህሪ በሚያሳይ ወቅት ኮቪድ እንደተያዘ ማሰብ የተሳሳተ መሆኑን ነው የጠቆሙት።

ኢትዮጵያ ውስጥ መደበኛ ክትባት በሚሰጥባቸው ጤና ጣቢያዎች በመሉ የኮቪድ ክትባት የሚሰጥ ሲሆን፣ ለበሽታው ተጋላጭ ናቸው የሚባሉት የማኅበረሰብ ክፍሎች በቅድሚያ ማግኘት ይችላሉ።
የኮቪድ ክትባት በኢትዮጵያ ውስጥ እየተሰጠው ያለው ምልከታ የተሳሳተ ነው። ባልተረጋገጡና ሳይንሳዊ ባልሆኑ መረጃዎች ስለክትባቱ የተሳሳተ አመለካከት ሊኖር አይገባም። በዚህ የተሳሳተ ምልከታ ሕይወታቸውን ያጡ እንዳሉ ሊታወቅ ይገባል። በክትባቱ ዙሪያ የሚሰጡ የተሳሳቱ መረጃዎች ክትባቱን ሰዎች እንዳይወሰዱ እያደረገ ስለሆነ ሕብረተሰቡ ጠቀሜታውን ይበልጥ መገንዘብ እንዳለበት መብራቱ ጠቁመዋል።


ሕብረተሰቡ በሕገ-ወጥ መንገድ ከሚቀርቡ የኮቪድ-19 ክትባቶች መቆጠብ እንደሚገባው ተገለጸ

የጤና ሚኒስቴር ሕብረተሰቡ በሕገ-ወጥ መንገድ ከሚቀርቡ የኮቪድ 19 ክትባቶችም ሆነ መድኃኒቶች ራሱን መጠበቅ እንደሚገባ አስታወቀ።
ሕብረተሰቡ የኮቪድ-19 ክትባቶችንም ሆነ ሌሎች መድኃኒቶችን በሕገ-ወጥ መንገድ ከሚያቀርቡ ሰዎች ራሱን መጠበቅ እና ለፖሊስ መጠቆም እንደሚገባው ሚኒስቴር መሥሪያ ቤቱ አስታውቋል።

ለሕብረተሰቡ የኮቪድ-19 ክትባቶች የሚሰጡት በመንግሥታዊ ጤና ተቋማት በነፃ ብቻ መሆኑን አውቆ ከሕገ-ወጦች ራሱን መጠበቅ እንዳለበት አሳስቧል።
በአራዳ ክፍለ ከተማ በተለምዶ ደጃች ዉቤ አካባቢ የኮቪድ-19 መከላከያ ክትባቶችን በሕገ-ወጥ መንገድ ሲገበያዩ የነበሩ ግለሰቦች በአዲስ አበባ ፖሊስ በቁጥጥር ስር ውለው ምርመራ እየተደረገባቸው መሆኑን አስታውሷል።

የ ኮቪድ-19 ክትባቶች ከጤና ሚኒስቴር ካዘጋጀው ኘሮግራም ውጭ ለመገበያየት መሞከር በአያያዙና በአወሳሰዱ ላይ እክል የሚፈጥር በመሆኑና ጉዳቱ የከፋ ስለሚሆን ሕብረተሰቡ ጥንቃቄ ሊያደርግ ይገባል ሲል ነው ጤና ሚኒስቴር ያስታወቀው።
ሕገ-ወጦችንም በመከታተል ማጋለጥ እንዲሁም በሕገ-ወጥ መንገድ ክትባቶቹን የሚገበያዩትን በመጠቆም በቁጥጥር ሥር እንዲውሉ ማድረግ ይገባል ሲል ተቋሙ ገልጿል።

ሕብረተሰቡ የኮቪድ 19 ክትባትንም ሆነ ሌሎች ተያያዥ መረጃዎችን ጤና ሚኒስቴርና የኢትዮጵያ ሕብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት የሚያወጡት ብቻ በመጠቀም ከእውነት ከራቁ ሐሰተኛ መረጃዎች ራሱን እንዲጠብቅ አሳስቧል።


ቅጽ 3 ቁጥር 147 ነሐሴ 22 2013

Comments: 0

Your email address will not be published. Required fields are marked with *

error: Content is protected !!