የእለት ዜና

ንግድ ወይስ አላግባብ መበልጸግ

Views: 315

ነጻ የኢኮኖሚ ሥርዓትን የሚከተሉ አገራት ለነጋዴዎቻቸው በፈለጉት ዋጋ እንዲሸጡ ይፈቅዱላቸዋል። መሠረታዊ ፍጆታዎችን ወይም ታሪፍ ወጥቶላቸው በመንግሥት ድጎማ የሚቀርቡትን ግን ይቆጣጠራሉ። ነጻ ገበያ ነው እየተባለ ቢነገርም፣ ሆን ተብሎ ሸቀጥን እያከማቹ ዋጋ እንዲጨምር ማድረግ አይቻልም። በዚህ አይነት ሕገ-ወጥ መንገድ የሚገኝን ሀብት “አላግባብ መበልጸግ” በሚል የሕግ አንቀፅ እንደሚያስቀጣ የሕግ ባለሙያዎች ይናገራሉ።

አንድ ሰው በተሰማራበት የንግድ ዘርፍ ማትረፍ የሚችለው አስከ 15 በመቶ ነው ቢባልም፣ እውነታው ግን ከ100 በመቶ በላይም ይሄዳል። ከውጭ የሚገቡትን ለመቆጣጠር የተገዙበትን ዋጋና አጠቃላይ ወጪያቸውን ማወቁ አስቸጋሪ ቢሆንም፣ እዚሁ የሚመረቱትን ሲሚንቶ የመሳሰሉትን የሚመረቱበትንም ሆነ የሚከፋፈሉበትንና የሚቸረቸሩበትን ዋጋ ለማወቅ አያስቸግርም።

ይህን ያነሳነው በያዝነው ሳምንት ከሲሚንቶ ንግድ ጋር በማኅበራዊ ሚዲያ መነጋገሪያ የሆነ ጉዳይ ተከስቶ ስለነበር ነው። አንድ ማንነቱን የማንነግራችሁ ግለሰብ ሲሚንቶ መነገድ ከጀመረ ከ6 ወራት በኋላ የ2021 ሞዴል የሆነች ሬንጅ ሮቨር መኪና መግዛት ቻለ ብሎ ጓደኛው የለጠፈውን ተመርኩዞ የተሰጡ አስተያየቶች ናቸው። መኪናው ግብርን ሳይጨምር መግዣው ብቻ ወደ 5 ሚሊዮን ሲሆን፣ የቅንጦት እንደመሆኑ ግብሩም በተመሳሳይ በሚሊዮኖች እንደሚሆን ይታወቃል።

ወደ ሲሚንቶ ንግድ ገብቶ በዚህ በአጭር ጊዜ ይህን ያህል የሚያወጣ መኪና መግዛቱ የንግድ ሥርዓቱ ምን ያህል እንደተዛባ ያሳያል ሲሉ ብዙዎች ተችተውታል። ፋብሪካዎች በ400 ብር የሚያቀርቡትን ምርት ከእጥፍ በላይ እየሸጡ ሊገርመን አይገባም ያሉም ነበሩ። “መብቱ ነው ነጻ ገበያ ነው” ብሎ የተከራከረለት ባይኖርም፣ ብዙዎች በዘርፉ ያለውን ችግር ቁልጭ አድርጎ የሚያሳይ ነው ብለውታል።

መንግሥት ቁጥጥሩን አንስቶም ሆነ ተቆጣጥሮ ለውጥ ማምጣት ባለመቻሉ ችግሩ እንዳለ ይታመናል። “ሕገ-ወጥ ደላሎች” እየተባለ የዳቦ ስም የተሰጣቸው ዋጋውን የሚያንሩትን ኹሉም እንደሚያውቃቸው የተናገሩ አሉ። ከፋብሪካዎቹ እነማን ገዝተው እንደሚቸረችሩ በግልጽ ይታወቃል ያሉ አስተያየት ሰጪዎች፣ በሞኖፖል የያዙት ስለሆነ ተመሳጥረው እንደፈለጉ ለማድረግ ይጠቅማቸዋል ሲሉ ስር የሰደደ ችግር እንደሆነ ጠቅሰዋል።

በተለያዩ ዘርፎች የሚነግዱ ላይ የሚስተዋል ችግር ነው የሚሉ በርካቶች ሲሆኑ፣ ነጋዴዎች ለሕዝብ ማሰብ መተዋቸውን የሚያሳይ፣ እርስበርስ ከመፎካከር ይልቅ ተስማምተው አገርና ሕዝብን የሚበዘብዙበት እንደሆነ ካስተዋሉት ተነስተው አስተያየታቸውን ይሰነዝራሉ። መነጋገሪያ የሆነው የሲሚንቶ ነጋዴውን የመሳሰሉ አቅም ያላቸው ከበርቴዎች፣ የበቃኝ አስተሳሰብ ስለሌላቸውና የሚያስቆማቸው እስከሌለ ለማንም እንደማያዝኑ በርካቶች ይናገራሉ። ሕዝብን ማደኽየት ዞሮ ዞሮ ራስን ድሃ ማድረግ እንደሆነ እስኪገባቸው፣ ምን ጨነቀኝ የሚሉትን እስኪጨንቃቸው ማስተማር ተገቢ መሆኑን ብዙዎች አንጸባርቀዋል።


ቅጽ 3 ቁጥር 147 ነሐሴ 22 2013

Comments: 0

Your email address will not be published. Required fields are marked with *

This site is protected by wp-copyrightpro.com