የእለት ዜና

የግጭት መንስዔዎችና የዕርቅ መንገዶች፡- ከሥነ-ልቦና አኳያ

የሠላምና ልማት ማዕከል ለትርፍ ያልተቋቋም፣ መንግሥታዊ ያልሆነ አገር በቀል ድርጅት ሲሆን፣ ከማንኛውም የፖለቲካም ሆነ የሌላ ወገንተኝነት የጸዳ፣ በአገሪቱ የሠላም ባህል እንዲስፋፋ፣ በውይይት እና በንግግር የሚያምን ማሕበረሰብን ለመፍጠር የሚሰራ ተቋም ነው።
ተቋሙ ከተመሰረተበት 1982 ዓ/ም አነስቶ በተለያዩ የሠላም ግንባታ ሥራዎች ላይ ተሰማርቶ በመንቀሳቀስ ላይ ይገኛል። በተለይም ደግሞ ግጭትን ለመፍታት እና የሠላም ባህልን ለመገንባት የሚያስችሉ አገር በቀል እውቀቶችን በማዳበር በተለያዩ አካባቢዎች የሚከሰቱ አለመግባባቶች በውይይት እንዲፈቱ ሲያደርግ ቆይቷል። በተለይም ደግሞ በቦታ እና በሁኔታ አለመመቸት ምክንያት ለብዙ ተቋማት ለመድረስ አመቺ አይደሉም የሚባሉ የአገራችን አካባቢዎች ጭምር ሳይቀር በመግባት ከታችኛው የማሕበረሰብ አደረጃጀቶች ጋር ሰፊ የሠላም ግንባታ ሥራዎችን በማከናወን ላይ ይገኛል። ተቋሙም በተሰማራበት የሥራ ዘርፍ ምንም እንኳ እንደአገር ያለብን ችግር ዘርፈ ብዙ እና ሰፊ ቢሆንም የአቅሙን በማበርከት ላይ ከመሆኑም በላይ አመርቂ የሚባሉ ውጤቶችን በማስመዝገብ ላይ ይገኛል። ተቋሙም አሁን ያሉ ፕሮጅክቶችን በማስፋት እና ወደተጨማሪ ቦታዎች በመንቀሳቀስ፣ እንዲሁም የተለያዩ ማሕረሰብ አቀፍ የሆኑ የሰላም ጥረቶችን በመደገፍ እንዲሁም አቅማቸውን ጭምር በመገንባት ለችግሮች ተመጣጣኝ የሆነ ምላሽ ለመስጠት የበኩሉን አስተዋፅኦ በማበርከት የሚቀጥል ይሆናል።
ሠላምና ልማት ማዕከል

በቡራዩና አዲስ አበባ ወጣቶች መካከል ተከስቶ የነበረውን ግጭት ተከትሎ የኹለቱን አካባቢ ወጣቶች አቀራርቦ በመካከላቸው ዕርቅ ለማውረድ በሠላምና ልማት ማዕከል አስተባባሪነት የተከናወነውን ተግባር በተከታታይ ዕትሞች ስናቀርብላችሁ ቆይተናል። ይህን መልካም ጅማሮ በማስመልከት ስለግጭት መንስዔዎች፣ እንዲሁም ምን አይነት የዕርቅ መንገዶች በዘላቂነት ለውጥ ያመጣሉ ብለን የሥነ-ልቦና ባለሙያ አነጋግረናል። ሰው ወደ ግጭት የሚያመራበትን ሥነ-ልቦናዊ ምክንያቶችን በተመለከተ፣ እንዲሁም ከሥነ-ልቦና አኳያ ዕርቀ ሠላም እንዴት ማውረድ እንደሚቻልና የዕርቅ አስፈላጊነትን በተመለከተ፣ የዕርቅ ማዕድ ሚዲያና ኮሚዩኒኬሽን የሥነ-ልቦና ማማከር አገልግሎት ባለሙያ የሆኑትን ቃልኪዳን ኃይሉን አነጋግረናል።

ባለሙያዋ ወጣቶችን ወደ ግጭት የሚመራቸው ዋናው ምክንያት አስተዳደጋቸው ነው ይላሉ። ያደግንበት ማኅበረሰብ፣ የኖርንበት ኑሮና ባሕሪያችን ለግጭት ያለንን አመለካከት ይወስነዋል። ወደ ግጭት ለመግባትም ሆነ ወደ ዕርቅ ለማምራት የግለሰቦች ሥነ-ልቦና ትልቁን ቦታ እንደሚይዝ ይናገራሉ።

አንድ ሰው የበታችነት ስሜት እየተሰማውም ሆነ የበላይነት ስሜት ኖሮበት ካደገ ወደግጭት የማምራት ዕድሉ ሠፊ እንደሆነ ባለሙያዋ ያስረዳሉ። ኹሌ የጥፋተኝነትና የተሸናፊነት ስሜት እንዲኖረው ተደርጎ ያደገ ሰው የበታችነት ስሜቱን ለመሸፈን ሲል ለሰዎች የበላይ መስሎ ለመታየት ሲጥር ይኖራል። የበላይነት የሚገኘው ሌላውን በማጥቃት፣ መብታቸውን በመንፈግ፣ የሌላውን ድርሻ በመውሰድ ወይም ወሰናቸውን አልፎ በመሄድ ይመስለዋል። የበታችነት እየተሰማቸው ያደጉ እንደማይፈለጉ እንዲያምኑ ስለሚደረግ፣ ሐሳባቸው ተቀባይነት የሚያገኝ ስለማይመስላቸው ብቸኛ ማሳመኛ መንገድ ጉልበት እንደሆነ ያምናሉ።

በሌላ በኩል፣ በአስተዳደጋቸው ወቅት እነሱ ብቻ መሰማትና መከበር፣ እንዲሁም መፈራት እንዳለባቸው እየተነገራቸው ያደጉ ደግሞ የበላይነት ስሜታቸው እያደገ መጥቶ ሌላውን ወደ ማጥቃትና መጉዳት ያመራሉ። የለመዱት የበላይነትን ለማሳየት በሌሎች ላይ ጉልበትን መጠቀም ስለሚመርጡ ይህ አስተሳሰብ አእምሯቸው ላይ ተቀርፆ ይቀራል። የበላይ ነን ብለው የሚያስቡ እኩል ነን ቢባሉ እንኳን ለመቀበል ይቸግራቸዋል። “የእንዲህ አካባቢ፣ የእገሌ ልጅ ነኝ፣ እኔ የእገሌ ዘር ነኝ” እያሉ ስለራሳቸው አፍራሽ በሆነ አሉታዊ መንገድ ስለሚገልፁ፣ ያ አመለካከታቸው ተቀባይነት እንዲያገኝ ይጋጫሉ።

ኹለቱንም አይነት አስተሳሰብ ያላቸው ግለሰቦች እየበዙ ስለመጡ በየቦታው ግጭቶች ተበራክተዋል ብለው የሚያስቡት ቃልኪዳን፣ የሰብዕና ግንባታው ከልጅነት ጀምሮ ዳብሮ የሚመጣ ስለሆነ ግለሰቡ ከጎረመሰ በኋላ ለማስተካከል እንደሚያስቸግር ይናገራሉ። እንዲህ አይነት የሥነ-ልቦና አመለካከታቸው የተዛባባቸው ሰዎች ውስጣዊ ስሜታቸውን ለማካካስ ሲሉ አስተዳደጋቸው ባሳደረባቸው ተጽዕኖ ወደ ግጭት የሚያመሩ እንደሆነ ምልከታቸውን ይናገራሉ።

ሰው ማኅበራዊ እንስሳ ነው እንደሚባለው፣ “እኛና እነሱ” የሚል አስተሳሰብም ስር እንደሰደደ ይናገራሉ። ይህ ስለራስ ባለ የተዛባ አመለካከት የሚፈጠረውና መቦዳደንን የሚያመጣው፣ ያለመፈለግ ስሜት ወይም በጣም ተፈላጊ ነኝ ብሎ በማሰብ እንደሆነም ባለሙያዋ ነግረውናል። በእንዲህ አይነት ስሜት ውስጥ የሚዋዥቅ ራሱን የሆነ ቡድን ውስጥ ይከታል። በእንዲህ አይነት ሥነ-ልቦና ውቅር ውስጥ ራሳቸውን ከተው የሚቦዳደኑ ሰዎች ለፈጠሩት ስብስብ በብሔርም ይሁን በኃይማኖት አሊያም በአካባቢ ሽፋን የሚሆናቸውን ስም ይሰጡታል። እነዚህ ግለሰቦች ቡድን መስርተው ጽንፍ የሚይዙበትን ምክንያት ይፈልጋሉ። ከለላ የሚያገኙት በዘር ወይም ዕምነት ጥላ ስር ቢሆኑ እንደሆነ ስለሚያስቡ፣ የበታችነት ስሜት የሚሰማቸው ራሳቸውን ለመደበቂያ ሲጠቀሙበት፣ የበላይነት ስሜት የሚሰማቸው ደግሞ ራሳቸውን ለተቀረው ዓለም ማስተዋወቂያ አድርገው ስለሚወስዱት ጉልበት ለመፍጠር ይቦዳደናሉ። በዚህ የሥነ-ልቦና ምክንያት የተፈጠረውን ቡድን ትንንሽ ምክንያት እያስያዙ ትልልቅ ጥፋት እንዲያጠፋ እንደሚያደርጉ ቃልኪዳን ያስረዳሉ።

የሥነ-ልቦና ማማከር አገልግሎትን የሚሰጡት እኚህ ባለሙያ እንደሚሉት፣ ውስጣዊ አመለካከታቸውን አውጥተው በርካቶችን የሚያሳትፍ ግጭት ውስጥ የሚገቡ ወጣቶች እንዲህ የሚያደርጉት ከልጅነታቸው ጀምሮ የመፈለግና የመወደድ ስሜት እንዲኖራቸው ተደርገው ስላላደጉ ነው። “ይህን ካላደረግክ ምንም አይደረግልህም” የሚል በነገሮች ላይ የተመሠረተ አስተዳደግ እነሱ ሳይሆኑ ሥራቸው ብቻ የሚፈለግ እንዲመስላቸው ያደርጋል። በዚህ ስሜት ያደጉ ተደማጭ ለመሆንና ተፈላጊ ሆኖ ለመቀጠል ማጥፋትን እንደ አንድ መንገድ ይቆጥሩታል።

በሥነ-ልቦና ቀውስ ውስጥ ልጆች እንዳያድጉ ማኅበረሰቡ ትልቅ ኃላፊነት አለበት የሚሉት ቃልኪዳን፣ ምክር ቢለግሷቸው፣ ትክክለኛውን መንገድ ቀርበው ቢያሳዩዋቸው ግጭት እንዳይፈጥሩ አስቀድሞ መሥራት ይቻላል። ልጆቻቸው የሰብዕና ችግር እንዳለባቸው ያወቁ ወላጆችም፣ መቀየር ሲጀምሩባቸው አንስቶ የሥነ-ልቦና አገልግሎት እንዲያገኙ ማድረግ እንደሚጠበቅባቸው ምክራቸውን ይለግሳሉ።

የሥነ-ልቦና ችግር ውስጥ ያሉ የሕብረተሰብ ክፍሎች ይህን ያህል ይሆናሉ ብሎ መናገር እንደማይቻል የሚናገሩት ባለሙያ፣ አብዛኞቻችን በሆነ የአስተዳደግ ዕርከናችን ወቅት የበላይነትም ሆነ የበታችነት ስሜት እንዲሰማን ተደርገን አድገናል። ማኅበረሰቡ ሲያሳድገን እያነፃጸረ እንዳሳደገ የሚያስረዱ ሲሆን፣ “የእነ እገሌ ልጅን አታዩም…” እየተባልን ሥነ-ልቦናችን ላይ መበላለጥ እንዲቀረጽ ተደርገን ማደጋችንን ይገልጻሉ። በዚህ መንገድ ያደግን ብዙ ስለሆንን አሁን አሁን ግጭቶች እየተበራከቱ ለመምጣታቸው ምክንያት ሳይሆን እንደማይቀር ይገምታሉ።

ወጣቱ በራሱ አመዛዝኖ ሳይወስን ሌላውን የሚከተለው አስተዳደጉ በሥነ-ልቦናው ላይ ባሳደረው ተጽዕኖ ነው የሚሉት ቃልኪዳን፣ የበላይነት የሚሰማቸው የበታችነት የሚሰማቸውን ወደሚፈልጉት አቅጣጫ በመውሰድ ሲማግዷቸውና ሲጠቀሙባቸው ይታያል። መጠቀሚያ የሚሆኑትም ተፈላጊ የሆኑ ስለሚመስላቸው ተሰሚነት ለማግኘት ሲሉ ይከተሏቸዋል። ተቀባይነት ለማግኘትና እደነቃለሁ በሚል አስተሳሰብ ሌሎች ናቸው ብለው የፈረጁላቸው ላይ ጥቃት ከማድረስ አይቆጠቡም። ይህም በቀላሉ ፀረ- ማኅበረሰብ እንደሚያደርጋቸው ይናገራሉ።

ወደ ግጭት ላለመግት ኹላችንም ቁጭ ብለን ማሰብ ይጠበቅብናል የሚሉት እኚህ ባለሙያ፣ ማንም ቢሆን ላጠፋው ነገር ይቅርታ ለመጠየቅ ጊዜ መውሰድ የለበትም ይላሉ። በደል እንደ ዕዳ ነው ያሉ ሲሆን፣ የተበደለ መቼም ስለማይረሳው በዳይ ይቅርታ ለመጠየቅ መፍራት አይገባውም። ጠያቂ ባይኖርም የበደለ በራሱ ይቅርታ ቢያደርግም ዕርቅን ለማውረድ ትልቅ ጥቅም እንዳለው ይናገራሉ። በደልን ይቅር ማለት ካልተቻለ ቂም አርግዞ ግጭት መፍጠሩ ስለማይቀር ከስር መሠረቱ ተነጋግሮ ይቅር መባባሉ በጣም አስፈላጊ ነው። ዝም በሉ በሚል አስተሳሰብ እንዲዳፈን ማድረጉ ስለማያዛልቅ፣ ቁስሉ አመርቅዞ ሕመሙ ከማገርሸቱ በፊት ኹሉንም ወገን አገናኝቶ በማወያየት ማስታረቅ እንደሚያስፈልግ ያሳስባሉ።

ካልሸነፍ ባይነት ባህሪያችን ጋር ቀድሞ ይቅርታ ለመጠየቅ አስቸጋሪ የሚሆንበት አጋጠሚ ሊፈጠር ከቻለም፣ አስታራቂዎች ትልቅ ሚናን መጫወት እንደሚጠበቅባቸው ባለሙያዋ ያስረዳሉ። በራስ ተነሳሽነት መታረቅ ካልተቻለ የአገር ሽማግሌዎች በባሕላችን የዳበረውን መንገድ ተጠቅመው ክፍተቱን መሙላት ይጠበቅባቸዋል። የሽማግሌዎች ኃላፊነት ከፍተኛ ቢሆንም ራሳቸው የተጋጩት ወገኖች ይሁንታ ከሌለበት ውጤታማ የመሆኑ ዕድል ዝቅተኛ ነው ብለዋል። የተበደልነውን ተናግሮ ይቅርታ መጠየቅ ጥቅሙ የበደልነውንም እንድናቅ ስለሚያደርገን መፍትሔ ለማምጣት ይጠቅማል። መጥተው ይቅርታ ይጠይቁኝ የሚል ግብዝነትን በማስቀረት ኹሉም ከራሱ ቢጀምርና ልምዱን ለሌላ ቢያስተላልፍ በቀላሉ ውጤታማ መሆን ይቻላል።

ከሽማግሌዎች ባልተናነሰ የሠላምና ልማት ማዕከልን የመሳሰሉ ተቋማትን በመጠቀምም ውጤታማ ሥራን መሥራት እንደሚቻልም ይናገራሉ። እነዚህ ተቋማት ሊደገፉ ይገባል የሚሉት ቃልኪዳን፣ በወጣቶች መካከል ገብተው እርቅ እንዲወርድ የሚሠሩትን ሥራ ከሌሎች ተመሳሳይ ግብረሰናይ ድርጅቶች ጋር ተቀናጅተው ቢያከናውኑ ይበልጥ ውጤታማ ይሆናሉ ብለውናል። ከሥነ-ልቦና ባለሙያዎች ጋር አብረው በመሥራትም በአጭር ጊዜ ትልቅ ለውጥ ማምጣት እንደሚችሉ ዕምነታቸው መሆኑን ያስረዳሉ። የተለያዩ መድረኮችን እያዘጋጁ ግጭት ውስጥ የነበሩ ወጣቶችን በማቀራረብ በመካከላቸው ዕርቅ እንዲወርድ ማድረጋቸው ይበልጥ ተጠናክሮ መቀጠል እንዳለበትም ይናገራሉ።

ለግጭቶች መበራከት ከሥነ-ልቦና ምክንያቶች ባሻገር ውጫዊ መንስዔዎች እንዳሉ የሚናገሩት የሥነ-ልቦና ባለሙያዋ፣ የሥራአጥ ቁጥሩ መብዛቱ፣ የኑሮ ውድነትና ተስፋ ማጣት ወጣቱ ወደ ግጭት በቀላሉ እንዲያመራ ያደርገዋል። ሥራ የፈታ አእምሮ፣ “ተበድለሀል” ለሚሉ ቀስቃሾች ስለሚጋለጥ ክፉ ለማድረግ ወደ ኋላ አይልም ያሉ ሲሆን፣ ይህን ችግር በመቅረፍም ወጣቱ ወደአልተፈለገ ተግባር እንዳይገባ አስቀድሞ መሥራት እንደሚቻል ያምናሉ። ዕርቅ ሒደት በመሆኑ አንድ ጊዜ ተከናውኖ የሚቋረጥ ሳይሆን ወጣቶች ተመልሰው እንዳይገቡበት በዘላቂነት እንዲኖር ታስቦ መሠራት ያለበት እንደሆነ ቃልኪዳን ይናገራሉ።

ለግጭት የሚዳርጉት አስተሳሰቦችም ሆኑ ሁኔታዎች በዘላቂነት እንዳይኖሩ ትምህርት ትልቁን ቦታ እንደሚይዝ ቃልኪዳን ያምናሉ። በመደበኛው ስርዓተ ትምህርት ውስጥ ተካቶ ከልጅነት ጀምሮ ስለግጭት ያለ አመለካከት መቀየር አለበት የሚሉት እኚህ ባለሙያ፣ አስተሳሰቡ ያደገባቸውን ደግሞ ኢ-መደበኛ በሆነ መንገድ ማስተማር እንደሚያስፈልግ ያስገነዝባሉ።

መንግስት ከማንም የተሻለ መዋቅር ስላለው እሱን ተጠቅሞ እስከቀበሌ ድረስ፣ በሥነተዋልዶ ጤና ላይ እንደተሰራው ውጤታማ ሥራ ስለግጭት አስከፊነትና ስለዕርቅ ጠቃሚነት ሕብረተሰቡ እንዲረዳ ማድረግ ያስፈልጋልም ይላሉ። ሲያጠፉ መቅጣቱ ዘላቂ መፍትሔ ስለማይሆን፣ በራስ ላይ እንዲሆን የማይፈለግን ሌላ ላይ አለማድረግን ባሕል እስከምናደርገው ትምህርቱ መቋረጥ እንደሌለበት ያስረዳሉ።

በሌላ በኩል፣ ሕብረተሰብን ከማስተማር አኳያ እንደኃይማኖት ተቋማት ውጤታማ መሆን የሚችል እንደሌለ ይናገራሉ። መንፈሳዊ የሆኑ ትምህርቶችን ከኃይማኖት ትምህርቱ ጋር በማቀናጀት በየመርሃ ግብራቸው በማካተት አስቀድሞ ግጭት ውስጥ የማይገባ ትውልድ መፍጠር እንደሚቻል ያምናሉ። ግጭት ቢፈጠርም ከማባባስ ይልቅ ዕርቅ ለማውረድ ይቅር መባባልን ማኅበረሰቡ እንዲለምደው ማድረግ እንደሚቻላቸው ይገልጻሉ። የሰው መልዓክ እንደሌለና ኹላችንም ላይ ችግር እንዳለብን ከተቀበልን በሠላም ለመኖር አያዳግተንም የሚሉት ቃልኪዳን፣ ትምህርቱ አይታወቅብኝም የሚል አስተሳሰብን በማስቀረት ከመጋጨትና ከመጠፋፋት ይልቅ እንድንፋቀር፣ እንዲሁም ከመለያየት ይልቅ እንድንቀራረብ የማድረግ ሚናው ትልቅ ነው ይላሉ።


ቅጽ 3 ቁጥር 147 ነሐሴ 22 2013

Comments: 0

Your email address will not be published. Required fields are marked with *

This site is protected by wp-copyrightpro.com