የእለት ዜና

ዛሬን እንደ አንድ እርምጃ!

ኢምፓቲ ፎር ላይፍ ኢነተግሬትድ ዴቨሎፕመንት አሶሴሽን(ኤሊዳ) የተቀናጀ የልማት ሥራን በመሥራት ሴቶችን፣ ልጃገረዶችን፣ ወጣቶችን እና ህጻናትን በትምህርት፣ በጤና እና በኢኮኖሚ በመደገፍ እንድሁም በዴሞክራሲ ባህል ግንባታ እና ዘላቂ ሰላም ላይ የሚሠራ እና ማኅበራዊ ኀላፊነታቸውን የሚወጡ ፣ ምርታማ እና አርቆ አሳቢ ዜጎችን ለማፍራት በማለም 2008 (እ.ኤ.አ)ሴቶች የተመሠረተ አገር በቀል የሲቪክ ማኅበረሰብ ድርጅት ነው።

በዚህ ገፅ ላይ የተካተቱ የተለያዩ አካላት ሐሳቦች የኤሊዳንም ሆነ የድጋፍ ሰጪ ድርጂቱን አቋም ላያንጸባርቁ ይችላሉ።

ከውጤት ይልቅ ሂደት ትልቅ ድርሻ እንዳለው ብዙዎች ያምናሉ። በሕይወት ሳይቀር ከመዳረሻ ይልቅ ውጤታማ ሆነም አልሆነ፣ ወደዛ መዳረሻ የሚወስደው መንገድና የተደረገው ወይም የሚደረገው ጉዞ እንደሆነ የበርካቶች እምነት ነው። እንደምን የተባለ እንደሆነ፣ በጉዞ ውስጥ የሚገኝ ልምድ እንዲሁም ትምህርት ትልቅ ድርሻ ስላለው ነው። መደናቀፍ፣ መውደቅ አልያም ከስኬት መድረስ አለመቻል ቢከሰት እንኳ፣ ቀጥሎ አንድ ብሎ ቢጀመር መንገዱ ቀላል ይሆናል በሚል እምነትም ጭምር ነው።

የኢትዮጵያ 6ኛው አገራዊ ምርጫ በመግቢያችን እንዳነሳነው ያለ፣ ከውጤቱ ይልቅ ጉዞው አስተማሪ የሆነ ምርጫ ነው። ምንም እንኳ በሰሜኑ የኢትዮጵያ ክፍል ተቀስቅሶ ያለው ጦርነት እንደ አገር ሰላምን የነሳ አሳሳቢ ጉዳይ ቢሆንም፣ ምርጫው ግን ሳይካሄድም ሆነ ከተካሄደና ውጤቱ ከታወቀ በኋላ ሰላማዊ ሆኖ መቆየቱ ብዙዎች ‹ኢትዮጵያ አሸነፈች› እንዲሉ አድርጓቸዋል።

ከዚህ በተጓዳኝ ሊነሳ የሚችለው የሴቶች ተሳትፎ ጉዳይ ነው። በዚህ ምርጫ በድምሩ ከፓርቲዎች ከቀረቡ ጠቅላላ እጩዎች ማለትም 9505 (ዘጠኝ ሺሕ አምስት መቶ አምስት) እጩዎች መካከል ሴቶች 1987 ያህል ናቸው። ይህ ጥርጥር በሌለው መልኩ ዝቅተኛ እንደሆነ እሙን ነው። ግማሹን እንኳ የተጠጋ አይደለምና። ነገር ግን የሚናቅና የማይደነቅም አይደለም።

ሴት መራጮችን በሚመለከት ያለውን አሃዝም ስንመለከት በድምሩ የምርጫ ካርድ ከወሰዱ 37 ሚሊዮን በላይ ሰዎች፣ ሴቶች 17 ሚሊዮን የሚሆኑት ናቸው። ይህ ከቀደሙ ምርጫዎች ጋር ሲተያይ ብዙ ለውጥ ያሳየ አይደለም። በእርግጥ የመራጮች ቁጥር ባለፉት አራት እና አምስት ምርጫዎች በየአንዳንዳቸው እድገት አሳይቷል፣ በቁጥርም ጨምሯል። ከዚህም ጋር በተጓዳኝ የሴት መራጮች ቁጥርም ለውጦችን አስመዝግቧል።

ይህም ቢሆን ግን በመቶኛ ስሌት ሲታይ ከጠቅላላ ተመዝጋቢ መራጭ ብዛት አንጻር ግማሽ በመቶውን እንኳ አይሞላም፤ አልሞላምም። ነገር ግን ሳይቀንስ ከመራጮች ድምር ቁጥር ጋር አብሮ እያደገ መሄዱም፣ ቢያንስ ከፍተኛ የሴቶች የመራጭነት ተሳትፎ ለውጥን ማምጣት ባይቻልም ያለውን ግን ማስቀጠል እንደተቻለ ማሳያ እንደሆነ ሊቆጠር ይችላል።

ከተመራጭ እጩዎች አንጻር ምንም እንኳ አሸናፊ የሆኑ ሴት እጩዎችን ብዛት በተመለከተ የጠራ የአሃዝ መረጃ የተቀመጠ ባይሆንም፣ የድምር እጩዎች ብዛት አነስተኛ ከመሆኑ አንጻር ቀሪ የቤት ሥራዎች እንዳሉ የሚያመላክት ነው።
በምርጫ ቦርድ የስርዓተ ጾታና ማኅበራዊ አካታችነት ኀላፊ መድኃኒት ለገሰ እንደተናገሩት፣ በምርጫው ከሴቶች ተሳትፎ አንጻር መነቃቃቶች ታይተዋል። አክለው እንደገለጹት፣ ምርጫ ቦርድ አስቀድሞ ሲያደርጋቸው ከነበሩ ጥረቶች፣ የሲቪክ ማኅበራት ከሠሯቸው ሥራዎችና በየመስኩ ከተደረጉ እንቅስቃሴዎች አኳያ የተሻለ የሴቶች የተሳትፎ ንቃት የታየበት ነው ማለት ይቻላል።

እዚህ ላይ ሳይጠቀስ የማይታለፈው፤ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድን በመምራት ሴቶች ከፍተኛ ድርሻ ነበራቸው፤ አሁንም የቀረውንና በኹለተኛ ዙር የሚካሄደውን ምርጫ በማስፈጸም ድርሻ እንደሚኖራቸው ግልጽ ነው። በምርጫ ታዛቢነትም የተሳተፉ ሴቶች በተመሳሳይ ቀላል የማይባል ድርሻን ተወጥተዋል። ይህም ሁሉ በድምሩ ምርጫው ከሴቶች የአመራርና የማስፈጸም ተሳትፎ አንጻር ደኅና የሚባል እንደሆነ እንደማሳያ ይጠቀሳል።

ይህ ጉዞ በቀጣይ ምርጫዎች ከዚህ በላይ እየተጠናከረ እንዲሄድ እንጂ እንዲቀንስ አይጠበቅም። ከዚህ ቅድመ ምርጫ እንዲሁም ድኅረ ምርጫ ሂደቶች መረዳት የሚቻለው እውነትም፣ ከውጤቱ ይልቅ ጉዞው ውጤታማ ሊባል የሚችል እንደነበር ነው።
እንዲያም ሆኖ በኢትዮጵያ ካሉ 50 በመቶ ሴቶች መካከል ማንበብ እና መጻፍ የሚችሉት 29 በመቶ ናቸው። ከላይ እንዳልነው የሴቶች የፖለቲካ ተሳትፎ መጠን እየጨመረ ይሁን እንጂ በኢትዮጵያ ካሉ ሴቶች ቁጥር አንጻር ዝቅተኛ የሚባል ነው።

የምርጫ 2013ን ጉዞና ሂደት መማሪያና እርምጃ አድርገን ስንወስድ፣ እነዚህን ነጥቦች ጨምሮ ሴቶች በፖለቲካ በንቃት እንዳይሳተፉ የሚያደርጉ ምክንያት ተብለው የሚቀመጡ ችግሮችን ለመቅረፍ የሚያስችል እንቅስቃሴንም በማድረግ ነው። ይህም የምርጫ ሰሞን የሚደረግ መሆን የለበትም። የምርጫ ትምህርቶችን ከመስጠት ጀምሮ የሴቶችን የትምህርት ተደራሽነት በማስፋት ቢያንስ ማንበብና መጻፍ የሚችሉ ሴቶችን ቁጥር መጨመርና በውሳኔአቸው ማገዝ ተገቢ ይሆናል።


ቅጽ 3 ቁጥር 147 ነሐሴ 22 2013

Comments: 0

Your email address will not be published. Required fields are marked with *

This site is protected by wp-copyrightpro.com