የእለት ዜና

ጦርነቱ ያስከተለው ተጽዕኖ

ሚኪያስ ከተማ ይባላል። የአዲስ አበባ ከተማ ነዋሪ የህግ ባለሙያ ነው። አንድ ሀገር ጦርነት ውስጥ በምትሆንበት ወቅት የተለያዩ ማህበራዊ፣ ኢኮኖሚያዊ እና ስነልቦናዊ ቀውሶች በማህበረሰቡ ላይ እንደሚያስከትል ይናገራል። በሀገር ሰላም ሲጠፋ ለሰዎች ህይወት መጥፋት ፣ ለአካል ጉዳት እንዲሁም ለንብረት መውደም እና ከመኖሪያ ቦታ ለመፈናቀል ምክንያት እንደሚሆን ይናገራል። ለጦርነት የሚያስፈልጉ የተለያዩ መሳረያዎችን እና ቁሳቁሶችን ለማሟላት ሀገራዊ በጀት ስለሚወጣ በሀገር ላይ ከፍተኛ የሆነ የኢኮኖሚ ጫና እንደሚያስከትል ጠቅሷል።

ከውጭ ሀገር መሳሪያዎች ግዢ በዶላር ሲፈጸም ሀገሪቷ ላይ የዶላር እጥረት የሚያጋጥም ሲሆን፣ ይህም ሁኔታ በምርቶች ላይ የዋጋ ንረት የሚያስከትል መሆኑን አንስቷል። በሀገር ላይ ጦርነት ሲኖር ለልማት መስሪያነት የታቀዱ በጀቶች ለጦርነት መሳሪያ እና ሌሎች መገልገያዎችን ለመግዛት የሚውል በመሆኑ ሀገሪቷ በልማት እንዳታድግ ትልቅ እንቅፋት እንደሚሆን ለአዲስ ማለዳ ተናግሯል።

በጦርነት ምክንያት በማህበረሰቡ ላይ የሚደርሰው ተጽዕኖ እንደየሰዉ የሚለያይ ነው ያለው ሚኪያስ፣ ለዚህም እንደ ምሳሌ ያነሳው በሀገራቸው ላይ ገንዘባቸውን ኢንቨስት የማድረግ እቅድ ያላቸው ሰዎች እቅዳቸውን ከግብ እንዳያደርሱ ማድረጉን ነው። በተመሳሳይ ጦርነቱ ያልደረሰባቸው አካባቢዎች የሚኖሩም ቢሆኑ፣ ጦርነቱ ወደ ተለያዩ ስፍራዎች እንዳይዛመት ከፍተኛ የሆነ ስጋት ውስጥ እንደሚገቡ ተናግሯል። ጦርነቱ እየተካሄደ የሚገኘው በአንድ ሀገር ላይ ባሉ ህዝቦች መካከል በመሆኑ በመጀመሪያ በጦርነቱ አሸናፊ የሚሆን አካል የማይኖር ሲሆን፣ ከጦርነት መጠናቀቅ በኋላ በህዝቦች መካከል የሚፈጠረው ተጽዕኖ ከባድ ሊሆን እንደሚችልም አንስቷል።

እንደ ሚኪያስ ገለጻ ከተለያዩ አለም አቀፍ ሚዲያዎች፣ የሀገር ውስጥ ሚዲያዎች እና ከማህበራዊ መገናናዎችን መረጃዎችን ያገኛል። ይህን ለማድረግም እንደመነሻ የጠቀሰው፣ የሚገኙትን መረጃዎች ተዓማኒነት ለማረጋገጥ የተለያዩ ሚዲያዎችን እንደሚከታተልም ነው። በሀገራዊ ጉዳይ ላይ መገናኛ ብዙኃኖች በህብረተሰቡ ላይ ከፍተኛ በሆነ መልኩ ተጽዕኖ ማድረስ የሚችሉበት ሁኔታ ሰፊ እንደሆነ አስታውቋል።

በአለም አቀፍ ደረጃ የተመዘገበውን የጥምቀት በዓልን በጎንደር ለማክበር ዕቅድ የነበረው ይህ የህግ ባለሙያ፣ በሰሜኑ ክፍል በተፈጠረው ጦርነት ምክንያት በሌሎች አካባቢዎችም ላይ ስላለው የሰላም ጉዳይ እርግጠኛ ባለመሆኑ የነበረውን ዕቅድ ለጊዜው የተወበት ሁኔታ መኖሩን ጠቅሷል።

የውጭ ሀገራት በኢትዮጲያ ውስጥ ያለውን ጦርነት እንደ ጥሩ አጋጣሚ አይተውት ተጽዕኖ እንዳያሳድሩም ስጋት እንዳደለበት ተናግሯል። በተለያዩ ሀገራቶች የሚስተዋለው የውጭ ሀገራት ጣልቃ ገብነት ሲታይ፣ ጥቅም ከማግኘት ይልቅ ሀገር የማፈራረስ አላማ ይዘው ሊንቀሳቀሱ እንደሚችሉ ስለሚያሳይ ኢትዮጲያን አደጋ ውስጥ እንዳይከቷት ፍራቻ እንዳለው አክሏል።

ሚኪያስ ከአዲስ ማለዳ ጋር በነበረው ቆይታ የሰላም ማጣት በማህበረሰብ ብሎም በሀገር ደረጃ ላስከተለው ተጽዕኖ እንደ መፍትሄ ሃሳብ የሚያነሳው፣ ማንኛውም አካል የጦርነትን አስከፊነት በመረዳት ሰላምን በሀገር ላይ የማስፈን ስራ መስራት እንዳለበት ነው።
ሌላዋ ሃሳቧን ያካፈለችን ሳሮን አሰፋ ትባላለች። የአዲስ አበባ ከተማ ነዋሪ እና መንግስት ሰራተኛ ነች። ጦርነት በሀገር ላይ መኖሩ ማህበረሰቡን ለአካለዊ እና ስነልቦናዊ ጉዳት ይዳርጋል ትላለች። በሰዎች ላይ የሚደርሰውን የህይወት መጥፋትንና የአካል ጉዳት መከሰትን እንደ አካላዊ ጉዳት የምትወስድ ሲሆን፣ በዜጎች ላይ የሚደርሰውን የጭቀት እና ስጋትን በተመለከተ የሥነልቦና ቀውስ ሊባል እንደሚችል ተናግራለች። በሀገሪቷ ላይ አሁን ያለው ሁኔታ ሀገርን ወደ ድህነት የመውሰድ አዝማሚያ በስፋት እየታየ እንደሚገኝ አንስታለች።

በጦርነት ምክንያት የሚፈጠረውን የሰላም ማጣት እና በሰዎች ዘንድ የሚፈጥረውን ተጽእኖ እንደ ግለሰብ መመልከት ቢቻል ከፍተኛ የሆነ ስጋት ውስጥ እንደሚከት ታነሳለች። ለዚህም እንደ ምክንያት ያነሳችው፣ አሁን ያለችበት ቦታ ከጦርነት ቀጠና ወጭ ቢሆንም እሷ ወደምትኖርበት አካባቢ አለመድረሱን እርግጠኛ የሚረጋት ሁኔታ አለመኖሩ፣ “እኔስ ነገ ምን እሆናለው” የሚለው ጉዳይ እንደሚያሰጋት ለአዲስ ማለዳ ተናግራለች።

በሀገረቱ ላይ የተከሰተው ጦርነት የፈጠረው የጸጥታ ስጋት በእሷ ላይ አካላዊ ጉዳት ባያደርስም የምትፈልገውን ስራ እንዳትሰራ ትልቅ ተጽዕኖ እንዳሳደረባት ማንሳት ችላለች። የሀገሪቷ ኢኮኖሚ ከቀን ወደ ቀን እየተናጋ በመሆኑ ድርጅቶች እና መሰል ተቋማት የሰራተኛ ቅጥር አያከናውኑም ትላለች። ይህም ስራ ለማግኘት እና ለተመራቂ ተማሪዎች ከፍተኛ ስጋትን ከመፍጠር ባሻገር ለለውጥ ትልቅ ማነቆ እንደሚሆን አስታወቃለች።

ከዚህ ቀደም በሀገሪቷ ላይ በነበረው የስራ አጥ ቁጥር ብዛት ላይ የኮቪድ 19ወረርሽኝ የጨመረውን ከፍተኛ ችግር እስካሁን ድረስ መቅረፍ አለመቻሉን ያነሳች ሲሆን፣ በዚህም ላይ ሀገር ጦርነት ውስጥ መሆንዋ ትልቅ ኪሳራ ሊያስከትል ያችላል ብላለች። ሳሮን መረጃዎችን ከተለያዩ የመገናኛ ብዙኃን የምታገኝ ሲሆን፣ ከዚህ በተጨማሪም ችግሮች አሉባቸው በሚባሉት አካባቢዎች የሚገኙ ሰዎችን በማነጋገር መረጃዎችን ለማግኘት ሙከራ እንደምታደርግ ጠቅሳለች።

መረጃዎችን ከተቻለ በቀጥታ ችግሩ ከተፈጠረባቸው አካባቢዎች ከሚገኙ ሰዎች አልያም የመረጃ ምንጮችን በመቃኘት ትክክለኛነቱ የተረጋገጠ መረጃ ለማግኘት ወሳኝ ሚና እንደሚኖረው ገልጻለች። በማህበራዊ ድረገጾች የምታገኛቸው መረጃዎች እንዳንዶቹ የተረጋገጡ ባለመሆናቸው እና ለግል አላማቸው ብለው በሚለቁት የተጋነነ መረጃዎች ከፍተኛ ተጽእኖ እንደሚደርስባት ታወሳለች። ሳሮን እንደ መፍትሄ ሃሳብ የምታነሳው ማህበረሰቡ በተቻለው አቅም እራሱን እንዲሁም አካባቢውን በንቃት መጠበቅ እንደሚኖርበት እና በዋነኛነትም የሰላምን ጥቅም መረዳት እንደሚገውባ ጠቁማለች።

በሀገሪቷ ላይ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ የሚስተዋለው የሰላም ማጣት እና ጦርነት አሳሳቢ ደረጃ ላይ ይገኛል የሚለው ሌላው አስተያየት ሰጪ ተማሪ ቴዎድሮስ ፍቅሩ ነው። በጦርነት ምክንያት ንጹኃን ዜጎች ለህልፈት እና ለአካል ብሎም ለሥነ ልቦናም ጉዳት፣ እንዲሁም ሀገራቸውን ለቀው ወደ ተለያዩ አጎራባች አካባቢዎች ለመፈናቀል ምክንያት እንደሚሆን እሱም ያምናል። እንደ ሀገር በጦርነት ምክንያት በመንግስት በጀት ተመድበው የተሰሩ የመሰረተ ልማት ግንባታዎች ጉዳት በሚደርስባቸው ጊዜ ትልቅ የኢኮኖሚ ኪሳራ እንደሚደርስም ያነሳል።

በጦርነት ስጋት ምክንያት ሰዎች ተረጋግተው ስራቸውን እንዳይሰሩ ጥርጣሬ እንደሚፈጠርባቸውም ያስረዳል። እንደ ግለሰብ ግጭቶች መቼና የት እንደሚከሰቱ እርግጠኛ ለመሆን ስለሚያስቸግር ደህንነት ስጋት እንደሚፈጥር ያነሳል። በጦርነቱ ምክንያት በአንዳንድ አካባቢዎች የጸጥታ ስጋት በመፈጠሩ የትራንስፖርት እንቅስቃሴዎች እንደ ከዚህ ቀደሙ ባለመኖራቸው የዋጋ ንረት እያስከተለ እንደሚገኝ ጠቅሷል። የሃይማኖት ክብረ በዓላትን በአክሱም ሄዶ ማክበር እቅድ ይዞ የነበረ ቢሆንም ጦርነቱ የፈጠረው ስጋት ግን ዕቅዱን እንዳያሳካ እንቅፋት እንደሆነበት አንስቷል።

ቴድሮስ ለአዲስ ማለዳ እንደተናገረው መረጃዎችን ከተለያዩ የመንግስት እና ማህበራዊ ድረገጾች ላይ እንደሚከታተል ይናገራል። አንዳንድ ሚዲያዎች ለራሳቸው ጥቅም ሲሉ የራሳቸውን ሃሳብ ሲያስተላልፉ ይመለከታል። ከማህበራዊ ድረገፀ ላይ የሚገኙ መረጃዎች እውነተኛ እንዳልሆኑ ቢታወቅም እንኳን፣ ሰዎችን ስጋት ውስጥ ከመክተት እንደማይቆጠቡ ይናገራል። “ጭስ በሌለበት እሳት አይኖርም “የሚል አባባል በመኖሩ ሰዎች ምን ታስቦ ነው በማለት መረጃውን እንደ ፍንጭ ሊወስዱ ይችላሉ ያላል። ማንኛውም ሰው ከስልጣን እና ከሁሉም ነገር በላይ ሀገርና ህዝብ መቅደሙን በመገንዘብ የሚኖራቸውን ጥያቄ በተገቢው መንገድ መግለፅ እንደሚገባ እንደ መፍትሄ ሀሳብ አንስቷል። በተጨማሪም የውጭ ሀገራት በሀገር ላይ ለማሳደር የሚሞክሩትን ተፅዕኖ ህብረተሰቡ በመገንዘብ የውጭ ሀገራት ጣልቃ ገብነትን በጋራ ለመከላከል ህብረት መፍጠር ያስፈልጋል ብሏል።

ከዚህ ጋር በተያያዘ ሃሳባቸውን ለአዲስ ማለዳ ያካፈሉን የግብርና ኢኮኖሚስት እና የግል አማካሪ የሆኑት ደምስ ጫንያለው (ዶ/ር) ናቸው። እንደ እሳቸው ገለጻ፣ በሰዎች ዘንድ ስጋት የተፈጠረው ጦርነቱ ከመጀመሩ በፊት እንደነበርና በአሁኑ ወቅትም እየተባባሰ እንደሚገኝ አንስተዋል። በየትኛውም ሀገር የሚከሰት ጦርነት ሀገርን በኢኮኖሚው የማክሰር አቅም እንደሚኖረው ጠቅሰዋል። የውጭ ሀገራት የራሳቸውን ኢኮኖሚ ለማሳደግ ሌሎች ሀገራትን ችግሮች ውስጥ በመክተት የመሳሪያ እና መሰል የጦር መገልገያዎችን ከማምረት እስከ መሸጥ ደረጃ የገቢ ምንጫቸው የሚያደርጉበት ሁኔታ መኖሩን አውስተዋል።

ጦርነቱ ከመጀመሩ በፊት በቀጣይ በሀገርም ሆነ በሰዎች ላይ የሚደርሰውን ኪሳራ ለመቀነስ እየተሰራ እንደነበር ተናግረዋል። ጦርነቱ በሀገር ላይ መጀመሩ የሀገር በጀት ወደ ጦር እንዲዞር አድርጎታል፣ ይህም የሀገር ኢኮኖሚ እና ልማት ላይ ጫና እንደሚያሳድር አስታውቀዋል። በአሁን ወቅት የሚታየው የዋጋ ንረት በቀጥታ የጦርነቱ መንስኤ ነው ባይባልም ትልቅ አስተዋጽኦ ግን ይኖረዋል ብለዋል። ነጋዴዎች በሸቀጦች ላይ የዋጋ ጭምሪ እና የምርት ክምችት ሲያደርጉ የሚስተዋል ሲሆን፣ ይህም በጦርነት ስጋት ምክንያት እንደሆነ አመልክተዋል። እሳቸው እንደ መፍትሄ ያነሱት በጦርነት የሚከሰተውን የኢኮኖሚ ቀውስ ሁሉም ተረድቶ ሰላም ለማምጣት መስራትን ነው።

የመረጃ ምንጭን በተመለከተ ጋዜጠኛ ሄኖክ ተሬቻ፣ ሕብረተሰቡ ማህበራዊ ድረገፆችን ምንጭ አድርጎ ለመውሰዱ እንደዋና ምክንያት የሚያነሳው፣ የመንግስት መገናኛ ብዙሀን የማህበረሰቡን ፍላጎት ያሟሉ አለመሆናቸውን ነው። የመንግስት መገናኛ ብዙሀን ታማኝነት እና ፈጣን መረጃን ወደ ህብረተሰቡ ቢያደርሱ ማንኛውም ሰው በማህበራዊ ድረ ገጾች ላይ የሚፃፈውን ለማመን አይገደድም ነበር ብሏል።

በማህበራዊ ድረ ገጾች ላይ የሚለቀቁ ሀሰተኛ እና የፈጠራ መረጃዎች በስፋት በማህበረሰቡ ዘንድ ተቀባይነት ለማግኘታቸው ሌላው ምክንያት፣ በመንግስት ሚዲያዎች ዘንድ ክፍተት መኖሩን ነው። በማህበራዊ ድረ ገጾች ላይ መረጀዎችን የሚለቁ ሰዎች የማይታወቁበት ሁኔታ፣ እንዲሁም የገቢ ምንጫቸው በመሆኑ አንዳንዴ ያልተፈጠረ እና ወገንተኛ የሆነ መረጃን ያሰራጫሉ። በዚህም ምክንያት ሰዎች እውነተኛ ነው ብለው ስለሚያስቡ እራሳቸውን ለተለያዩ ችግሮች አሳልፈው እንደሚሰጡ ተናግሯል።

በአንዳንድ የሚዲያ ተቋማት የተማረ እና የሰለጠነ ጋዜጠኛ እጥረት መስተዋሉ በመረጃ አዘጋገቡ ረገድ ክፍተት ለመፈጠሩ መንስኤ እንደሆነ የሚናገረው ሄኖክ፣ የመንግስት እና የግል የመገናኛ ብዙኃን በመጀመሪያ የቆሙለትን አላማ ማወቃቸው ዋናው የመፍትሄ መንገድ ነው ብሎ ያምናል።

በአንድ ሀገር ላይ ጦርነት ሲኖር ከጦርነቱ በፊት፣ በጦርነት ወቅት እና በኋላ ከሰዎች ጋር አብሮ የሚቆይ የድብርት እና የተለያዩ የዓዕምሮ ህመም ችግሮችን ያስከትላል ያሉት የሞሽን ማማከርና ስልጠና ድርጅት ምክትል ሥራስኪያጅ የሆኑት የሥነልቦና አማካሪ እና አነቃቂ ንግግሮችን ተናጋሪው ብርሃኑ ራቡ ናቸው።

ሰዎች የጦርነት ስጋት በሚኖራቸው ጊዜ በቀጣይ የመኖር ስጋት ውስጥ እንደሚገቡና በነገሮች ተስፋ የመቁረጥ ሁኔት እንደሚያጋጥማቸው ጠቁመዋል። ሰዎች በቀጣይ ያቀዱትን አላማ እና ግባቸውን ለማሳካት ጥረት እንዳያደርጉ እንቅፋት ይሆናልም ብለዋል። በሚገጥማቸው የድብርት እና የመረበሽ ስሜት ወደ ተለያዩ ሱሶች የሚገቡበት ሁኔታም ሰፊ እንደሚሆን አንስተዋል።

የሚሰራጩ መረጃዎች በአይምሮ ላይ የሚያደርሱት ጫና በቀላሉ የሚታይ ባለመሆኑ የሚዲያ ሰዎቸ ጥንቃቄ በተሞላበት መንገድ ማስተላለፍ ይገባቸዋል ብለዋል። ማህበረሰቡም የሚወስደውን መረጃ በጥንቃቄና እና ሳይበዛ እንደአስፈላጊነቱ መጠቀም እንደሚገባው ጠቁመዋል። በጦርነቱ ምክንያት የቅርብ ሰው በማጣትም ሆነ አጣለሁ ብሎ በመስጋት ሰዎች ከፍተኛ ለሆነ ጭንቀት ይጋለጣሉ፤ ይህም ለአይምሮ ህመም የሚዳርግ ይሆናል ብለዋል። ማንኛውም ሰው ስለሌላው የሚናገረውን በመጠንቀቅ የጥላቻ ንግግር አጸያፊነትን ሊረዳ ይገባልም ሲሉ ሐሳባቸውን አካፍለዋል።


ቅጽ 3 ቁጥር 147 ነሐሴ 22 2013

Comments: 0

Your email address will not be published. Required fields are marked with *

error: Content is protected !!