የእለት ዜና

የኢትዮጵያ ወቅታዊ ኹኔታ እና የምዕራባዊያን ተጽዕኖ

Views: 203

ጥቅምት 24/2013 በሰሜኑ የኢትዮጵያ ክፍል የተከሰተዉ እና በትግራይ ክልል ብቻ ተወስኖ የቆየዉ ጦርነት አሁን መልኩን እና ይዘቱን ቀይሮ ወደ ሌሎች አጎራባች ክልሎች እየተስፋፋ መምጣቱን ተከትሎ ኢትዮጵያ ዘርፈ ብዙ ቀዉሶችን እያስተናገደች ትገኛለች። በዚህ ጦርነት እና ቀዉስ የተነሳ ኢትዮጵያ ዉስጣዊ እና ዉጫዊ ተጽዕኖ እየበረታባት እንደሆነ ይነገራል። የፌደራል መንግሥት በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አሸባሪ ተብሎ ከተፈረጀዉ ህወሓት ጋር እያደረገ ባለዉ ጦርነት የተለያዩ የዉጭ አገራት መንግሥት ላይ በተለያየ ጊዜ ፀባይ እና መልኩን የሚቀያይር ጫና ሲያሳድሩበት ይስተዋላል። ይህ ጫና በአገሪቱ ዲፕሎማሲ እና የዉጭ ጉዳይ ግንኙነት ላይ ያለዉ ተጽዕኖ የጎላ መሆኑን ምሁራን ይናገራሉ።
ዓለም ዐቀፍ የዕርዳታ ሰጪ ተቋማት እና ምዕራባውያን በፌደራል መንግሥት እና በህወሓት መካከል የቀጠለው ጦርነት እንዲቆም አወንታዊ ሚና ከመጫዎት ይልቅ፣ ለህወሓት ያመዘነ ሐሳብ በማንጻበረቅ እና የሐሰት ፕሮፓጋንዳ እንዲሰራጭ በማድረግ ኢትዮጵያን የለየለት ቀዉስ ዉስጥ ለመክተት ደፋ ቀና እያሉ እንደሚገኙ የውጭ ግንኙነት ባለሙያዎች ይናገራሉ። የአዲስ ማለዳዉ ወልደ አማኑኤል ይርዳዉ ጉዳዩን የዓለም አቀፍ የፖለቲካ ምሁራኖችን፣ የዉጭ ግንኙነት ፖሊሲ እና የሚዲያ ባለሙያዎችን አነጋግሮ የሐተታ ዘማለዳ ርዕሰ ጉዳይ አድርጎታል።

ኢትዮጵያ አሁን ከገጠሟት ችግሮች አንጻር ዓለም ዐቀፉ ማኅበረሰብ እና ተቋማት እንዲሁም የዓለም ኃያላን አገራት ጫና እየበረታ መምጣቱ ችላ የሚባል ጉዳይ አይደለም። አንድ አገር በማኅበራዊ አገልግሎት፣ በሰብዓዊ መብት አያያዝ፣ በኢኮኖሚ እና በፖለቲካ ጉዳዮች ሰፊ እንቅስቃሴ ማድረግ ከሌሎች አገራት ጋር የሚኖረው ወዳጅነት ወደር የሌለዉ እና አዎንታዊ ለዉጥ ሊያመጣ የሚችል ተግባር ነዉ። ኢትዮጵያም በማኅበራዊ፣ ኢኮኖሚያዊ፣ ፖለቲካዊ እና ሌሎች ጉዳዮችን በተመለከተ ዘርፈ ብዙ ለውጦችን ለማምጣት ላለፉት ሦስት ዓመታት ስትሠራ ቆይታለች። እነዚህን ተግባራት ከግብ ለማድረስና ለዜጎቿ ምቹ ሁኔታዎችን ለመፍጠር፣ በተለይም በኢኮኖሚ ጠንካራ አገር ለመሆን በመታተር ለይ ትገኛለች።

አሁን ባለዉ ወቅታዊ ሁኔታ አገራችን ከገጠማት ጦርነት ለመዉጣት፣ የዜጎቿን ሠላምና ደኅንነት ለማስጠበቅ፣ የአገር ሉዓላዊነትን ለማስቀጠል፣ ጠንካራ መንግሥት ለመገንባት እና ኢኮኖሚዋን ለማሳደግ በምትታትርበት ወቅት፣ ዲፕሎማሲዉ እና የዉጭ ግንኙነቱ ጠንካራ መሆን እንዳለበት ይነሳል። አሁን ኢትዮጵያ የለየለት ጦርነት ዉስጥ ትገኛለች፤ ጥቅምት 24 ቀን 2013 ዓ.ም. በትግራይ ክልል የተነሳዉ ጦርነት እራሱን እያሰፋ ዘጠኝ ወራትን አስቆጥሯል።

ኢትዮጵያ ይሄ የዉስጥ ጦርነት ሲገጥማትና በጦርነት እና ተያያዥ ቀዉሶች ስትተራመስ የዓለም ኃያላን አገራት ምን ሚና ነበራቸዉ ቢባል፣ ኢትዮጵያን እንደ አንድ ሉዓላዊ አገር ከማየት እና አግባብነት ያለዉ ፍርድ ከመስጠት ይልቅ የመንግሥትን እጅ ሲጠመዝዙ እና አሸባሪ ተብሎ ለተፈረጀው ህወሓት የሚያደሉ የፕሮፓጋንዳ ወሬዎች በሚዲያዎቻቸዉ በማሰራጨት ተፅዕኖ ለማሳደር ሲሞክሩ ቆይተዋል። ዓለም ዐቀፍ የእርዳታ ድርጅቶች እና ኃያላን አገራትም በዚህ ዙሪያ ያላቸዉ ተጽዕኖ ቀላል የሚባል አይደለም።

በተለይም አሜሪካ በተለያየ ጊዜ የተለያዩ ኢኮኖሚያዊ እና ፖለቲካዊ ጫናዎችን ከማሳደርም ባለፈ አትዮጵያ ከጎረቤት አገር ሱዳን ጋር ያላትን ግንኙነት እንዲሻክር ለማድረግ ብዙ ስትጥር ቆይታለች። አሁንም ከዚህ ድርጊቷ እንዳልተቆጠበች ይነገራል። ጎረቤት አገር ሱዳንም ይህንን ኢትዮጵያ የገጠማትን ቀዉስ እና ግጭት እንደ አጋጣሚ በመጠቀም የድንበር ዉዝግብ እና ጦርነት ስታስነሳ ቆይታለች። ለዚህ ደግሞ የአሜሪካ ሱዳን ላይ ያላት ተጽዕኖ ከፍ ያለ መሆኑ ይገለፃል።

በዚህም ምክንያት ኢትዮጵያ አሁን ላይ ከገጠማት የአገር ውስጥ ጦርነት ባሻገር እጅግ የበረታዉ የዉጭ አገራት ተጽዕኖ ሌላ የራስ ምታት ከሆነባት ሰነባብቷል። ይህም አገሪቱ የመወሰን አቅሟን የፈተነ እና ይልቁንም በኢኮኖሚ እና መሰል ጉዳዮች ወደ ኋላ የሚያደርግ ተግባር ነዉ። በዉጭ አገራት ጫና ምክንያት አገራዊ መግባባት እንዳይኖር ከመድረጉም በላይ፣ በአገር ዉስጥ ያሉ የፖለቲካ ጥቅማቸዉ ያልተሟላላቸዉ ኃይሎች ተመሳሳይ ጥፋቶችን እንዲተገብሩ በር የከፈተ ጉዳይ ሆኗል። በተጨማሪም የኢትዮጵያ ወዳጆች እና የቅርብ አጋር አገራት በጦርነቱ ላይ የተሳሳተ ግንዘቤ እንዲኖራቸዉ ማድረጉም ተስተውሏል።

ኢትዮጵያ ከአፍሪካ አገራት መካከል በዲፕሎማሲ እና በተለያዩ የዉጭ ግንኙነቶች የነበራት የበላይነት የአፍሪካ ሕብረት መቀመጫ ከመሆኗ ያለፈ መሆኑ የታወቀ ጉዳይ ነዉ። አንድ አገር ሉዓላዊነቷን አስጠብቃ እና ነፃነቷን አስከብራ ለመኖር ከየትኛዉም አይነት የዉጭ ጣለቃ ገብነት ተጽዕኖ ነፃ መሆን እንዳለባትም የሚዘነጋ ሐቅ አይደለም።

በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አሸባሪ ተብሎ የተፈረጀዉ ህወሓት በሰሜን ዕዝ ላይ በከፈተዉ ጥቃት መነሻነት ኢትዮጵያ ባለፉት ዘጠኝ ወራት ስትታመስ ቆይታለች። በዚህ ጦርነት ምክንያት አገሪቱ የለየለት ዉዝግብ እና ጫና ዉስጥ መግባት አልቀረላትም። በተለይ ደግሞ በአገሪቱ ሰሜናዊ ክፍል በተከሰተዉ ጦርነት የተለያዩ የዉጭ ኃያላን አገራት እና ዓለም ዐቀፍ የድጋፍ ሰጪ ተቋማት የሚያሳድሩት ያልተገባ ተጽዕኖ የበረታ መሆኑ ችግሩን አባብሶታል ይላሉ የተለያዩ የፖለቲካ ተንታኞች።

በደብረ ብርሃን ዩኒቨርስቲ የዓለም ዐቀፍ ፖለቲካ እና የዉጭ ግንኙነት ፖሊሲ መምህሩ ረ/ፕ ዳምጠዉ ተሰማ ይህን የዉጭ አገራት ጫና ካለፈዉ የቅኝ ግዛት ዘመን ጋር አያይዘዉ ይገልፁታል። “በአማርኛዉ አጠራር ትህነግ ወይም በትግርኛ አጠራሩ ህወሓት የተሰኘዉ አሸባሪ ቡድን ኢትዮጵያ የጋራ እሴት እንዳይኖራት ላለፉት ሦስት አስርት ዓመታት ሲሠራ ቆይቷል” በማለት ኢትዮጵያ በተለይ የፖለቲካ ባህሏ ጥገኛ እንዲትሆን አድርጓል ይላሉ። በመሆኑም አሁን ህወሓት ከኢትዮጵያ ጋር በሚያደርገዉ ጦርነት በቀጥታም ሆነ በተዘዋዋሪ የሚጠቀሙ አገራት አሉ ያሉት መምህሩ፣ የዓለም ኃያላን አገራት እንደ ኢትዮጵያ ያሉ አገራትን የመራገጫ ሜዳቸው በማድረጋቸው ጫናዉ ይበረታል ብለዋል።

ልኂቃኑ እና የዲፕሎማሲ ሥርዓቱ ባለፉት አመታት ህወሓት ሥልጣን ላይ በነበረበት ጊዜ የነበሩ እና በወቅቱ በነበረዉ የፖለቲካ ሥርዓት የተቃኙ መሆናቸዉ ደግሞ ችግሩን ከማባባሱም በላይ የዉጭ ግንኙነት ፖሊሲያችን ደካማ እንዲሆን አድርጎታል። ከዚሁ ጋር አያይዘዉም በአሜሪካ እና ቻይና መካከል ያለዉ የፖለቲካ ሽኩቻ ኢትዮጵያ ላይ ቀላል የማይባል ተጽዕኖ እንደሚያሳድር ይናገራሉ። ህወሓት የጣሊያን ወረራ እና ስትራቴጂ የሚያንፀባርቅ እና የመከፋፈል ትርክት በሠፊዉ ሕዝብ ላይ ሲነዛ ከመቆየቱም ባለፈ፣ ኢትዮጵያዉያንን በባህል፣ በኃይማኖት፣ በቋንቋ፣ በዘር በመከፋፈል እንዲሁም የጋራ እሴት እንዳይኖራቸው በማድረግ፣ ጥገኛ የዉጭ ፖሊሲ እና የፖለቲካ ሥርዓት በመገንባት ይህ ነዉ የማይባል ወንጀል ፈፅሟል ያሉት የፖለቲካ ምሁሩ፣ አሁን ኢትዮጵያ ለገጠማት ቀዉስ የአንበሳዉን ድርሻ ይወስዳል፤ ለዚህ ደግሞ የዉጭ አገራት በተለያየ መንገድ እየደገፉት ይገኛሉ ነዉ ያሉት።

ከዚሁ ጋር አያይዘዉም በጦርነቱ ምክንያት የተፈጠሩ ሰብዓዊ ቀዉሶችን ሚዛናዊ ባልሆነ እይታ በማየት እና ኢትዮጵያ ላይ ዘርፈ ብዙ ጫና ለማድረስ ያፈነገጠ ቡድንን መደግፍን ዋናኛ ዓላማቸዉ አድርገዉ እየሠሩ ይገኛሉ ብለዋል። አሁን ኢትዮጵያ ካለችበት ችግር ለመዉጣት ምናልባትም ቀድሞ የነበራትን የዲፕሎማሲ የበላይነት ማስጠበቅ እና ሌሎች የትኩረት አቅጣጫዎችን ማየት ይኖርባታል። ይህ ጦርነት ቀዉስ ብቻ አይደለም፤ ለአዲስ ለዉጥ እንደመስፈንጠሪያም ነዉ። ለዚህ ደግሞ በተለይ ኢኮኖሚያዊ አቅማችን እና የሕዳሴዉ ግድብ ግንባታን በስኬት በማጠናቀቅ ጠንካራ ኢኮኖሚ መገንባት ከቻልን ከዉጭ ተጽዕኖ መዉጣት እንችላለን ሲሉ ሐሳባቸዉን ያጠቃልላሉ።

ሌላዉ በዚሁ ጉዳይ ላይ ከአዲስ ማለዳ ጋር ቆይታ ያደረጉት በደብረ ማርቆስ ዩኒቨርስቲ በረዳት ፕሮፌሰርነት ማዕረግ የጋዜጠኝነት መምህር የሆኑት እና በአሁኑ ሰዓት በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የዶክትሬት ዲግሪ ተማሪ የሁኑት ደሳለዉ ጌትነት ናቸው። እሳቸው እንደገለፁት “በተለይ የአሜሪካ የዕርዳታ ድርጅት ኃላፊዋ ሳማንታ ፓወር በትግራይ ክልል ያለዉን ወቅታዊ ሁኔታ እና ጦርነት በተመለከተ ሚዛናዊ ያልሆነ እና በትግራይ ክልል ዉስጥ ብቻ የሚደረገዉን ሰብዓዊ ጥሰት በተደጋጋሚ በማንሳት፣ በአንጻሩ ግን በአፋር እና በአማራ ክልሎች በተለይም በራያ ቆቦ አጋምሳ በምትባል ቦታ በአሸባሪዉ ህወሓት የተገደሉትን ቁጥራቸዉ ከ240 የሚልቅ ዜጎችን እና የወደመዉን ንብረት እና የተፈናቀለዉን ማኅበረሰብ ችላ በማለት በፌደራል መንግስቱ እና ኢትዮጵያ ላይ ያላቸዉን ያልተገባ ሐሳብ ሲያንፀባርቁ ይስተዋላል።”

ኢትዮጵያ ባለፉት ስምንት ወራት በርካታ ሰብዓዊ ቀዉሶች አስተናግዳለች። በቅርቡ በአሸባሪነት የተፈረጀዉ ህወሓት በአፋር እና አማራ ክልል ከፈጠረዉ ቀዉስ በተጨማሪ በዚህ ጦርነት ምከንያት ከ2 ሚሊዮን የሚጠጉ ዜጎች አስቸኳይ ሰብዓዊ ድጋፍ እንደሚያስፈልጋቸዉ እየታወቀ ዓለም አቀፍ የዕርዳታ ሰጪ ተቋማት ነገሩን ችላ ማለታቸዉ በተለይ የአሜሪካ የእርዳታ ድርጅት ተቋም (USAID) በትግራይ ክልል ብቻ የተወሰነ ድጋፍ ማድረጉ ኢትዮጵያ ላይ እየደረሰ ካለዉ የዉጭ ጫና የበለጠዉ ነዉ ይላሉ። በተለይ የሳማንታ ፓዎር ንግግሮች የሰብዓዊ ድጋፍ ከማድረግ በዘለለ ትርጉማቸዉን የለወጡ ናቸው በማለት ደሳለው ለአዲስ ማለዳ ሐሳባቸዉን አጋርተዋል።

አሁን አገሪቱ ከገጠማት ችግር ጋር ተያይዞ የሚመጣ የዉስጥ እና የዉጭ ጫና ምናልባትም ኢትዮጵያ በጦርነቱ ከምታጣዉ የሰዉ ሀብት እና ንብረት፣ እንዲሁም ከሚደርስባት ጉዳት በተጨማሪ ችግሩ በዚሁ ከቀጠለ ለሉዓላዊነቷ እና አንድነቷም አሳሳቢ መሆኑ አይቀርም ሲሉም ሐሳባቸዉን ገልፀዋል።

በሌላ በኩል፣ በባህር ዳር ዩኒቨርሲቲ በሚዲያ እና ኮሙኒኬሽን ጥናት የዶክትሬት ዲግሪ ተማሪ የሆኑት ሙሉቀን አሰግደዉ ለአዲስ ማለዳ እንደተናገሩት፣ በተለይ ዓለም ዐቀፉ ማኅበረሰብ እና የሚዲያ ተቋሞቻቸዉ የሚዘግቡት ዘገባዎች ትክክለኛነት የጎደላቸዉ በመሆኑ፣ ኢትዮጵያ አሁን ላለችበት ቀዉስ መባባስ ምክንያት ሁኗል። ህወሓት ለፕሮፓጋንዳ እንዲጠቀምበት ከመሆኑም ባለፈ ዓለም ዐቀፉ ማኅበረሰብ እና የአዉሮፓ ኅብረት ኢትዮጵያ ዉስጥ ያለዉን ጦርነት በትክክል ከመረዳት ይልቅ ችግሩን የሚያባብስ ሥራዎች ሲሠሩ ይስተዋላል ይላሉ። አያይዘዉም፣ የዓለም የሰብዓዊ መብት ተሟጋች፣ የአሜሪካ ዕርዳታ ድርጅት (USAID)፣ የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት፣ አምነስቲ ኢንተርናሽናል እና ሌሎችም ተቋማት ጫናቸዉ የበረታ ነዉ ብለዋል።

በተጨማሪም፣ በዓለም ዐቀፍ ሕግ መሰረት ዕድሜያችዉ ለጦርነት ያልደረሰ ሕጻናትን፣ ሴቶችን(“አንዳንዶቹ ነፍሰ ጡር”) እንዲሁም ሽማግሌዎችንም ጭምር ጦርነቱ ላይ ማሳተፉ፣ ድርጊቱ ከሕግ ዉጪ መሆኑን እያወቁ እነሱ ግን ነገሩን ወንጀል መሆኑን ከመናገር ይልቅ ለህወሓት እንደ ማበረታቻ አድርገዉ መዘገባቸዉን የኒዉ ዮርክ ታይምስ(New York Times) ዘገባን ዋቢ አድርገዉ ጠቅሰዋል። በተመሳሳይም ዓለም ዐቀፍ ሚዲያዎች መተዳደሪያ መርህ ያላቸዉ ቢሆንም፣ በሌሎች አገሮች ላይ በሚፈጸም ቀዉስ እና ግጭት ግን የራሳቸዉን መብት እስካልነካ እና ጥቅማቸዉን እሰካላስቀረ ድረስ እንዲሁም የሚፈልጉትን ሐሳብ የሚከተል መንግሥት እስካልሆነ ድረስ ግድ አይሰጣቸዉም በማለት በቅርቡ በደቡብ ሱዳን ላይ አሜሪካ ያደረገችዉን ማየቱ አስፈላጊ ነዉ ይላሉ።

አሜሪካ የኢትዮጵያ እና ኤርትራ አብሮ መሆን ያሳሰባት እስኪመስል ድረስ የተለያዩ ማዕቀቦች እና እገዳዎችን በተደጋጋሚ ስታሳርፉ ይስተዋላል። ይህም አሁን ላይ ኢትዮጵያ እና ኤርትራ መስማማታቸዉ ራስ ምታት እንደሆነባት ማሳያ ነዉ በማለት፣ ከዚህ በፊት የነበራቸዉን ጸብ ይፈልጉት እንደነበርም አይዘነጋም ሲሉ ሐሳባቸዉን ለአዲስ ማለዳ አጋርተዋል። በሌላ በኩል የኤርትራ ወታደር ከትግራይ ክልል እንዲወጣ ማድረግ የኢትዮጵያ እና የኤርትራ ጉዳይ ሆኖ ሳለ፣ አሜሪካም ሆነች ሌሎች የአዉሮፓ አገራት ጣልቃ መግባት የለባቸዉም። ይህ ደግሞ ኢትዮጵያ ከሌሎች አገሮች ያነሰ መብት ስለሌላት፣ የራሷ የሆነዉን ችግር መፍታት ያለባትም ኢትዮጵያ እንጂ አሜሪካ ወይም ሌላ አገር አይደለም ነዉ ያሉት።

ጠንካራ የዲፕሎማሲ ስትራቴጂ ለመቅረፅ እና የዉጭ ግንኙነት ለመፍጠር አዲስ አቅጣጫ ሊቀመጥ ይገባል። መንግሥትም በዚህ ዙሪያ ሰፊ ሥራ መሥራት ይጠበቅበታል ሲሉ ምክረ ሐሳባቸዉን ይሰጣሉ።
አንድ አገር የራሷን ሉዓላዊነት አስከብራ በነጻነት የመኖሯን ያህል፣ በየምክንያቱ ጣልቃ የሚገቡ አልፎ ተርፎም በአገር ጉዳይ ዉሳኔ ለማሳለፍ የሚጥሩ አገራት አልታጡም። በትግራይ ክልል በተከሰተዉ ጦርነት ምክንያትም በተለያየ ጊዜ የዉጭ ጣልቃ ገብነት ሲስተዋል መቆየቱ መዘንጋት የለበትም። ለዚህም ማሳያ መንግሥት ያለፈዉ ሰኔ 21 የተናጠል ተኩስ አቁም ስምምነት መምረጡ እና መከላከያ ሠራዊቱንም ከክልሉ ማስወጣቱ የሚታወስ ነዉ። ይህም የዓለም ዐቀፉ ማኅበረሰብ በተለይም አሜሪካ እና የአዉሮፓ ኅብረት ያላቸዉ ተጽዕኖ የጎላ ነዉ ያሉት ምሁራኑ፣ ኢትዮጵያ ያላትን የዲፕሎማሲ አቅጣጫ መቀየር እና አማራጭ የትኩረት አቅጣጫዎችን መጠቀም ይኖርባታል ብለዋል።

የዓለም ኃያላን አገራት ኢትዮጵያን አሁን ያለችበትን ሁኔታ በአግባቡ ካለመረዳታቸዉም በላይ ችግሩን በተገቢዉ መንገድ እና ሉዓላዊነቷን ባረጋገጠ መልኩ ለመፍታት ከመሞከር ይልቅ አንዱን ወገን የደገፈ ሌላዉን ደግሞ የሚነቅፍ ድርጊት ሲፈጽሙ እና ዉሳኔ ሲያሳልፉ ማየቱ የተለመደ ሆኗል።

ኢትዮጵያ በተለይም በምስራቅ አፍሪካ ያላትን የዲፕሎማሲ ሥርዓት የፈተነ እና የዉጭ ግንኙነቱን ያሻከረ የዲፕሎማሲ ጫና የበረታበት ሁኔታ የተባባሰ መሆኑን በጦርነቱ መከሰት ማግስት ሱዳን የፈጠረችዉን የድንበር ዉዝግብ ማየቱ በቂ ነዉ። ከዚህ ጋር ተያይዞም፣ አሜሪካ ባለፉት ጊዜያት ሦስቱን አገራት፤ ኢትዮጵያ፣ ግብጽ እና ሱዳን በታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ ዙሪያ ለማደራደር ያደረገችዉ ሙከራ ሚዛናዊ የጎደለው ለመሆኑ ማሳያ ነዉ።


ቅጽ 3 ቁጥር 147 ነሐሴ 22 2013

Comments: 0

Your email address will not be published. Required fields are marked with *

This site is protected by wp-copyrightpro.com