የእለት ዜና

የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ በማስተማር ላይ ከተሠማሩ ሲቪል ማኅበረሰብ ድርጅቶች ጋር ተወያየ

የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ነሔሴ 17/2013 አገር ዐቀፍ ምርጫውን አስመልክቶ በማስተማር ላይ ከተሠማሩ ሲቪል ማኅበረሰብ ድርጅቶች ጋር ውይይት ማካሄዱን ገልጿል።
በሲቪክና የመራጮች ትምህርት ክፍል አስተባባሪነት ማኅበራቱ በቡድን በቡድን ሆነው በምርጫው ወቅት አሳካናቸው ስለሚሏቸው እና ተግዳሮቶች ነበሩ ስላሏቸው እንዲሁም በቀጣይ ምን መሠራት አለበት ስለሚሉት ነገር ተወያተዋል። ማኅበራቱ በቡድን ሆነው ባካሄዱት ውይይት የደረሱባቸውን ዝርዝር ነጥቦች በቡድን ተወካዮቻቸው አማካይነት ያቀረቡ ሲሆን፤ ለመራጮች ትምህርት የተጠቀሟቸውን የማስተማሪያ አማራጮችና ቋንቋዎች በዝርዝር አስረድተዋል። በዚህም የምርጫው ሠላማዊነት፣ መራጮች በነቂስ ወጥተው መምረጣቸው፣ ትምህርቱ በብሬልና በኦዲዮ መታገዙ እንደ ስኬት ከተወሰዱ ነጥቦች መካክል ሲጠቀሱ፤ የፀጥታ ሁኔታ፣ ሎጀስቲክና ፋይናንስ በምርጫው ትምህርት ላይ ውሱንነት ከፈጠሩባቸው ዝርዝሮች ውስጥ ተጠቅሰዋል።
የቦርድ አመራር አባል የሆኑት አበራ ደገፋ (ዶ/ር) በመድረኩ መዝጊያ ላይ ባደረጉት ንግግር፣ ምርጫ የኹሉም ብቁ ዜጋ ሥራና ኃላፊነት እንደሆነ ገልጸው፣ በምርጫ ትምህርት ጊዜ የሚሰጠው ትምህርት በተለይም የድምጽ መስጫ ወረቀት አጠቃቀምን አስመልክቶ የሚሰጠው ትምህርት ወሣኝ እንደሆነና የተበላሹ ድምጽ መስጫዎችን በማስቀረት የዜጎች ድምጽ እንዳይባክን እንደሚረዳ ገልጸዋል።
በዕቅድ አፈጻጸም ወቅትም የትኞቹን ማስቀደምና የትኞቹን ደግሞ ማዘግየት እንደሚቻል ለይቶ ወደ ሥራ መግባቱ አፈጻጸሙን የተሻለ እንደሚያደገው፣ ሪፖርቶችንም በጊዜ ለቦርዱ ማስገባት ትልቅ ፋይዳ እንዳለው አብራርተዋል። በማኅበራቱ የተጠቀሱትን ተጨባጭነት ያላቸውን ውሱንነቶችም ቦርዱ እንደሚሠራባቸው፤ ያም ሲባል ግን ሁሉም ችግሮች በአንዴ ይፈታሉ ማለት እንዳልሆነ አጽንዖት ሰጥተዋል። ቦርዱ ቀደም ሲል ሐምሌ 23/2013 አገር ዐቀፍ ምርጫውን አስመልክቶ ቀዳሚ መግለጫ ካወጡና በመታዘብ ላይ ከተሠማሩ የሲቪል ማኅበረሰብ ድርጅቶች ጋር ውይይት ማካሄዱ ይታወሳል።


ቅጽ 3 ቁጥር 147 ነሐሴ 22 2013

Comments: 0

Your email address will not be published. Required fields are marked with *

This site is protected by wp-copyrightpro.com