የእለት ዜና

ቅሬታ የተነሳባቸው የምርጫ ጉዳዮች እና የቦርዱ ውሳኔዎች

Views: 147

የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ስድስተኛው አገራዊ ምርጫ በአንድ ጊዜ ለማካሄድ ባለመቻሉ፣ ምርጫውን በኹለት ዙር ለማካሄድ መወሰኑ የሚታወስ ነው። ምርጫ ቦርድ ሰኔ 14/2013 ያካሄደውን የመጀመሪያ ዙር ምርጫ ውጤት ይፋ ማድረጉ የሚታወስ ነው።
ቦርዱ የመጀመሪያ ዙር ምርጫ አካሂዶ ውጤት ይፋ ቢያደርግም፣ አጠቃላይ የምርጫ ውጤቱን ለማወቅ ሰኔ 14 ምርጫ ባልተካሄደባቸው አካባቢዎች ምርጫ ማድረግ ስላለበት፣ ኹለተኛውን ዙር ምርጫ መስከረም 20/2014 ለማካሄድ ባሳለፍነው ሳምንት መወሰኑ የሚታወስ ነው። በመጀመሪያው ዙር ምርጫ ያልተካተቱ ክልሎችና ከክልሎች ተቆርጠው የቀሩ አካባቢዎች ላይ ደግሞ ቅሬታዎች ነበሩ።

የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ባሳለፍነው ሳምንት የመራጮች ምዝገባ ባልተደረገባቸው እና ምርጫ የተቋረጠባቸው የምርጫ ክልሎችን አስመልክቶ ውሳኔ አስተላልፏል። ቦርዱ 6ተኛው አጠቃላይ ምርጫ በዋናነት ሰኔ 14/2013 አስፈጽሟል። ይሁን እንጅ በመራጮች ምዝገባ ሒደት ጉልህ ግድፈቶች የታዩባቸውን እና በመራጮች ምዝገባ ላይ አቤቱታዎች የቀረቡባቸውን ለማጣራት ጊዜ በማስፈለጉ፣ እንዲሁም ከጸጥታ ችግር ጋር በተያያዘ ሰኔ 14/2013 ምርጫ ያልተደረገባቸው ቦታዎች መኖራቸው ይታወቃል።
በመሆኑም የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ የሥራ አመራር ቦርድ ሰኔ 14 ምርጫ ያልተከናወነባቸው የምርጫ ክልሎችን፣ የምርጫው ሒደት ያለበትን ሁኔታ እና የመሳሰሉትን በመገምገም ውሳኔዎችን አሳልፏል።

በመጀመሪያው ዙር ምርጫ ሙሉ በሙሉ ካልተካታቱ ክልሎች መካከል የሶማሌ ክልል አንዱ ነው። በክልሉ የመራጮች ምዝገባ እየተከናወነ በነበረበት ወቅት ከፓለቲካ ፓርቲዎች በቀረበ አቤቱታ ቦርዱ የመራጮች ምዝገባ ሒደቱ መጣራት ይገባዋል ብሎ በማመኑ፣ የመራጮች ምዝገባ እንዲቆም አድርጓል። በዚህም 10 የምርጫ ክልሎች ላይ የመራጮች ምዝገባን የሚመረምር ከተለያዩ ሲቪል ማኅበራት የተወጣጣ አጣሪ ቡድን በመላክ የመራጮች ምዝገባ ሒደት ላይ የቀረቡትን አቤቱታዎች አጣርቻለሁ ብሏል።

በማጣራት ሒደቱም አቤቱታ የቀረበባቸው ምርጫ ክልሎች ላይ የፓለቲካ ፓርቲዎች ተወካዮችን ምስክርነት በመስማት፣ የሰነድ ማስረጃዎችን በመመርመር፣ የመራጮች ምዝገባ ሒደቱን በየጣቢያዎች በመጎብኘት ሪፓርት እና የውሳኔ ሐሳብ ለቦርዱና ለፓለቲካ ፓርቲዎች አቅርቧል። ቦርዱ ሪፓርቱን በመመርመር፣ ፓርቲዎች በሪፓርቱ ላይ አስተያየት እንዲሰጡ በማድረገወ የመርማሪ ቡድኑን ግኝት ሪፓርቶች መሠረት አድርጎ ውሳኔ አሳልፏል።

ቦርዱ የአጣሪ ቡድኑ ግኝትን መሠረት በማድረግ በኹለት የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት እና አራት የክልል ምክር ቤት የምርጫ ክልሎች ላይ የመራጮች ምዝገባ ሙሉ ለሙሉ በድጋሚ እንዲከናወን ወስኗል።

ቦርዱ ሙሉ ለሙሉ የመራጮች ምዝገባ እንዲደገም ውሳኔ የሰጠባቸው የተወካዮች ምክር ቤት ምርጫ ክልሎች ጅጅጋ አንድ እና ጅጅጋ ኹለት ምርጫ ክልል ናቸው። ሙሉ በሙሉ የመራጮች ምዝገባ እንዲደረግ የተወሰነባቸው የክልል ምክር ቤት ምርጫ ክልሎች ቀብሪደሃር ከተማ ምርጫ ክልል፣ ቀብሪደሃር ወረዳ ምርጫ ክልል፣ መኢሶ ምርጫ ክልል እና አፍደም ምርጫ ክልል መሆናቸውን ቦርዱ አሳውቋል።

በክልሉ በምርጫ ክልል ደረጃ የመራጮች ምዝገባ ሙሉ በሙሉ እንዲደገም ከተወሰነባው በተጨማሪ ምርጫ ጣቢያዎች ላይ የመራጮች ምዝገባ እንዲደገም ተወስኗል። ከነዚህም ምርጫ ጣቢያዎች መካከል ዋርዴር ምርጫ ክልል ውስጥ አዶ ቀበሌ አንድ ምርጫ ጣቢያ እና ኤልድብር ቀበሌ ኹለት ምርጫ ጣቢያዎች፣ ፊቅ ምርጫ ክልል አንድ ቀበሌ ምርጫ ጣቢያ 01 – 1 ምርጫ ጣቢያ፣ ገላዴን ምርጫ ክልል አንድ ምርጫ ጣቢያ፣ ጎዴ ከተማ ምርጫ ክልል አራት ምርጫ ጣቢያዎች፣ ምስራቅ ኢሜ ምርጫ ክልል ሦስት ምርጫ ጣቢያዎች እና ቤራኖ ምርጫ ክልል ሦስት ምርጫ ጣቢያዎች መሆናቸውን ቦርዱ አስታውቋል።

በክልሉ የመራጮች ምዝገባ አቤቱታ የተነሳ የመራጮች ምዝገባ ከመጠናቀቁ በፊት በተቋረጠባቸው ቦታዎች ሁሉ ለአምስት ቀናት ያህል የመራጮች ምዝገባ ተሟልቶ እንዲጠናቀቅ ምርጫ ቦርድ መወሰኑን አስታውቋል።
የክልል ምርጫ ሙሉ በሙሉ ወደ ኹለተኛው ዙር የተሸጋገረበት ሐረሪ ክልል ሲሆን፣ ቦርዱ የክልሉን የመራጮች ምዝገባ አስመልክቶ ውሳኔ ሰጥቷል።

በሐረሪ ክልል ቦርዱ በሰጠው የአመዘጋገብ አሠራረር መሠረት የመራጮች ምዝገባ ባለመከናወኑ ምዝገባው ተቋርጦ ቦርዱ በሚሰጠው ውሳኔ መሠረት እንደሚከናወን መገለጹ ይታወሳል። በዚህም መሠረት ቦርዱ በሐረሪ የተከናወነውን የመራጮች ምዝገባ ከመረመረ በኋላ ውሳኔ አሳልፏል።

በጀጎል ዙሪያ እና ሁንደኔ የምርጫ ክልል በተለያየ የክልል እና የተወካዮች ምክር ቤት መቀመጫዎች የሚመርጡትን የሐረሪ ብሔረሰብ ተወላጆችን እና ከብሔረሰቡ ውጪ ያሉ ተወላጆች ተቀላቅለው በመመዝገባቸው ምዝገባው ተለያይቶ እንደአዲስ እንዲካሄድ መወሰኑን ቦርዱ አስታውቋል።

በጀጎል ልዩ ምርጫ ክልል የመራጮች ምዝገባ ተቋርጦ ስለነበር ለአምስት ተጨማሪ ቀናት የማሟያ ምዝገባ እንዲከናወን የተወሰነ ሲሆን፣ በሰበር ችሎት በተወሰነው መሠረት ከክልሉ ውጪ የሚኖሩ የብሔረሰቡ ተወላጆች የሚመርጡባቸው ምርጫ ጣቢያዎች እንዲቋቋሙ ወሳኔ ተስጥቷል።

የሐረሪ ክልል ተወላጆች ከክልሉ ውጭ በሚኖሩባቸው አካባቢዎች የምርጫ ጣቢያ ተቋቁሞላቸው እንዲመርጡ ይደረግ በማለት ክልሉ ምርጫ ቦርድን መክሰሱ የሚታወስ ነው። በፍረድ ቤቱ ውሳኔ መሠረት የክልል ተወላጆች በአዲስ አበባ ከተማ መስተዳድር፣ ኦሮሚያ ብሔራዊ ክልል ( አዳማ፣ ጭሮ፣ ኮምቦልቻ፣ ጉርሱም፣ ፈዲስ፣ ደደር እና ሐሮማያ)፣ ድሬዳዋ ከተማ መስተዳድር፣ ሶማሌ ብሔራዊ ክልል እና ደቡብ ብሔር ብሔረሰቦች እና ሕዝቦች ክልል የምርጫ ጣቢያ ተቋቁሞላቸው እንዲመርጡ ተወስኗል።

በቅድ ምርጫ ዝግጅት ወቅት በደቡብ ብሔር ብሔረሰቦች እና ሕዝቦች ክልል ያለአግባብ ምዝገባ የተከናወነባቸው የምርጫ ክልሎች የድጋሚ ምርጫ ሙሉ ለሙሉ እንዲከናወን ውሳኔ ላይ መደረሱን ቦርድ ገልጿል። በክልሉ ሙሉ በሙሉ ምርጫ እንዲደገም የተወሰነባቸው ምርጫ ክልሎች ዘልማም፣ ፣ ሱርማ ፣ ሙርሲ እና ዲዚ ልዩ ምርጫ ክልል እንዲሁም ማጀት መደበኛ ምርጫ ክልል (ከልዩ ምርጫ ክልሎች ውጪ ያሉት ነዋሪዎች የሚመዘገቡበት) ናቸው።

በደቡብ ክልል በጉራፈርዳ ወረዳ የሚገኙ በቴፒ እና ሸኮ ልዩ የሚጠቃለሉ ጣቢያዎችን በተመለከተ ቦርዱ ተጨማሪ ውሳኔን እንደሚያስተላልፍ ነሐሴ 17/203 ባወጣው መግለጫ ጠቁሟል።
ኢትዮጵያ ስደስተኛውን አገራዊ ምርጫ ከብዙ ውጣ ውረድ በኋላ በመላው አገሪቱ ባይሆንም ባለሳለፍነው ሰኔ አካሂዳለች። ሰኔ 14 በተካሄደው ስድስተኛው አገራዊ ምርጫ ሙሉ በሙሉ ያልተካተቱ እና በከፊል ምርጫ የተካሄደባቸው ክልሎች አሉ። ሙሉ በሙሉ ምርጫ ያልተደረገባቸው ሱማሌ፣ ትግራይና ሐረሪ ክልል ሲሆኑ፣ በከፊል ምርጫ ከተካሄደባቸው ክልሎች መካከል አማራ፣ ኦሮሚያ፣ ቤኒሻንጉል ጉምዝና ደቡብ ክልል ይገኙበታል።

በከፊል ምርጫ ከተደረገባቸው ክልሎች መካከል ቤኒሻንጉል ጉምዝ ክልል ካሉት ሦስት ዞኖች ምርጫ የተካሄደው በአንዱ መሆኑ የሚታወስ ነው። በቤኒሻንጉል ጉምዝ ክልል ምርጫ ያልተደረገባቸው ኹለት ዞኖች መተከልና ካማሺ ዞኖች ሲሆኑ፣ በዞኖች በተፈጠረው የጸጥታ ችግር የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ምርጫ ማካሄድ አልችልም በማለቱ ነው።

የመጀመሪያው ዙር ምርጫ የተካሄደባቸው ከቤኒሻንጉል ክልል ውጭ አብዛኛውን ክፍል ያካተተ ሲሆን፣ በክልሎች የተወሰኑ አካባቢዎች ምርጫ ሳይከናወን የቀረው በጸጥታ ችግር እና ድምጽ መስጫ ወረቀት ኅትመት ላይ ባጋጠመ ችግር መሆኑን የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ መግለጹ የሚታወስ ነው።

ሰኔ 14/2013 የተካሄደውን የመጀመሪያ ዙር አገራዊ ምርጫ ውጤት ከግማሽ ወር በኋላ ባሳለፍነው ሐምሌ 3/2013 በኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ይፋ ሆኗል። ቦርዱ ይፋ ባደረገው የምርጫ ውጤት 547 መቀመጫዎች ካሉት ኢትዮጵያ ሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት በመጀመሪያው ዙር ምርጫ 465 የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት መቀመጫዎች ተካተዋል። ይህም ማለት ከመጀመሪያው ዙር ምርጫ ተቆርጠው የቀሩ የሕዝበ ተወካዮች ምክር ቤት መቀመጫዎች ብዛት 82 መቀመጫዎች ናቸው።

የመጀመሪያ ዙር ጊዜያዊ ውጤት ይፋ ያደረገው የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ፣ ከ436 የሕዝብ ተወካዮች መቀመጫ ገዥው ብልጽግና 410 ወንበሮችን ማሸነፉን ቦርዱ መገልጹ የሚታወስ ነው። ቦርዱ በገለጸው ውጤት መሰረት በመጀመሪያው ዙር ምርጫ 26 የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት በተፎካካሪ ፖለቲካ ፓርቲዎች እና በግል ተወዳዳሪዎች ተይዘዋል።


ቅጽ 3 ቁጥር 147 ነሐሴ 22 2013

Comments: 0

Your email address will not be published. Required fields are marked with *

This site is protected by wp-copyrightpro.com