የእለት ዜና

ለአውቶብሶች ብቻ በተዘጋጀው መስመር ሲጠቀሙ የተገኙ ዘጠኝ ሺሕ ተሽከርካሪዎች መቀጣታቸው ተገለጸ

አዲስ አበባ ከተማ በተለይ በሥራ መግቢያና መውጫ ሰዓት ያለውን የትራፊክ መጨናነቅ ለመቀነስ በሚል የሕዝብ ማመላለሻ ተሽከርካሪዎች እንዲጓጓዙበት ተብሎ ለሌሎች የተከለከለን መስመር የተጠቀሙ ዘጠኝ ሺሕ ተሽከርካሪዎች መቀጣታቸው ተገለጸ::

የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ትራንሰፖርት ቢሮ ያዘጋጀው መመርያ ለሕዝብ ማመላለሻ(አውቶቢስ) ተሽከርካሪዎች ብቻ ተብሎ በተፈቀደው የመንገድ መስመር ላይ ሌሎች ተሽከርካሪዎች መጠቀም እንደማይችሉ ተደንግጓል:: ይሁን እንጂ ይህን ክልከላ በመተላለፍ ሌሎች በርካታ ተሽከርካሪዎች የመንገድ መስመሩን እየተጠቀሙ እንዳሉ እና በትራፊክ ፍሰቱ ላይ አሉታዊ ተጽዕኖ እያሳደሩ እንደሚገኙ ነው የከተማው ትራንስፖርት ቢሮ ለአዲስ ማለዳ የገለፀው::

መመሪያው ተግባራዊ ከሆነ በኋላ ሕጉን የተላለፉ የተለያዩ አሸከርካሪዎችን ግንዛቤ እንዲጨብጡ እየተደረገና ጥፋተኛ የሆኑትም ላይ የማስጠንቀቂያ ዕርምጃ እየተወሰደ የሚገኝ ሲሆን፣ ለውጥ ያላመጡ አሽከርካሪዎች ላይ የገንዘብ ቅጣት ዕርምጃ እየተወሰደ መሆኑን የአዲስ አበባ ትራንስፖርት ቢሮ ሕዝብ ግንኑነት ኃላፊ አረጋዊ ማሩ አስታውቀዋል።

ኃላፊው እንደተናገሩት በከተማዋ አምስት ቦታዎች ማለትም ከሜክሲኮ-ጀሞ፣ ከሜክሲኮ -ስታዲየም፣ ከለጋሃር -ፒያሳ፣ ከአምበሳ ጋራጅ -ጎሮ እና ከላምበረት-ወሰን እስከ ካራ አገልግሎቱ ተግባሪዊ እንደሆነ ተናግረዋል። መስመሩ ያስፈለገው ለአውቶቢሶች ለምልልስ እንዲያመች፣ ለእሳት አዳጋ፣ ለመከላከያ፣ ለአንቡላንስ ተሸከርካሪዎች ተጨማሪ አግልግሎቶች እንዲውል እንደሆነ አስረድተዋል።

የትራፊክ ደንብ እና ሕግን በመተላለፍ ከ 4ሺሕ 440 በላይ አሽከርካሪዎች፣ እንዲሁም በተንቀሳቃሽ ስልክ እያወሩ የሚያሽከረክሩ ከ 10 ሺሕ በላይ አሽከርካሪዎች ላይ ዕርምጃ ተወስዷል ብለዋል።
በከተማዋ ላይ ለሚስተዋለው የትራፊክ አደጋ እንደ መንስኤ በሚጠቀሰው ከተቀመጠው የፍጥነት ልክ በላይ በማሽከርከር 1 ሺሕ 20 በሚሆኑ አሽከርካሪዎች ላይ የቅጣት ዕርምጃ እንደተወሰደ አረጋዊ ለአዲስ ማለዳ ተናግረዋል።

በደንብ 395 መሠረት የአሽከርካሪዎች የጥፋት መጠን ተደምሮ የሚጨምር የነጥብ እርከን መነሻነት 290 የሚደርሱ በሰው ላይ ሞት ያስከተሉ እና 827 ከባድ ጉዳት ያስከተሉ በድምሩ 1 ሺሕ 117 የሚደርሱ አሽከርካሪዎች የመንጃ ፈቃዳቸው ሙሉ በሙሉ የታገደ ሲሆን፣ የሚፈጸመው የትራፊክ ጥሰት በነጥብ ላይ እየተደመሩ የመንጃ ፈቃድ እስከማሳገድ የሚደርስበት ሁኔታ መኖሩን አንስተዋል።

እንዲሁም የትራፊክ ማመላከቻዎችን፤ መቆም የሚከለክለውን፣ መታጠፍን እና አስገዳጅ ምልክቶችን የተላሉፉ 30 ሺሕ አሽከርካሪዎች ላይ ዕርምጃ መወሰዱን አክለዋል። በቀጣይ 2014 ከዚህ ቀደም የነበሩትን አምስት መስመሮችን ከሜክሲኮ-ጀርመን አደባባይ የነበረውን መስመር ወደ ጀሞ፣ ከሜክሲኮ-ሳር ቤት የነበረውን አስከ ኃይሌ ጋርመንት፣ ከመገናኛ-ላምበረት የነበረውን ወደ ሰላም ሆቴል፣ ከሜክሲኮ-ፒያሳ የነበረውን አዲሱ ገበያ ድረስ የማሻሻል ሥራ እንደሚሠራ አስታውቀዋል።

እንዲሁም፣ አዲስ መስመሮችን ከፒያሳ-ዊንጌት፣ ከጦር ኃይሎች-አየርጤና፣ ከቅዱስ እስጢፋኖስ-አራት ኪሎ-ሽሮሜዳ፣ ከመገናኛ-ቀበና መስመር ለመዘርጋት በዕቅድ እንደተያዘ እና በተያዘው በጀት ዓመት አጋማሽ ተግባር ላይ እንደሚውል ኃላፊው ለአዲስ ማለዳ ተናግረዋል። ከዚህ ቀደም 1ሺሕ 300 የትራፊክ ተቆጣጣሪዎች ሥራውን ያከናውኑ የነበረ ሲሆን፣ ቀጣይ በሚከወነው የመስመር ማሻሻል አና ጭማሪ ተመሳሳይ የትራፊክ ተቆጣጣሪዎች እንደሚካተቱ ተመላክቷል።


ቅጽ 3 ቁጥር 147 ነሐሴ 22 2013

Comments: 0

Your email address will not be published. Required fields are marked with *

error: Content is protected !!