የእለት ዜና

የቆዳ ኢንዱስትሪው ለማግኘት ካቀደው የውጭ ምንዛሬ ከግማሽ በታች ማሳካቱን አስታወቀ

የኢትዮጵያ ቆዳ ኢንዱስትሪ ልማት ኢንስቲትዩት በ2013 በጀት ዓመት ለማስገባት አቅዶ ከነበረው የውጭ ምንዛሬ ገቢ ውስጥ ከግማሽ በታች የሆነውን ብቻ ማግኘቱን አስታወቀ።
ተቋሙ በበጀት አመቱ 100 ሚሊዮን የአሜሪካን ዶላር ለማስገባት አቅዶ ወደ ሥራ ቢገባም ማሳካት የቻለው ግን 40 ሚሊዮን ዶላር ብቻ መሆኑን የተቋሙ ኮሚዩኒኬሽን ጉዳይ ዳይሬክተር የሆኑት ብርሀኑ ሰርጀቦ ለአዲስ ማለዳ አስታውቀዋል።

በመላው ዓለም የተከሰተው የኮቪድ-19 ወረርሽኝ ዘርፉን እጅጉን እንደፈተነው የሚገልጹት ብርሀኑ፣ የታቀደውን ያህል የውጭ ምንዛሬ እንዳይገኝም ትልቅ እንቅፋት እንደፈጠረ አያይዘው አንሰተዋል።
የቆዳ ኢንደስትሪው የታሰበውን ያህል የውጭ ምንዛሬ አንዳያስገኝ በተጨማሪ ምክንያትነት የተነሳው ግብዓቶችን ለማስገባት የሚያስፈልገው የውጭ ምንዛሬ አለመገኘት መሆኑ ተነስቷል።

የውጭ ምንዛሬ ዕጥረቱ በፋብሪካዎች ለሚከወነው የምርት ሒደት አስፈላጊ የሆኑ የኬሚካል ምርቶችን በተገቢው ጊዜ እነ መጠን ወደ አገር ውስጥ ለማስገባት እክል በመፍጠሩ የተፈለገውን ያህል የውጭ ምንዛሬ ላለመገኘቱ የራሱን ሚና ተጫውቷል።
ለግብዓትነት የሚያገለግሉ ኬሚካሎችን ከማስገባት ጋር በተያያዘ የተከሰተው የውጭ ምንዛሬ ዕጥረትን በተመለከተ ከፍተኛ የመንግሥት ኃላፊዎችን ጨምሮ ከባንኮች ጋር ውይይት እየተደረገ ነው። ይህ ውይይት ውጤት አምጥቶ በሚቀጥለው የበጀት ዓመት ላይ የተሻለ አፈጻጸም ለማስመዘገብ ትኩረት ተደርጎ እየተሠራ እንደሆነ ታውቋል።

በ2013 በጀት ዓመት የኮቪድ-19 ሥርጭት ይቀንሳል በሚል ዕሳቤ 100 ሚሊዮን የአሜሪካ ዶላር በውጭ ምንዛሬ ለማግኘት ታቅዶ እንደነበር የሚያነሱት ዳይሬክተሩ፣ ሥርጭቱ ግን ከመቀንስ ይልቅ አድማሱን አስፍቶ የኢትዮጵያን ምርት በሚቀበሉ አገራት ከቤት አለመውጣት በመታወጁ ምክንያት ይገኛል ተብሎ የታሰበው የውጭ ምንዛሬ ግኝት ማሽቆልቁል ታውቋል።

በ2013 በጀት አመት መንግሥት በተቀዛቀዘው ገበያ ምክንያት ፋብሪካዎች ሠራተኞቻቸውን እንዳይበትኑ ከማድረግ አንጻር የተሳካ አካሄድ ማስመዘገቡን የሚገልጹት ብርሀኑ፣ ከዛም ባለፈ ገበያው ባይኖር እንኳን ፋብሪካዎች አምርተው እንዲያስቀምጡ የማድረግ ሥራ ሲሠራ መቆየቱን ገልጸው። ይህም በኮቪድ ምክንያት ተዘግተው የቆዩ አገራት ሲከፈቱ ምርትን በአፋጣኝ ለመላክ እንዲረዳ ለማስቻል ታስቦ መሆኑን ይጠቅሳሉ።

እንደነዚህ አይነት የመፍትሔ መንገዶችን መጠቅም በመቻሉ ለ2014 በጀት ዓመት ተስፋ ሰጪ ምልክቶች እየታዩ መሆኑን የሚናገሩት የኮሚዩኒኬሽን ዳይሬክተሩ፣ በሐምሌ ወር ብቻ 2.8 ሚሊዮን ዶላር ገቢ መገኘት መቻሉንና ይህም ተስፋ ሰጪ መሆኑን ጨምረው ያነሳሉ።
በፋብሪካዎች መካከል በሠፊው የሚታየውን የቅንጅት ጉደለት እና በመሀል የሚፈጠርን ክፍተት ለመሙላት መንግሥት ፋብሪካዎችንን አቀራርቦ ለማሠራት ጥረት እያደረገ መሆኑ ተናግረዋል። በዚህም ሒደት የጥራትና የምርት መጠንን ለመጨመር እንቅስቃሴ ውስጥ ተገብቷል።

የኢትዮጵያ ቆዳ ኢንዱስትሪ ልማት ኢንስቲትዩት በ2014 በጀት ዓመት ከ100 እስከ 120 ሚሊዮን የአሜሪካ ዶላር ላመግኘት አቅዶ እንቅስቃሴ ውስጥ ገብቷል የሚሉት ብርሀኑ፣ ይሄንንም ለማድረግ በ2013 በጀት ዓመት ያጋጠሙ ችግሮችን በመለየት ለ2014 በመቅረፍ ዕቅዱን ለማሳከት እንደሚሠራም ጨምረው ገልጸዋል።

በተጨማሪም በዓመቱ ስድስት ጥናቶችን ተቋሙ ያስጠና መሆኑ እና ከነዚህ ጥናቶች መሀል ከውጭ የሚገቡ እንደ ኬሚካል ያሉ ግብዓቶችን በአገር ውስጥ ምርት በመተካት ለመቀነስ የሚያስችል ጥናት ተሰርቶ ተስፋ ሰጪ ነገሮች በመታየታቸው ተጠናክሮ የሚቀጥልበት ሁኔታ እንደሚመቻች ተጠቁሟል። ከዚህም በተጨማሪ ከፋብሪካ በሚወጡ ተረፈ ምርቶች የአካባቢ መበከል እንዳይከሰት ከፋብሪካዎቹ ጋር በቅርበት እየተሠራ መሆኑንም ብርሀኑ ሰርጀቦ ለአዲስ ማለዳ ተናግረዋል።


ቅጽ 3 ቁጥር 147 ነሐሴ 22 2013

Comments: 0

Your email address will not be published. Required fields are marked with *

error: Content is protected !!