የእለት ዜና

የተቀናጀ ፣ የአጋርነት እና የማህበረሰብ ፍላጎት እና ጥቅም የማስቀደም አሰራር ስርአትን ማጠናከር ለተሻለ ውጤት

Views: 118

ፒ.ኤች.ኢ ኢትዮጵያ ኮንሶርትየም የተቀናጀ አሰራርን ለማስተዋወቅ እና በስፋት እንዲተገበሩ በማድረግ የሰዎች እና የአካባቢ መስተጋብር ተጠጥሞ ዘላቂ ልማትን እውን ርዕይን አንግቦ በ2000 ዓ.ም የተመሰረት ድርጅት ነው።
ድርጅቱ ከተመሰረተበት ጊዜ አንስቶ እስካሁን ድረስ የአካካቢ፣ የሥነ-ሕዝብ፣ የማኅበራዊ፣ የኢኮኖሚ እና የጤና ጉዳዮችን ያቀናጁ የተለያዩ የልማት ሥራዎች ሲያከናውን ቆያቷል።
በዚህ ገጽ ላይ የተካተቱት የተለያዩ አካላት ሐሳቦች የፒኤችኢ ኢትዮጵያን አቋም ላያንጸባርቁ ይችላሉ።

ፒ ኤች ኢ ኢትዮጵያ ኮንሰርቲም 71 የሀገር ውስጥና አለም አቀፍ ሲቪክ ማህበራት በአባልነት አቅፎ የያዘ የሲቪክ ማህበር ነው፡ ጥምረቱ በስነ-ህዝብ፤ ጤና ፤ የአካባቢ እና አየር ንብረት ለውጥ ፤ ዲሞክራሲ ግንባታ ፤ እንዲሁም ሰብአዊ መብት ላይ የሚሰራ ሲሆን ፤ ሁሉም ባለድርሻ አካላት የሚጠበቅባቸውን ሚና ከተወጡ የተሻለ ውጤት እንደሚመጣ በመገንዘብ በአጋርነትና በቅንጅት የመስራትን ፋይዳ በብዙ መልኩ ያረጋገጠ ተቋም ነው።

በተለያዩ የውይይት መድረኮች እንዲሁም ስልጠናዎች የተለያዩ አጀንዳዎች በመቅረጽ ያወያያል፤ ‹‹በኢትዮጵያ የምግብ ሥርዓትን ለመለወጥ የወጣቶች ሚና›› በሚል መሪ ቃል ነሐሴ 12 ዓለም ዐቀፍ የወጣቶች ቀንን ተመርኩዞ ‹‹የምግብ ስርዓትን በኢትዮጵያ ለመለወጥ የወጣቶች ሚና›› በሚለው ጉዳይ ላይ ቁልፍ ባለድርሻ አካላት በተገኙበት የግማሽ ቀን ውይይት አዘጋጅቶ ነበር። የውይይት መድረኩ ወጣቶች እና አርሶ አደሮች የምግብ ስርዓቶችን ለሕዝቦች ደኅንነት መለወጥ ላይ በሚደረገው ትግል ውስጥ በተሻለ ሁኔታ እንዲቀመጡ ለመደገፍ በመሳሪያዎች፣ ፖሊሲዎች እንዲሁም የተለያዩ የልምድ ልውውጦች የተደረጉበት ነበር።

የስነ ህዝብ ጤና እና አካባቢ ላይ ትኩረቱን በማድረግ እየሰራ የሚገኘው ፒ ኤች ኢ ኢትዮጵያ ኮንሰርቲም የዘንድሮውን የአለማአቀፍ የወጣቶች ቀን የፌደራል ከፍተኛ የስራ ሃላፊዎች ከተለያዩ የማህበረሰብ ክፍል የተወከሉ ወጣቶችን ጨምሮ በርካታ ባለድርሻ አካላት በተገኙበት በዓሉን በፓናል ውይይት አክብሯል። በውይይቱ ላይ በክብር እንግድነት የተገኙት የሴቶች ህጻናትና ወጣቶች ሚኒስቴር ሚኒስትር ዲኤታ ወ/ሮ ሕይወት ሀይሉ የበዓሉን አስፈላጊነት በተመለከተ ማብራሪያ ሰጥተዋል።

‹‹በአሉ የተባበሩት መንግስታት ድርጅት የወጣቶችን ፍላጎት መሰረት በማድረግ በሚያወጣቸው መሪ ቃሎች በየዓመቱ የሚከበር፣ የሚታወስ ሆኖ ይገኛል። እንግዲህ ዘንድሮም ከምግብ ስርዓት ለውጥ ጋር ተያይዞ፤ ከወጣቶች ፈጠራና ለሰው ልጆች ብሎም ለምድራችን ጤና ጋር በማያያዝ የወጣቶች ቀን ቡድን›› ተዘጋጅቷል ብለዋል።

የፓናል ውይይቱ አላማ በምግብ ስርዓት ላይ የወጣቶች ሚና ምን መምሰል አለበት የሚል ሲሆን፣ ወጣቶችም ሚናቸውን በግልጽ አውቀው እንዲወጡ ለማስቻል መሆኑም ተገልጿል።
አለማአቀፍ ቡድኑን ከፒ ኤች ኢ ኢትዮጵያ ኮንሰርቲም መልክ ጋር መጥቶ የወጣቶች ሚና በምግብ ስርዓት መሻሻል ላይ ምንድነው የሚለውን ማየት ችለናል ሲሉ ወ/ሮ ፍሬዘር ይሄይስ ፒ ኤች ኢ ኢትዮጵያ ኮንሰርቲም ኮሚኒኬሸን ሀላፊ ገልጸዋል።

ከመንግስትም ፣ ከሲቪል ሶሳይቲ አንድ ላይ ቁጭ ብለው መነጋገራቸው አንድ የአንዱን ክፍተት የሚያይበት ነው። በመቀጠልም ከዚህ ባለፈ ውይይቱ ቢያልፍም ራሱን የቻለ ውጤት እና አቅጣጫ እንደሚኖረው ያነሱት ፍሬዘር በዚህ መልኩ ለውጥ ማምጣት ይቻላልም ብለዋል።
በውይይቱ ላይ የተሳተፉ ወጣቶችም የአለም ወጣቶች ቀን በተለይም ዘንድሮ በመሪ ቃልነት በተመረጠው ‹‹ ወጣትና የአመጋገብ ስርዓት ሽግግር›› የሚለው ላይ በማተኮር መከበሩ ተገቢ መሆኑን ከአለምአቀፍ ግብረሰናይ ደርጅት ፓዝፋይንደር ወክለው የተገኙት አበበ ካሳ ገልጸዋል።

ወጣቶች በስራ ፈጠራ እና ፈጠራ የታከለበት እንቅስቃሴ እንዲያደርጉ እድል የሚሰጥ በመሆኑ ልዩ እንደሚያደርገው ጠቁመዋል።
አብዛኛው የኢትዮጵያ የህብረተሰብ ክፍል ወጣት እንደመሆኑ መጠን ወጣቱን ያላሳተፈ ምንም አይነት እንቅስቃሴ ግቡን እንደማይመታና በዚህ ረገድ በኢትዮጵያ በአብዛኛው የሚስተዋለው የምግብ ስርዓት መዛባትን ለማረም ወጣቱ ዋነኛ ተዋናይ ሊሆን እንደሚገባው የውይይቱ ተሳታፊዎች አንስተዋል።

ከተሳታፊዎች መካከል ከወጣት ሴቶች ክርስቲያናዊ ማህበር የተገኘችው ወጣት ማርያማዊት ገዛኸኝ ወጣቱን በማነጋገር ለምንድነው ባህልን በዚህ መልኩ የቀየረው ምንድነው የጋበዘው በማለት ተጠይቋል።
በዚህም ባለማወቅ አንድ ምግብ ከውጭ ብቻ ስለመጣ ጥሩ ምግብ ነው ወይም ከኢትዮጵያ ምግብ ይበልጣል ብሎ መውሰድ ላያስፈልግ ይችላል ስትል ማርያማዊት ገልጻለች።
ወጣቶች በዚህ ላይ ትልቅ ሚና አላቸው የሚሉት ከእሴት ሰንሰለት አማካሪ ድርጅት የተገኙት የውይይቱ ተሳታፊ ወ/ሮ ሩታ ፍርድይንደሳው ናቸው።

እንደዚህ አይነት መድረኮችም ወሳኝ መሆኑን መረዳታቸውንና መነጋገር የሚያስፈልግ ጉዳይ መሆኑን ከአለም አቀፍ የሲቪክ ማህበር ተወክለው ውይይቱን የተሳተፉት ወ/ሮ ሩታ ገልጸዋል።
የፒኤችኢ ዋና ዳይሬክተር ነጋሽ ተክሉ በዕለቱ እንደገለጹት፣ PHE ያለውን ኃላፊነት መሠረት በማድረግ ከፍተኛ ባለሥልጣናት በተገኙበት ቀኑን ውይይት በማካሄድ አክብሮታል ሲሉ ገልጸዋል።

ዓለም ዐቀፍ የወጣቶች ቀን በተባበሩት መንግሥታት ድርጅት በወሰነው መሰረት በየዓመቱ ነሐሴ 12 ቀን ይከበራል። የተባበሩት መንግስታት ጠቅላላ ጉባኤ በ1999 የውሳኔ ሐሳብ 54/120ን ካጸደቀ በኋላ የመጀመሪያው የወጣቶች ቀን በፈረንጆች 2000 ተከብሮ ነበር። ዓላማውም ግንዛቤን ለመፍጠር እና በዓለም ዙሪያ ላሉት የተለያዩ ማኅበራዊ እና ባህላዊ ተግባራትን በማከናወን የወጣቶች ጉዳይ ትኩረት ለመሳብ በማሰብ ይከበራል። የተባበሩት መንግሥታት በወጣቶች ላይ ያተኮረበት ነጥብ ከወጣት አደረጃጀት እና በወጣቶች ልማት ውስጥ የተባበሩት መንግስታት የኢንተር- ኤጀንሲ አውታር መረብ አባላት ፣ ወጣቶች እና ሲቪል ማሕበረሰቡ የግንዛቤ ማስጨበጫ ሥራዎችን እንዲያደራጁ ለማበረታት ቀኑ ይከበራል።

በኢትዮጵያ ከ70 በመቶ በላይ የሚሆኑት ከ30 ዓመት በታች ያሉ ወጣቶች መሆናቸው የሚታወቅ ሲሆን፣ እነዚህ ወጣቶች ላይ ትኩረት ሰጥቶ መሥራት እንደሚገባ ተረፈ ተከተል የጤና ሚኒስቴርን በመወከል ተናግረዋል።
በዓለም ዐቀፍ ደረጃ የተከበረውን የወጣቶች ቀን ፒኤችኢ ትኩረት ሰጥቶ ማክበሩ መበረታታት ያለበት ነውም ብለዋል። የእናትና ወጣቶች ጤና በሚል ስትራቴጂ በመንደፍ ሚኒስቴር መሥሪያ ቤቱ እየሠራ እንደሚገኝ ተነስቷል።
በጤና ሚኒስቴር የሚዘጋጅ ከ300 ሰዎች በላይ የሚሳተፉበት የወጣቶች ቀንን የሚያመላክት ዝግጅት መኖሩ ተጠቁሟል።

የወጣቶች ጤናን በተመለከተ ግንዛቤን በመፍጠር እና የመከላከል ሥራዎችን በመሥራት የሚታወቀው ጤና ሚኒስትር፣ የአእምሮ ጤናን በመጠበቅ ትኩረት ሰጥቶ እየሠራ ይገኛል ብለዋል።
የሴቶች፣ ሕፃናት እና ወጣቶች ሚኒስትር ዲኤታ የሆኑት ሕይወት ኃይሉ በበኩላቸው፣ የዓለም ዐቀፍ የወጣቶች ቀንን በማስመልከት የእንኳን አደረሳችሁ መልዕክት አስተላልፈዋል።
ሚኒስቴር መሥሪያ ቤቱ ወጣት ተኮር ፖሊሲዎችን በመቅረጽ እና ግንዛቤን በመፍጠር ማክበር እንደሚገባው በማመን መከበሩ ጠቃሚ ነው ብለዋል።

በዘንድሮ ዓመት የሚከበረው የምግብ ስርዓት ጋር በማያያዝ መከበሩ ወጣቶችን ጠቃሚ ማድረግ ያስችላል።
ወጣቶች ለአገር ሠላም የሚያበረክቱትን አስተዋጽኦ በማሰብ ሚኒስቴር መሥሪያ ቤቱ አንድ ወር ሙሉ እያከበረው እንደሚገኝ ሕይወት ጠቁመዋል።
በዕለቱ የተለያዩ ጥናቶች የቀረቡ ሲሆን፣ ጥናቱን ካቀረቡት መካከል ሚሊዮን በላይ የአፍሪካ የምግብ ሉዓላዊነት ጥምረት አስተባባሪ ይገኙበታል። ሚሊዮን እንደገለጹት 80 ከመቶ በላይ አርሶ አደር ባለባት አገር ማምረት የሚገባውን እና ጥራቱን የጠበቀ ምግብ ማምረት ያስፈልጋል።

ፒኤችኢ ኢትዮጵያ ኮንሰርቲየም ለአየር ንብረት ለውጥ በመቋቋም እና የአካባቢን ዘላቂነት በማረጋገጥ፣ በኢትዮጵያ ውስጥ የሕዝብ ጤና እና አካባቢን ውህደት ለዘላቂ ልማት ለማሳደግ የሚፈልግ መንግሥታዊ ያልሆነ ድርጅት ነው።
አህመድ መሐመድ የፒኤችኢ ኢትዮጵያ ኮንሰርቲም የሥነ-ሕዝብ ፕሮግራም አስተባባሪ እንደገለጹት፣ ወጣቶች የአገር ተረካቢ እንደመሆናቸው መጠን በየዓመቱ የሚከበረው ዓለም ዐቀፍ የወጣቶች ቀን ሐሳብን በመደገፍ ፒኤችኢ ኢትዮጵያ አክብሮታል።
በሥነ ሕዝብ ጤና እና አካባቢ የሚሰራው ፒኤችኢ ኢትዮጵያ ኮንሰርቲም፣ ከተመሠረተ በፈረንጆቹ 2008 ጀምሮ ለሕብረተሰቡ ዘላቂ የልማት አቅጣጫዎች መፍትሄ የማምጣት ሥራዎችን ሲሠራ ቆይቷል። ድርጅቱ ከአፍሪካ በሕዝብ ብዛት በ2ኛ ደረጃ የምትገኘው ኢትዮጵያን የሥነ ሕዝብ ሒደት ከልማት ጋር በማስታርቅ ለውጦችን ለማምጣት እየሠራ የሚገኝ ነው።

ፒኤችኢ በብዛት የሚሠራው ጥብቅ የሆኑ ቦታዎችን፣ የተፋሰስ አካባቢዎችን፣ ደረቅ ቦታዎች እና የደን አካባቢዎችን መነሻ በማድረግ ነው።
የአካባቢ ጥበቃ መብትን በተመለከተ ፒኤችኢ ከኮሚሽኑ ጋር በጋራ በመሆን የተለያየ ባለ ድርሻ አካላት አባል የሆኑበት አገር ዐቀፍ መድረክ (ፕላትፎረም) አቋቁሟል። በአጋርነት እና ትብብር የሚያምነው ፒኤችኢ በሽርክና እና በጥምረት ግንባታ ስኬታማ የሆኑ የብዙ የውህደት ዘርፎችን በመፍጠር ከመንግሥት አካላት ፣ ከአባል ድርጅቶች ፣ ከልማት አጋሮች እና ከሌሎች ባለድርሻ አካላት ጋር እየሠራ ይገኛል።


ቅጽ 3 ቁጥር 147 ነሐሴ 22 2013

Comments: 0

Your email address will not be published. Required fields are marked with *

This site is protected by wp-copyrightpro.com