የእለት ዜና

ወደማንሸናነፍበት ውጊያ አንግባ!

በሰው ልጆች ታሪክ መሸናነፍ የነበረ፣ ያለና የሚኖር ነው። በግለሰቦች መካከል ግጭት መፈጠሩ እንደማይቀር ሁሉ፣ ግጭትንም በፀብ አሊያም ተቦዳድኖ በውጊያና ረጅም ጊዜ በሚወስድ ጦርነት መፍታት የተለመደ ነው። በልጅነታችን “ይከባበሩ፤ ይዋጣላቸው” ተብሎ የተናናቁ ሕጻናትን ማደባደቡ፣ አንዱ አምኖ ተሸናፊ እስከሚሆንና በቃኝ እስኪል የሚዘልቅ ነበር።

እኛ ኢትዮጵያውያን መሸነፍን ካለመውደዳችን የተነሳ በአቅም ማነስም ሆነ በአጋጣሚ ብንሸነፍም፣ አሸናፊያችንን በፀጋ ተቀብለን ዕድሜልካችንን መሸነፋችንን አምነን አንቆይም። አቅም ያገኘን በመሰለን ወቅት ደግመን እንደምንፈታተሽ ይታወቃል። አውራው የጭላዳ ግመሬ የደከመ ሲመስላቸው ጎረምሶች እየደጋገሙ በማጥቃት እንደሚባሉት ዓይነት ወይም እንደጠገበ ኮርማ የበላይነትን ለማግኘት እንደሚዋጋው፣ የእኛ የሰዎች ተግባርም እንስሳዊ መምሰል ከጀመረ ሠነባብቷል።

ከያዝነው ዓመት መጀመሪያ አንስቶ በሰሜኑ የኢትዮጵያ ክፍል የተቀሰቀሰው ጦርነት ለእንስሳዊው የደመነፍስ ባህሪያችን መገለጫ ጥሩ ማሳያ ነው። እንደአድዋው የውጭ ጠላት ሳይመጣብን እርስበርስ ለመጠፋፋት መፈላለጋችን ወራቶችን አስቆጥሮ የበርካቶችን ሕይወት ቀጥፎ፣ የብዙዎችን ኑሮ አናግቶ፣ በርካቶችንም አፈናቅሏል። ዘጠኝ ወራትን የዘለቀው ጦርነት በርካታ ውጊያዎችን እያስከተለ፣ አሁንም በቅርብ ስለመቋጨቱ ምንም አመላካች ነገር ባለመኖሩ በአዲስ አስተሳሰብ ሊታይ እንደሚገባ አዲስ ማለዳ ማሳሰብ ትወዳለች።

የእስካሁኑ አለማዋጣቱን ለማስተዋል ጠቢብ መሆንን አይጠይቅምና የእስካሁኑ ያልሰራበት ምክንያቱን ለማጥናት ተመሳሳይ ጭንቅላት ከሚጨነቅ፣ ከሳጥኑ ውጭ ለሚያስቡ ብሩህ አእምሮ ላላቸውና አራት ዐይና እየተባሉ ይታወቁ ለነበሩ አርቆ አስተዋዮች ጆሮም ሆነ መድረኩ ቢሰጣቸው መልካም ነው።

‹ተመሳሳይ መንገድ እየሄድክ አዲስ መዳረሻ አገኛለሁ ብለህ አትጠብቅ› እንደሚባለው፣ ሰው በተመሳሳይ መልክ እንዲያልቅ እየቀሰቀሱ መማገዱ በኋላ ተጠያቂ ማድረጉ ስለማይቀር አዲስ ስልትን መቀየስ ግድ ይላል። ሕብረተሰቡ ሰላም አግኝቶ ወደነበረበት ሕይወት እንዳይመለስ የሚያደርግ፣ ቂም የሚያስቋጥር እልቂት ውስጥ ከመገባቱ በፊት አስቀድሞ ተዋጊውን ከተራው ሕዝብ የመለያየት ሥራ ሊሠራ ይገባል። መንግሥታትም ሆኑ ቡድኖች እንደአገርና ሕዝብ ዘላቂ ስለማይሆኑ፣ ጦርነቱ በሕዝብ መካከል መመለስ የማይቻል በቀል እንዳያስቋጥር ኃላፊነት ይሰማኛል የሚል ወገን አስቀድሞ ምሳሌ መሆን እንዳለበት አዲስ ማለዳ ማስገንዘብ ትወዳለች።

አውሬ ወቅቷ ያልደረሰን እንስት በተራክቦ እንደማይገናኝ እየታወቀ፣ የእኛ ዘመን ሰዎች ግን ሴትን አስገድዶ መድፈርን የጦር ስልት ያደረጉት ይመስላል። ይህ ዓይነት አሳፋሪ ተግባር ምን ላይ እንደሚጥለን ከአሁኑ ውጊያ ካልተማርን፣ መጨረሻችን መጠፋፋት እንደሚሆን ግልፅ ነው። በኹለቱም ወገን የሚፈፀሙ ይህን መሰል ኢ-ሰብዓዊ ተግባራት ጦርነቱን ምን ያህል እንዳባባሱት እየታወቀ፣ ይህን መሰል አሳፋሪ ተግባር አሁንም መቀጠሉ እንደ ሕዝብ አንገት የሚያስደፋ ነው።

በጦርነት ወቅት ከሕዝብ ዘርፎ መብላት ከተለመደ 500 ዓመት ባይሞላውም፣ በሽለላ ወቅት “ዘራፍ!” እያልን እስካሁን መፎከሪያ ያደረግነው ተግባር ነው። ይህ ባህል ቢመስልም፣ ወታደር የሚበላው አጥቶ ያልታጠቀን ሲለምን እንደነበር በደርግ ዘመን የነበሩት የቀድሞ የጦር ሠራዊት አባላት ምስክር ናቸው። በወታደራዊ ሥነ ስርዓት ታንፀው ስለሰለጠኑ ጉልበታቸውን ተጠቅመው ሕዝብ ላይ በደል ሲያደርሱ ተሰምቶ አይታወቅም። አሁን ግን በኢትዮ-ኤርትራ ጦርነት ወቅት ተፈፅሟል በተባለ ዝርፊያና ውድመት፣ እንዲሁም የህወሓት ቡድን በዘመኑ ከሕዝብ ላይ ፈፅሞታል በተባለ ዝርፊያና ውድመት ሳቢያ በቀል የፈፀሙ እንደነበሩ ባለፉት 8 ወራት ሲነገር የቆየ ነበር።

ተፈፀሙ ስለተባሉት ተግባራት እየተጣራ ነው ከማለት ውጭ አስተማሪ የሆነ ቆራጥና የማያዳግም ዕርምጃ ባለመወሰዱ፣ ቅስቀሳውም በመቀጣጠሉ ያለፈው አንድ ወር ያስከተለው መዘዝ የሚረሳ አይደለም። “ሒሳብ እናወራርዳለን” በሚል ስሌት የመንግሥት ተቋማትን በመዝረፍና በማውደም የተጀመረው እንቅስቃሴ፣ መካሪም ሆነ የሚያስቆም ባለማግኘቱ ወደ ገበሬው ማምራቱን አርሶ አደሩ በምሬት እየተናገረ ለሌላ ዙር በቀል እየጋበዘ ይገኛል። ሊጥና እርሾ ሳይቀር ሌማቱን ባዶ አድርገውብን ሔዱ የሚሉ ልባቸው የተሰበረባቸው ድሃዎችን ማየቱ እየተለመደ ሲሄድ፣ አጥፊዎቹም ያሰቡት የበቀል በቀል አላጠረቃ ብሏቸው ሌላ ዘግናኝ ተግባር መፈፀማቸውን እየሰማን እንገኛለን።

ከብት እንኳን የማይዋጋውን ወገኑን አሳዶ አይገልም። የሌላ አውሬ ዝርያ ቢሆን እንኳን ከሸሸው ይተወዋል። እኛ የአሁን ዘመን ሰዎች ግን ይህን የመሳሰለ ማነጻፀሪያ ምሳሌ የሚሆን የሕሊና ምክርን ከማዳመጥ ቦዝነን እንገኛለን። ክፉና ደጉን የሚነግረንን ልቦናችንን ሰምተን እንደአውሬ ማዘን እንኳን ተስኖን፣ የማይነኩንን ንጹሐን በጅምላ መጨፍጨፋችን አላሳዘነንም። ጥላቻችን ሥር ሰዶ ተግባራችን ቀጪም ሆነ ምላሽ የማያመጣ መስሎን በጀመርነው ግፍ ስንቀጥል ቆይተናል።

ሰው መጨካከኑ አሁን የጀመረ ባይሆንም፣ እርስበርሳችን መሆኑ አልበቃ ብሎን ወገን የማይዙትን የማንም የሚሆኑትን የቤት እንስሳት እስከመጨፍጨፍ አድርሶናል። አህያ እንኳን “እኔ ከሞትኩ ሰርዶ አይብቀል” አለች እንጂ፣ በሕይወት እያለች የምትበላው ነገር ጨርሶ እንዲጠፋ አልጠየቀችም፣ ወይም እንዲጠፋ ብላ አላወደመችውም። “የማን እናት ሞታ የማን ትቀራለች” እየተባለ በሚሸለልበት አገር “ማን ተርቦ ማን ይተርፋል” መባሉ የማይቀር ነው። ማንስ ተጠምቶ ለሌላ ያስተላልፋል ብለን ማሰብ የተሳነን እስኪመስል፣ በእኛ ትውልድ ሊቋጭ የማይችል ረመጥ እያቀጣጠልን እንዳለን መገንዘብ ተስኖናል።

በአንድ አገር እየኖርን፣ እንደሕንድና ፓኪስታን ብንለያም እንኳን እነሱ ያሉበት ዓይነት የመጠፋፋት አዙሪት ውስጥ ከገባን በእኛ እልኸኛነት በምዕተ ዓመትም ችግሩ አይቋጭም። ጉርብትናው ተፈጥሯዊ ቢሆንም፣ ቂም የተቃባ እንደሰሜን ኮሪያና አሜሪካ ሩቅ ለሩቅ ቢሆንም ለመጠፋፋት መፈላለጉ የማይቀር የሰው ልጆች ባህሪ ነው። ይህ ትውልድ የማይወጣበት ገደል እየገባ መሆኑን እያወቀ፣ አሁንም ግን ዘር መተካቱን አያቆምም። ልጆቹን ገደል ከቶ መውጫ በሌለበት አረንቋ ውስጥ ሊያጋድላቸው ሲማስን፣ የጋራ ጠላቶቻችን እንደሚደሰቱ ልናውቅ እንደሚገባ አዲስ ማለዳ ማስታወስ ትወዳለች።

አንድ ሰው ትዳር መስርቶ፣ ልጅ ወልዶ ትውልድን በሚያፈራበት ወቅት፣ በአንድ ምዕተ ዓመት ብቻ ምን ያህል ዘሩ ሊበዛ እንደሚችል ከሥነ ተዋልዶ አኀዙም ሆነ የሥነ ሕዝብ ባለሙያ አነጋግሮ ማወቁ ቀላል ነው። ኢትዮጵያ በፊት ከነበራት የሕዝብ ቁጥር አንጻር በቅርብ እንኳን ያደረገቻቸው ጦርነቶች ምን ያህል በቁጥር እንዳሳነሷት መገመት ይቻላል። በተለይ የአሁኑ ዓይነት የእርስበርስ ጦርነት፣ በጋራ ሊያጠፋን የሚፈልግ አካል ያለንበት ሳይመጣ፣ ከወገኖቹም ምንም ሳይጎልበት በቀላሉ የሚያሳካው ነው።

የትግራይ ሕዝብ ከሌላው ተለይቶ ማንነቱን መሠረት አድርጎ ከተደራጀ ካለፈው 50 ዓመታት ወዲህ የማኅበረሰቡ ቁጥር ምን ያህል እንደቀነሰ ከራሱ ከነዋሪው በላይ የሚያውቀው የለም። ምንም ዓይነት ነገር ተደርጎ ለማካካስ ቢሞከር መመለስ የማይቻል እንደሆነ ያለፉት 30 ዓመታት አመላካች ናቸው። ዕምነትንም ሆነ ባሕልን በሚሸረሽር መልኩ ማንነትን የሚቀይር ተግባር ማከናወን፣ መጀመሪያውኑ ቆመንለታል የሚሉትን ዓላማ የሚያሳጣ እንደመሆኑ ዕድሜ ያስተማራቸውም ሆኑ ማስተዋልን የተቸሩት የማኅበረሰቡን አዛዦችን ሊያመለክቷቸው ይገባል። እምቢ ካሉም መጨረሻቸው ምን ሊሆን እንደሚችል ለሚወዱት ሕዝብ ሲሉ ማሳወቅ ግዴታ ይኖርባቸዋል።

ለ50 ዓመታት ውጤታማ ያልሆነን አደረጃጀት እያዩ እነሱን ተመልክቶ እንደነሱ እንደራጅ ብሎ የሚቀሰቅስም ሕዝብን በተመሳሳይ ከሌላው የሚለይና የሚያስጨርስ እንደሚሆን አምኖ፣ የሌላም ቢሆን ካለፈ ስሕተት ተምሮ ከአሁኑ አካሄድን ማስተካከሉ እንደሚሻል ግልፅ ነው። ታጥቆ ሊያጠፋ የመጣን፥ ታጥቆ መመለሱ አነጋጋሪ ባይሆንም፣ ከሚፈለገው ውጤትና ከቆመለት ዓላማ አኳያ ታይቶ የሚያመናምነን እንዳይሆን ሊታሰብበት እንደሚገባ አዲስ ማለዳ አጽንዖት ትሰጣለች።

“እሾህን በሾህ” እያሉ አባቶቻችን የገባብንን እሾህ ለማውጣት ተመሳሳይ የሆነ እሾህን ወይም ወገኑ ያልሆነ የበለጠ ጠንካራ እሾህን ተጠቅመን ፈንቅለን እንድናወጣው ሲመክሩን ኖረዋል። መንቀያው እሾህ የሚገኘው የወጋን አካባቢ ስለሆነ፣ እዛው ፈልገን ካወጣንበት በኋላ በደም የጨቀየውን ይዘነው እንደማንዞር ግልፅ ነው። ይህ ማለት ግን ተወግተን ደማችንን እያፋሰስን ፍለጋ ከምንገባ ማውጫ ወረንጦ ወይም ልብስ መስፊያም የሚሆን መርፌ ይዘን አንዙር ማለት አይደለም። በተለይ የምንጓዝበት መንገድ በእሾህ የተከበበ ከሆነ መከላከያ ጫማችንንም አልፎ ሊወጋን ስለሚችል፣ ማውጫው ከእጃችን ባይለየን መልካም እንደሆነ አዲስ ማለዳ ታምናለች።


ቅጽ 3 ቁጥር 147 ነሐሴ 22 2013

Comments: 0

Your email address will not be published. Required fields are marked with *

error: Content is protected !!