የእለት ዜና

የኢትዮጵያ አየር መንገድ እና ቦይንግ ኩባንያ በጋራ ለመስራት የሚያስችል ስምምነት ተፈራረሙ

Views: 160

የኢትዮጵያ አየር መንገድ እና ቦይንግ ኩባንያ፤ ኢትዮጵያን የአፍሪካ የአቪዬሽን ማዕከል ለማድረግ የሚያስችል ስትራቴጂክ የመግባቢያ ስምምነት ተፈራርመዋል።

የኢትዮጵያ አየር መንገድ እና ቦይንግ ኩባንያ የ70 ዓመት የጋራ የአቪዬሽን ታሪክ ያላቸው ሲሆን፤ የተፈራረሙት የመግባቢያ ስምምነትም “ኢትዮጵያ ለአፍሪካ” በሚል ማዕቀፍ፤ ኢትዮጵያን የአፍሪካ የአቪዬሽን መዳረሻ ለማድረግ ያለመ መሆኑን ወርልድ ኤርላይ ኒውስ አስነብቧል።

ቦይንግ ኩባንያ የኢትዮጵያ አየር መንገድን በአህጉሪቱም ይሁን በዓለም የበረራ ስርዓት ውስጥ ከፍተኛ ድርሻ እንዳለው እንደሚያምን የተገለፀ ሲሆን፤ የመግባቢያ ስምምነቱ ቦይንግ እና የኢትዮጵያ አየር መንገድን እርስ በርስ የሚስማማ ዓለም አቀፍ የበረራ ሽርክና ለመመስረት ያላቸውን ፅኑ ፍላጎት የሚያመለክት ነው ተብሏል።

በዚህም መሰረት የጋራ ራዕያቸውን ለማሳካት በስትራቴጂካዊ ትብብር አራት መስኮች ማለትም፤ በኢንዱስትሪ ልማት፣ በላቀ የአቪዬሽን ሥልጠና፣ በትምህርት አጋርነት እንዲሁም በስራ አመራር ብቃት ላይ በሦስት ዓመት ጊዜ ውስጥ በአጋርነት ለመሥራት መስማማታቸው ታውቋል።

ይህንንም የአጋርነት ስምምነት ለመተግበር የጋራ ሁለገብ ቡድኖች የተቋቋሙ ሲሆን አስፈላጊ ደረጃዎችም ቀድሞውኑ መሟላታቸውም ተገልጿል።

የኢትዮጵያ አየር መንገድ ዋና ሥራ አስፈጻሚ ተወልደ ገብረማርያም “ይህን ታሪካዊ የመግባቢያ ስምምነት ከረዥም ጊዜ የበረራ ባልደረባችን ከሆነው ከቦይንግ ኩባንያ ጋር መፈራረማችን፤ የምዕራባውያን ክንውኖችን ተግባራዊ ለማድረግ መሰረት የምንጥልበት ምዕራፍ በመሆኑ ተደስተናል።” ሲሉ ተናግረዋል።

የአፍሪካን አህጉር ለማገልገል ከ70 ዓመታት በላይ በአቪዬሽን ውስጥ በተለያዩ ትላልቅ ፕሮጀክቶች ከቦይንግ ጋር በመተባበር እየሠራን ቆይተናል ያሉት ዋና ሥራ አስፈጻሚው ይህ ስምምነት በብዙ መስኮች የአየር መንገዱን አቅም የሚያጎለብት እንደሚሆንም ገልፀዋል።

“በአፈፃፀሙ ላይ ባለን ቁርጠኝነት ምክንያት የመግባቢያ ስምምነቱ ኢትዮጵያን የአህጉሪቱ የአየር በረራ መዳረሻ የማድረግ ግቡ፤ በተሳካ ሁኔታ እንደሚያሳካ ጽኑ እምነት አለኝ።”ሲሉም ተናግረዋል።

በተጨማሪም “ግቦቻችንን ለማሳካት የአሜሪካ አጋር ኩባንያዎቻችን ያላቸውን ወሳኝ ሚና ከፍተኛ ዋጋ እንሰጣለን። በመሆኑም እንደ ቦይንግ፣ ጂኢ፣ ፕራት እና ዊትኒ እና ኮሊንስ እና ኤሮስፔስ ከመሳሰሉ ቁልፍ የአሜሪካ የአቪዬሽን መሪዎች ጋር በጋራ መስራታችንን እንቀጥላለን ማለታቸውም ታውቋል።

Comments: 0

Your email address will not be published. Required fields are marked with *

This site is protected by wp-copyrightpro.com