የእለት ዜና

በቤኒሻንጉል ጉምዝ ክልል መስከረም 20/2014 ምርጫ እንደማይካሄድ ተገለጸ

በቤኒሻንጉል ጉምዝ ክልል የመጀመሪያ ዙር ምርጫ ባልተካሄደባቸው መተከል እና ካማሽ ዞን መስከርም 20/2014 ምርጫ እንደማይካሄድ በክልሉ የሚንቀሳቁ ፖለቲካ ፓርቲዎች ገለጹ፡፡

የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ስደስተኛውን አገራዊ ምርጫ በአንድ ዙር ማካሄድ አለመቻሉን ተከትሎ ምርጫውን በኹለት ዙር ለማካሄድ መወሰኑ የሚታወስ ነው፡፡ በኹለተኛው ዙር ምርጫ ከሚካተቱት ክልሎች መካከል ቤኒሻንጉል ጉምዝ አንዱ ሲሆን፣ በክልሉ ካሉት ሦስት ዞኖች የመጀመሪያው ዙር ምርጫ የተካሄደው በአሶሳ ዞን ብቻ ነው፡፡

ቦርዱ የመጀመሪያው ዙር ምርጫ ባልተካሄደባቸው አካባቢዎች መስከረም 20/2014 ምርጫ ለማካሄድ መወሰኑ የሚታወስ ነው፡፡ መተከል እና ካማሽ ዞኖች መስከረም 20/2014 ምርጫ ይካሄድባቸዋል ተብሎ ቢታሰብም፣ ቦርዱ ባሳለፍነው ሰኞ ነሐሴ 24/2013 በክልሉ ከሚወዳደሩ ፓርቲዎች እና ከባለድርሻ አካላት ጋር ባደረገው ውይይት በኹለቱ ዞኖች ምርጫ ማካሄድ እንደማይችል ማወቃቸውን በውይይቱ የተሳተፉ ፓርቲዎች ለአዲስ ማለዳ ገልጸዋል፡፡

ምርጫ ቦርድ  በቤኒሻንጉል ጉምዝ ክልል የመተከል እና የካማሽ ዞን ምርጫን ወደ ኹለተኛው ዙር ያሸጋገረው በወቅቱ በዞኖቹ ምርጫ ለማካሄድ የሚስችል የጸጥታ ኹኔታ ባለመኖሩ ነበር፡፡ ቦርዱ ባሳለፍነው ሰኞ የክልሉን ምርጫ አስመልክቶ ከባለድርሻ አካላት ጋር ውይይት ማድረጉን በውይይቱ የተሳተፉት የቤኒሻንጉል ሕዝብ ነጻነት ንቅናቄ(ቤሕነን) ሥራ አስፈጻሚ አባል መርቀኒ አቡዜር ለአዲስ ማለዳ ገልጸዋል፡፡

ቦርዱ ባካሄደው ውይይት የመተከል ዞን ኮማንድ ፖስት ሰብሳቢ ሌተናል ጀነራል አስራት ደኔሮ፣ ሰላም ሚኒስቴር፣ የክልሉ ርዕሰ መሥተዳድር አሻደሊ ሐሰን እና በክልሉ በምርጫ ተሳታፊ የሆኑ ፖለቲካ ፓርቲዎች የተሳተፉ ሲሆን፣ የመተከል ዞን ኮማንድ ፖስት እና ብልጽግና ፓርቲ በክልሉ ምርጫ ለማካሄድ የሚስችል የጸጥታ ኹኔታ መኖሩን በመጥቀስ ምርጫው መስከረም 20/2014 ማካሄድ እንደሚቻል ሐሳብ አቅርበዋል፡፡ ኮማንድ ፖስቱ ለምርጫ ቦርድ ባቀረበው ሐሳብ መሠረት በክልሉ አሁን ባለው የጸጥታ ኹኔታ 80 በመቶ ምርጫ ለማካሄድ ያስችላል ብሏል፡፡

ይሁን እንጅ፣ በክልሉ የሚንቀሳቀሱ ፖለቲካ ፓርቲዎች በበኩላቸው በክልሉ ያለውን የጸጥታ ኹኔታ በዝርዝር አጥንተው ለቦርዱ ማቅረባቸውን መርቀኒ ጠቁመዋል፡፡ ፓርቲዎቹ ባቀረቡት ጥናት በኹለቱም ዞኖች መስከረም 20 ምርጫ ለማካሄድ የሚያስችል ኹኔታ እንደሌለ ለቦርዱ ገልጸዋል፡፡ በክልሉ የሚንቀሳቀሱ ተፎካካሪ ፖለቲካ ፓርቲዎች በበኩላቸው ባቀረቡት ጥናት፣ በክልል ምርጫ ባልተካሄደባቸው መተከል እና ካማሽ ዞን 87 በመቶ ምርጫ ማካሄድ የማይቻልበት የጸጥታ ኹኔታ መኖሩን ለቦርዱ አቅርበዋል፡፡

ምርጫ ቦርድ በበኩሉ በክልሉ ምርጫ ለማካሄድ በክልሉ ያለው መራጭ ሕዝብ መረጋጋት እንዳለበት የገለጸ ሲሆን፣ መራጭ ባልተረጋጋበት ኹኔታ ምርጫ ማካሄድ እንደማይችል በውይይቱ ላይ አንስቷል ተብሏል፡፡ በውይይቱ ላይ የተሳተፉ ፖለቲካ ፓርቲዎች ለአዲስ ማለዳ እንደገለጹት ከሆነ፣ ምርጫ ቦርዱም አሁን ላይ በክልሉ ካለው የጸጥታ ሁኔታ አንጻር ምርጫ ባልተካሄደባቸው መተከልና ካማሽ ዞኖች ምርጫ ማካሄድ እንደማይችል በምክክር መድረኩ ላይ አቋሙን ገልጿል፡፡

በክልሉ የሚንቀሳቀሱ ፖለቲካ ፓርቲዎች እንደሚሉት ከሆነ፣ በመተከል እና በካማሽ ዞኖች ያለው የጸጥታ ሁኔታ ተባብሶ ቀጥሏል፡፡ የፖለቲካ ፓርቲዎቹ አቋም በምርጫ ከሚገኝ ሥልጣን በፊት የሕዝብ ደኅንነት ቅድሚያ ሊሰጠው ይገባል የሚል ሲሆን፣ መንግሥት የክልሉን ሠላም ማረጋገጥ ላይ ቅድሚያ ሰጥቶ ሊሠራ እንደሚገባ ተጠቁሟል፡፡

ምርጫ ቦርድ በክልሉ ያለው የጸጥታ ኹኔታ ለውጥ ካላመጣ በኹለተኛው ዙር ምርጫ ማካሄድ አልችልም ማለቱን አዲስ ማለዳ መዘገቧ የሚታወስ ነው፡፡

በምርጫ አሸናፊ የሆነው ፓርቲ አዲስ መንግሥት የሚመሠርተው በሚቀጥለው መስከረም መጨረሻ ላይ ሲሆን፣ መስከረም 20/2014 በቤኒሻንጉል ጉምዝ ክልል ምርጫ ካልተካሄደ አዲስ በሚመሠረተው ፓርላማ ውስጥ መተከልና ካማሽ ዞን ተወካይ አይኖራቸውም፡፡

Comments: 0

Your email address will not be published. Required fields are marked with *

error: Content is protected !!