የእለት ዜና

የበዓል ዕለት

“ሲቄ” የሚለው የኦሮምኛ ቃል ‹አለንጋ› የሚል ትርጉም አለው። በገዳ ትውፊታዊ አስተዳደር ውስጥ በባሏ ጥቃት የደረሰባት ሚስት፣ ከሌሎች ሴቶች ጋር በመሆን ባሏ ላይ የካሣ ውሳኔ የምታሳልፍበት ስርዓት ሲቄ ይባላል።

ኢትዮጵያ በራሷ የዘመን ቀመር ቀናትን የምትቆጥርና በዓላትን የምታከብር ቀደምት አገር ነች። አሮጌው ዓመት አልቆ አዲስ ዓመት ሲመጣ በወርሃ መስከረም የመጀመሪያው ዕለት ቅዱስ ዩሐንስ፣ ዓውደ ዓመት፣ አዲስ ዓመት በመባል ይጠራል። በአዲስ አመት ምድሩ በአደይ አበባ ይሸፈናል፤ ምድሩ ብቻ ሳይሆን በወርሃ መስከረም ሰውም በአዲስ ተስፋና ዕቅድ፣ ሠላምን ሰንቆ ዓመቱን ይጀምራል።

የክረምቱ ወቅት በሠላም አልቆ በበጋ መተካቱን አስመልክቶ በዋዜማው ሰዎች በጋራ “ችቦ” ያበራሉ። በዓሉ የአዲስ ዓመት ምኞት በመለዋወጥ ይከበራል። በቅዱስ ዩሐንስ ማለዳ ሴት ታዳጊዎች ወደ ሰዎች ቤት በማምራት የተለያዩ በዓሉን ሊገልጹ የሚችሉ ግጥሞችን በመግጠም፣ “እንኳን አደረሳችሁ” እያሉ ያዜማሉ። ይህም በዓሉን ከሌሎች በዓላት ለየት ያደርገዋል። የ”አበባ አየሽ ወይ” አጨፋፈር እንደ አካባቢው የሚለያይ ሲሆን፣ ሁነቱም በአንዳንድ አካባቢዎች ላይ ቀደም ብሎ እንዲሁም ከበዓሉ በኋላ ይከወናል። በዓሉን ከሚያሳምሩት መካከል ሰዎች በባሕላዊ አለባበስ ተውበው መታየታቸው እና በቤትም ምግብና መጠቱ በየአይነቱ ተሰርቶ ባህላዊ ምግቦቹ ማለትም ዶሮ ወጥ፣ ድፎ ዳቦ፣ ጠላ፣ ጠጅ፣ ለበዓሉ መቅረባቸው ነው።

“ለኔ ቅዱስ ዮሐንስ የተለየና እጅግ አድርጌ የምወደው በዓል ነው” ያሉት አዲስ ማለዳ በዓሉን በማስመልከት ያነጋገረቻቸው አበበች አለሙ ናቸው። አበበች የአዲስ አበባ ከተማ ነዋሪ ሲሆኑ ባለትዳርና የስድስት ልጆች እናት ናቸው። በዓልን ከቤተሰብ ጋር በጋራ ሆነን ከሐምሌ ጨለማ ከዝናብ ወቅት በሠላም አልፈን ለወርሃ መስከረም በመድረሳችን ነው የቅደስ ዮሐንስ በዓል በተለየ መልኩ የምወደው ይላሉ።

በዓሉን በዋዜማው ችቦ በማብራት ይጀምራሉ። “ባለቤቴ እና ልጆቼ ለበዓል ዶሮ ወጥ እና ጠላ ከሌለ ቅር ይላቸዋል፤ ለነገሩ እኛም ብንሆን ደስተኛ አንሆንም” በዚህም ምክንያት ለቅዱስ ዩሐንስ በዓል ዶሮ ወጥ እና ጠላ እንደሚያዘጋጁ አንስተዋል። ዶሮ ወጥ የኢትዮጵያ ባሕላዊ ምግብ ሲሆን በንጽህና፣ በብዙ ቅመማ ቅመሞች የሚዘጋጅ እና የሴት ልጅ ሙያዋም የሚለካበት በመሆኑ ተጨንቀው እንደሚያዘጋጀት ይናገራሉ። በበዓል ዕለት ብዙ ጊዜ በድካም ስሜት ውስጥ ሆነው እንደሚያሳልፉም ጠቅሰዋል። ቅዱስ ዩሐንስ (አዲስ ዓመት) ዕርድ የሚከናወንበት በዓልም በመሆኑ ሴቶች የበዓል ሥራ ሊያደክማቸው እንደሚችል ይጠቁማሉ።

በዓልን ያለቤተሰብ ማክበር ከባድ ሲሆን፣ ሴቶች የበዓል ሥራዎችን በመሥራት አዲስ ዓመትን ያደምቁታል። ሆኖም ግን ወንዶች ቢያግዙም፣ ኃላፊነቱ ሙሉ በሙሉ ማለት በሚያስችል ሁኔታ ሴቶች ላይ በመጫኑ በዓልን በድካም ስሜት ለማሳለፍ ይገደዳሉ። የቤት ውስጥ ሥራ ለሴት ልጅ ብቻ የተሰጠ የሚመስላቸው የማኅበረሰባችን ክፍሎች መኖራቸው ግልጽ ነው። የበዓል ሥራ መሥራት ለሴቶች ግዴታ እና ዕገዛ የማይፈልግ የሚመስላቸው አንዳንድ ወንዶች ሴቶችን ሲረዱ አይስተዋልም። በዚህ ረገድ ሴቶችን በሥራ ማገዝ እንደ አገር መለመድ ያለበት ተግባር ነው። በተለይ በበዓል ኹላችንም እኩል የደስታውም ሆነ የሥራው ተካፋይ መሆን ይጠበቅብናል።


ቅጽ 3 ቁጥር 148 ነሐሴ 29 2013

Comments: 0

Your email address will not be published. Required fields are marked with *

error: Content is protected !!