የእለት ዜና

“የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ራስን ለመቻል ያላቸው አስተዋጽዖ” በሚል ርዕስ ጉባዔ ተካሄደ

በቅድስት ማርያም ዩንቨርሲቲ አዘጋጅነት በየአመቱ ሲካሄድ የቆየው በአፍሪካ ከፍተኛ የትምህርት ተቋማት ላይ ትኩረት የሚያደርገው አለም አቀፍ ጉባዔ ለ19ኛ ጊዜ ነሀሴ 27/2013 በበይነ መረብ አማካኝነት ተደርጓል።
ለ19ኛ ጊዜ በተደረገው ጉባዔ የከፍተኛ ትመህርት ተቋማት ራስን ለመቻል ያላቸው አስተዋጽዖ (Higher Education and its contribution to self-reliance) በሚል ርዕስ የተዘጋጀ ሲሆን፣ ጉባዔው ከዚህ ቀደም በአዳራሽ የሚካሄድ ቢሆንም አሁን ላይ በአለም አቀፍ ደረጃ በተስፋፋው የኮቪድ-19 ወረርሺን ምክንያት በበይነ መረብ አማካኝነት እንዲካሄድ አድርጓል ተብሏል።
“ይሕ ርዕስ የተመረጠበት ዋነኛ ምክንያት አገራችንም ሆነች አህጉራችን በብዙ ችግሮች ተተብትበው ያሉበት ጊዜ በመሆኑ እና ራሳቸውን ባለመቻላቸው ምክንያት በተፈጥሮ እና ሰው ሰራሽ አደጋዎች ተጎጂ እየሆንን ስለሆነ ከነዚ ችግሮች ለመላቀቅ ራስን መቻል ወሳኝ ነገር በመሆኑ በዚህ ጉዳይ ለመመወያያት መነሻ ሆኗል።” ሲሉ በዩኒቨርሲቲው ምርምርና ዓለምአቀፍ ግንኙነት ምክትል ፕሬዘዳንት የሆኑት ምስጋናው ሰለሞን(ዶ/ር) ለአዲስ ማለዳ ተናግረዋል።
በተጨማሪም “በአፍሪካ ደረጃ ራስን መቻል የ2063 አጀንዳ በመሆኑና ይሄ እንዲሳካ ደግሞ የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት አስተዋጽዖ ከፍተኛ በመሆኑ ቀድሞ ለመዘጋጀት እንዲረዳ ከወዲሁ ለመጀመር በማሰብ ይህን ርዕስ ለመወያያነት መርጠነዋል።” በማለት ያክላሉ።
እንደዚህ አይነት ጉባዔዎች ማዘጋጀት እንደ አገርም ሆነ አህጉር ብዙ ትርፍ የሚገኝበት እንደሆነ የተነሳ ሲሆን፣ በአገር ውስጥ ለሚገኙ የግልም ሆነ የመንግስት ከፍተኛ የትምሕርት ተቋማት ከዚህ ብዙ ልምዶችን እንዲያገኙና ምርምር የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ባህል መሆን እንዳለበት ማስገንዘቢያ መድረክ እንደሆነም ተጠቅሷል።
በጉባዔው ላይ የተላያዩ ዩኒቨርሲቲዎች አመራሮች፣ የትምህርት ባለሙያዎች፣ ፖሊሲ አውጪዎች፣ ተመራማሪዎች እና ከተለያዩ የአለም ክፍል የተውጣጡ ድርጅቶች ተሳትፈውበታል።


ቅጽ 3 ቁጥር 148 ነሐሴ 29 2013

Comments: 0

Your email address will not be published. Required fields are marked with *

error: Content is protected !!