የእለት ዜና

የሰሜኑ ጦርነት እና የጦር ምርኮኞች አያያዝ

Views: 226

በኢትዮጵያ ትግራይ ክልል ጥቅምት 24/2013 በፌደራል መንግሥት እና በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት በሽብርተኝነት በተፈረጀው ህወሓት መካከል የተጀመረው የኃይል ፍልሚያ፣ እስካሁንም ድረስ እንደቀጠለ ነው። ለስምንት ወራት በትግራይ ክልል ተገድቦ የቆየው ጦርነት፣ የፌደራል መንግሥት የተናጠል ተኩስ አቁም ዐውጆ ሰኔ 21 ክልሉን ለቆ መውጣቱን ተለከትሎ ጦርነቱ ወደ አማራ እና አፋር ክልል ተስፏፍቷል።

ታዲያ ለስምንት ወራት በትግራይ ክልል ተገድቦ በቆየው እና አሁን ላይ ወደ ኹለቱ ክልሎች በተስፋፋው ጦርነት ሒደት በኹለቱም ኃይሎች በኩል ተዋጊዎች መማረካቸውን እየተገለፀ ነው። ኹለቱም ኃይሎች በተቃራኒ ተሰልፈው ሲፋለሙን ነበር ያሏቸውን ተዋጊ ምርኮኞች ምስል በየሚዲያዎቻቸው ሲያሳዩ ነበር። የጦር ምርኮኞች ሰብዓዊ መብታቸው እንዲከበርላቸው ዓለም ዐቀፉ ሕግ ያስገድዳል።

ይሁን እንጅ በጦርነቱ ሒደት የተማረኩ የጦር ምርኮኞች አያያዝ በተለይም በህወሓት ተማከርከዋል የተባሉ የፌደራል ኃይሎች በሚዲያ ከመታየታቸው ውጭ ያሉበት ሁኔታ በግልጽ እንደማይታወቅ እየተገለጸ ነው።

ዓለም ዐቀፉ የቀይ መስቀል ማኅበር ባሳለፍነው ሐምሌ ወር በህወሓት ኃይሎች ተማርከዋል የተባሉ የፌደራል ኃይሎችን ጎብኝቻለሁ ማለቱ የሚታወስ ነው። ቀይ መስቀል በትግራይ ክልል በእስር ላይ የሚገኙ ፌደራል መንግሥት ኃይሎች አባላትን መጎብኘቱን ከመግለጽ ውጪ ስለ ጦር ምርኮኞቹ አያያዝ ዝርዝር መረጃ እና ስላለቡት ሁኔታ ያለው ነገር የለም። ማኅበሩ በህወሓት ኃይሎች ተማርከዋል የተባሉ የፌደራል ኃይሎችን መጎብኘት መጀመሩን ይግለጽ እንጂ፣ እስካሁን ድረስ ምርኮኞቹ ያሉበትን ሁኔታ ይፋ አለማድረጉ ዕጣ ፈንታቸው ግልጽ እንዳይሆን አድርጎታል።

በህወሓት ኃይሎች የተማረኩ ናቸው የተባሉ በርካታ ቁጥር ያላቸው የፌደራል ኃይል ሠራዊት አባላትን የሚያሳይ ምስል በውጭ ሚዲያዎች እና በማኅበራዊ ሚዲያ ሲሰራጭ ነበር። ይሁን እንጅ እነዚህ የጦር ምርኮኛ ናቸው የተባሉት ሰዎች ስላሉበት ሁኔታ በግለጽ የተነገረ ነገር አለመኖሩ፣ የጦር ምርኮኞች አያያዝ አሳሳቢ እንደሆነ አዲስ ማለዳ ያነጋገረቻቸው አንድ የሕግና አንድ የወታደራዊ ባለሙያ ይገልጻሉ። የጉዳዩን አሳሳቢነት የሚገልጹት ወታደራዊ ባለሙያው በህወሓት በኩል የሚሰነረዙ ጥቃቶች የበቀል ስሜት ያነገቡ መሆናቸውን እንደምክንያት በማንሳት ነው።

የቀድሞው ጦር ሠራዊት የልማትና የድጋፍ ማኅበር ፕሬዝዳንት ኃምሳ አለቃ ብርሃኑ አማረ እንደሚሉት፣ በሰሜኑ ኢትዮጵያ ክፍል እየተካሄደ ባለው ጦርነት በተለይ በህወሓት በኩል የጦር ምርኮኞች አያያዝ በግልጽ አለመታወቁ አሳሳቢ መሆኑን ይናገራሉ።
በፌደራል መንግሥት ኃይሎች የተማረኩ የህወሓት ታጣቂዎች አያያዝ አሳሳቢና ስጋት ውስጥ የሚከት እንዳልሆነ የሚገልጹት ኃምሳ አለቃ ብርሃኑ፣ በፌደራል ኃይሎች የተማረኩ የህወሓት የጦር ምርኮኞች በህወሓት በኩል ተማርከዋል ከተባሉት የፌደራል ኃይሎች ይልቅ ያሉበት ሁኔታ ይታወቃል ይላሉ። ይሁን እንጅ በኹለቱም ኃይሎች በኩል የሚማረኩ የጦር ምርኮኞች ከተማረኩ በኋላ ሰብዓዊ መብታቸው ሙሉ በሙሉ ሊከበርላቸው እንደሚገባ ይገልጻሉ።

“ወታደር በጦር ሜዳ ከተማረከ ሰብዓዊ መበቱ ሙሉ በሙሉ እንዲከበርለት ዓለም ዐቀፍ ሕግ ያስገድዳል፤ እንዲያውም ከሰብዓዊ መብት መከበር በላይ ልዩ ክትትልና ድጋፍ ሊደረግለት ይገባል” ይላሉ ወታደራዊ ባለሙያው ኃምሳ አለቃ ብርሃኑ። ኢትዮጵያ የፈረመችው ዓለም አቀፉ የጀኔቫ ኮንቬንሽን በጦርነት ወቅት ቆስሎም ይሁን ሳይቆስል የተማረከ የጦር ምርኮኛ፣ ሰብዓዊ መብቱ መከበር እንዳለበት እንደሚያስገድድ ባለሙያው ጠቅሰዋል።

በኹለት ተቃራኒ ኃይሎች መካከል በሚደረግ ጦርነት ወቅት የተማረኩ የጦር ምርኮኞች በጦር ሜዳ እንደተሰለፈ ተዋጊ ኃይል ሳይሆን፣ እንደማንኛውም ሰው ሰብዓዊ መብታቸው መከበር እንዳለበት የሕግ ባለሙያው ካፒታል ክብሬ ይናገራሉ።

ዓለም ዐቀፉ የቀይ መስቀል ማኅበር የጦር እስረኞች በዓለም ዐቀፍ የሰብዓዊነት ሕግ መሰረት መብታቸው የተጠበቀ እንደሆነ ይገልፃል። ሦስተኛው የጄኔቫ ስምምነት ለጦር እስረኞች ሰፊ ጥበቃን ይሰጣል። ዓለም ዐቀፍ የሰብዓዊነት ሕግ (International Humanitarian Law) በትጥቅ ግጭት ሳቢያ ነጻነት የተነፈጉ ሰዎችንም መብት ይጠብቃል። ዓለም ዐቀፉ የሰብዓዊነት ሕግ በጦርነት ጊዜ የተማረኩ “Prisoners of war” ብሎ የሚጠራቸው የጦር ምርኮኞች ሰብዓዊ መብታቸው መከበር እንዳለበት በግልጽ ያስቀምጣል።

የሕግ ባለሙያው ካፒታል እንደሚሉት፣ ከዓለም ዐቀፍ ሕጎች በተጨማሪ በኢትዮጵያም የጦር ምርኮኞችን ሰብዓዊ መብት ጥበቃ የሚያስገድዱ ሕጎች እንዳሉ ይጠቅሳሉ።

በዓለም ዐቀፍ ደረጃ የጦር ምርኮኞችን የሚመለከተው የጀኔቫ ኮንቬንሽን አንዱ ሲሆን፣ የጦር ምርኮኞች አያያዝን የሚዘረዝረው ኮንቬንሽን “Prisoners of war” ብሎ ለሚጠራቸው የጦር ምርኮኞች ሕክምና፣ ምግብ፣ አልባሳት እንዲያገኙና ልዩ ክትትልና ድጋፍ እንዲደረግላቸው እንደሚደነግግ ባለሙያው ጠቁመዋል።

የጀኔቫ ኮንቬንሽን የጦር ምርኮኞችን ወይም በኮንቬንሽኑ አጠራር “Prisoners of war” የተባሉት ሰብዓዊ መብታቸው ሙሉ በሙሉ እንዲከበርላቸው የሚደነግግ ሲሆን፣ ኢትዮጵያም የኮንቬሽኑን ድንጋጌዎች ተቀብላ ተግባራዊ እንደምታደርግ የሕግ ባለሙያው ተናግረዋል።

ኢትዮጵያ የተቀበለችውና ተፈጻሚ የምታደርገው ዓለም ዐቀፉ የጀኔጃ ኮንቬንሽን “The rules protecting prisoners of war (POWs)” የጦር ምርኮኞችን የሚጠብቁ ሕጎች በኮንቬንሽኑ መወሰናቸውን ቀይ መስቅል ማኅበር በድህረ ገጹ ላይ ስለ ጦር ምርኮኞች የሕግ ከለላ ባሰፈረው ጽሑፍ ላይ ገልጾታል።

የጦር ምርኮኞች ወይም እስረኞችን አያያዝና መብት የሚደነግገው የጀኔቫ ኮንቬንሽን በመጀመሪያ በ1929 የወጣ ሲሆን፣ ኹለተኛው ኮንቬንሽን ደግሞ ከኹለተኛው የዓለም ጦርነት በኋላ በ 1977 “ተጨማሪ ፕሮቶኮል አንድ” ተብሎ ተሻሽሏል። የጦር ምርኮኞችን ሰብዓዊ መብት ለመጠበቅ የወጣው የጀኔቫ ኮንቬንሽን በየጊዜው እየተሻሻለ የዓለም አገራት ተግባራዊ እያደረጉት ይገኛል። በኮንቬንሽኑ የጦር እስረኞችን መብት ለመጠበቅ የተደነገገው ሕግ “The rules protecting prisoners of war (POWs)” ተፈጻሚነት፣ የትጥቅ ግጭት ውስጥ ብቻ ነው።

የጦር እስረኞችን ለመጠበቅ የተደነገገው ሕግ ከለላ የሚሰጠው አብዛኛውን ጊዜ በግጭቱ ተጋላጭ ወገኖች ውስጥ የወደቁት የአንዱ የጦር ኃይል አባላትን ነው። ሦስተኛው የ1949 የጄኔቫ ኮንቬንሽን የጦር እስረኞች ያላቸውን መብት እና እንደ ጦር እስረኛ ሊወሰዱ የሚችሉ የሌሎች ሰዎች ምድቦችን ይለያል። እንደ ኮንቬንሽኑ ድንጋጌ ከሆነ የጦር እስረኞች የሚባሉት በጦርነት ተሳታፊ ሆነው በተቃራኒ ቆመው የተማረኩ ናቸው።

ወታደራዊ ባለሙያዉ ኃምሳ አለቃ ብርሃኑ በበኩላቸው፣ የጦር ምርኮኛ(እስረኛ) ማለት በኹለት ተቃራኒ ኃይሎች መካከል በሚደረግ ጦርነት ቆስሎ ይሁን ሳይቆስል በተቃራኒ በቆመው አካል ቁጥጥር ስር የሚውል ነው ይላሉ። ባለሙያው አክለውም በውትድርና ሳይንስ አንድ ሰው የጦር ምርኮኛ ሊባል የሚችለው በቀጥታ ከተቃራኒ ኃይል ጋር ለመዋጋት ወደ ጦር ሜዳ ገብቶ ቆስሎም ይሁን ሳይቆስል ሲማረክ ነው ይላሉ።

“The rules protecting prisoners of war (POWs)” መሠረት “የጦር ምርኮኞች መታሰር የቅጣት ዓይነት አይደለም፤ ነገር ግን በግጭቱ ውስጥ ተጨማሪ ተሳትፎን ለመከላከል ብቻ ነው” ይላል። በኹለቱ ተፋላሚ አካላት መካከል የሚደረገው የኃይል ፍልሚያ ካለቀ በኋላ የጦር እስረኞቹ መለቀቅ እንዳለባቸውም ተቀምጧል። ይሁን እንጅ በተቃራኒ ጎራ በተሰለፈ አካል የተማረኩ የጦር እስረኖች በእስር ላይ በሚቆዩበት ጊዜ የጦር ወንጀሎች ሊፈጸሙ እንደሚችሉ ቀይ መስቀል በጽሑፉ ይገልጻል። በጦር ምርኮኞች አያያዝን በተመለከት የተቀመጠውን የጀኔቫ ኮንቬንሽን ጥሶ የጦር ወንጀል መፈጸም በዓለም ዐቀፉ የስብዓዊነት ሕግ መሠረት ሕጋዊነት እንደሌለው ተገልጿል።

የጦር እስረኞችን ለመጠበቅ የወጣው ሕግ የጦር ምርኮኞች በማንኛውም ሁኔታ ሕክምና የማግኘት ከማንኛውም የጥቃት ድርጊት ፣ እንዲሁም ከማስፈራራት ፣ ከስድብ እና ከመሳቀቅ የመጠበቅ መብት አላቸው።

ዓለም ዐቀፉ የሰብዓዊነት ሕግ ደግሞ የጦር እስረኞቹ እንደ መጠለያ ፣ ምግብ ፣ ልብስ ፣ ንጽህና እና የሕክምና እንክብካቤ የመሳሰሉትን ጉዳዮች የሚያገኙበት ዝቅተኛ የእስር አያያዝ ሊኖራቸው እንደሚገባ ይገልጻል።

የሕግ ባለሙያው ካፒታል፣ የጦር ምርኮኞች በእስር ላይ በሚቆዩበት ጊዜ መሠረታዊ የሆኑ ሰብዓዊ መብቶቻቸው እንዲከበሩላቸው ኢትዮጵያ የተቀበለቻቸው ዓለም ዐቀፍ ሕጎች እንደሚያስገድዱ ጠቁመዋል።

ዓለም ዐቀፋዊ ባልሆኑ የትጥቅ ግጭቶች ውስጥ የ1949 የጄኔቫ ስምምነት እና ተጨማሪ ፕሮቶኮል II አንቀጽ 3 ከግጭቱ ጋር በተያያዙ ምክንያቶች ነጻነታቸውን የተነፈጉ ሰዎች በኹሉም ኹኔታዎች ውስጥ ሰብዓዊ አያያዝ ሊኖራቸው እንደሚገባ ይደነግጋል። በተለይም ከግድያ፣ ከማሰቃየት፣ እንዲሁም ከጭካኔ፣ ከመዋረድ ወይም ከሚያዋርድ አያያዝ የተጠበቁ ናቸው።

ኢትዮጵያ ውስጥ አሁን ላይ እየታየ ያለው የጦር ምርኮኞች አያያዝ ግልጽነት የጎደለው ከመሆኑ ጋር ተያይዞ፣ የጦር እስረኞች መብታቸው እየተከበረ ስለመሆኑ ባይታወቅም፣ የአገሪቱም ይሁን ዓለም ዐቀፍ ሕጎች መከበር እንዳለባቸው የሕግ ባለሙው ጠቁመዋል።
በሰሜኑ የኢትዮጵያ ከፍል እየተካሄደ ባለው ጦርነት በኹለቱም ኃይሎች ተማርከዋል የተባሉ የጦር እስረኞች አያያዝ ከዓለም ዐቀፉ እና ከኢትዮጵያ ሕግ ያፈነገጠ ከሆነ እስከ ጦር ወንጀል የሚደርስ የሕግ ተጠያቂነት እንደሚያስከትል ጠቁመዋል። በጦር ምርኮኞች አያያዝ ላይ የተቀመጡ ዓለም ዐቀፍ እና አገር ዐቀፍ ሕጎችን የጣሰ አካል ከአምስት ዓመት እስከ 25 ዓመት ጽኑ እስራት እንደሚቀጣ የሕግ ባለሙው ጠቁመዋል። በጦር እስረኞቹ ላይ ከፍተኛ የሰብዓዊ መብት ጥሰት ወይም ግድያ የፈጸመ አካል በጦር ወንጅል ከተከሰሰ ከእድሜ ልክ እስራት እስከ ሞት ቅጣት ሊያስበይነበት የሚችል የሕግ ድንጋጌ መኖሩን ካፒታል ጠቁመዋል።

በፌደራል መንግሥት እና በሽብርተኝነት በተፈረጀው ህወሓት ኃይሎች ተማርከዋል የተባሉ የጦር እስረኞች፣ በኹለቱም ወገን ተገቢ ላልሆነ የፕሮፖጋንዳ መጠቀሚያ እየሆኑ መሆኑን የሕግም ሆኑ የወታደራዊ ባለሙያው ይገልጻሉ።

በኹለቱም ኃይሎች በኩል የተማረኩ የጦር እስረኞችን በየሚዲያው እያወጡ የፕሮፖጋንዳ መጠቀሚያ ማድረግ ከውትድርና መርሕ ያፈነገጠ መሆኑን ኃምሳ አለቃ ብርሃኑ ጠቁመዋል። የሕግ ባለሙው ካፒታል በበኩላቸው፣ የጦር ምርኮኞችን በሚዲያ እያቀረቡ ለፕሮፖጋንዳ ትርፍ መጠቀም በሕግም በሞራልም ትክክል አለመሆኑን ጠቁመዋል። በመሆኑም ኹለቱም ኃይሎች የጦር ምርኮኞችን መብትና ሞራል ማክበር እንደሚገባቸው ባለሙያዎቹ ጠቁመዋል።


ቅጽ 3 ቁጥር 148 ነሐሴ 29 2013

Comments: 0

Your email address will not be published. Required fields are marked with *

This site is protected by wp-copyrightpro.com