የእለት ዜና

ሥለ ጫት ክልከላው…!

ከሠሞኑ መነጋገሪያ ከሆኑ ጉዳዮች መካከል በወሎ ግዛት በተለይም በደሴ ከተማ ጫት ማስቃምም ሆነ መቃም መከልከሉን ተከትሎ የተወራው ነው። ባሳለፍነው ሳምንት መገባደጃ ላይ ወጣቶች አዳራሽ ሞልተው የውጭ እግር ኳስ ውድድርን ሲመለከቱ የተነሳ ፎቶ፣ በሌላ አካባቢ ወደ ጦር ግንባር ከሚዘምቱ ወጣቶች ጋር እያነፃፀሩ ብዙዎች ሲሳለቁበቀቸው፣ አንዳንዶች ደግሞ ሊያሳፍሯቸው ሲሞክሩ ነበር።

ጦርነቱ እየተፋፋመ በመጣበት በዚህ ወቅት ወጣቶች ወደጦር ሜዳው ማምራት እንጂ ሸሽተው በየአዳራሹ ተሰብስበው መዝናናትና ማውካካት እንደሌለባቸው ሊመክሩ የጣሩ ብዙ ነበሩ። አንዳንዶች፣ ወጣቱን ቀስቅሶ በፈቃዳቸው እንዲዘምቱ ወይም ባሉበት ሆነው እንዲያግዙ ማድረግ ካልተቻለ ማስገደዱ ውጤታማ ስለማይሆን መተዉ ይሻላል ያሉ ነበሩ። ወዶ ገብ ዘማች ካልሆነ እንደቀድሞ ዘመን በአፈሳ የሚካሄድ ጦርነት አዋጭ ስላልሆነ ወጣቶቹ እንዲሳተፉ ማበረታቻ የሚሆነን ነገር ማስነገር ያሻላል ያሉ ቢበዙም፣ የማረካችሁትን መሣሪያ ውረሱ መባሉም አዳዲስ ዘማቾችን ያን ያህል አልሳበም እያሉ ሐሳቡን የሚያጣጥሉት አልጠፉም።

ጦርነቱን ሕዝባዊ ለማድረግ በኹለቱም ወገን ከሚደረገው ሩጫ አንፃር የትኛውም ወገን እንዳልተሳካለት የሚናገሩ አንዳንዶች፣ ተስፋ የቆረጠና አማራጭ ያጣን የሚያዘምቱ የመኖራቸውን ያህል በስሜት ተነሳስተው በፈቃደኝነት የሚዘምቱትን እንደሚመጣጠኑ ይናገራሉ። ብዛት ያለው ወጣት ወደ ጦር ማሠልጠኛ ገብቶ እየተመረቀ ነው በሚባልበት በዚህ ወቅትም ቢሆን፣ ተመዝገቡና ተቀላቀሉ፣ ሕዝባችሁንም ጠብቁ የሚሉ ቅስቀሳዎች ይሠማሉ። በአንዳንድ አካባቢዎች እንዝመት ያሉ መሣሪያ ያልታጠቁን ወጣቶች የመንግሥት አካላት ተመልሰው በአካባቢያቸው ረግተው እንዲጠብቁ ማድረጋቸውም የሐሳብ ፍጥጫ አስከትሎ ነበር።

ይህ በእንዲህ እንዳለ፣ በወሎ ግንባር የሚካሄደው ጦርነት በተፈለገው ፍጥነት ፈቀቅ አልል ያላቸው የመንግሥት አካላትም ሆኑ የማኅበረሰብ አንቂዎች መላ ብለው የዘየዱትን አዲስ ሐሳብ አፍልቀዋል። በጦርነቱ ወቅት በወሎ ግዛት ጫት የሚባል ተክል እንዳይሸጥ፣ ማስቃሚያና ሺሻ ቤቶች ውጊያው ተጠናቆ ጦርነቱ እስኪገባደድ ድረስ ወጣትን ፍራሽ ላይ እንዳያውሉ ዕገዳ ተጥሎባቸዋል።

ከተለያዩ የሰሜን ወሎ ግዛቶች ተፈናቅሎ የመጣ ወጣት እንደሌሎች አካባቢዎች ተደራጅቶ ለመመለስና አገሩን ለመጠበቅ ከመጣር ይልቅ፣ በሱሳ ሱስ ተጠምዶ መዋል የለበትም በሚል የተወሰነው ውሳኔ ብዙዎችን ቢያስደስትም የተቃወሙት ነበሩ። በነካ እጃችሁ መጠጥ ቤቶችንና ቁማር ቤቶችንም ዝጉ ያሉ የመኖራቸውን ያህል፣ በጎንደር የእግር ኳስ አቋማሪ ቤቶች በመዘጋታቸው የተገኘን ውጤት እያነሱ ተግባሩ መቀጠሉ ጥሩ እንደሆነ የተናገሩ በርካቶች ናቸው።

በሌላ በኩል፣ ዕርምጃው ኑሯቸውን በጫት ላይ የመሠረቱ፣ አብዛኛው የእርሻ መሬታቸውን በጫት የሸፈኑ ገበሬዎችን ሕይወት የሚያመሳቅል፣ በዘርፉ ላይ ለተማመኑ ነጋዴዎችም ዱብ ዕዳ የሆነ፣ ማኅበራዊ ሕይወትን የሚያናጋ ነው ብለው ሌላ መዘዝ እንዳያመጣ ሲሉ ሥጋታቸውን ያሠሙ ነበሩ። ገበሬው፣ ነጋዴው፣ አስቃሚው ወይስ ቃሚው ነው በውሳኔው የሚጎዳውና የሚጠቀመው በማለት ጥያቄ አዘል አስተያየታቸውን የሰነዘሩም ነበሩ። ወጣቱ የሚቅመው ጫት ሲያጣ ይዘምታል ተብሎ ባይጠበቅም፣ ቤት ውስጥ ውሎ አሉባልታ ከሚያናፍስ ወጣ ብሎ ቢያንስ አካባቢውን ይጠብቃል ያሉ አሉ።

የየመኖቹ ሁቲዎች እየቃሙ መርቅነው ከመዋጋት ያገዳቸው የለም ብለው አስተያየታቸውን ለሰነዘሩም ምላሽ የሰጡ ነበሩ። መርቅነው መዋጋታቸው ቢጠቅማቸው ኑሮ ጦርነቱ ይህን ያህል ዓመት ፈጅቶ አገራቸውንም ባላወደመ ሲሉ ሐሳቡን ኮንነዋል። በአንድ ወቅት ቃሚ የሆኑ የማኅበረሰብ ክፍሎች የሀራራ ሰዓታቸው ሲደርስ ውጊያ አቋርጠው ጠላታቸውን፣ “ቦታው የኔ ነው ካሉ፣ ምለው ይውሰዱ” አሉ ተብሎ የሚነገረው መዘንጋት የለበትም።


ቅጽ 3 ቁጥር 148 ነሐሴ 29 2013

Comments: 0

Your email address will not be published. Required fields are marked with *

error: Content is protected !!