የእለት ዜና

የሥነ ሕዝብ ቀን ከፒ ኤች ኢ ኢትዮጵያ ኮንሰርቲየም እና ኮርሃ ጋር ተከበረ

Views: 122

ፒ.ኤች.ኢ ኢትዮጵያ ኮንሶርትየም የተቀናጀ አሰራርን ለማስተዋወቅ እና በስፋት እንዲተገበሩ በማድረግ የሰዎች እና የአካባቢ መስተጋብር ተጠጥሞ ዘላቂ ልማትን እውን ርዕይን አንግቦ በ2000 ዓ.ም የተመሰረት ድርጅት ነው።
ድርጅቱ ከተመሰረተበት ጊዜ አንስቶ እስካሁን ድረስ የአካካቢ፣ የሥነ-ሕዝብ፣ የማኅበራዊ፣ የኢኮኖሚ እና የጤና ጉዳዮችን ያቀናጁ የተለያዩ የልማት ሥራዎች ሲያከናውን ቆያቷል።
በዚህ ገጽ ላይ የተካተቱት የተለያዩ አካላት ሐሳቦች የፒኤችኢ ኢትዮጵያን አቋም ላያንጸባርቁ ይችላሉ።

ፒ ኤች ኢ ኢትዮጵያ ኮንሰርቲም 71 የአገር ውስጥና ዓለም ዐቀፍ ሲቪክ ማኅበራት በአባልነት አቅፎ የያዘ የሲቪክ ማኅበር ነው፡ ጥምረቱ በሥነ-ሕዝብ፣ ጤና፣ የአካባቢ እና አየር ንብረት ለውጥ፣ ዲሞክራሲ ግንባታ፣ እንዲሁም ሰብዓዊ መብት ላይ የሚሠራ ሲሆን፣ ሁሉም ባለድርሻ አካላት የሚጠበቅባቸውን ሚና ከተወጡ የተሻለ ውጤት እንደሚመጣ በመገንዘብ በአጋርነትና በቅንጅት የመሥራትን ፋይዳን በብዙ መልኩ ያረጋገጠ ተቋም ነው።

በተለያዩ የውይይት መድረኮች እንዲሁም ሥልጠናዎች የተለያዩ አጀንዳዎች በመቅረጽ ያካሂዳል። የሥነ-ሕዝብ ጤና እና አካባቢ ላይ ትኩረቱን በማድረግ እየሠራ የሚገኘው ፒ ኤች ኢ ኢትዮጵያ ኮንሰርቲም እና ኮርሃ የዘንድሮውን የዓለም ዐቀፍ የሥነ-ሕዝብ ቀን የፌደራል ከፍተኛ የሥራ ኃላፊዎች ከተለያዩ የማኅበረሰብ ክፍል የተወከሉ ማኅበረሰቦችን ጨምሮ በርካታ ባለድርሻ አካላት በተገኙበት በዓሉን በፓናል ውይይት አክብሯል።

አለማአቀፍ የስነህዝብ ቀን በተከበረበት ወቅት የተለያዩ ጥናቶች የቀረቡ ሲሆን ፖሊሲዎችን ለመሻሻል መሰራት እንደሚገባ ተጠቁሟል። እንደ ሀገር በፈረንጆቹ 1993 የነበረው የስነህዝብ ፖሊሲ ለ10ዓመት ያገለገለ በመሆኑ እንዲሁም ይህ ፖሊሲ በፈረንጆቹ 2013 በኋላ ባለመሻሻሉ እስከአሁን በቀድሞው እየተመራ ይገኛል። በመሆኑም ይህ ፖሊሲ ማሻሻያ ማድረግ እንደሚገባ ተገልጿል። ከዚህ በተጨማሪም የስነህዝብ ፖሊሲ የ10ዓመት እቅድ ውስጥ የተካተተ ሲሆን በቀጣይ ተሻሽሎ ወደ ስራ መግባት አለበት ተብሏል።
ከዚሁ ጋር ተያይዞ የስነ ህዝብ ምክርቤት በክልልና በፌደራል ደረጃ እንዲቋቋም በእለቱ ጥሪ የቀረበ ሲሆን በሴቶች ላይ የሚፈጸመው ያለእድሜ ጋብቻ ትኩረት ተሰጥቶት በፖሊሲ ውስጥ እንዲካተት ተጠይቋል።
በኢትዮጵያ የሥነ ሕዝብ ትሩፋት ለመተግበር አስፈላጊ ሥራ ተጠናክሮ መቀጠል ይገባዋል ሲሉም የፒኤችኤ ዳይሬክተር ነጋሽ ተክሉ ተናግረዋል።

ፒኤችኢ በቤስት ዌስት ፕላስ ከበርካታ ባለድርሻ አካላት ጋር ያደረገውን ውይይት የመክፈቻ ንግግር ያደረጉት የኢፌድሪ የጤና ሚኒስትር ዶ/ር ሊያ ታደሰ ናቸው። በውይይቱ ላይ በክብር እንግድነት የተገኙት የኢፌድሪ ጤና ሚኒስቴር ሚኒስትር ዶ/ር ሊያ ታደሰ የበዓሉን አስፈላጊነት በተመለከተ ማብራሪያ ሰጥተዋል።

የዓለም ዐቀፍ ሥነ-ሕዝብ ቀን በሚከበርብት ቀን መገኘታቸው እንዳስደሰታቸው ዶ/ር ሊያ ተናግረዋል። በኢትዮጵያ ከሚገኙ 115 ሚሊዮን ሕዝብ ውስጥ 70 በመቶው ከ30 ዓመት በታች ሲሆን፣ እነዚህ ወጣቶች በአቅማችው ልክ አምራች አይደሉም። በመሆኑም የጤና ስርዓትን በማሻሻል ማኅበረሰብን የመገንባት ሥራ እየተሠራ እንደሚገኝ ሚኒስትሯ ጠቁመዋል።

የጤና ሚኒስትር የወሊድ ወቅት የሚከሰቱ ሞትን በመከላከል እና የእናቶችና ህጻናት ጤና በማሻሻል አገልግሎት እየሰጠ ይገኛል።

የኮቪድ-19 ወረርሽኝ በተከሰተበት ወቅት ክልሎች ላይ ከፍተኛ የሥነ ተዋልዶ ችግር ተፈጥሯል። እንደ አገር ወረርሽኙን እየተከላከልን መሠረታዊ አገልግሎቶችን ለማሳደግ ሰፊ ሥራ መሥራት አለብን ብለዋል። ፒኤችኢ ኢትዮጵያ የሥነ-ሕዝብ ቀን በትኩረት በመስራት እንደዚህ ቀኑን ማክበሩ ትልቅ ቦታ የሰጡት ደ/ር ሊያ ምስጋናቸውንም አቅርበዋል። የዓለም ዐቀፍ የሥነ-ሕዝብ ቀን ማክበርን በማስመልከት የተለያዩ ጥናታዊ ጽሁፎች እና ፖሊሲዎች ቀርበዋል።

በኢትዮጵያ ለ28ኛ ጊዜ በተከበረው የሥነ ሕዝብ ቀን የሕዝብ ቁጥር መጨመር፣ ድህነት፣ የተፈጥሮ ሚና መዛባት፣ የጤና ሥርዓት ተደራሽነት ብቁ አለመሆን እንዲሁም የኮቪድ 19 ወረርሽኝ የወቅቱ የዓለም ሥጋት መሆናቸው ተነስቷል።
በሕዝብ ቁጥር መጨመር ውስጥ የሚከሰቱ ችግሮችን ለመቅረፍ መንግሥት ብቻ ሳይሆን ግብረሰናይ ድርጅቶችም የበኩላቸውን በማድረግ ሚናቸውን መወጣት እንደሚገባቸውም ጥሪ ቀርቧል።

በዕለቱ የሥነ ሕዝብ ቀን መከበር እንደሚገባው የሚያጠነጥን ፖሊሲዎች ይፋ ተደርገዋል።

የጤና ሚኒስቴር አዲስ ፖሊሲዎችን እና ስትራቴጂዎችን በመቅረጽ እንደ መንግሥት በጀት በመመደብ እና አጋር ድርጅቶችና ባለድረሻ አካላትን በማስተባበር የማኅበረሰብ ጤና በማሻሻል ምርታማና ለኢኮኖሚ ዕድገት አስተዋጽኦ የሚያደርግ ማኅረሰብ ለመገንባት ሠፊ ሥራ እየሠራ እንደሚገኝ ጤና ሚኒስትሯ ዶ/ር ሊያ ጠቅሰዋል።

ጥናቶቹ በዋናነት ትኩረት ያደረጉት ከመንግሥትና መንግሥታዊ ካልሆኑ ተቋማት እና ሲቪክ ማኅበራት ጋር ያለው የትብብር ሥራ መቀጠል እንዳለበት ነው።
የሥነ-ሕዝብ ጉዳይ የአንድ ተቋም ባለመሆኑ የሁሉም ተቋማት ኃላፊነት እንደመሆኑ መጠን ሁሉም ተረባርቦ በሥነ-ሕዝብ ልማት እናወደፊት በጋራ አብሮ መስራት እንዴት እንደሚቻል የሚዳስሱ ጥናቶች ቀርበዋል። በአሁኑ ሰዓት የሥነ-ሕዝብ ችግሮች ምንድን ናቸው በማለት ለችግሮቹ መፍትሄ የሚያቀርቡ ሦስት የተለያዩ ሐሳቦችም ተነስተዋል። ከዛሬ 30 አመት በፊት ያለው የወሊድ መጠን ሲታይ የሕዝብ ብዛት የተፈለገውን ያህል መቀነስ አለማሳየቱን በጥናቶቹ ተነስተዋል።

በአማካይ አንድ ሴት ልጅ መውለድ የሚገባት ምን ያህል እንደሆነ በፖሊሲ ቢቀመጥም ተግባራዊነቱ አነስተኛ ሆኖ መገኘቱን በጥናቱ ተካቷል። በተለይ በክልሎች ያለው የወሊድ መጠን መብዛት እንደሚታይበት በጥናቶቹ ቀርበዋል። እንደ ክልል መንግሥታዊ ካልሆነ ድርጅቶች እና ሲቪል ሶሳይቲ ጋር በጋራ በመሆን ለመሥራት ማቀዱን ከኦሮሚያ ፕላንና ኢኮኖሚ ልማት ኮሚሽን የሥነ-ሕዝብ ቡድን አስተባባሪ ፍቃዱ አብዲሳ ገልጸዋል።

የፌደራል ፕላኒንግ ኮሚሽን የሥነ-ሕዝብ ዳይሬክቶሬት ያለው ሲሆን፣ በተለያዩ ዘርፍ ያሉት የሥነ-ሕዝብጉዳይ የሚመለከታቸውን በማስተባበር፣ በማገናኘት እና በትብብር እንዲሠሩ የሚያደርግ መሆኑን ፍቃዱ ጠቅሰዋል። የዓለም ዐቀፍ የፖፑሌሽን ቀን በየአመቱ ጁላይ 11 የሚከበር ሲሆን፣ በአገራችን ባለመከበሩ ፒኤችኢ ቀኑን ብቻ ሳይሆን ሀሳቡን ለማንጸባረቅ በማሰብ አክብሮት አልፏል።

በሥነ-ሕዝብ ቀን መነሳት ያለባቸውን ሐሳቦች በማንሳት እና የፖሊሲ ለውጥ መኖር ካለበት እንዲቀየር ያስችላል ሲሉ በፒኤችኢ ኢትዮጵያ የኸልዝ እና ጀንደር ፕሮግራም አስተባባሪ ጽጌ ገብረጻዲቅ ተናግረዋል።
ፒኤችኢ ሥራዎችን ወደ መሬት ለማውረድ የተቀናጀ እና የተለያዩ ሴክተሮችን በማጣመር የሚያሰራ ተቋም ነው። ሥነ-ሕዝብ ደግሞ አብዛኛው እንደ ትምህርት ተቋም፣ ጤና፣ ግብርና እና ጾታን መሰረት ያደረጉ አካላት በሙሉ ይመለከታቸዋል። የዘንድሮ የሥነ-ሕዝብ ቀን ሲከበር የታየው ከኮቪድ-19 ወረርሽኘን ተከትሎ የመጣው ጉዳት የወሊድ መጠን እንዲጨምር አድርጎታል።

ኮቪድ ወረርሽኝ መከሰቱ በአብዛኛው የትምህርት ቤቶች መዘጋት፣ የጥቃቅንና አነስተኛ ንግዶች መቀዛቀዝና በቤት የመቀመጥ ሁኔታ ወሊድ እንዲጨምር አድርጎት ነበር። ያለን የጤናና ስነ ተዋልዶ ስርዓት መጎልበት የሚገባው ሆኖ ሳለ የወሊድ መጠን መብዛት ደግሞ የሁሉም ዘርፍ ኃላፊነት እንደመሆኑ መጠን ሁሉም አካላት ተረባርበው በጋራ መሥራት ይገባቸዋል ሲሉ ገልጸዋል።

ኢትዮጵያ የሥነ-ሕዝብ ፖሊሲ ካወጣች ጀምሮ ፒኤች ኢ ለሕብረተሰቡ ማኅበራዊ ኢኮኖሚያዊ የተፈጥሮ ለውጥ በተሳሰረ በተቀናጀ ዘላቂ ልማት ለማሳካት የሚጥር ነው።71 አባላትን ይዞ የሚንቀሳቀሰው ፒኤችኢ ኮንሰርቲየም የዘንድሮው የሥነ-ሕዝብ ቀን ሲከበር ትኩረት የሚስብ ለማድረግ ጥረት ተደርጓል። በዓለማችን የሕዝብ ቁጥር አሁንም ከፍተኛ የሆነ መጨመር እያሳየ ይገኛል ሲሉ የፒኤች ኢ ዳይሬክተር ነጋሽ ተክሉ ገልጸዋል። በአሁኑ ሰዓት የአለማችን የሕዝብ ቁጥር 7.7 ቢሊዮን ደርሷል።በአፍሪካ ደረጃ 1.4 ቢሊዮን እንዲሁም በኢትዮጵያ 115 ሚሊዮን በላይ ሕዝብ አለ።

በኢትዮጵያ የሥነ ሕዝብ ትሩፋት ለመተግበር አስፈላጊ ሥራ ተጠናክሮ መቀጠል ይገባዋል ብለዋል። የዜጎችን መብት ከማክበር አንጻር የተከበረው የሥነ-ሕዝብ ቀን ሲቪል ማኅበረሰቡ ከፍተኛ ትኩረት እንደሚሰጠው በእለቱ ተነስቷል። ፒኤችኢ ኢትዮጵያ ኮንሰርቲየም ለአየር ንብረት ለውጥ በመቋቋም እና የአካባቢን ዘላቂነት በማረጋገጥ፣ በኢትዮጵያ ውስጥ የሕዝብ ጤና እና አካባቢን ውህደት ለዘላቂ ልማት ለማሳደግ የሚፈልግ መንግሥታዊ ያልሆነ ድርጅት ነው።

በሥነ ሕዝብ ጤና እና አካባቢ የሚሰራው ፒኤችኢ ኢትዮጵያ ኮንሰርቲየም፣ ከተመሠረተ በፈረንጆቹ 2008 ጀምሮ ለሕብረተሰቡ ዘላቂ የልማት አቅጣጫዎችና መፍትሄ የማምጣት ሥራዎችን ሲሠራ ቆይቷል። ድርጅቱ ከአፍሪካ በሕዝብ ብዛት በ2ኛ ደረጃ የምትገኘው ኢትዮጵያን የሥነ ሕዝብ ሒደት ከልማት ጋር በማስታርቅ ለውጦችን ለማምጣት እየሠራ የሚገኝ ነው። ፒኤችኢ በብዛት የሚሠራው ጥብቅ የሆኑ ቦታዎችን፣ የተፋሰስ አካባቢዎችን፣ ደረቅ ቦታዎች እና የደን አካባቢዎችን መነሻ በማድረግ ነው።

የአካባቢ ጥበቃ መብትን በተመለከተ ፒኤችኢ ከኮሚሽኑ ጋር በጋራ በመሆን የተለያየ ባለ ድርሻ አካላት አባል የሆኑበት አገር ዐቀፍ መድረክ (ፕላትፎረም) አቋቁሟል። በአጋርነት እና ትብብር የሚያምነው ፒኤችኢ በሽርክና እና በጥምረት ግንባታ ስኬታማ የሆኑ የብዙ የውህደት ዘርፎችን በመፍጠር ከመንግሥት አካላት ፣ ከአባል ድርጅቶች ፣ ከልማት አጋሮች እና ከሌሎች ባለድርሻ አካላት ጋር እየሠራ ይገኛል።


ቅጽ 3 ቁጥር 148 ነሐሴ 29 2013

Comments: 0

Your email address will not be published. Required fields are marked with *

This site is protected by wp-copyrightpro.com