የእለት ዜና

ጦርነት እና ኢኮኖሚ

Views: 180

በሰሜን ኢትዮጵያ ያለው ጦርነት በኢኮኖሚው ላይ ቀላል የማይባል ተጽዕኖ እያሳደረ ነው። በትግራይ ክልል ተገድቦ ለስምነት ወራት የዘለቀው ጦርነት፣ የፌደራል መንግሥት የተናጠል የተኩስ አቁም አውጆ ትግራይን ለቆ መውጣቱን ተከትሎ ወደ አጎራባች ክልሎች በመስፋፋቱ በኹለት እግሩ ያልቆመውን የአገሪቱን ኢኮኖሚ እያተረማመሰው መሆኑን የዘርፉ ባለሙያዎች ይገልጻሉ።
በጦርነቱ ወታደራዊ ወጪን ሳይጨምሮ 100 ቢሊዮን ብር በስምንት ወራት ጊዜ ውስጥ መውጣቱ የኢትዮጵያን ኢኮኖሚ ወደ ኋላ የሚጎትት በመሆኑ፣ ኢኮኖሚው ከገጠመው ሥብራት ይጠገን ዘንድ ከወትሮው የተለየ የኢኮኖሚ ሥርዓት እንደ አማራጭ መመልከት እንደሚገባ ባለሙያዎች ይመክራሉ።
በጦርነቱ የሚወጣውን ገንዘብ እና የሚወድመውን ኢኮኖሚ ለመታደግ ብሎም ኢኮኖሚው ብዙ ጉዳት ሳይገጠመው እንዲያገግም ለማድረግ ወቅቱን የዋጀ የኢኮኖሚ ሥርዓት ማጤን የሚገባን ወቅት ላይ ነን።
በፌደራል መንግሥት እና በሽብርተኝነት በተፈረጀው ህወሐት መካከል እየተካሄደ ባለው ጦርነት ምክንያ ቀድሞም ግስጋሴው ያልተገታው የዋጋ ግሽበት ተባብሶ ቀጥሏል። የዋጋ ግሽበት ወትሮውንም የኢትዮጵያን ኢኮኖሚ ከሚፈትኑ ተግዳሮቶች መሀል ዋነኛው ቢሆንም፣አሁን ባለው ወቅታዊ ሁኔታ የሚታየውን የመባባስ ዝንባሌ መግታት እንደሚገባ ባለሙዎች ይጠቁማሉ።
በሰሜኑ ጦርነት ምክንያት የደረሰውን የኢኮኖሚ ሥብራት እና ጦርነቱ ከተጠናቀቀ በኋላ ኢትዮጵያ መከተል ስለሚገባት የኢኮኖሚ ሥርዓት የአዲስ ማለዳው አቤል ኃይሉ ባለሙያዎችን አናግሮ የማለዳ ዘ ሐተታ ርዕሰ ጉዳይ አድረጎታል።

ኢትዮጵያ በኢኮኖሚ ጸንተው በኹለት እግራቸው ካልቆሙ አገራት መካከል እንደሆነች ይታወቃል። ኢትዮጵያ በየዓመቱ ዓለማችን ላይ ካሉ እንደ ኢንተርናሽናል ሞኒተሪ ፈንድ(አይ ኤም ኤፍ) እና የዓለም ባንክን ከመሳሰሉ ተቋማት እና ኢኮኖሚያቸው በርትቶ ከራሳቸው ተርፎ ለሌሎች ማበደር እና መመጽወት ከቻሉ አገራት ደጃፍ ላይ እጃቸውን ዘርግተው ኢኮኖሚያቸውን ለማበርታት ከሚጥሩ አገራት መካከል እንደሆነች ይነገራል።

ኢትዮጵያ ከፍተኛ የዕዳ መጠን ያለባት በመሆኑ ምክንያት የተለያዩ አበዳሪ ተቋማት ብድር ለማቅረብ ሲያቅማሙ ይስተዋላል። በብድርና በእርዳታ ጎዶሎዋን የምትሞላው አገር ቋቷን ለመሙላት ብዙ ድካም እንዳሚጠብቃት ይታሰባል።
በገቢ እና ወጪ ንግድ አለመመጣጠን ምክንያት የራሱ የሆነ ችግር ያለበት የኢትዮጵያ ኢኮኖሚ አፋጣኝ የሆነ የለውጥ መንገድ መከተል እንዳለባት በዘርፉ ባለሙያዎች በተደጋጋሚ ሲነሳ ይሰማል።

የኢትዮጵያ ኢኮኖሚ በኹለት እግሩ ሳይቆም በአገሪቱ በተለያዩ አካባቢዎች የሚፈጠሩ የጸጥታ ችግሮች፣ በተለይም በ2013 መጀመሪያ በህወሓት እና በፌደራል መንግሥት መካከል የተፈጠረው ጦርነት ለኢኮኖሚው እንቅፋት ሆኗል። በፌደራል መንግሥቱ እና በወቅቱ የትግራይን ክልል ሲያስተዳድር በነበረውና አሁን ላይ በሽብርተኝነት በተፈረጀው ህወሓት መካከል የነበረው አለመስማማት ወደ ጦር መማዘዝ አድጎ አሁን ላይ ጦርነቱ ወደ አማራ እና አፋር ክልል ተስፋፍቷል። በሰሜኑ የኢትዮጵያ ክፍል ተባብሶ የቀጠለው ጦርነት ደግሞ በነበረው የአገሪቱ የኢኮኖሚ መንገራገጭ ላይ የከፋ ነገር ጨምሮ ኢኮኖሚውን ሊፈታተነው እንደሚችል ባለሙያዎች ያነሳሉ።

የኢትዮጵያ ኢኮኖሚ እንኳንስ ጦርነት ተጨምሮበት ይቅርና በፊትም በረጂ እና በአበዳሪ አገራት ትከሻ ላይ ተመርኩዞ የቆመ መሆኑን ባለሙያዎች ይስማሙበታል።
የኢትዮጵያን ኢኮኖሚ በአበዳሪዎች ትከሻ ላይ የተንጠለጠለ ነው የሚሉት የዘርፉ ባለሙያዎች፣ ኢትዮጵያ በአሁኑ ጊዜ ትልቅ ኢኮኖሚያዊ ማሻሻያዎችን ማድረግ የምትሻበት ጊዜ ላይ እንደምትገኝ ይገልጻሉ።

ኢትዮጵያ በአሁኑ ጊዜ የጦርነት ኢኮኖሚ መስመር ለይ መሆኗን የሚጠቅሱት በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የኢኮኖሚክስ ትምህርት ክፍል መምህር አጥላው አለሙ(ረ/ፕ) ናቸው። የጦርነት ኢኮኖሚ ከሠላም ጊዜ ኢኮኖሚ ለየት የሚል ነው የሚሉት ባለሙያው፣ የጦርነት ኢኮኖሚ ዋነኛ ዓላማ በጦርነቱ ድልን መቀዳጀት በመሆኑ የውስጥ ሀብትንና የሰውን ጉልበት የሚያደራጅ ነው ይላሉ። ይህም ማለት ፍጆታውና አጠቃላይ ምርቱ ኹሉ ለጦርነት የሚያግዝ እና የሰው ኃይሉም ለጦርነቱ የሚዘጋጅበት ማለት እንደሆነ ይገልጻሉ።

“ጦርነት አነሰም በዛም ሀብት ማጥፋቱ አይቀርም። ነገር ግን ጊዜው በረዘመ ቁጥር ግን በኢኮኖሚ ላይ ድቀት በከፍተኛ ሁኔታ የሚያመጣ ነገር ነው። ሆኖም ጦርነት በአጭር ጊዜ መጠናቀቅ የሚችል ከሆነ የሰው ኃይሉም ወደ መደበኛ የምርት ሒደት የሚመለስ በመሆኑና መንግሥትም ፊቱን ወደ መደበኛ ሥራው እንዲያዞር ስለሚረዳው ኢኮኖሚው ወደ አረንቋ ሳይገባ ማዳን የሚቻል ይሆናል። ዋናው ነገር ግን ጦርነቱ የሚያበቃበት ጊዜ በኢኮኖሚው ላይ ለሚከሰቱ አዎንታዊም ሆነ አሉታዊ ውጤቶች ትልቅ አስተዋጽኦ እንዳለው ይታመናል” ሲሉ ረዳት ፕሮፌሰሩ ሐሳባቸውን ያነሳሉ።

ጦርነት ታስቦበት እና ሳይታሰብበት የተገባ ከሆነ የተለያየ አይነት የኢኮኖሚ መንገድን መከተል እንደሚገባ የሚያነሱት ደግሞ የኢኮኖሚ ባለሙያ የሆኑት ደምስ ጫንያለው (ዶ/ር) ናቸው ። ኢትዮጵያ አሁን ያለችበት የጦርነት ሁኔታ በድንገት የተከሰተ ነው የሚሉት ደምስ፣ በእንደዚህ አይነት ጊዜ ጦርነቱ የአመራረት፣ የአገልግሎት አቀራረብና የሀብት አደላደል አቅጣጫዎችን ይቀይረዋል። በተለይ የመንግሥትን ሀብት ከልማታዊ እንቅስቃሴ ወደ ጦርነቱ እንደሚያዞር ይገልጻሉ።

በዚህ ጊዜ ልማቱ የሚጎዳ በመሆኑ በሌላ አማራጭ መንገድ መደገፍ እንደሚገባው የኢኮኖሚ ባለሙያው ያስረዳሉ። ሆኖም የመንግሥት ዓቅም ብቻውን በቂ ላይሆን ይችላል ሲሉም ያክላሉ። እንደማሳያ የሚያነሱትም የፌደራል መንግሥት በ2013 በጀት ዓመት 476 ቢሊዮን ብር መድቦ በትግራይ ክልል በተደረገው ጦርንት ወታደራዊ ወጭዎችን ሳይጨምር ከጦርነቱ ጋር በተያያዘ ወደ 100 ቢሊዮን ብር ወጪ ማድረጉን በማስታወስ ነው። በትግራይ ጦርነት 100 ቢሊዮን ብር መውጣቱ በአገሪቱ ኢኮኖሚ ላይ ቀላል የማይባል ተጽዕኖ እንዳለው ጠቁመዋል።

“ጦርነቱ ካለቀ በኋላ የጠፉ ነገሮችን በሙሉ መልሶ ማቋቋም ያስፈልጋል። እንደምንሰማው ከሆነ ግን እንስሳቶች ተገድለዋል፤ ቤቶች ተቃጥለዋል፤ተቋማት ተዘርፈዋል በተጨማሪም መሠረተ ልማቶች ፈርሰዋል። እነዚህን እንደገና ለማቋቋም እጅግ ከፍተኛ የሆነ ወጪ ያስፈልጋል። በዚህም ምክንያት ኢኮኖሚው ከፍተኛ ጫና ውስጥ ሊገባ እንደሚችል ይጠበቃል” የሚሉት አጥላው አለሙ ናቸው።

ጦርነቱ በአንድም ይሁን በሌላ መንገድ ለዋጋ ግሽበት ትልቅ አስተዋጽኦ እንደሚኖረው በዓለማችን ላይ ጦርነቶች ሲካሄዱ እና ከተካሄዱ በኋላ የሚታየውን ግሽበት መመልከት በቂ ነው። በኢትዮጵያም በሰሞኑ የታየው የተጋነነ የዋጋ ግሽበት አሁን ካለው ወቅታዊ ጉዳይ ጋር የተገናኘ መሆኑ እየተገለጸ ነው።

በኢትዮጵያ ያለው የዋጋ ግሽበት ከጦርነቱ በፊትም የነበረ መሆኑን የሚገልጹት አጥላው፣ ጦርነት የምርት ዕጥረትን እና የዋጋ ንረትን ማባባሱ የሚታወቅ ሐቅ መሆኑን ጠቁመዋል። ሆኖም ሕዝብ ለመተባበር በር መክፈት ከቻለ እና ከተሳሰበ ይህን ችግር ወደ ጥሩ አጋጣሚ መቀየር እንደሚቻል የሚያነሱት አጥላው፣ አላስፈላጊ ናቸው ተብለው የሚታሰቡ ወጪዎችን በመቀነስ፣ አልያም በመሰረዝ ወደ ጦርነቱ ማዞር ኢኮኖሚውን ጦርነቱ በጉልህ ሳይጎዳው እንዲጠናቀቅ ማድረግ እንደሚቻል ጠቁመዋል። ከምንም በላይ ግን የሕዝብ ትብብር መኖር ትልቅ ሚና ይኖረዋል ይላሉ። ኢኮኖሚውን ለመደግፍ በውጭ የሚኖሩ ኢትዮጵያውያንን አቅምና ዕውቀት አስተባብሮ መጠቀም ልንገባባት ከምንችለው የኢኮኖሚ ችግር መውጫ በር ሊሆን ስለሚችል በዚህ ላይ ትልቅ ሥራ መሥራት እንደሚገባ አመላክተዋል።

በእንደነዚህ አይነት የችግር ወቅቶች የመፍትሔ ሐሳቦችን ተከትሎ ወደፊት ለመሔድ የሚያስችሉ በርካታ መንገዶች ቢኖሩም፣ በዋነኛነት ግን ራስን ለመቻል ጥረት ማድረግ መተኪያ የሌለው መሆኑን ባለሙያው ይናገራሉ። በኢኮኖሚ ራስን የመቻል ጉዳይን አስመልክቶ በተደጋጋሚ በባለሙያዎች ለመንግሥት ሐሳብ ቢቀርብም ሰሚ ጆሮ አግኝቶ ወደ ተግባር መቀየር ባለመቻሉ አሁን ላለንበት የብድር እና ዕርዳታ ጠባቂነት ዳርጎናል ይላሉ ባለሙያው።

“ብድር መበደር በራሱ ክፋት የለውም፤ ችግር የሚሆነው ግን የተበደርነውን ገንዘብ በትክክል መጠቀም ካልቻልን ብቻ ነው። የወሰድነውን ብድር ላልተገባ ዓላማ የምናውለው ከሆነ የዕዳ ቋጥኝ ተሸክመን ከመቀመጣችን ባለፈ አበዳሪ እና ዕርዳታ ሰጪ አገር እስከማጣት የሚያደርስ ችግር ውስጥ ሊያደርስን ይችላል” ሲሉ ባለሙያው ሥጋታቸውን ገልጸዋል።

አሁን የሚታዩት ብድር የመከልከል እና የማዘግየት ዝንባሌዎች በአንድም ይሁን በሌላ መንገድ አሁን በሰሜኑ የአገራችን ክፍል እየተካሄደ ካለው ጦርነት ጋር በተያያዘ መሆኑ ይገለጻል።
ይሄ አይነቱ ብድርና ዕርዳታን መከልከልና ማጓተት ተራውን የአገሬውን ሕዝብ እንደሚጎዳው የታመነ ሐቅ ነው። ጥያቄው መሆን ያለበት እንዴት ከእንደዚህ ያለ ኢኮኖሚያዊ ቅርቃር ውስጥ መውጣት እንችላለን የሚለው ነው። ይህንን በተመለከተ ለአዲስ ማለዳ ሐሳበቸውን ያጋሩት አጥላው ሲናገሩ፣ “በዋነኝነት ለዚህ ጉዳይ እንደ መፍትሔ መቀመጥ ያለበት ጉዳይ በአገር ውስጥ ጥሪት ላይ መተማመን ላይ መድረስ ነው” ይላሉ። ከዚህ በተጨማሪም ግን ብድርም ሆነ እርዳታቸውን ላዘገዩት ምላሽ ይሆን ዘንድ በርካታ ሊረዱን የሚችሉ አገራት በመኖራቸው ወደእነሱ ጠጋ ብሎ የሚሰጡትን መቀብል፣ ኢኮኖሚውን መጠገን እና ከጦርነቱ በኋላ ኢኮኖሚው በቶሎ እንዲያገግም ለማድረግ ከአሁኑ ጥረት መጀመር ተገቢ መሆኑን ጠቁመዋል።

አሁንም ቢሆን ጊዜው ባለመርፈዱ በግዢ ላይ የተመሠረተውን ኢኮኖሚ በመቀነስ በአገር ውስጥ ማምረትን ማበረታታት እና በውጪ ላይ የተንጠለጠለውን ኢኮኖሚ መቀየር እንደሚስፈልግ ይገልጻሉ። “ከውጭ የምናመጣው ከአቅማችን በላይ መሆኑን ለማየት የገቢና እና ወጪ ንግዱን አለመመጣጠን መመልከት በቂ ነው። ኢኮኖሚው ደግሞ ካቅሙ በላይ መኖር የለበትም” ሲሉም ያክላሉ።

የአበዳሪ አገሮች እና ድርጅቶች ዕርዳታ በመንግሥት በጀት ላይ ያለው አስተዋጽኦ እዚህ ግባ የሚባል አለመሆኑን የኢኮኖሚ ባለሙያው ደምስ ይናገራሉ። ከውጭ የሚመጣውም ገንዘብ በጥናትና በመሳሰሉት ጉዳዮች ተመልሶ የሚወጣ ነው የሚሉት የኢኮኖሚ ባለሙያው፣ በእነሱ ላይ ከመተማመን ይልቅ በውጭ አገራት በሚገኙ ኢትዮጵያውያን እና ትውልደ ኢትዮጵያውያን ላይ ትኩረት አድረጎ መሥራት እና የሚልኩትን ገንዘብ ሕጋዊ በሆነ መልከ እንዲልኩ በማድረግ የዶላር ክምችትን ከፍ ማድረግ ያስፈልጋል ይላሉ። በዚህም በኢኮኖሚው ላይ የሚመጡ ተጽዕኖዎችን ለመቋቋም ጥረት ማድረግ እንደሚገባ ባለሙያዎች ይስማሙበታል።

የውጭ አበዳሪዎችም ሆኑ ዕርዳታ ሰጪዎች በሚወስኑት ውሳኔ መደንገጥ አያስፈልግም የሚሉት ደምስ ምክንያታቸውንም ሲያስረዱ፣ አሜሪካ በአብዛኛው ለኢትዮጵያ የምታደርገው ድጋፍ ሰብዓዊ እርዳታን በተመለከት መሆኑን በማስረዳት ነው። ይህም ከ800 ሺሕ በላይ ለሚሆኑ የውጭ አገራት ስደተኞች የሚውል መሆኑን የሚያነሱት ባለሙያው፣ ይህ የሚያሳየው የሚደረገው ድጋፍ በኢትዮጵያ ኢኮኖሚ ላይ የሚጨምረው ነገር የጎላ አለመሆኑን ነው።
በየትኛውም የዓለማችን ክፍል ላይ ለሚከሰት የኢኮኖሚ ችግር በዋነኛነት ፖለቲካው የሚጫወተው ሚና ከፍተኛ እንደሆነ ባለሙያዎች ይገልጻሉ።

በአገራችንም የፖለቲካው መበላሸት ኢኮኖሚው ላይ ጣጣ ይዞበት እንደመጣ የሚናገሩት አጥላው፣ ፖለቲካው የሚዘወርበት የዘር፣ የትስስርና የትውውቅ አካሄድን መበጣጠስ ካልተቻለ ከጦርነቱም በኋላም ኢኮኖሚውን በኹለት እግሩ ለማቆም የሚደረገው ጉዞ ረጅም እና በሕመም የተሞላ ይሆናል ሲሉ ሥጋታቸውን ያጋራሉ።

በጦርነት ምክንያት ኢኮኖሚው ላይ የሚከሰተውን ጫና ለመቀንስ ከዚህ በፊት አገራት የተለያዩ መፍትሔዎችን እንደወሰዱ የተጠቆመ ሲሆን፣ ከነዚህም መካከል ግብር መጨመር የመጀመሪያው አማራጭ መንገድ እንደሆነ ይነሳል። ሌላኛው ደግሞ በሰለጠኑ አገራት የሚዘወተር እንደሆነ የሚጠቀሰው የጦርነት ቦንድ መሸጥ መሆኑን ባለሙያው ያነሳሉ። እንደ ኢትዮጵያ ባሉ አገራት ግን እነዚህ ተግባራት ብዙ ያልተለመዱ መሆናቸውን የሚገልጹት ባለሙያው፣ ከዚያ ይልቅ እንደ በፊቱ ኹሉ ጦርነቱ ሕዝቡ ካመነበት በአብዛኛው ገንዘቡ ከሕዝብ የሚገኝ ይሆናል።

ጦርነት ለአጭር ጊዜ የሚካሄድ ከሆነ ለጦርነቱ ግብዓትን በሚያቀርቡ ሥራዎች ላይ መነቃቃትን የሚፈጥር እንደሚሆን ዕሙን መሆኑን የሚያስረዱት ደምስ፣ ነገር ግን ጦርነቱ ለረጅም ጊዜ የሚዘልቅ አይነት ከሆነ አገሪቱ ያላትን ሀብት አሟጣ እንድትጠቀም የሚያስገድድ በመሆኑ አገርን ችግር ውስጥ የሚጥል ጉዳይ ሊሆን እንደሚችል ይገልጻሉ።

የጦርነቱ መምጣት ሲጠበቅ የነበረ ጉዳይ ከመሆኑ አንጻር በመከላከያ በኩል ቀደም ተብሎ ዝግጅት እንደነበር የሚገምቱት እኚህ ደምስ፣ የተለየው ነገር የመጣበት አቅጣጫ ነው ይላሉ። ይህም ማለት ከሕዳሴ ግድብ ጋር በተያያዘ ግጭት ሊኖር ይችላል በሚል ሥጋት ዝግጅት ሲደረግ ከመቆየቱ አንጻር፣ አቅጣጫውን ቀይሮ ለመጣው ጦርነት በመከላከያ በኩል አዲስ የሆነ የወጪ ጉዳይ ይኖራል ብለው እንደማያስቡ ጨምረው ያነሳሉ።

በጦርነት ጊዜም ሆነ በኋላ የዋጋ ግሽበት ሊኖር መቻሉ የሚጠበቅ ጉዳይ ነው የሚሉት ደምስ፣ መንግሥት መጠንቀቅ የሚገባው በጦርነቱ ምክንያት እየተጠቀመበት ያለውን ሀብት እና ምርት መተካት የማይችል ከሆነ ነው ይላሉ። ይህን ማድረግ አለመቻል ከጦርነቱ በኋላ ለሚከሰት ከአሁኑ ለባሰ የዋጋ ግሽበት ተመቻችቶ የመጠበቅ ያህል መሆኑንም ይገልጻሉ።

ከዚህ በላይ ግን መፍራት ያለብን ጦርነቱ ካመጣው ክስትተ ጋር በተያያዘ በገበያው እና ኢኮኖሚው ላይ የሚከሰት ግሽበት ጤናማ ሆኖ እንዳይቀጥል የሚያደርጉ አሻጥረኞች የሚፈጥሩትን ነገር ነው። ይህ አደገኝነቱ ከጦርነቱም በላይ አገር እና ሕዝብን በከፍተኛ ሁኔታ ሊጎዳ ስለሚችል ጥንቃቄ ሊደረግበት እንደሚገባ ባለሙያዎቹ ያሳስባሉ።


ቅጽ 3 ቁጥር 148 ነሐሴ 29 2013

Comments: 0

Your email address will not be published. Required fields are marked with *

This site is protected by wp-copyrightpro.com