የእለት ዜና

የቡራዩና አዲስ አበባ ወጣቶችን ግጭት ለማስቆም የተደረጉ ውይይቶች ውጤታማነት

በኢትዮጵያ ካለፉት 3 ዓመታት ወዲህ በርካታ ጥቃቶችና ግጭቶች በተለያዩ አካባቢዎች ተከስተዋል። ከነዚህ መካከል እንደመጀመሪያ የሚቆጠረውና በብዙዎች ዘንድ ተስፋ ያስቆረጠው ክስተት የተፈጠረው እዚሁ ዋና መዲናዋ አዲስ አበባ ውስጥ ነው። በስደት የነበሩ የፖለቲካ ፓርቲ አመራሮችን ለመቀበል በነበረ ሒደት፣ “ቀለም አንቀባለን! አትቀቡም!” በሚል የቡራዩና የአዲስ አበባ ወጣቶች የተጋጩበት ክስተት ለብዙዎች ሕይወት መጥፋት፣ ለበርካቶች መታሰርና እስካሁን ድረስ ለዘለቀ መፈናቀል የዳረገ ነበር። ግጭቱ ወዲያው ዕልባት ባለማግኘቱ የኹለቱ አካባቢ ወጣቶች በኃይማኖታዊ ክብረ በዓላት ላይ በየዓመቱ ሲሳተፉ ለተመሳሳይ ግጭቶች ይዳረጉ ነበር።

ይህን ግጭት በዘላቂነት ለማስቆምና ተሳታፊ የነበሩትን ለማቀራረብ መርሃ-ግብር ቀርጸው ሲንቀሳቀሱ ከነበሩት መካከል የሠላምና ልማት ማዕከል አንዱ ነው። የማዕከሉ የፕሮግራም ሥራ አሥኪያጅ የሆኑትን ወንድይፍራው ግርማቸው አግኝተን ስለአጠቃላይ የዕርቅ ሒደቱ ጠይቀናቸዋል። ኢንተርናሽናል ሪፐብሊካን ኢንስቲትዩት(IRI) ባደረገው ድጋፍ መሠረት የተካሄደውን የውይይት ሒደት ዕሳቸው በዋናነት እንደማስተባበራቸው ከመነሻው ጀምሮ የነበረውን ለውጥ ያውቁታል።

ከ32 ዓመት በፊት የተመሠረተው ይህ ማዕከል ለግጭት ተጋላጭ የሆኑ ቦታዎች ላይ ትኩረት በማድረግ የተለያዩ የሠላም ግንባታ ሥራዎችን ሲያከናውን እንደቆየ ይናገራሉ። አገር በቀል ዕውቀቶችን በመጠቀም በተለይ ከከተማ ውጭ ባሉ ወሰንተኛ አካባቢዎች ይበልጥ እንደሚሠሩ የተናገሩት ወንድይፍራው፣ በኹሉም ክልሎች ሊባል በሚችል መልኩ ሠላም ለማምጣት መርሃ-ግብር ተቀርፆ ሲሠራ ቆይቷል።

የቡራዩና የአዲስ አበባ ወጣቶች መካከል የተከሰተውን አለመግባባት ለማርገብ በሠላም ሚኒስቴር የተጀመረውን ሒደት በዘላቂነት እንድናስቀጥል በቀረበልን ጥሪ መሠረት ሥራውን ጀምረናል ያሉት እኚህ የሒደቱ የበላይ አስተባባሪ፣ ከተለያዩ የሲቪክ ማኅበረሰብ ተቋማት ጋር በመሆን ሥራቸውን በተለያዩ መንገዶች እያከናወኑ ይገኛሉ። የአቅም ግንባታና የውይይት ተግባሮች ላይ የሚያተኩሩ ሲሆን፣ ወጣቶች ለሠላም ያላቸውን ሚና ከፍ የሚያደርጉ የተለያዩ መርሃ-ግብሮችን በማዘጋጀት በመካከላቸው የትብብር መንፈስ እንዲፈጠር እንደሚሠሩም ይናገራሉ።

የቡራዩ ወጣቶችና የአዲስ አበባ በተለይ የኮልፌ ክፍለ ከተማ የወረዳ 10 ወጣቶችን ለማወያየት 12 መድረኮች መዘጋጀታቸውን የሚናገሩት ወንድይፍራው፣ በጅምሩ ወቅት ከተጠበቀው በላይ ውጤታማ እንደነበሩ ይናገራሉ። ወጣቶቹ ሒደቱ ሲጀመር በጥርጣሬ ያዩ ነበር ያሉን ሲሆን፣ እያደር ዓላማችንን ሲረዱ ጥርጣሬያቸው ተወግዶ እርስበርስ የነበራቸውም አለመተማመን መቅረቱን ይጠቅሳሉ።

በቅድሚያ የተደረገው ኹለቱን ወገኖች የሚወክሉ በበጎ አድራጎት የተመለመሉ አስተባባሪዎችን ሥልጠና መስጠት ነበር። እነዚህ ወጣቶች ያለማንም ጣልቃገብነት ውይይትን የማመቻቸት ክህሎት እንዲያዳብሩ ከተደረገ በኋላ፣ ራሳቸው የሚመሩት የዕርቅ መርሃ-ግብር እንዲሆን ተደርጓል። የሠላምና ልማት ማዕከል ነገሮች ፈር አንዳይለቁ ከመከታተልና ከኋላ ሆኖ በሐሳብም ሆነ በፋይናንስ ከማገዝ ውጭ ጣልቃ ሳይገባ ሒደቱ በሠላም እንደተጠናቀቀ የመርሃ-ግብሩ ሥራ አስኪያጅ ይናገራሉ። የመንግሥት አካላት እያንዳንዱን ሒደት እንዲያውቁትና የወጣቶቹን አመለካከት እንዲረዱ ከመሳተፍና እንዲታዘቡ ከማድረግ ውጭ በቀጥታ እንዳይገቡበት መደረጉንም ከነምክንያቱ ይናገራሉ። ወጣቶቹ ነፃነት ተሰምቷቸው እንደልብ እውነቱን ተነጋግረው መፍትሔ የሚሉትንም እንዲናገሩ መድረክ ማመቻቸት ስለሆነ ዓላማው፣ ያንን የሚያስተጓጉል ማንኛውም ነገር እንዳይፈጠር ከፍተኛ ጥንቃቄ ሲደረግ መቆየቱንም ያስታውሳሉ።

መጀመሪያ ተከናውኖ ከነበረው የአሥተባባሪዎች መረጣ በኋላ፣ እነዛው የሠለጠኑ ተወካዮች ማዕከሉ ባዘጋጃቸው መሥፈርቶች መሠረት ለመጀመሪያው ዙር ውይይት ተሳታፊ የሚሆኑትን ራሳቸው መልምለዋል። ፆታን መሠረት ያደረገና ይመለከታቸዋል የተባሉ ወጣቶች ላይ እንዲተኮር በተዘጋጀው መሥፈርት መሠረት የኹለቱም ወገን ተወካዮች አርባ አርባ ወጣቶችን ከየአካባቢያቸው በመምረጥ ዝርዝሩን አሳውቀው ለውይይቱ ጋብዘዋቸዋል። በዚህ ሒደት ወጣቶቹ ሳይቀላቀሉ ለየብቻቸው እንደልባቸው ተወያይተው ችግርነው ብለው ያሉትንና ለግጭት ዳርጎናል ብለው የሚያስቡትን ምክንያት አንስተው በመጀመሪያው ቀን ውይይት አምስት የችግር መንስዔ ያሉዋቸውን እንዲለዩ ተደርጓል።

የኹለቱም አካባቢ ወጣቶች በየፊናቸው በኹለት ውይይቶች ላይ ችግር ያሉትን ይዘው ከቀረቡ በኋላ በሦስተኛው ውይይት እንዲገናኙ ተደርጓል። የመጀመሪያዎቹ ውይይቶች በአቅራቢያቸው ለእነሱ በሚመቻቸው ቦታ የተደረገ ሲሆን፣ የጋራ ውይይቱ ግን ለኹሉም ማዕከላዊ በሆነ ቦታ ተደርጓል። የጦር ኃይሎች መኮንኖች ክበብ ለተያዘው ዓላማ ተመራጭ ስለነበር የኹለቱ አካባቢ ወጣቶች የተገናኙት እዚያ እንደሆነ ወንድይፍራው ይናገራሉ።

በነበረው የጋራ ውይይት ወጣቶቹ በቀጥታ ወደ ጉዳዩ እንዳይገቡ ተደርጓል። ይህ የሆነው እነሱን የበለጠ ለማስተዋወቅ፣ ለማቀራረብና እነሱና እኛ የሚለው አስተሳሰብ ተወግዶ መሰናክል የነበረ ሰው ሠራሽ ልዩነት እንዲወገድና እንዲላመዱ ነበር። ወጣቶቹ በተለያዩ በጨዋታ መልክ የቀረቡ አሳታፊ መርሃ-ግብሮች ላይ እንዲሳተፉ ከተደረገ በኋላ፣ መቀራረባቸው ታይቶ ወደ ቀጣዩ ዋና ጭብጥ እንዲገቡ መደረጉን የማዕከሉ አስተባባሪ ይናገራሉ።

ወጣቶቹ ለየብቻ በተወያዩበት መድረክ ይዘዋቸው የነበሩትና የመረጧቸውን ዋና ዋና 5 ጉዳዮችን በንግግር እንዲያቀርቡና ሌላኛው ወገን እንዲሰማቸው ተደርጎ ነበር። ማብራሪያ የተፈለገባቸው ላይ አቅራቢዎቹ ዝርዝር ሐሳብ እያቀረቡ በመነጋገር ሐሳባቸውን በተነጋገሩበት መንፈስ እንዲያቀርቡ ከተደረገ በኋላ፣ በጋራ ከቀረቡት ጭብጦች የተደጋገሙትን ለይተው የጋራቸውን እንዲያወጡ ተደርጓል። የጋራ ነጥቦቹንም ይዘው እንደልባቸው እንዲነጋገሩ መልሰው በተለያየ ቦታ እንዲወያዩባቸው ተደርጓል።

በዚህ ሒደት የተነሱት ሐሳቦች ምስጢራዊነታቸው እንዲጠበቅ ስምምነት ስለነበረ ዝርዝር ጉዳዮችን አንስቶ ምክንያት ባሉት ላይ መነጋገር አይቻልም ያሉን ወንድይፍራው፣ አብዛኞቹ ከአመለካከት ጋር የተገናኙ ጉዳዮች እንደሆኑ ተናግረዋል። በተነሱት ጉዳዮች ላይ የሐሳብ ፍጭት ከተደረገ በኋላ፣ “እኛ በእንሱ ቦታ ሆነን ቢሆን ምን ይሰማን ነበር?” ብለው እንዲያስቡ፣ እንዲሁም እነሱ በእኛ ቦታ ቢሆኑስ ኑሮ እያሉ አንዳቸው ስለሌላቸው እንዲያስቡ ተደርጓል።

እርስበርስ እንዲተሳሰቡ ብቻ ሳይሆን መፍትሔ የሚሉትን፣ እንዲደረግ የሚፈልጉትንም ሆነ እንዲደረግላቸው የሚፈለጉትን አርቅቀው ለጋራ ውይይቱ እንዲያቀርቡ ተደርጓል። ይህ ሒደት ጊዜን የሚወስድ እንደመሆኑ በዋና በዋና ጉዳዮች ላይ ለማተኮር ተገደው እንደነበር የሚያስታውሱት አስተባባሪው፣ በተያዙት ጭብጦች ላይ በቂ ውይይት ከተደረገ በኋላ እንደአካባቢ ተወካይነታቸው መቀየር ያለባቸውን ለመቀየር ቃል ተገባብተው፣ ይበልጥም ተግባብተው እንደተለያዩ ተናግረዋል። በዚህ መልክ የተለያዩ ወጣቶችን በማሳተፍ 8 የተናጥል ውይይቶችንና 4 የጋራ መድረኮችን ማዘጋጀት መቻሉን ይናገራሉ።

የውይይቱ ውጤታማነትን ለክቶ ይህን ያህል ነው ማለት እንደማይቻል የሚናገሩት ወንድይፍራው፣ ከተሳታፊዎቹ አንደበት እንደሰሙትም ሆነ በዓይናቸው እንዳዩት በጠላትነት ይተያዩ የነበሩትን ወጣቶች አቀራርቧል። የጋራ ኮሚቴ አቋቁመው ቤት ማደስን በመሳሰሉ አገራዊ የልማት ሥራዎች በጋራ ለመሥራት እስከመጠራራት ደርሰዋል ያሉን ሲሆን፣ ይህ ብቻ በቂ ስላልሆነ እያንዳንዳቸው ቢያንስ 20 ሰዎችን መቀየር እንዳለባቸው መግባባት ላይ ስለተደረሰ፣ ጥቅሙንም ስላስተዋሉት በራሳቸው ተነሳሽነት እየተንቀሳቀሱ ነው ብለዋል።

የአመለካከት ለውጥ እንዲመጣ ውይይቶቹ ከማገዛቸውም በላይ፣ ወጣቶቹ ተዋውቀው በጋራ እንዲሠሩና በዘላቂነት በመካከላቸው ግጭት እንዳይፈጠር ረድቷል ብለውናል። ይህ ሒደት በሌሎች አካባቢዎችም መቀጠል እንዳለበት ተሳታፊዎቹ ጭምር የሚጋሩት ሐሳብ ነው ያሉን አስተባባሪው፣ ማዕከሉም ለገጣፎ፣ ገላንና አቃቂ ቃሊቲን በመሳሰሉ በሌሎች የአዲስ አበባ ዙሪያዎች ባሉ አካባቢዎችም ከተለያዩ ግብረሰናይ ተቋማት ጋር በመሆን የጀመረውን ሥራ አጠናክሮ እንደሚቀጥል ነግረውናል። ከአይ አር አይ(IRI) ጋርም አብረው እየሠሩ እንደሆነና፣ በቀጣይነትም እገዛቸው ጠቃሚ ስለሆነ አብረዋቸው ለመሥራት ፍላጎታቸውን ስለገለጹ ደስተኛ መሆናቸውን ነግረውናል። ተከታታይነት ያላቸውን ሥራዎችንም ለወደፊት አብረውን እንዲሠሩም እንፈልጋለን ብለውናል።

በውይይት ሒደቱ ብዙ ጠቃሚ ነገሮች የተገኙትን ያህል ችግሮችም ተከስተው እንደነበር ወንድይፍራው ተናግረዋል። ከተሳታፊዎች ምልመላ ጀምሮ፣ ጥቅም በመፈለግ ደጋግሞ ለመሳተፍ መሞከር አንዱ እክል የነበረ ሲሆን፣ የሴቶች ተሳትፎም በሚፈለገው መልኩ ያልሆነበት አጋጣሚም እንደነበር አስታውሰዋል። እንዲሳተፉ የሚፈለጉ ወጣቶችን በመተው፣ በኮታ እነእገሌም ይድረሳቸው በሚል ዕሳቤ ይሠራ የነበረው እንዲቀር ለማድረግ አስቸጋሪ የነበረ ቢሆንም፣ ቀስበቀስ መግባባት መቻሉን ይጠቅሳሉ። ዋናው ችግር ሆኖ የነበረው፣ በአንድ ቀን ውይይት ግጭት ኹሉ ቀርቶ ውጤት ይገኛል የሚለው አስተሳስብ ነበር ብለዋል። በእንዲህ አይነት አመለካከት የተወሰኑ ወጣቶች ገና ሒደቱ ሲጀመር ሌላውን በማነሳሰት እክል ለመፍጠርና ተቀባይነቱን ለማሳጣት ሲጥሩ ነበር። ይህን የመሰለውን ችግር በብልሃት ትዕግስት እንዲኖራቸው በማድረግ ያለምንም እንቅፋት እንዲፈታ ማድረግ መቻሉንም ተናግረዋል።

ደፍሮ በማውራትና በመነጋገር ነው ለውጥ ማምጣት የሚቻለው ብለው የሚያምኑት የማዕከሉ የመርሃ ግብሮች ሥራ አሥኪያጅ፣ በውይይቶቹ ወቅት ያልተገራና ይበልጥ ወጣቶችን ለግጭት ሊጋብዝ የሚችል ንግግር የሚናገሩ እንደነበሩ አውስተዋል። እነዚህ ጥቂት ወጣቶች የብዙኃኑን ስሜት ሊቀሰቅስ የሚችል ስሜታዊ ንግግር በማድረጋቸው አካሄዱ ሊበላሽ ይችል እንደነበረ በማስታወስ፣ ነገሩ ከማዕከሉ አቅም በላይ ስላልነበረ ከነበረ ልምድ በመነሳት ተቆጣጥሮ ወደተፈለገው የመተሳሰብና የመግባባት መንፈስ ሒደቱ እንዲመለስ ማድረግ መቻሉን ተናግረዋል።


ቅጽ 3 ቁጥር 148 ነሐሴ 29 2013

Comments: 0

Your email address will not be published. Required fields are marked with *

error: Content is protected !!