የእለት ዜና

የኩላሊት ህሙማን ዕጣ ፋንታ

Views: 171

ህይወት ተሾመ ይባላሉ። የነርስ ባለሙያ ምሩቅ ሲሆኑ፤ በዚሁ የስራ ዘርፍ በመሰማራት በአንድም በሌላም ምክንያት ችግር ደርሶባቸው ወደ ጤና ጣቢያ የሚያቀኑ ዜጎችን በቀናነት በማገልገል ኃላፊነታቸውን ሲወጡ ኑረዋል። ህይወት ተሾመ የሁለት ልጆች እናት ሲሆኑ፤ ቤተሰባቸውን የሚያስተዳድሩት በዚሁ ሙያቸው ተቀጥረው በሚያገኙት ወርሃዊ ደመወዝ ነው።

ህይወት ተሾመ ጊዜያቸውን የሚያሳልፉት የራሳቸውን ጥቅም ከማስቀደም ይልቅ ለሌሎች ደፋ ቀና በማለት ነው። ከሙያቸው በተጨማሪ የቤተሰብ ኃላፊነትን የተሸከሙት ህይወት፤ ህጻናት ልጆቻቸውና ጡረተኛ አባታቸው የመኖር ተስፋቸውን የጣሉባቸው በመሆናቸው ለቤተሰባቸው ከመታተር በዘለለ ለራሳቸው ጊዜ ሰጥተው አያቁም።

በስራቸው ደከመኝ ሰለቸኝ ማለት በህሊናቸው ዘንድ ተቀባይነት የለውም። የቤተሰባቸውንና የህመምተኞችን ችግር ለማስወገድ ሁሌም ከወፎቹ ዜማ ጋር ሁሌም ማልደው መነሳቱንና ወደ ስራ ቦታ መገስገሱን ተያይዘዉታል። ይህ በእንዲህ እንዳለ፣ ከእለታት በአንደኛው ቀን የወሊድ አገልግሎት ለማግት ወደ የጤና ተቋም ጎራ ባሉበት ወቅት ድንገታዊ የደም ግፊት ተከሰተባቸው።

በሐኪም እርዳታ ለጊዜው ፋታ በማግኘት ልጃቸዉን አቅፈው ወደ ቤታቸው ቢመለሱም፣ በምርመራው ወቅት ኩላሊታቸው ችግር እንደለበት ነበር የተነገራቸው። ሆኖም ግን ቤተሰባቸውን ከማስተዳደርና ለስራቸው ከመታተር በዘለለ የኩለሊታቸውን ጉዳይ ጊዜ ሰጥተው የህክምና ክትትል አላደረጉም ነበር።

ከቀን ወደ ቀን ያልለመዱት የተለየ የህመም ስሜት እየተሰማቸው ሲመጣ ወደ ጤና ተቋም ጎራ ለማለት ተገደዱ። ምርመራውን ሲያካሂዱ የተፈጠረው ነገር አስደንጋጭ ነበር። ኩላሊታቸው ከፍተኛ ችግር ላይ እንደሆነ ከዶክተሮች መርዶ ደረሳቸው።
ህይወት ተሾመ በታላቅ ፍርሃትና ድንጋጤ ላይ ወደቁ፤ ከመታመማቸው ይልቅ ተስፋ አድርጎ ሲወጡና ሲገቡ በስስት የሚያያቸው ቤተሰባቸው የአኗኗር ሁኔታ የማይፈታ እንቆቅልሽ መስሎ ታያቸው። አሁን ላይ ወደ ስራ መገስገሱ፤ ሰው መርዳቱ በኩላሊት ህመም ተይዞ ጣሪያ እየቆጠሩ አልጋ ላይ ዉሎ ማደር ተቀይሯል።

ህይወት ኩላሊታቸው ችግር ላይ ነው ከተባለ ድፍን አራት ዓመትን ያስቆጠሩ ሲሆን፤ የዲያሊሲስ ክትትል ማደረግ ከጀመሩ ዘጠኝ ወራትን አስቆጥረዋል። በሃኪም ትዕዛዝ መሰረት በሳምንት ሶስት ጊዜ የኩላሊት እጥበት እንደሚያስፈልጋቸው ተነግሯቸው እስካሁን በመንግስት ጤና ተቋም በኩል ህክምናውን እያገኙ ቢቆዩም፤ አሁን ላይ መንግስት ወደ ሌሎች ወቅታዊ ተላላፊ በሽታዎች ፊቱን በማዞሩ አገልግሎቱን ለመስጠት አቅም በማነሱ ወደ ግል የህክምና ተቋማት ሂደው እንዲታከሙ አድርጓቸዋል።
ህይወት ተሾመ ኩላሊታቸውን በሳምንት ሶስት ጊዜ እንዲታጠብ የታዘዙ ሲሆን፤ በዚህ ወቅት በግል የጤና ተቋማት እየታከሙ ይገኛሉ። በየእለቱ እየናረ ካለው የመድሃኒት የዋጋ ጭማሪ አንፃር ለመታከም ፈተና እንደሆነባቸው ይናገራሉ።

በመንግስት ሆስፒታል ለህክምናው ተመጣጣኝ ዋጋ እንዳለ የተገነዘቡት ህይወት ተሾመ ወደ ተቋማቱ መቀላቀል ቢሹም ወረፋ ማግኘት አልቻሉም።
በግል ሆስፒታሎች ለመታከም ደግሞ ነገሮች በተቃራኒው ነው የሆኑባቸው። ይኸውም ለአንድ ዲያሊሲስ 3ሺህ ብር የሚከፍሉ ሲሆን፤ በሳምንት ውስጥ ሶስት ጊዜ ለመታከም 9ሺህ ብር ያስፈልጋቸዋል።
በአንድ ወር ውስጥ 36ሺህ ብር ለህክምና የሚያወጡ ሲሆን፤ ይህም በዓመት ውስጥ አራት መቶ ሰላሳ ሁለት ሺህ ብር ያስፈልጋቸዋል። ህይወት ነገሮች በእንቅርት ላይ ጆሮ ደግፍ እየሆኑባቸው ይገኛሉ። ለዲያሊሲስ ህክምና ከሚያወጡት ወጭ በተጨማሪ የሚጠበቅባቸው ሌላ ወጭም ሳይኖር አልቀረም።

የደም ማነስ ስላለባቸውና በዲያሌሲስ ህክመናው ወቅት ደማቸውን ለማቅጠን የሚያስችል መድሃኒት ያስፈልጋቸዋል። መድሃኒቱ በጳውሎስ ሆስፒታል 130 ብር የሚሸጥ ቢሆንም በቂ አቅርቦት ሰለሌለ በግል ክልኒኮች የሚገዙ ሲሆን፤አሁን ላይ ዋጋው በመጨመሩ ምክንያት ለመግዛት ተቸግረዋል።

መድሃኒቱ በግል ክሊኒኮች ዋጋው 800 ብር የነበረ ሲሆን፤ አሁን ላይ ወደ 1ሺህ 200 ብር ከፍ ብሎባቸዋል።

የዲያሊሲስ ህክምናቸውን የሚከታተሉት በጎ አድራጊና አንዳንድ ቤተሰብ በሚያደርግላቸው ድጋፍ ነው። አሁን ላይ ድጋፉ እየቀዘቀዘ የህክምናው ወጭ እየጨመረ በመምጣቱ በሳምንት አንድ ጊዜ ኩላሊታቸውን ለመታጠብ የማይችሉበት ደረጃ ላይ ደርሰዋል።
የኑሮ ውድነቱን ተከትሎ ይህን ከባድ ወጭ ያለምንም ገቢ መሸፈን እንዳለባቸው ሲያስቡ የመኖር ትርጉሙ ይደበላለቅባቸዋል።

የመኖር ተስፋቸው ከሌሎች ሰዎች እጅ በሚገኘው ብር የተገደበ ይመስላቸዉና ተስፋ ይቆርጣሉ። በተለይም ወደ ኋላ መለስ ብለው የነበሩበትን ሙያና ተስፋ ያደረጋቸውን ቤተሰብ ሲያስቡ ይበሳጫሉ።
ጤነኛ ሆነው እየሰሩ በነበረበት ወቅት እንኳን ኑሮን ለመምራት የሚፈትነው የኑሮ ውድነት ያለምንም ገቢ እንዴት እየገፉት እንደሆነ ሲያስቡ ካሁን ያደረሳቸውን ማህበረሰብ ለማመስገን ቃል ያጥራቸዋል።
ከፈጣሪ በታች የድርሻውን እየተወጣ እስካሁን የረዳቸውን መንግስት፤ ቤተሰብና በጎ አድራጊዎችን ሲያስቡ ደግሞ የመኖር ተስፋቸው ይለመልማል።

ህይወት ተሾመ ትብብር አድራጊዎች ሁሉ የተለመደውን ድርጊታቸውን እንዲለግሷቸውና የሚመለከተው አካል የግል ጤና ተቋማት የሚያደርጉትን የዋጋ ንረት ማስተካካያ ይሰጥበት ዘንድ ከአዲስ ማለዳ ጋር በነበራቸው ቆይታ ገልጸዋል።
በአገራችን የኩላሊት ህመም ከቀን ወደ ቀን እየጨመረ መምጣቱ በምሁራን ዘንድ ይነገራል። በተለይም የኮሮና ወረርሽኝ መከሰቱን ተከትሎ የሰዎች አትኩሮት ወረርሽኙን ወደ መከላከል በማጋደሉ በአሁኑ ወቅት ውስጥ ለውስጥ በሽታው ዜጎችን እያጠቃቸው መሆኑን ባለሙያዎች በአጽንኦት ሲናገሩ ይደመጣሉ።

ለእያንዳንዱ ህመም መንስኤ እንደሌለው ሁሉ ለኩላሊት ህመም መከሰት እንደምክንያት የሚመዘዙ ነገሮችም አልጠፉም። ከእነዚህም መካከል ለብዙ ጊዜ ያለ ምንም እንቅስቃሴ ታጥፎ መቀመጥ ከዋና ዋናዎቹ መንስኤዎች አንዱ እንደሆነ ይነገራል።
በአገራችን የዋጋ ንረት በአንድም በሌላም ምክንያት እየጨመረ በመምጣቱ ዜጎች ለመኖር እየተፈተኑ መሆኑን ሲያወሱ መስማት ሰንበትበት በማለቱ አሁን ላይ እየተለመደ መጥቷል።
ከዚህም አንጻር ወደህክምና ተቋዋማት ሂዶ በቀላሉ መታከም አቀበት በመሆኑ፤ ዜጎች በአቅም ማነስ ምክንያት ለኩላሊት ህመም ተዳርገው ይገኛሉ።

ጤነኞች ሆነው እየሰሩ ገቢ የሚያሰባስቡ ዜጎችን እንኳን እየተፈታተነ ያለው ይህ የኑሮ ውድነት፣ ከምንም በላይ አልጋ ላይ በሚዉሉ የኩላሊት ህመምተኞች ላይ የእንቅርት ላይ ከጆሮ ደግፍ እየሆነ መምጣቱ ይነገራል።
የግል ኪሊኒኮች የሚያደርጉት ከልክ ያለፈ የመድኃኒት የዋጋ ንረት፣ ሰርተው በመግባት ፈንታ በኩላሊት ህመም የተዳረጉ ሰዎች ህይወታቸው ላይ ችግር እያስከተለባቸው መሆኑን ሲያወሱ ይሰማሉ።

አዲስ ማለዳ ካነጋገረቻቸው የኩላሊት ህሙማን መካከል ሁሴን አህመድ የተባሉት ግለሰብ የዲያሊሲስ ህክምና ማድረግ ከጀመሩ ሰባት አመታትን ያስቆጠሩ ሲሆን፤ አስቤዛን ለማሟላት ካለው የዋጋ ንረት በተጨማሪ በግል የጤና ተቋማት የሚደረገው የመድኃኒት የዋጋ ንረት ከአቅማቸው በላይ እንደሆነ ገልጸዋል።

ሁሴን እነደተናገሩት ከሆነ መድሃኒቶች በቀላሉ አይገኙም በሚል ሰበብ 300 ብር ይገዙት የነበረውን መድኃኒት አሁን ላይ 1ሺህ 500 ብር እንደሚገዙ ገልጸዋል። አክለውም መንግስት የመድሃኒት ዋጋ ላይ ጭማሪ የሚያደርጉ አካላትን በመቆጣጣር እርምጃ ሊወስድ ይገባል በማለት ነው የተናገሩት።

ሌላኛው የዲያሊሲስ ክትትል የሚያደርጉት አበባው ጌታቸው የተባሉት ግለሰብ የግል ሆስፒታሎች “ውድድር ነው የያዙት አንዱ ሲጨምር ሌላኛውም ይጨምራል፤ የኩላሊት ህመምተኛ ብር ከየትም ሊያመጣ አይችልም። ግን ካልታጠበ በስተቀር መዳን አይችልምና ከየትም ያመጣል በሚል ምክንያት ነው ብር የሚጨምሩት’’ ሲሉ ነው የገለጹት።

በዘውዲቱ መታሰቢያ ሆስፒታል የኩላሊት ህመምተኞች እጥበት የሚሰጠው የበጎ አድራጎት ድርጅትም ጉዳዩን በማስመልከት ባሳለፍነው ነሐሴ 25/2013 በማሮት ሆቴል በሰጠው መግለጫ አዲስ ማለዳ መታደም ችላለች።
የኩላሊት ህመምተኞች በጎ አድራጎት ድርጀት ዋና ስራ አስኪያጅ ሰለሞን አሰፋ እንደገለጹት ከሆነ፤ ከአንዱ ህክምና ተቋም የመድሃኒት ዋጋ በመነሳት ሌላኛው የህክምና ተቋም የሚያደርገዉ ሰው ሰራሽ የዋጋ ንረት የዲያሊሲስ አገልግሎት ለማግኘት ህሙማኑ ላይ ችግር እያስከተለ መሆኑን አብራርተዋል።

ሰለሞን አያይዘዉም በግል ሆስፒታሎች ዘንድ የአንድ ዲያሊሲስ ዋጋ 3ሺህ ብር መሆኑን ተከተሎ በሳምንት ሶስት ጊዜ መታከም ያለባቸው ህመምተኞች 9ሺህ ብር፤ እንዲሁም በወር ወስጥ 36ሺህ ብር ለማዉጣት መገደዱን ነው የገለጹት።
ችግሩን ለመቅረፍም ከጤና ሚኒስቴር ጋር ስብስባ ያደረጉ ሲሆን፤ የአንድ ዲያሊሲስ ዋጋን ከ3ሺህ ብር ወደ 500 ብር ዝቅ በማድረግ ለ400 ህሙማኖች መፍትሄ የሚሰጥ 100 ማሽኖችን ጤና ሚኒስቶሩ ሊገዛ የፈቀደ ቢሆንም፣ እስካሁን ባለመገዛቱ ህመምተኞቹን ከዋጋ ንረቱ ገፈት ቅምሻ መታደግ እንዳልተቻለ ነው አዲስ ማለዳ ያረጋገጠችው።

በኮሮና ወረርሽኝ ምክንያት የተቋረጠው የኩላሊት ንቅለ ተከላ አገልግሎት እስካሁን አለመጀመሩ በህሙማኖች ላይ ተፅዕኖ እያሳደረ ነው ያሉት ዋና ስራ አስኪያጁ፤ አገልግሎቱ እንዲጀመርና ወደ ስራ ይገባ ዘንድ ጥያቄ ያቀረብንበት የኩላሊት ባንክ መንግስት አፋጣኝ ውሳኔ ሊሰጥበት ይገባል ብለዋል።

አክለውም ከ1ሺህ በላይ የኩላሊት ህክምና ክትትል የሚያደርጉ ህሙማን እንዳሉ የገለጹ ሲሆን፤ 110 ህሙማኖች የአዲስ አበባ ከንቲባ ጽ/ቤት በመንግስት ሆስፒታል ለአንድ አመት እንዲቆዩ ቢፈቅድም አሁን ላይ ፈቃዱ እየተጠናቀቀ በመሆኑ ለግል ህክምና አቅም የሌላቸው ህሙማኖቹ ትልቅ ጭንቀት ውስጥ ናቸው ብለዋል።

ስለሆነም የመድኃኒት የዋጋ ንረት የተጋረጠባቸው የኩላሊት ህሙማንን ለመታደግ መንግስት በግል ሆስፒታሎች አስፈላጊውን እርምጃ ይወስድ ዘንድ፤ ወቅታዊ ሁኔታን ግምት ውስጥ በማስገባት የዲያሊሲስ ነጻ አገልግሎቱን ያረዝምላቸው ዘንድ፣ እንዲሁም ጤና ሚኒስቴር ማሽኖቹን ይገዛላቸው ዘንድ አሳስበዋል።

አክለውም “መርዳት ከራስ ቀንሶ ለራስ ማዋጣት ነውና” ማንኛዉም የመንግስት ሰራተኛ ከወር ደመወዙ ኹለት ኹለት ብር በቋሚት እንዲለግሳቸው ጠይቀዋል።
አዲስ ማለዳ ጉዳዩን በማስመልከት ወደ ጤና ሚኒስቴር በተደጋጋሚ ስልክ ብትደውልም ምላሽ ለመስጠት ፍቃደኛ ስላልሆኑ ሀሳባቸውን ማካተት አልቻለችም።


ቅጽ 3 ቁጥር 148 ነሐሴ 29 2013

Comments: 0

Your email address will not be published. Required fields are marked with *

This site is protected by wp-copyrightpro.com