የእለት ዜና

የዲጂታል ዲፕሎማሲው ዘመቻ

አሁን ባለንበት ዓለም ላይ ኹሉም ነገር በሚባል ደረጃ ተለዋዋጭ ነው። በተለይ በቴክኖሎጂው ዘርፍ ላይ ያለው የመለዋወጥ ባህሪ አንዱን በአግባቡ ተረድተነው እና ተጠቅመንበት ሳንጨርስ የተሻሉና ሕይወትን ቀላል ማድረግ የሚያስችሉ ሌሎች ነገሮች ይፈበረካሉ። የተለዋዋጭነት ሒደቱ ደግሞ ይዞት የሚመጣው የራሱ የሆነ በጎም ሆነ መጥፎ ጎኖች አሉት። በነዚህ መለዋወጦች ምክንያት ቀድሞ ከነበሩበት አካሄድ እየወጡና እየተቀየሩ ካሉ ዘርፎች መካከል የዲፐሎማሲው መንገድ ተጠቃሽ ነው።

በአሁን ዘመን አገራት እንዳለፈው ዘመን በየአገራቱ በመደቧቸው አምባሳደሮችና ዲፕሎማቶች ላይ ብቻ ተማምነው ሥራቸውን የሚያከናውኑበት ጊዜ እያለፈ እንደሆነ ብዙዎች ይስማሙበታል። ለዚህም እንደምክንያት የሚነሳው ከቴክኖሎጂው መስፋፋት ጋር ተያይዞ የመጣው የዲጂታል ዲፕሎማሲ ነው።

”ዲጂታል ዲፕሎማሲ ማለት የዲጂታል ቴክኖሎጂዎችን ከዚህ በፊት ከነበረው የዲፕሎማሲ መንገድ በተለየ ለጥቅም ማዋል ማለት ነው” ሲሉ የሚያነሱት በዓባይ እና በተለያየ አገራዊ ጉዳዮች ላይ የዲጂታል መስኩን በመጠቀም እንቅስቃሴ በማድረግ የሚታወቁት ጋዜጠኛ ሰላም ሙሉጌታ ናቸው።

”ዲጂታል ቴክኖሎጂው በአሁን ሰዓት ሚናው እየጎላና እየበረታ የመጣ በመሆኑ በዲፕሎማሲው ላይ እንደ አንድ መጠቀሚያ መሣሪያ ሆኗል። ከመጠቀሚያነትም አልፎ የዲጂታል ዲፕሎማሲ ወደሚባል ዘርፍነትም ከፍ ብሏል። ዘርፍ ስንል ራሱን የቻለ ባሕሪ፣ ሙያተኛ፣ አካሄድ እና አሠራር ያለው ትልቅ የዲፐሎማሲ ክንፍ ነው” ሲሉ ያብራራሉ።

ከቴክኖሎጂው ማደግ እና መዘመን ጋር በተያያዘ የተዋንያን ለውጥም እየታየበት እንደሆነ ባለሙያው የሚያነሱት ጉዳይ ሲሆን፣ ከዚህ ቀደም ቴክኖሎጂዎቹ ባልነበሩበት ወቅት ፖሊሲ አውጪዎች የመንግሥት ባለሥልጣናት ወይም ዲፕሎማቶች በዲፕሎማሲው ላይ ትልቅ ተጽዕኖ ነበራቸው ብለዋል። ሆኖም፣ አሁን ላይ ባለው ነባራዊ ሁኔታ ምክንያት በዲፕሎማሲው ላይ የነሱ ብቻ ድምጽ ለውጥ ማምጣቱ እየቀነሰ ለመሄዱ እንደ ምክንያትነት የሚያነሱት፣ ከመንግሥት ውጪ ያሉ ተቋማትና ግለሰቦች ተጽዕኖ ፈጣሪነታቸው በጉልህ እየታየ ያለበት ጊዜ በመሆኑ እንደሆነ ባለሙያው ይገልጻሉ።

የዲጂታል ዲፕሎማሲ ጉዞ በኢትዮጵያ
በሌሎች የአለም አገራት የዲጂታል ዲፕሎማሲው በከፍተኛ ሁኔታ የተስፋፋና ሥር የያዘ ነው። ይህም የሆነው የበይነ መረብ መስፋፋት እንደ ኢትዮጵያ ካሉ ታዳጊ አገራት ይልቅ በስፋትም በርቀትም የተሻለ ሆኖ በመገኘቱ በተሻለ ሁኔታ እንዲጠቀሙበት እንዳስቻለ ባለሙያዎች ይናገራሉ።

በአገራችን ከዲጂታል አለም ጋር ትውውቁ ብዙ አመታትን ያላስቆጠረ ከመሆኑ ጋር በተያያዘ በዚህ ዘርፍ ላይ ከኋላ ጀማሪዎች ነን የሚሉት ባለሙያዎች፣ ይህ ለመሆኑ ደግሞ ከበይነ መረብ ግንኙነት ጋር ያለን ቁርኝት ከተደራሽነት እና ከጥራት ጋር በሚነሱ ችግሮች ምክንያት እንደሆነ ያነሳሉ።

”በኢትዮጵያ የዲጂታል ዲፕሎማሲው በስፋት የተስተዋለው በታላቁ ሕዳሴ ግድብ ጋር በተያያዘ ግብጾች በሚያነሱት የተሳሳተና የተዛባ መረጃ ምክንያት ነው” የሚሉት ደግሞ በዲጂታል ዲፕሎማሲው መስክ እንቅስቃሴ እያረጉ የሚገኙት ጋዜጠኛ እስሌማን አባይ ናቸው።
በታላቁ ሕዳሴ ግድብ ጉዳይ የተነሳሳው የዲጂታል ዲፐሎማሲ ነገር አሁን ላይ ከአገር ሉዓላዊነት ጋር በተገናኙ ሁነቶች፣ በየቀኑ በሚባል ደረጃ፣ በተለይም የማኅበራዊ ሚዲያ ዘርፍ ከሆነው ውስጥ ትዊተርን በመጠቀም ከፍተኛ እንቅስቃሴ ውስጥ እንደተገባ በማሳያነት ጋዜጠኛ እስሌማን ያነሳሉ።

በግድቡ ጉዳይ ወደ ዲጂታል ዘርፉ ይገባ እንጂ አሁን ላይ የበይነ መረብ ትስስር መፍጠኑ፣ የአጠቃቀሙ ቀላል መሆን፣ ወጪ ቆጣቢ በሆነ መንገድ መረጃን ማሰራጨት በመቻሉ ምክንያት አገራችንም ወደዚህ መንገድ በስፋት እንድትገባ ማስገደዱን የሚያነሱት ደግሞ ጋዜጠኛ ሰላም ሙሉጌታ ናቸው።

“በአገራችን ዲጂታል ዲፕሎማሲውን እንደ አንድ መንገድ በማድረግ የመጠቀም ሒደት ላይ ብዙ ይቀረን ነበር፣ ሆኖም ግን አሁን ላይ በዋና ዋና አገራዊ ጥቅሞቻችን ላይ የተጋረጡትን አደጋዎች ከመከላከል እና ጥቅሞቻችንን ከማስከበር አንጻር ይበልጥ በይነ መረብን ተከትለው የተፈጠሩ የማኅበራዊ መገናኛ አውታሮችን በአግባቡ መጠቀም አለመቻላችን ብዙ ችግር እያስከተለ በመሆኑ ወደዚህ መንገድ በስፋት እንድንገባ አስገድዷል” በማለት ሐሳባቸውን ያክላሉ።

የሌሎች አገራት ተሞክሮ
ከዲጂታል ተጽዕኖና እና እሱን በዲጂታል ዲፕሎማሲ መልሶ በማሸነፍ ረገድ በትልቁ የሚነሱት ቻይናና የቻይና መንግሥት ናቸው። ይህ ዲጂታል ተጽዕኖን መፍጠር የተጀመረው በቻይና ላይ ነበር በማለት የሚያስታውሱት ጋዜጠኛ እስሌማን አባይ፣ ”በመቀጠል የሶሪያው መሪ በሽር አል አሳድ ላይ ያተኮረ ነበር። አሁን ላይ ደግሞ በኢትዮጵያ እና በኢትዮጵያ መንግሥት ላይ ነው” በማለት ያነሳሉ።

“በዲጂታል ዲፕሎማሲው መስክ የተሳካ እንቅስቃሴ በማድረግ ረገድ ግን ቻይናን የሚስተካከል ለማግኘት አዳጋች ነው። በሽር አል አሳድን በተመለከተ ግን መንግሥትን መለወጥ ባይችሉም ያደረሱትን ውድመት ኹሉም የሚያውቀው ጉዳይ ሲሆን፣ አሁን ላይ ደግሞ አይናቸው ኢትዮጵያ ላይ ነው። ይህ ኹሉ የሚሆነው የዲጂታል መስኩን በመጠቀም ነው” ሲሉ እስሌማን ያስረዳሉ።

በተለይ የቻይናን ኹኔታን ሲያነሱም፣ “የቻይና ጉዳይ የተጀመረው በፈረንጆቹ 2012 ሲሆን፣ የመንግሥትን ተዓማኒነትን ለማሳጣት እና አምባገነን ነው ለማለት የተለያዩ የመገናኛ መንገዶችን ተጠቅመው ነበር። ይሁን እንጂ የቻይና መንግሥትም ይህን ውንጀላ እና ጣልቃ ገብነት ለመከላከል እንዲያስችለው በእያንዳንዱ ግዛት ውሰጥ የዲጂታል ሠራዊት በማቋቋም የተከፈተበትን የሐሰት ውንጀላ እና የተዛባ የመረጃ ውንጀላ በተቀናጀ እና በተናበበ ሁኔታ ለመመከት ችሏል። ይህ አይነቱ የመከላከል ሥራ የሚሠራው በአብዛኛው ከቻይና የተለያዩ ግዛቶች በተውጣጡ በጎ ፈቃደኞች ሲሆን፣ አሁን ላይ የበጎ ፈቃደኛ የዲጂታል ሠራዊት ቁጥር ከ20 ሚሊዮን በላይ ደርሷል።

እነዚህ በጎ ፈቃደኞች የሚያከናውኑት በአገራቸው ጉዳይ ላይ የተሳሳተ አልያም የውሸት መረጃ በሚቀርብ ጊዜ ትክክለኛው ምን እንደሆነ በማሳየት ላይ ያተኮረ ነው። ከነዚህ በጎ ፈቃደኛች በተጨማሪ በመንግሥት ተከፋይ የሆኑ ከኹለት ሚሊዮን በላይ የሆኑ የዲጂታል ዲፕሎማሲን በትምህርት ጭምር ያካበቱ ግለሰቦች ያሉበት ቡድን የዚህን ዘርፍ ሥራ በአግባቡ እየመራው ይገኛል” በማለት የቻይናን ተሞክሮ በዝርዝር ያስረዳሉ።

ከመንግስት ተቋማት ጋር ያለ ግንኙነት
በአሁን ሰዓት ከመንግሥት በኩል የዲጂታል ዲፕሎማሲውና ጥቅሙን በተመለከተ ትልቅ መረዳት እየመጣ ነው በማለት የሚያስረዱት ጋዜጠኛ ሰላም ሙሉጌታ፣ “ያጋጠመንን እና እያጋጠመን ያለው ችግር ግን በመንግሥት ብቻ የምንወጣው ባለመሆኑ መተጋገዝ የግድ ነው” ሲሉ አጽንዖት ይሰጣሉ።

በምክንያትም ሲያስረዱ “መንግሥት መድረስ የሚችልበት የራሱ መድረሻ አለው። መድረስ የማይችልባቸው፣ ቢደርስም እንኳን ለውጥ ማምጣት የማይችልባቸው ሜዳዎች አሉ። እነዛን ደግሞ መንግሥታዊ ባልሆነ አካል እንዲሸፈን ማድረግ ተገቢ ነው። አሁን ላይ መንግሥታዊ ባልሆኑ አካላት የሚደረጉትን እንቅስቃሴዎች መንግሥት እየተረዳ ነው” በማለት ይናገራሉ።

“የመንግሥት ተቋማት በአሁን ወቅት ላይ ባለው እንቅስቃሴ ምክንያት ውጤቱን እየተረዱት ነው” የሚሉት ደግሞ ጋዜጠኛ እስሌማን አባይ ናቸው። “ጥቅሙን መረዳት የነበረባቸው ከዐስር አመት በፊት ነበር። ምክንያቱም አሁን አገራችንን እየገጠሟት ያሉት ነገሮች በሙሉ ሌሎች አገራት ከዐስር አመታት በፊት የገጠሟቸው ጉዳዮች ናቸው። ለምሳሌ፣ አሜሪካም ሆኑ ሌሎች ምዕራባውያን አሁን እያደረጉ ያሉት በሌሎች አገራት ላይ ከዚህ በፊት ያደረጉትን ነው። በዛን ወቅት ይሄም ችግር ወደኛ መምጣቱ አይቀርም በሚል ቀድሞ ገምቶ መዘጋጀት ቢኖርብንም አላደረግነውም” ሲሉ ያስረዳሉ።

ዲጅታል ዲፕሎማሲው የቀጣይ አመታት የሉዓላዊነታችን መጠበቂያና መከላከያ ከሆኑት መንገዶች አንዱ መሆኑን ተረድተን ቀድመን ተዘጋጀትን መጠበቅ ቢኖርብንም፣ ሳናደረግው በመቅረታችን አሁን የሚታየው ነገር ሊከሰት እንደቻለ እስሌማን ይናገራሉ።
“አሁን ላይ ግን መነቃቃቱ እየተፈጠረ ነው። እየታየ ባለውም ውጤት እያመኑበት ነው። ለዚህም ማሳያው ግለሰቦች ባለን ኢ-መደበኛ አደረጃጀት የምናቀርበውን ሐሳብ የሚቀበሉበት መንገድ ተለውጧል። በዋነኛነት ግን ይህን እንቅስቃሴ ወደተደራጀና ተቋማዊ ወደሆነ ሁኔታ እንዲሸጋገር መንግሥት ትልቅ ሚና መጫወት ይኖርበታል” በማለት ሐሳባቸውን ይሰጣሉ።

በሒደቱ ያጋጠሙ ችግሮች
በዲጂታል ዲፕሎማሲው እንቅስቃሴ ወቅት ከሚስተዋሉ ችግሮች መካከል ያለመናበብ ዋነኛው ችግር እንደሆነ ይነሳል። ይህም ችግር በተለይም በአገር ውስጥ እና በውጭ ባሉ ኢትዮጵያዊያን መካከል ተናቦ የመሥራት ትልቅ ክፍተት መኖሩን በሚደረጉ ዲጂታል ዘመቻዎች ላይ የሚሳተፉ ሰዎች ያነሳሉ።

በዋነኝነት ግን ዲጂታል ዲፕሎማሲውን ለማፋጠን በሚደረጉ ሒደቶች ወቅት አጀንዳ የመቅረጽ ችግር ትልቅ መሆኑን እስሌማን ይናገራሉ። “ውጪ ያለው የራሱን አጀንዳ ይቀርጻል፤ አገር ውስጥ ያለው የራሱን ይቀርጻል፤ በዚህ አለመናበብ መሀል መነሳት ያለባቸውና ውኃ ማንሳት የሚችሉ ጉዳዮች እንደ ቀልድ ተድበስብሰው ያልፋሉ። ይሄ ደግሞ ለማምጣት ለምናስበው ውጤት ትልቅ እክል እየሆነ ነው” በማለት ሐሳባቸውን ያጋራሉ።

በተጨማሪም፣ ሳይቀየሩ ብዙ የሚቆዩ አጀንዳዎች በመኖራቸው ምክንያትም በሚደረጉት እንቅስቃሴዎች ተጽዕኖ ከመፍጠር እና ውጤት ከማምጣት ይልቅ ተሳታፊውን ወደ ማሰልቸት የሚያደርሱም እንዳሉ ትዝብታቸውን ይገልጻሉ።
በምሳሌነት ሲያነሱም፣ በቅርቡ ጠቅላይ ሚንስትር ዐቢይ አሕመድ(ዶ/ር) በትዊተር ገጻቸው ላይ በዚህ አስቸጋሪ ወቅት አብረውን ለቆሙ አፍሪካዊያን ምስጋና ያቀረቡበትን ጽሁፍ በሚፈለገው መጠን ማስተጋባት አልተቻልም። በዚህም ምክንያት አፍሪካውያንን ይበልጥ ከጎናችን ማድረግ የሚያስችለንን ትልቅ ዕድል ሳንጠቀምበት ማለፉን እያነሱ ይቆጫሉ።

ዲፕሎማሲውን ለማጠንከር ምን ይደረግ?
በተለመደው የዲፕሎማሲ መንገድ ብቻ ተወስኖ አሁን ያለውን እና ወደፊት የሚመጣውን የውጭ ጣልቃ ገብነትና ጫና መቋቋም ማሰብ ከባድ መሆኑን የሚያነሱት አስተያየት ሰጪዎቹ፣ ዲጂታል ዘርፉን ማጠናከርና ነባሩን የዲፕሎማሲ መንገድ ይበልጥ እንዲያጠነክረውና ጉልበት እንዲሆነው ማድረግ እንደሚገባ ያነሳሉ።

በቅርቡ የኮሚዩኒኬሽን መሥሪያ ቤትን መልሶ ለማቋቋም ታላሚ ያደረገ ውይይት መደረጉን የሚያነሱት እስሌማን አባይ፣ በነበረው አይነት የኮሚዩኒኬሽን መንገድ መቀጠል ግን ዋጋ እንደማይኖረውም ያነሳሉ። እንደመፍትሄ ሐሳብም “በዲፕሎማሲው መስክ ትልቅ ተጽዕኖ መፍጠር ከተፈለገ በትንሽ ወጪ ትልቅ ውጤት የሚያመጣውን የዲጂታል መስክ መዘንጋት በዲፕሎማሲው ለተሸናፊነት መዘጋጀት ማለት በመሆኑ ለዲጂታል ዲፕሎማሲው ትልቅ ስፍራ ሊሰጠው ይገባል” በማለት ያስረዳሉ።

ዲጂታል መስኩን ያገናዘበ የኮሚዩኒኬሽን መንገድ መቅረጽ፣ አገርን በዲፕሎማሲ መንገድ ከማቀናት አንጻር ትልቅ አስተዋጽዖ ያለው ጉዳይ በመሆኑ ትኩረት ተሰጥቶበት ሊሠራ የሚገባው ትልቅ የቤት ሥራ ነው ሲሉ አስተያታቸውን ሰጥተውናል።
የዲጂታል ዲፕሎማሲውን ማገዝ የሚችሉ የተማሩ በጎ ፈቃደኞችን በሰፊው በማሰማራት በዲፕሎማሲው መስክ የበላይነትን ማግኘት እንደሚቻልም ባለሙያው ሐሳባቸውን ለአዲስ ማለዳ አጋርተዋል።


ቅጽ 3 ቁጥር 148 ነሐሴ 29 2013

Comments: 0

Your email address will not be published. Required fields are marked with *

error: Content is protected !!