የእለት ዜና

የሱማሌ ክልል የመራጮች ምዝገባ በተወሰኑ የምርጫ ክልሎች እንዲደገም ተወሰነ

መስከረም 20/2014 ለሚካሄደው ኹለተኛው ዙር ምርጫ የመራጮች ምዝገባ ተካሂዶ ነገር ግን ችግር የተገኘባቸው የሱማሌ ክልል ምርጫ ክልሎች የመራጮች ምዝገባ እንደሚደገም የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ አስታወቀ።
በሱማሌ ክልል እየተከናወነ በነበረው የመራጮች ምዝገባ ላይ በቀረበ ከፍተኛ አቤቱታ እና ማስረጃ መሠረት ቦርዱ ማጣራት አስፈላጊ ነው ብሎ በማመኑ የአጣሪ ቡድን ተልኮ ውጤቱ እስኪወሰን ድረስ የመራጮች ምዝገባ መቋረጡ ይታወሳል። ቦርዱ ባደረገው ማጣራት መሰረት የመራጮች ምዝገባ ሙሉ በሙሉ እንዲደገምባቸው የተወሰነባቸው የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ምርጫ ክልሎች ጅጅጋ አንድ እና ጅጅጋ ኹለት ምርጫ ክልሎች ሲሆኑ፣ የክልል ምክር ቤት ምርጫ ክልሎች ቀብሪደሃር ከተማ ምርጫ ክልል፣ ቀብሪደሃር ወረዳ ምርጫ ክልል የመራጮች ምዝገባ ሙሉ በሙሉ እንዲደገም ቦርዱ ወስኗል።
እንዲሁም መኢሶ ምርጫ ክልል እና አፍደም ምርጫ ክልል ቀድሞ የመራጮች ምዝገባ በጸጥታ እና ሌሎች ምክንያቶች ሳይከናወንባቸው በመቅረቱ በምርጫ ክልሎቹ የመራጮች ምዝገባ ይከናወናል ተብሏል።
የመራጮች ምዝገባ እንዲደገም ቦርዱ ከወሰነባቸው ምርጫ ጣቢያዎች መካከል ዋርዴር ምርጫ ክልል ውስጥ አዶ ቀበሌ አንድ ምርጫ ጣቢያ እና ኤልድብር ቀበሌ ኹለት ምርጫ ጣቢያዎች ሲሆኑ፣ በጣቢያዎቹ የመራጮች ምዝገባ ቀድሞ በሚከናወንበት ወቅት አለመደረጉ በመገለጹ በአሁኑ ምዝገባ እንደአዲስ እንዲከናወን ተወስኗል ተብሏል።
እንዲሁም ፊቅ ምርጫ ክልል አንድ ቀበሌ ምርጫ ጣቢያ 01 አንድ ምርጫ ጣቢያ፣ የመራጮች ካርድ ከምርጫ ጣቢያው ወጥቶ ተሰብስቦ በመገኘቱ ፣ እንዲሁም በቀሪ ላይ ምንም ነገር ባለመሞላቱ በዚህ ጣቢያ ላይ የተደረገው የመራጮች ምዝገባ የሕግ ጥሰት የተፈጸመበት መሆኑን የአጣሪ ቡድኑ ሪፓርት ያደረገ እና የውሳኔ ሐሳብም ያቀረበ በመሆኑ ቦርዱ የመራጮች ምዝገባው አንዲደገም ወስኗል።
ገላዴን ምርጫ ክልል አንድ ምርጫ ጣቢያ፣ የመራጮች ምዝገባ ካርዶች በተወዳዳሪ የፓለቲካ ፓርቲዎች መሰብሰባቸው፣ በቀሪ ካርዶች ላይም መረጃዎች በሚገባ አለመሞላታቸው በመታየቱ፣ እንድሁም እጎዴ ከተማ ምርጫ ክልል አራት ምርጫ ጣቢያዎች፣ ምስራቅ ኢሜ ምርጫ ክልል ሦስት ምርጫ ጣቢያዎች እና ቤራኖ ምርጫ ክልል ሦስት ምርጫ ጣቢያ፣ በአጣሪ ቡድኑ የመራጮች መዝገብ በሚታይበት ወቅት ከፍተኛ የአመዘጋገብ ችግሮች በመታየታቸው እና በነዚህ ጣቢዎች ላይ ያለው የመራጮች ምዝገባ ፍትሃዊነትን የሚያረጋግጥ ሆኖ ባለመገኘቱ ምዝገባው እንዲደገም ተወስኗል ተብሏል።


ቅጽ 3 ቁጥር 148 ነሐሴ 29 2013

Comments: 0

Your email address will not be published. Required fields are marked with *

error: Content is protected !!