የእለት ዜና

የኹለተኛው ዙር ምርጫ ዝግጅት

የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ስደስተኛውን አጠቀላይ ምርጫ በአንድ ቀን ለማካሄድ አስቦ ሲሠራ ቢቆይም፣ በአገሪቱ በተለያዩ አካባቢዎች በገጠሙ የጸጥታ ችግሮችና በፍርድ ቤት የተያዙ የምርጫ ጉዳዮች ባለመጠናቀቃቸው ምክንያት ምርጫውን በኹለት ዙር ለማካሄድ ተገዷል። በመሆኑም የመጀመሪያ ዙር ምርጫ እንዲካሄድ በተያዘለት ጊዜ ሰኔ 14/2013 ተከናውኗል።

የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርደ ስድስተኛውን አገራዊ ምርጫ ለማካሄድ የምርጫ ቅድመ ሥራዎችን እያከናወነ ባለበት ኹኔታ የምርጫ ሒደቱ በተለያዩ የአገሪቱ አከባቢዎች በተፈጠሩ የጸጥታ ችግሮች ከመደበኛ አከባቢዎች አኩል መሔድ አልቻለም። ከጸጥታ ችግር በተጨማሪም በደምጽ መስጫ ወረቀት ኅትመት ላይ ቦርዱ ችግር እንደገጠመው መገለጹ የሚታወስ ነው።

በዚህም ቦርዱ ምርጫውን በአንድ ጊዜ ማካሄድ እንደማይችል እና ስድስተኛው አገራዊ ምርጫ በኹለት ዙር እንዲካሄድ መወሰኑ ተከትሎ፣ አሁን ላይ የኹለተኛውን የቅድመ ምርጫ ዝግጅት እያደረገ ይገኛል። የመጀመሪያው ዙር ምርጫ ሰኔ 14 ያካሄደው ምርጫ ቦርድ፣ ቀደም ሲል ኹለተኛው ዙር ምርጫ ጳጉሜ 1/2013 ለማከናወን ያሳለፈ ቢሆንም፣ የቅድመ ምርጫ ዝግጅቱ በታቀደው ልክ ባለመጠናቀቁ ኹለተኛው ዙር ምርጫ መስከረም 20/2014 እንድካሄድ ውሳኔ አሳልፏል።

የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ስድስተኛውን አገራዊ ምርጫ ከትግራይ ክልል ውጭ በተመሳሳይ ጊዜ ለማድረግ አቅዶ ሲሠራ ቢቆይም፣ በአንዳንድ አከባቢዎች ላይ በጸጥታ ምክንያት የምርጫ ቅድመ ሥራዎችን በተገቢው ሁኔታ ባለመሠራታቸው ኹለተኛ ዙር ምርጫ ለማካሄድ ተገዷል። ይሁን እንጅ በኹለት ዙር በሚካሄደው አጠቃላይ ምርጫ የትግራይ ክልል አልተካተተም።

በመጀምሪያው ዙር ምርጫ ያልተካሄደባቸው ሐረሪ እና ሱማሌ ክልል ሙሉ በሙሉ ሲሆኑ፣ በቤኒሻንጉል ጉምዝ ክልል ካሉት ሶስት ዞኖች በኹለቱ ዞኖች ምርጫ አልተካሄደም። በሌሎች ክልሎች የመጀመሪዙ ዙር ምርጫ ቢካሄድም ያልተካሄደባቸው አከባቢዎች አሉ።
ቦርዱ የኹለተኛውን ዙር ምርጫ ጳጉሜ 1/2013 ለማካሄድ የቅድመ ምርጫ ሥራዎች አለመጠናቀቃቸውን ተከትሎ፣ ኹለተኛውን ዙር ምርጫ አዲስ መንግሥት በሚመሰረትበት ዋዜማ መስከረም 20 ለማካሄድ ወስኗል። ይህንን ተከትሎ ቦርዱ የመራጮች ምዝገባ ሥልጠና ሰጥቶ መስከረም 20/2014 ለሚካሄደው ድምፅ አሰጣጥ በሐረሪ፤ በሶማሌ እና በደቡብ ብሔር ብሔረሰቦች ክልል የመራጮች ምዝገባ ማካሄድ መጀመሩን አስታውቋል።

ቦርዱ መስከረም 20/2014 ለሚካሂደው ምርጫ የመራጮች ምዝገባ ለማከናወን ለምርጫ አስፈጻሚዊች ስልጠና ሰጥቷል። ቦርዱ ነሐሴ 22 እና 23 ለሐረሪ ክልል፣ ነሐሴ 23 እና 24 ደግሞ ለሱማሌ እና ለደቡብ ብሔር ብሔረሰቦች እና ሕዝቦች ክልል ለመራጮች ምዝገባ ምርጫ አስፈጻሚዎች ሥልጠናዎችን ሰጥቻለሁ ብሏል።

ቦርዱ ለሚያሰማራቸው ምርጫ አስፈጻሚዎች በቅድመ ምርጫ እና በምርጫ ወቅት ስለሚሠሩ ሥራዎች ዝርዝር ሥልጠና ስጥቻለሁ ብሏል። አስፈጻሚዎቹ ከወሰዷቸው ሥልጠናዎች መካከል የምርጫ የሕግ-ማዕቀፎች፣ የምርጫ ጣቢያ አደረጃጀት፣ የመራጮች ምዝገባ ፅንሰ ሐሳብና መሥፈርቶች፣ ለኮቪድ መከላከል ሊወሰዱ የሚገቡ ዕርምጃዎች፣ የሥርዓተ-ፆታና አካል ጉዳተኛ አካታችነት፣ የጊዜ ሠሌዳና የሥራ ሰዓት እና የምርጫ ጣቢያ ኃላፊዎች ሥነ-ምግባር ተካተተዋል።

እንዲሁም የምርጫ አስተዳደርና ሚና፣ የእያንዳንዱ የምርጫ ጣቢያ የሥራ መደብ ኃላፊነቶች፣ የምርጫ ታዛቢዎችና ወኪሎች እንዲሁም የብዙኃን መገናኛ ኃላፊነትና ሚና፣ የመራጮች ምዝገባ ቁሳቁስ/የምዝገባ ኪት፣ ለመራጮች መረጃ ስለሚሰጥባቸው ፖስተሮች፣ ከመራጮች ምዝገባ ቀን በፊት ስለሚከናወኑ ተግባራት፣ የምዝገባ ሒደት ቅደም ተከተሎች፣ የምርጫ ጣቢያ ቅሬታ ሰሚ ኮሚቴ ስለሚቋቋምበት ሒደት፣ የልዩ ምርጫ ክልሎች የመራጮች ምዝገባ ሒደት፣ ምርጫ ክልል ሪፖርት አቀራረብ፣ የመራጮች ምዝገባ ሒደት የደኅንነት ሕጎች፣ የምርጫ ቅሬታ አፈታቶች፣ ሎጀስቲክ፣ ኦፕሬሽንና አሥተዳደራዊ ጉዳዮች ይገኙበታል።

ቦርዱ ከዚህ ቀደም በአሰልጣኝነት ለተሳተፉ የአንድ ቀን የክለሳ ሥልጠና በመስጠት ለሐረሪ፣ ለሱማሌ እና ለደቡብ ብሔር ብሔረሰቦች እና ሕዝቦች ክልል የመራጮች ምዝገባ ምርጫ አስፈጻሚዎች ሥልጠናውን እንዲያከናውኑ ማድረጉን ጠቁሟል። ለሥልጠና ከሚውሉ ቁሳቁሶች በተጨማሪ ለመራጮች ምዝገባ የሚውሉ ቁሳቁሶች ሥርጭትም እንዲሁ ከማዕከል ወደ ምርጫ ክልሎች ነሐሴ 18 እስከ 21/2013 ማከናወኑን ቦርዱ አስታውቋል።

መስከረም 20/2014 ይካሄዳል ተብሎ ቀነ ቀጠሮ የተያዘለት ኹለተኛው ዙር ምርጫ አስካሁን ባለው ሁኔታ፣ የቅድመ ምርጫ ሥራዎች ከነሐሴ 19/2013 እስከ መስከረም 16/2014 የሚጠናቀቁ ይሆናል። ቦርዱ ባስቀመጠው የጊዜ ሰሌዳ መሠረት የምርጫ ጣቢያ ዝርዝር ይፋ ማድረጊያ ከነሐሴ 19 እስከ ነሐሴ 24/2013፣ የመራጮች ምዝገባ (አዲስ እና የተቋረጡ) ከነሐሴ 26 እስከ ጳጉሜ 5/2013 ሲሆን፣ የመራጮች ምዝገባ ይፋ ማድረጊያ፣ አቤቱታ ማቅረቢያና ማስተካከያ ከመስከረም 3 እስከ 12/2014 ነው።

ቦርዱ ባስቀመጠው የኹለተኛው ዙር ምርጫ ጊዜ ሰሌዳ መሠረት ፖለቲካ ፓርቲዎች የምርጫ ቅስቀሳ ማድረግ የሚችሉት ከነሐሴ 19/2013 እስከ መስከረም 15/2014 ሲሆን፣ ፖለቲካ ፓርቲዎች ቅስቀሳ ማድረግ የማይችሉበት የጥሞና ጊዜ ከመስከረም 16 እስከ መስከረም 19/2014 ነው።

የቁሳቅስ ዕሸጋ እና ቁሳቁስ ስርጭት ከነሐሴ 30/2013 እስከ መስከረም 13/2014፣የኦፕሬሽን ቁሳቁስ ከማዕከል ወደ ምርጫ ክልሎች ማሰራጨት ከመስከረም 5 እስከ መስከረም 14/2014 ሲሆን፣ የመጨረሻ የተረጋጋጠ የምርጫ ውጤት መስከረም 30/2014 ይፋ እንደሚደርግ ቦርዱ ባወጣው የጊዜ ሰሌዳ አስፍሯል።

በአጠቃላይ በሰኔ 14/2013 ምርጫ ተቆርጠው የቀሩ እና ኹለተኛው ዙር ምርጫ ማለትም መስከረም 20/2014 የሚካሄድባቸው በጥቅሉ 64 የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት መቀመጫዎች ናቸው። በክልል ደረጃ በመጀመሪያው ዙር ምርጫ ያልተካተተ ለኹለተኛው ዙር ምርጫ የተዘዋወሩ የክልል ምክር ቤት መቀመጫዎችን ሙሉ በሙሉ በተዛወረው ሱማሌ ክልል 72 የክልል ምክር ቤት መቀመጫዎች፣ በደቡብ ብሔር ብሔረሰቦች 22፣ በኦሮሚያ ሰባት፣ በሐረር ሶስት፣ በቤኒሻንጉል ጉምዝ 13፣ በአፋር ክልል ፣ በአማራ ክልል 9 ሲሆኑ፣ በጥቅሉ በመጀመሪያው ዙር ምርጫ ያልተካሄደባቸ 197 የክልል ምክር ቤት መቀመጫዎች ናቸው።

የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት 547 መቀመጫ ወንበሮች ያሉት ሲሆን፣ ሰኔ 14/2013 በተካሄደው በመጀመሪያው ዙር ምርጫ ካልተካተቱት መቀመጫዎች በተጨማሪ በሰኔ 14ቱም ይሁን በኹለተኛው ዙር በሚካሄደው ምርጫ በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት 38 መቀመጫዎች ያሉት የትግራይ ክልል አልተካተተም። በስድስተኛው አጠቃላይ ምርጫ የመጀመሪያ ዙር ምርጫ ማለትም የሰኔ 14 ምርጫ በ673 ምርጫ ክልሎችና 44 ሺሕ 372 ምርጫ ጣቢያች የተካሄደ ነበር።

በመጀመሪያው ዙር ምርጫ በቅድመ ምርጫ ወቅት ፖለቲካ ፓርቲዎች በሚደርጓቸው ቅስቀሳዎች እና እንቅስቃሴዎች ችግር እንደገጠማቸው የሚታወስ ሲሆን፣ ከገጠሟቸው ችግሮቸ መካከል የአባላት እስር፣ የቅስቀሳ ባነር መቀደድና መነሳት እና ቅስቀሳ እንዳያደርጉ መከልከል ዋና ዋናዎቹ ናቸው።

በመጀመሪያ ዙር ምርጫ የምርጫው ቅስቀሳ መቀዛቀዝና ተደራሽነቱ ውሱንነት የተያበት ሲሆን፣ በፖለቲካ ፓርቲዎች በኩል የሚነሱ በርካታ ምክንያቶ አሉ። የፖለቲካ ፓርቲዎች ለምርጫ ቅስቀሳ ተደራሽነትና መቀዛቀዝ ምክንያት ሆነዋል ብለው ከሚያነሷቸው ዋና ዋና ምክንያቶች መካከል፣ እዚህም እዚያም የሚታዩ የጸጥታ ችግሮች፣ በመንግሥት በኩል የሚደረግ አፈና እና የአቅም ውሱንነት ቀዳሚዎቹ ናቸው።

ከጽጥታ ጋር በተያያዘ የምርጫ ሒደቶች መስተጓጎል እንደገጠመው ምርጫ ቦርድ መግለጹ የሚታወስ ሲሆን፣ መንግሥት በጸጥታ ምክንያት አካባቢያቸውን ለቀው የተፈናቀሉ ዜጎችን ከምርጫ በፊት ወደ አካባቢያቸው እመልሳለሁ ቢልም መመለስ አለመቻሉ፣ ተፈናቃዮች ስለ ምርጫው ግንዛቤ እንዲኖራቸውና የፓርቲዎችን ሐሳብ ሰምተው የተሻላቸውን የሚመርጡበት ዕድል በወቅቱ አለመፈጠሩ የምርጫ ቅስቀሳ ተደራሽነቱንና የምርጫ ሒደት አሳታፊነቱን ጥያቄ ውስጥ ከተዋል ከተባሉ ምክንያቶች የሚጠቀሱ ነበሩ።


ቅጽ 3 ቁጥር 148 ነሐሴ 29 2013

Comments: 0

Your email address will not be published. Required fields are marked with *

error: Content is protected !!