የእለት ዜና

ጂኦስፓሻል ኢንፎርሜሽን ኢንስትቲዩት “ላይዳር” የተባለ አዲስ ቴክኖሎጂ በ80 ሚሊዮን ብር ገዛ

የቀድሞው የካርታ ሥራዎች ድርጅት የአሁኑ የኢትዮጵያ ጂኦስፓሻል ኢንፎርሜሽን ኢንሰትቲዩት በ80 ሚሊዮን ብር አዲስ ቴክኖሎጂ በመግዛት ወደ ሥራ ሊያገባው መሆኑን አስታወቀ።
የኢንስትቲዩቱ የጂኦስፓሻልና ኢኖቬሽን አናሊስቲክ ማዕከል ኃላፊ ሙሉአለም የሺጥላ ለአዲስ ማለዳ እንደገለጹት፣ ኢንስትቱዩቱ “ላይዳር” የተባለ አዲስ የጂኦስፓሻል ቴክኖሎጂን በመግዛት ወደ ሥራ ሊገባ መሆኑን ገልጸዋል።

የላይዳር ቴክኖሎጂ በቀንም ሆነ በማታ የሚሠራ የመሬትን እና በመሬት ላይ ያሉ ቁሶችን አቀማመጥ፣ ቅርጽና ከፍታ በሚሊ ሜትር ትክክለኛነት የሚሰበስብ የጂኦስፓሻል ቴክኖሎጂ ነው። ይህ ቴክኖሎጂ የመብራት ገመዶችን የመሰሉ ቀጫጭን ቁሶችን መለየት እና ሞዴል ማድረግ የሚችል መሣሪያ ሲሆን፣ ከዚህም በተጨማሪ ከደን ውስጥ ያሉ ቁሶችንና የመሬት አቀማመጥን ደኑን ዘልቆ በመግባት መሰብሠብ የሚያስችልም ነው ሲሉ ሙሉአለም ጠቁመዋል።
ላይዳር ቴክኖሎጂ ስዊዘርላንድ ከሚገኝ “ላይካ” የሚባል የቅየሳ መሣሪያዎች አቅራቢ የተገዛ ሲሆን፣ 80 ሚሊዮን ብር የወጣበት መሆኑም ታውቋል።

እንደ አገር ከመጣው ለውጥ ጋር ተያይዞ እንደ አዲስ የተቋቋመው ኢንስትቲዩቱ፣ የቀድሞው ካርታ ሥራ ድርጅት እና በኢንፎርሜሽን መረብ ደኅንነት ኤጀንሲ ሥር የነበረ የጂኦስፓሻል ዲቪዥን በጥምረት የፈጠሩት ተቋም ነው።
ተቋሙ በዋናነት የከፍታ መረጃዎችን ማቅረብ፣ የአየር ላይ ፎቶግራፍ ማንሳት፣ ለቅየሳ ሥራ የሚያገለግል የጂኦሎቲክ መሠረተ ልማት ማስተዳደር፣ አገር ዐቀፍ ዘርፉን የሚመሩ ፖሊሲዎችና መመሪያዎች ማውጣት፣ ለግል ተቋማት የቁጥጥር ሥራዎችን መሥራት፣ የሙያ ፍቃዶችን መስጠት ላለፉት ሦስት ዓመታት ሲሠራ የቆየ ነው።

ኢንስትቲዩት ከሆነ በኋላ ከነበረው የሥራ ድርሻ በተጨማሪ፣ የምርምር ተግባራት እንዲያከናውን ኃላፊነት ተሰጥቶታል። የካርታ ሥራዎች ድርጅት ላለፉት 70 ዓመታት ጥቅም መስጠት በነበረበት ደረጃ ሳይሰጥ በመቆየቱ አወቃቀሩን ለማስተካከል እና ምቹ ቦታ ለመፍጠር ዕድሳት እያካሄደ ይገኛል ተብሏል።

ተቋሙ ለኹሉም ዘርፍ መሠረታዊ መረጃዎችን የሚያቀርብ በመሆኑ የሚመለከታቸው ተቋማት ማለትም እንደ ከተማ ልማት፣ ግብርና፣ ጤና፣ የመሳሰሉት በጋራ በመሆን የሚቋቋም የ‹ጂኦስፓሻል ብሔራዊ ካውንስል› እንደሚኖር ተጠቁሟል።
የመሠረተ ልማቶችን በማቋቋም፣ ደረጃዎችን ለማስተግበር በሚኒስቴር ደረጃ በኃላፊነት የሚመራው አካል ተፈጥሮ ለመንቀሳቀስ ካውንስል እንዲቋቋም የተለያዩ ሠነዶችን በማዘጋጀት እየተሠራ ይገኛል ሲሉ ሙሉአለም ገልጸዋል።

የመሬት አስተዳደር መሠረተ ልማት የሚቋቋም እና የሚወጡ መመሪያዎች የሚያስተገብር ካውንስል የሚመሠረት ሲሆን፣ ይህን ካውንስል ለማቋቋም የሚረዳ ፖሊሲ ተዘጋጅቶ በቀጣይ ዓመት ወደ ፓርላማ ገብቶ የሚጸድቅ መሆኑን ሙሉአለም ተናግረዋል።
ኢንስትቲዩቱ የአየር ላይ ቅየሳ መረጃዎችን ከአውሮፕላን/ ሔሊኮፕተር/ እና ድሮን ላይ በመሆን የሚሰበሥብ እና ወደመረጃ የሚቀይር ተቋም ነው።

ቴክኖሎጂው ከሌሎች የጂኦስፓሻል መረጃ መሰብሠቢያ መንገዶች የሚለየው በአንድ ጊዜ ሰፊ ቦታን የሚሸፍን፣ ጥራት ያለው እና ሰዎች በማየደርሱበት ቦታ መረጃም መሰብሠብ የሚያስችል ዘርፍ መሆኑ ነው።
የጂኦስፓሻል ኢንፎርሜሽን ኢንስቲትዩት ከ2001 ጀምሮ ዓቅም ሲገነባ ቆይቶ በ2004 የአየር ላይ ቅየሳ ሥራዎችን ሙሉ በሙሉ በአገር ውስጥ አቅም እንደገና መሥራት የጀመረ ነው። እስከ 2013 ድረስ 450,000 ኪ.ሜ ስክዌር ስፋት ያለው ቦታ በአየር ፎቶግራፍ የተሸፈነ ነው።

አዲሱ የላይዳር ቴክኖሎጂ የፀሐይ ብርኃንን የማይንተራስ፣ እራሱን የቻለ የብርኃን ምንጭ ያለው፣ ጥቅጥቅ ባሉ ደኖች መካከል የሚገኙ ጥቂት ክፍተቶችን በመጠቀም ከደን በታች ያሉ እንዲሁም ከደመና በላይ የሚገኙ መረጃዎችን የሚሰብሥብ መሆኑም ታውቋል።
ተቋሙ ቀድሞ ይጠቀምበት የነበረው ፎቶግራሜትሪ ቴክኖሎጂ የከፍታ መረጃን የሚያገኘው ከፎቶዎች ድርብርብ በመነሳት ስለሆነ ድርብ ፎቶ የማያገኝባቸው ቦታዎች ላይ ከፍታውን ሞዴል አያደርገውም ነበር።ላይዳር ግን የከፍታ መረጃን ከእያንዳንዱ የሌዘር ጨረር የሚያገኝ በመሆኑ ምንም ዓይነት ክፍተት የሌለው መረጃን ይሰበሥባል።

በተጨማሪም፣ ፎቶግራሜትሪ ደንን ወይም ዛፎችን ሰርስሮ የመግባት አቅም የለውም። በዚህም ምክንያት ከዛፎች ስር ያለን ማንኛውም መረጃ መሰብሠብ አይችልም። ላይዳር በሌላ በኩል፤ ጥቅጥቅ ባሉ ደኖች መካከል እንኳን የተወሰን ክፍተት ተጠቅሞ የመግባት እና መረጃ የመሰብሠብ ዐቅም አለው።

ይህ ላይዳር የተሰኘው አዲስ ቴክሎጂ ተግባራዊ የሚሆንባቸው ተቋማት የመንገድ ባለሥልጣን፣ ባቡር እና ግድብ፣ የደን ልማት እና ቁጥጥር፣ የአርኪዮሎጂካል ቦታዎች አሰሳ ፣የፓርኮች ልማትና አሥተዳደር ፣ የመብራት መሠረተ ልማቶች አሥተዳደር ፣ መከላከያ ሠራዊት፣ መስኖ ልማት፣አደጋ መከላከል እና የማዕድን ቁፋሮ ናቸው።


ቅጽ 3 ቁጥር 148 ነሐሴ 29 2013

Comments: 0

Your email address will not be published. Required fields are marked with *

error: Content is protected !!