የእለት ዜና

በአዲስ አበባ በሚገኙ ሕገ-ወጥ የታክሲ ተራ አስከባሪዎች ላይ ዕርምጃ እንደሚወሰድ ተገለጸ

በሕገ-ወጥ የታክሲ ተራ አስከባሪዎች ላይ ዕርምጃ እንደሚወሰድ የአዲስ አበባ ትራንስፖርት ባለሥልጣን ለአዲስ ማለዳ አስታወቀ።
በሥራ ዕድል ፈጠራ ጽ/ቤት አማካይነት ተደራጅተው በመንግሥት ዕውቀና ካገኙት ዉጭ እየተንቀሳቀሱ ያሉ ሕገ-ወጥ የታክሲ ተራ አስከባሪዎች ተጣርተው ዕርምጃ እንደሚወሰድባቸው ነው ባለሥልጣኑ የገለጸው።
በሥራ ያልተሠማሩ ወጣቶች በሥራ ዕድል ፈጠራ ጽ/ቤት አማካይነት ተደራጅተው ታክሲ ተራ በማስከበር ሥራ እንዲሠማሩ በመንግሥት ዕዉቅና ያገኙ ቢሆንም፣ በመካከል በራሳቸው ፍላጎት የተደራጁ ሕገ-ወጥ ተራ አስከባሪዎች እንዳሉ የአዲስ አበባ ትራንስፖርት ቁጥጥር ኃላፊ ዮሴፍ ተስፋየ ተናግረዋል።

ዮሴፍ አክለውም በሥራ ዕድል ፈጠራ ዕቅድ የተቀመጡ ሌሎች የኮንስትራክሽን፣ የማኑፋክቸሪንግ መሰማሪያ ዘርፎች ያሉ ቢሆንም፣ ጥቅም የሚገኝበት ተራ አስከባሪነት ነው በሚል ዕሳቤ በብዛት አደራጅተው እንደሚልኩ ተናግረዋል።
ትራንስፖርት ባለሥልጣን ምን ያህል የሰው ኃይል እንደሚያስፈልግ በመለየት በሥነ-ምግባር ችግር የሌለባቸውን እና ሥራ አጥ ሴቶችን ጨምሮ ለተራ አስከባሪነት ዕውቅና ሲሰጥ የቆየ ቢሆንም፣ ከ2010 ጀምሮ ይህ ድርጊት እንዲቆም ተደርጓል ብለዋል።

በራሳቸው መንገድ እየተደራጁ ተራ አስከበርን የሚሉ ማኅበራት ዕውቅና እንደማይኖራቸው ለሥራ ዕድል ፈጠራ ደብዳቤ የተጻፈ ቢሆንም፣ ድርጊቱ ባለመቆሙ ባለሥልጣኑ በሕገ-ወጥ ታክሲ ተራ አስከባሪዎች ላይ አስፈላጊውን ዕርምጃ እንደሚወሰድ ነው ዮሴፍ የገለጹት።
“እኛ እናደራጃችሁ ስንላቸው ተደራጀን ብለው ደብዳቤ ለሚያመጡ አካላት ከትራንስፖርት ዋና ሥራ አስፈጻሚ ጋር በመነጋገር ችግሮቹ እንዲፈቱ እያደረግን ቢሆንም መደራጀቱ አልቆመም” ብለዋል።

ለማኅበሩ መደራጀት አለመቆም ምክንያቱ በአዲስ አመራሮች በኩል የመረጃ ክፍተት መኖር መሆኑን የጠቆሙ የቁጥጥር ኃላፊው፣ ተራ አስከባሪዎችን ከማደራጀታቸው ቀድመው ምን እንደሚያስፈልግ ትራንስፖርት ባለሥልጣንን መጠየቅ ነበረባቸው ነው ያሉት።
አያይዘዉም ከትራንስፖርት ባለሥልጣን ጋር ውይይት ሳያደርጉ ’’እዚህ መስመር ላይ ተደራጅታችኋል’’ በሚሉ የወረዳ ኃላፊዎች ላይ ያለውን ችግር ለመቅረፍ በአመራር ደረጃ ውይይት እየተካሄደ መሆኑን ነው ኃላፊው ያመላከቱት።
ጉዳዩን በማስመልከት አዲስ ማለዳ ያነጋገረቻቸው ሰዎችም በተራ አስከባሪዎቹ ምክንያት ችግር እየደረሰባቸው መሆኑን ተናግረዋል።

የታክሲ ተጠቃሚዎቹ እንደሚናገሩት ከሆነ ተራ አስከባሪዎች ከሹፌሮች እንዲቀበሉ የተመደበላቸው ዋጋ ሦስት ብር ሲሆን፡ ሃያና ከዛም በላይ ብር እየተቀበሉ ታክሲዎች ወደ ፈለጉት አካባቢ እንዲጭኑ ስለሚያደርጉ የትራንስፖርት ችግር እያጋጠማቸው መሆኑን ነው ለአዲስ ማለዳ የገለጹት።

አዲስ ማለዳ ካነጋገረቻቸው የታክሲ ተጠቃሚዎች መካከል ስማቸው እንዳይጠቀስ የጠየቁ ታክሲ ተጠቃሚ “ተራ አሰከባሪዎች መመደባቸው መልካም ነው፤ ሆኖም ግን ይህን የሚያደርጉት በምን መስፈርት እንደሆነ ባላውቅም በተመደቡበት ቦታ ተሳፋሪ እየተጉላላ ወደ ፈለጉት ቦታ የሚጭኑ ሹፌሮችን ዝም ብለው ነው የሚመለከቱት። እንደተመለከትኩት ከሆነ ሹፌሮች ይህን የሚያደርጉትም ከተራ አስከባሪዎቹ ጋር በመመሳጠር ነው’’ ሲሉ ገልጸዋል።

አዲስ ማለዳ ጉዳዩ ይመለከታቸዋል የተባሉትን የታክሲ ተራ አስከባሪዎች ጊዜያዊ ሰብሳቢ ግርማቸው ስለሺን ጠይቃለች “ምንም እንኳን በማኅበሩ ከተደራጁ አስተባባሪዎች መካከል ሥራቸውን በአግባቡ የማይወጡ አካላት ቢኖሩም፣ ለችግሩ መከሰት ዋነኛ ምክንያቱ ከማኅበሩ ዉጭ የሆኑ ግን በማስተባበር ሥራ የሚገኙ አካላት ናቸው። ለችግሩ መፍትሔ ለመስጠትም በየክፍለ ከተማው ተበታትነው የሚሠሩ አስተባባሪዎችን የሚቆጣጠር ኮሚቴ በማዋቀር ላይ ነን’’ በማለት ነው የገለጹት።
አክለውም “ተራ አስከባሪዎች ከሹፌሮች የተመደበላቸው ክፍያ ሦስት ብር መሆኑን በመጥቀስ ከዚህ በላይ የሚቀበሉትን አስከባሪዎች የመጠቆም ሥራ ከማኅበረሰቡ ዘንድም ይጠበቃል’’ ብለዋል።


ቅጽ 3 ቁጥር 148 ነሐሴ 29 2013

Comments: 0

Your email address will not be published. Required fields are marked with *

error: Content is protected !!