የእለት ዜና

ብሔራዊ ባንክ ይፋ ያደረጋቸው መመሪያዎች ለባንኮች ሥጋት መሆናቸው ተገለጸ

ብሔራዊ ባንክ ባሳለፍነው ሳምንት ይፋ ካደረጋቸው አራት መመሪዎች ውስጥ አብዛኞቹ ባንኮች ጋር ያለውን ተቀማጭ የገንዘብ እና የዶላር መጠን ወደ መንግሥት የሚያስገቡ ናቸው ሲሉ የሕብረት ባንክ የዳይሬክተሮች ቦርድ ሊቀመንበር እየሱስወርቅ ዛፉ ገለጹ።
በመመሪያው መሠረት የአገልግሎት እና የዕቃ አስመጪዎች ይዘውት ከሚመጡት የዶላር መጠን ከ45 በመቶ ወደ 40 በመቶ፣ እንዲሁም ባንከች ጋር የሚገባውን 25 በመቶ ወደ 10 በመቶ ዝቅ በማድረግ ዶላሩ ወደ ብሔራዊ ባንክ እንዲሸጋገር ተደርጓል።
ይህ መመሪያ ባንኮችም ጋ ሆነ አስመጪዎች ጋ የሚገባውን የዶላር መጠን መቀነሱ የራሱ የሆነ ከባድ ችግር እንደሚኖረው እየሱስወርቅ ጠቁመዋል።

በተጨማሪም ከ5 በመቶ ወደ 10 በመቶ ማሳደጉ ብቻም ሳይሆን፣ ከልማት ባንክ አንድ በመቶ ቦንድ እንዲገዙ ማስገደዱ ባንኮች ከሚሰበስቡት ገንዘብ 11 በመቶውን ከእጃቸው ላይ ይወስዳል ብለዋል።

ይህ ደግሞ 10 በመቶ መጠባበቂያ አድርጌ እይዘዋለሁ ያለው የገንዘብ መጠን ከንግድ ባንኮች ወስዶ ለሌላ ጥቅም እንዲውል የሚያደርግ ስለሚሆን ተመልሶ የገንዘብ መጠን መብዛ ይከሰታል የሚል ሥጋት እንዳላቸው ጠቁመዋል። እነዚህ ተጠቃሚዎች መልሰው ገንዘቡን ወደውጭ ካወጡት ብሔራዊ ባንክ ያሰበውን ውጤት ላያገኝ ይችላል ሲሉ ጠቁመዋል።

የአስቀማጮች ገንዘብ ዋስትና ያለው ቀደም ሲልም ቢሆን ብሔራዊ ባንክ ሲሆን፣ ባንኮች ከሚሰበስቡት ተቀማጭ ገንዘብ 5 በመቶ እየወሰደ ምንም ወለድ ሳይከፍል ቆይቷል።
ይህ ማለት የሚሰበስበውን ገንዘብ መልሶ እንዳያበድር የተወሰነውን በመያዣ ዋስትና መልክ ሲይዝ ቆይቷል። አሁን ደግሞ 10 በመቶ ማድረጉ ለሕዝብ በብድር የሚሰጠው ገንዘብ መጠን ይቀንሳል ማለት ነው። በገበያው ውስጥ የሚንቀሳቀሰው የገንዘብ መጠን መቀነሱ ሰዎች ለአገልግሎት የሚከፍሉትን ገንዘብ ይቀንስባቸዋል። ስለዚህ እንደልብ በየቦታው ማውጣት አይችሉም ሲሉ እየሱስወርቅ ገልጸዋል።

በዚህ ጊዜ ባንኮች የማበደር አቅማቸው ስለሚቀንስ ገበያ ውስጥ የሚንሸራሸረው የገንዘብ መጠን ይቀንሳል ብለዋል።
ብሔራዊ ባንክ ያወጣው ይህ መመሪያ በተፈለገው መጠን ውጤት ያመጣል ወይስ አያመጣም የሚለውን ኹሉም ሰው የሚያው ነው ሲሉ ጠቅሰዋል።
በየቀኑ የዋጋ ንረቱ እየጨመረ በመጣበት በዚህ ወቅት እንደዚህ አይነት መመሪያዎች አስፈላጊ ናቸው ብለዋል።

ከአገሪቱ የሠላምና የጸጥታ ሁኔታ ጋር የሚያያዘው የዋጋ ንረቱ፣ ጦርነቱ እንዲሁም ደግሞ በቅርቡ የኮቪድ ወረርሽኝ ተከትሎ ፍላጎት በየጊዜው እየጨመረ አቅርቦት ካለበት መነቃነቅ ስላልቻለ ከፍተኛ ደረጃ ላይ ደርሷል። ይህን የፈጠረው ተብሎ የሚታሰበው ሰዎች ጋር በርካታ ጥሬ ገንዘብ መኖሩና ለሚፈልጉት ዕቃ ብዙ የመክፈል አቅም የፈጠረላቸው መሆኑ ነው። ይህን ማስቆም ይረዳኛል በማለት ብሔራዊ ባንክ ከመስከረም አንድ ጀምሮ መመሪያዎችን ተግባራዊ ያደርጋል።

የውጭ ምንዛሬ በጣም እየተወደደ በሄደበት ወቅት አሁን ግለሰቦች በእጃቸው ያለው ገንዘብ እያነሰ ስለሚመጣ ጥቁር ገበያ ላይ መግዛት የሚያስችላቸው ገንዘብ አይኖራቸውም ብለዋል።
ባንኮች እና አስመጪዎች ከውጭ ምንዛሬ የሚያገኙትን ገቢ በመቀነስ ለመንግሥት የሚጨምር መሆኑ ባንኮች ጋር የሚኖረው የዶላር መጠን እንደሚቀንስ ጠቁመዋል።

ብሔራዊ ባንክ ካወጣቸው አራት መመሪያዎች ውስጥ የመጀመሪያው የባንኮች መጠባበቂያና የብሔራዊ ባንክ ማበደሪያ ወለድ ምጣኔ በተመለከተ ባንኮች ከሚሰበስቡት የገንዘብ መጠን ከ5 በመቶ ወደ 10 በመቶ ከፍ እንዲል እና ባንኮች ከብሔራዊ ባንክ የሚበደሩበት ዓመታዊ ወለድ ምጣኔ ከ13 በመቶ ወደ 16 በመቶ ከፍ እንዲል መደረጉን ይገልጻል።

የውጭ ምንዛሬ አጠቃቀም በተመለከተ ባንኮች ከውጭ ንግድ፣ ከግከሰብ ኃዋላ እና ከመንግሥታዊ ያልሆኑ ድርጅቶች ብቻ 30 በመቶ ለብሔራዊ ባንክ ያደርግ የነበረውን ገቢ 50 በመቶውን የሚያስገቡ ሲሆን፣ ቀሪዎቹ የውጭ ቀጥተኛ ኢንቨስትመንት፣ ከዲያስፖራ እና ከሌሎች የሚገኙ ዶላሮች ሙሉ በሙሉ የማይወሰዱ ናቸው ሲል መመሪያው ያስረዳል።

መመሪያው ከሚገልጻቸው አንዱ የሆነው ባንኮች ካላቸው ዓመታዊ የብድር ክምችት ውስጥ ከልማት ባንክ አንድ በመቶ የቦንድ ግዢ እንዲፈጽሙ የሚያደርግ ነው።


ቅጽ 3 ቁጥር 148 ነሐሴ 29 2013

Comments: 0

Your email address will not be published. Required fields are marked with *

error: Content is protected !!