የእለት ዜና

ክብር ለሚገባው ክብር እንስጥ!

“የስጦታ ፈረስ ጥርሱ አይታይም” እያለ የሰጪውን ማንነት እንጂ የስጦታውን ዓይነት በማይገመግም ሕብረተሰብ ውስጥ ብንኖርም፣ የድጋፉ ዓይነትና የሰጪው ማንነትን ትውልዱ አውቆት ለማስተማሪያነት መዋሉ አስፈላጊ የሆነበት ጊዜ ላይ እንገኛለን። ማኅበረሰባችን በክፉ ጊዜው የደረሱለትን የማይረሳውን ያህል፣ ሳይደርሱ የቀሩትንም እንደሚቀየም ይታወቃል። በደስታው ጊዜ እንኳ፣ “የደስታዬ ተካፋይ ሁኑ” ብሎ የጠራቸው ከቀሩበት እንደንቀትም ስለሚቆጥረው መቀየሙ አይቀርም። በደስታው ላይ የተገኙለት እንደዘመኑ ስጦታ ይዘው ሲመጡ በማይመዘገብበት በድሮ ወቅት እንኳን፣ ማን ምን እንዳመጣለት ማወቁ አይቀርም።

አገራችን ኢትዮጵያ አሁን ጦርነት ላይ እንደመሆኗ በድህነቷ ላይ የተጋረጠውን ይህን ክስተት መንግሥትም ሆነ ሌላ አካል ራሱን ችሎ ብቻውን እንደማይወጣው ይታወቃል። ለዚህም ሲባል የለጋሽ አገራትን ደጅ መጥናቱ እንዳለ ሁኖ፣ የእያንዳንዱን ኢትዮጵያዊ በር ማንኳኳቱም አልቀረም። ድርጅቶችም ሆኑ ግለሰቦች ጦርነቱ ከተጀመረ አንስተው እስካሁን ለሚደግፉት ወገን ድጋፋቸውን በግልጽም ሆነ በድብቅ ሲሰጡ ቆይተዋል። እንደሕዝብ አገርን ለማስቀጠል፣ እንዲሁም ወደጦር ሜዳ የተላኩ ወጣት ተዋጊዎች ችግር ላይ እንዳይወድቁ ለማድረግ ዐቅም በፈቀደ መጠን ድጋፉ መቀጠል እንዳለበት አዲስ ማለዳ ታምናለች።

በሰሜኑ የአገሪቱ ክፍል ውጊያ እንደማይቀር የገመቱ ጥቂቶች የመሆናቸው ያህል፣ ዝግጅት ሳይኖር ወደ ጦርነት እንደተገባ የሚናገሩ ብዙ ናቸው። “በቂ ጊዜ ወስደን አቅደን ጀምረነዋል” ያለ አካል እስካሁን ባለመኖሩ፣ “ሕግ የማስከበር ዕርምጃ” ተብሎ የነበረው ጦርነቱ ድንገት ለመከሰቱ ማስረጃ ይቀርባል። ያም ሆነ ይህ፣ ውጊያው ተጀምሮ ፍልሚያው ሲፋፋም ለተፋላሚዎቹ የጎረፈው ድጋፍና ስጦታ ብዙዎችን ያስደመመ ነበር።

የዛሬ ዘጠኝ ወር ገደማ ለተዋጊዎች ከሚሰጥ የገንዘብ ድጋፍ በተጨማሪ፣ ለምግብ የሚሆናቸው በርካታ የቁም ከብቶች ከተለያዩ የአገሪቱ አውራጃዎች ወደ ጦር ቀጠናው ጎርፈው ነበር። የመንግሥት ሠራተኛው ደሞዙን፣ ባለሀብቱ ገንዘቡን ከመለገሱ በላይ ለፍተው ያሳደጓቸውን ከብቶች ሳያመነቱ የሠጡ በርካታ አርሶ አደሮች አሉ። ሩቅ ሆነው ችግሩን በቅርብ እንዳለ ከተረዱት አርሶ አደሮችና አርብቶ አደሮች በተጨማሪ፣ በቅርብ ሆነው ቤታቸው ያፈራውን እንጀራም ሆነ ሌላ እህል ድህነታቸው ሳይጎረብጣቸው ያቀረቡና የላኩም፣ እንዲሁም አሁንም ድረስ የሚሰጡ በርካቶች ናቸው። እነዚህን የመሳሰሉ የዘመናችን ባለውለታዎች ጦር ግንባር ተሰልፈው ሕይወታቸውን እንደሚሰጡት ክብር ሊሰጣቸው እንደሚገባ አዲስ ማለዳ ማሳሰብ ትወዳለች።

ክብር ለሚገባቸው ክብርን ብቻ ሰጥቶ ዝም ማለት ብቻ ሳይሆን፣ በፈቃደኝነት እውቅና እንዲያገኙም ቢደረግ መልካም ይሆናል። ጦር ሜዳ የተሰው ውጊያ ከተጠናቀቀ በኋላ ዕውቅና ተሰጥቷቸው በሥማቸው ተዘርዝረው እንደሚዘከሩት፣ ድጋፍ ያደረጉም እንዲሁ ለማስተማሪያ እንዲሆኑ፣ ሌሎችም እንዲበረታቱ ማንነታቸው ሊታወቅ ይገባል። የሰጡት መጠን እንደአቅማቸው ይሁን አይሁን ፍላጎት ላይ የተመሠረተ ስለሚሆን ባይጠቀስም፣ ማንነታቸውም ጭምር ቢታወቅ ማን አጋዥ እንደነበረ እንደማኅበረሰብ ሕዝብ እንዲተዋወቅ ያደርጋል።

እንዲህ አይነት አገራዊ አደጋ ሲከሰት መዋጮ ብቻ ሳይሆን ዘመቻም በግድ ሊሆን እንደሚችል ቢደነገግም፣ በፈቃድ ላይ ሆኖ እንኳን ማንነታቸው መታወቁ ብዙ ጥቅም እንዳለው የሚናገሩ አሉ። “ማን ምን አደረገ” የሚለው ተመዝግቦ የማይያዝና የማይታወቅ ከሆነ ተደጋጋሚ ለሆነ ጥያቄ ሕብረተሰቡ እንዲጋለጥ ያደርጋል። ፉክክር ባለበት በዚህ ዘመን ያለ ትውልድ፣ “እገሌ ይህን አድርጎ እኔስ” የሚል ስሜት እንዲቆረቁረው ከማድረጉ ባሻገር፣ ፍርኃት ይዞት እንዳይቀር፣ ከኹለት ያጣ እንዳልሆን የሚልን አስተሳሰብ ያስቀራል። ለኹለቱም ተፋላሚ ወገኖች እያበላለጡ ሲረዱ የነበሩ የመታወቃቸውን ያህል፣ ሕዝብ እንዲያልቅና ጦርነቱ እንዲራዘም የሚያደርጉ እንዲህ ዓይነቶቹንም ለማጋለጥ ያግዛል።

ድጋፍ የሚያደርጉን ለማሳወቅ በየማኅበረሰቡ መገኛና በሚታወቁበት አካባቢ የተለያዩ መንገዶችን በመጠቀም ይፋ ማድረግ ይቻላል። ለምሳሌ፣ በፌደራል ደረጃ የሚረዱ ባለሀብቶችን በሚዲያም ሆነ በድረ-ገጽ በመዘርዘር ከነአስተዋጾአቸው ለሕዝብ ማሳወቅ ይቻላል። በየገጠሩ የሚለግሱትንም በየአካባቢያቸው ባሉ የማስታወቂያ መንገዶች በመጠቀም ማሳወቁ እንደሚጠቅም አዲስ ማለዳ ታምናለች።

በሌላው ዓለም እንዲህ አይነት ልገሳዎችን በችግር ጊዜ የሚያደርጉ ተዘርዝረው ስለሚያዙ ደግ ጊዜ ሲመጣ ውለታቸውን በተቻለ መንገድ ለመክፈል ይሞከራል። ለአገር ተብሎ የሚደረግ ተግባር ውለታ ተደርጎ መቆጠር ባይኖርበትም፤ በእከክልኝ ልከክልህ መሆን የለበትም ተብሎ ቢታመንም፣ አገር በቻለችበት በደግ ጊዜ እንዲህ አይነት በጎ አድራጊዎችንና ራሳቸውን ለአገር ሲሉ አሳልፈው የሰጡን ከነቤተሰቦቻቸው መጥቀሙ ክፋት የሌለው ከመሆኑ ባሻገር፣ አሁን የሚደረገውን ርብርብ የማፋጠኑ ሚና ከፍተኛ ነው። በችግር ጊዜያቸው የረዳናቸው ጃፓንና ኮሪያ ውለታችንን እስካሁን ሳይዘነጉ በተቻላቸው አጋጣሚ ውለታውን ለመመለስ እንደሚጥሩት፣ ለራስ ዜጋም ተመሳሳይ ተግባር ቢኖር ከጉዳቱ ጥቅሙ እንደሚያመዝን ይታመናል።

አገር በቸገራት ወቅት ድጋፍ የሚያደርጉ ብቻ ሳይሆኑ በደህናው ወቅት በጎ አድራጎት ተግባር ላይ ተሳትፈው ሕዝብን እንደመንግሥት የደገፉ ተጠቃሚ የሚሆኑበትን የተለያየ መንገድ ብዙ አገራት ተግባራዊ አድርገው ዜጎቻቸውን በቀጥታና በተዘዋዋሪ ተጠቃሚ ያደርጋሉ። እንዲህ አይነት ተግባራትን ሳይገደዱ የሚፈጽሙ ከዓመታዊ ግብራቸው ላይ እንዲታሰብላቸው የሚያደርጉ ብዙ አገራት ናቸው። ዘመቻ የሔዱ ቤተሰቦችን በደቦ እርሻቸውን ማገዝ፣ ከብቶቻቸውን መጠበቅ፣ ልጆቻቸውን በነጻ ማስተማር፣ እንዲሁም የሕክምና ወጪያቸውን የመሳሰሉ ድጋፎችን ማድረግ ጥሩ የሚሠሩን ለማበረታታት፣ እንዲሁም ለመሥራት ያልደፈሩን ለማጓጓትም ሆነ ለማስተባበርና ለማሳመን እንደሚያግዝ አዲስ ማለዳ ትረዳለች።

በቀደመው ዘመን እንዲህ አይነት በጎ ተግባር ላይ የተሳተፉ ያደረጉትን እያስመሰከሩ ክፍያም ሆነ ጥቅም ለመጠየቅ ይሉኝታ ቢይዛቸውም፣ የሚያውቅ እየመሰከረላቸው ሹመትንም ሆነ ድጋፍን በመሬት መልክ እንዲያገኙ ይደረግ እንደነበር ይነገራል። በቅርቡ ዘመን ከደርግ መንግሥት ጋር ሲዋጉ የነበሩት ሻዕቢያና ወያኔዎች፣ ከድላቸው ማግስት ያገዟቸውን ሲጠቅሙ መኖራቸው ይነገራል። ፍትሐዊ አካሄድን የተከተለ ባይሆንም፣ በ10 ሺሕዎች የሚቆጠሩ የእርሻ መሬት እንዲያገኙ በማድረጋቸው ድጋፋቸው እስካሁን ሳይለያቸው መኖራቸው ይታወቃል።

የሰው ልጅ መልካምነቱ የሚታየው በሠላምና ደግ ወቅት ሳይሆን ነገሮች አስቸጋሪ በሚሆኑበትና ዕጥረት ባለበት የአደጋ ወቅት በሚያደርገው ተግባር ነው። እንዲህ አይነት የቁርጥ ቀን ሰዎች ተስፋ እንዳይቆርጡ፣ እንዳይሰላቹ፣ ብቻቸውን የቀሩ እንዳይመስላቸውና ሥራቸውም እንደሚያስመሰግናቸው እንዲውቁ የሚመለከተው አካል አክብሮ ሥራቸው እንዲታወቅ ማድረግ አለበት። በተለይ ሳይተርፋቸውና ጥቅም አገኝበታለሁ ብለው ሳያስቡ ወይም የግል ፍላጎታቸው ላይ ሳይመረኮዙ ለአገርና ለወገን ብለው የሚረዱት ላይ የበለጠ ትኩረት ተደርጎ ማስተማሪያ ሊሆኑ እንደሚገባ አዲስ ማለዳ ታስገነዝባለች።

ለአንድ ወገን ተብሎ የሚረዳ ገንዘብም ሆነ በቁስ የሚሰጥ ድጋፍ፣ ለአንደኛው ተፋላሚ ብቻ ሳይሆን ለምርኮኛም ስለሚሆን ኹሉም ተጠቃሚ ይሆንበታል። “በርሃብ ከመሞት በጦርነት መሞት ይሻላል” እየተባልን አድገን፣ ለአገሩ ሊሞት ጦር ሜዳ የሔደ አንዳይርበው የማድረጉ ኃላፊነት የሕዝብ ሊሆን ይገባል። “የራበው ሕዝብ መንግሥትን መብላቱ አይቀርም” የተባለለት ጊዜ እንዳይደገም፣ ትጥቅን በውርስ ስንቅን ከራስ ማድረጉ ይመረጣል።


ቅጽ 3 ቁጥር 148 ነሐሴ 29 2013

Comments: 0

Your email address will not be published. Required fields are marked with *

error: Content is protected !!