የእለት ዜና

በአዲስ አበባ ቤቶች ልማት ኮርፖሬሽን የሠራተኞች ደሞዝ ልዩነት ቅሬታ አስነሳ

በአዲስ አበባ ቤቶች ልማት ኮርፖሬሽን ውስጥ በተመሳሳይ የሥራ ደረጃ ላይ የተሠማሩ ሠራተኞች ለኹለት ተከፍሎ የነበረው አወቃቀር አንድ ላይ ከተደረገበት ጊዜ ጀምሮ ደሞዛቸው የተለያየ መሆኑ ቅሬታ እንደፈጠረባቸው የኮርፖሬሽኑ ሠራተኞች ለአዲስ ማለዳ ገለጹ።
40/60 እና 20/80 ተብሎ የተሰየመው ኹለት የቤቶች ግንባታ አወቃቀር የአዲስ አበባ ምክትል ከንቲባ አዳነች አበቤ ወደ ሥልጣን ከመምጣታቸው በፊት በነበሩ አመራሮች ቤቶች ልማት ኮርፖሬሽን ወደሚባል አንድ አወቃቀር የተቀየረ ሲሆን፣ ከዚህ ጊዜ ጀምሮ በተመሳሳይ የሥራ ደረጃ ላይ የተሠማሩ ሠራተኞች ተመሳሳይ ደሞዝ ማግኘት የሚገባቸው ቢሆንም እያገኙ እንዳልሆነ ስማቸው እንዳይጠቀስ የጠየቁ የኮርፖሬሽኑ ሠራተኞች ተናግረዋል።

አዲሱ አወቃቀር ከመፈጠሩ በፊት 40/60 የቤቶች ግንባታ የራሱ የሆነ ቤቶች ልማት ኢንተርፕራይዝ የሚል ሥያሜ እንደነበረወና ከሌላኛው 20/80 ተብሎ ራሱን ችሎ ከተሠየመው የግንባታ ተቋም ጋር ተዋህዶ የአዲስ አበባ ቤቶች ልማት ኮርፖሬሽን ወደሚባል ሥያሜ መቀየሩን ሠራተኞቹ አብራርተዋል።

ሠራተኞቹ እንደተናገሩት ከሆነ ቤቶች ልማት ኢንተርፕራይዝ (40/60) ለትርፍም ጭምር የተቋቋመ ድርጅት በመሆኑ ደሞዙ ከፍተኛ ሲሆን፣ 20/80 ደግሞ ለትርፍ ያልተቋቋመ የቤት ግንባታ በመሆኑ ደሞዙ ዝቀተኛ እንደነበር ነው።
ይሁን እንጅ ኹለቱ ተቋማት ወደ አንድ አወቃቀር ከተዋኃዱ ጀምሮ ሠራተኞች በተመሳሳይ የሥራ ደረጃ የተሠማሩ ቢሆንም፣ “በአንድ መሥሪያ ቤት ውስጥ የተለያየ ደሞዝ ነው የሚከፈለን’’ በማለት ነው ቅሬታቸውን የገለጹት።
የደሞዝ ልዩነቱ “አንዳንድ ጊዜ እስከ 100 ፐርሰንት ይደርሳል’’ ያሉት ቅሬታ አቅራቢዎቹ፣ ደሞዛቸው እኩል እንደሚሆንላቸው ቢነገራቸውም ከአንድ ዓመት ጊዜ በላይ ችግራቸው እንዳልተቀረፈ ተናግረዋል።

በቤቶች ልማት ኮርፖሬሽን የነበሩ ሠራተኞች ቦታ የለም ተብለው ወደ ሌላ ቦታ እንዲደራጁ እየተደረጉ ከመሆኑም በላይ፣ በድርጅቱ ተመድበው እስካሁን ቦታ ያላገኙ ሰዎች እንዳሉም ነው የአዲስ ማለዳ ምንጮች የጠቆሙት።

ሠራተኞቹ አክለውም፣ ይህ በእንዲህ እንደቀጠለ ሆኖ፣ ኹለቱ መሥሪያ ቤቶች ወደ አንድ ተቋም ተቀይረው አዲስ አበባ ቤቶች ልማት ኮርፖሬሽንን ከመፍጠራቸው በተጨማሪ፣ በሌላ ዲዛይን ኢንተርፕራይዝ የሚል አወቃቀር አቋቁመው እንደነበር አመላክተዋል።
ቅሬታ አቅራቢዎቹ እንደሚሉት ከሆነ፣ በየጊዜው በሚቋቋመው መዋቅር የተፈጠረው ችግር ሣይፈታላቸው አሁን ላይ ደግሞ መሥሪያ ቤቱን አፍርሶ እንደገና ለማቋቋም እንደታሰበና ወደ ተግባር ለመግባት የመዋቅር ጥናት እንዲጠና ከከንቲባ ጽሕፈት ቤት መታዘዙን ማረጋገጣቸውን ነው የገለጹት።

በአንድ መሥሪያ ቤት ውስጥ ተመሳሳይ የሥራ ደረጃ ላይ ያሉ ሠራተኞች የተለያየ የደሞዝ ስኬል ሊኖራቸው አይገባም የሚሉት ሠራተኞቹ፣ “በዚህ አይነት አሠራር ከአንድ ዓመት በላይ በደል ደርሶብናል፤ የሚመለከተው አካል መፍትሔ ሊሰጠን ይገባል” በማለት ነው ለአዲስ ማለዳ የገለጹት።

ሠራተኞቹ አያይዘዉም መሥሪያ ቤቱ ምንም እንኳን ግንባታዎችን ቢያከናውንም፣ በተፈለገው ጊዜ እንዳልደረሰ እና መዋቅር በመቀያየር የተቋቋመበትን ዓላማ እየዘነጋ መሆኑን ነው የጠቆሙት። ቅሬታ አቅራቢዎቹ አክለውም፣ በቤቶች ልማት ኮርፖሬሽን ቢመደቡም እስካሁን ቦታ ያላገኙበትን ምክንያት የሚመለከተው አካል በአፋጣኝ መልስ ሊሰጥ ይገባል ብለዋል።

አዲስ ማለዳ የሠራተኞቹን ቅሬታ ይዛ ወደ አዲስ አበባ ቤቶች ልማት ኮርፖሬሽን በተደጋጋሚ ስልክ ብትደዉልም የሚመለከታቸው አካላት ምላሽ ለመስጠት ፈቃደኛ ባለመሆናቸው ምላሻቸውን ማካተት አልቻለችም።


ቅጽ 3 ቁጥር 148 ነሐሴ 29 2013

Comments: 0

Your email address will not be published. Required fields are marked with *

error: Content is protected !!