የእለት ዜና

በፈረቃ ሲሰጥ የነበረው ትምህርት ወደ መደበኛው ሒደት እንደሚመለስ ተገለጸ

በዓለም ዐቀፍ ደረጃ በተከሰተው የኮቪድ-19 ወረርሽኝ ምክንያት በፈረቃ ሲሰጥ የቆየው ትምህርት በ2014 የትምህርት ዘመን ወደ መደበኛው እንደሚመለስ ትምህርት ሚኒስቴር ለአዲስ ማለዳ አስታወቀ።
የኮቪድ-19 ቫይረስ ወረርሽኝን ለመከላከል እንዲረዳ በማሰብ በ2013 የትምህርት ዘመን ላይ በፈረቃ ሲሰጥ የነበረው ትምህርት እና ተማሪዎች ሲማሩበት የነበረው የቀናት ቁጥር በሳምንት ወደ ሦስት ቀን ተቀንሶ ተማሪዎች በቀናት ፈረቃ ተምረው ያሳለፉ ሲሆን፣ ከሚቀጥለው

የትምህርት ዘመን ጀምሮ ወደ ነበረበት ማለትም ከሰኞ እስከ አርብ የትምህርት ጊዜውን ለመመለስ መታቀዱን በትምህርት ሚኒስቴር የትምህርት ቤት መሻሻል ዳይሬክቶሬት ከፍተኛ ባለሙያ ከተማ ቀውይ ተናግረዋል።
በ2013 ትምህርት ዘመን በተለያየ የትምህርት ደረጃ ላይ ያሉ ተማሪዎች ተከፋፍለው ትምህርት መጀመራቸው የሚታወስ ሲሆን፣ በአዲሱ የትምህርት ዘመን ደግሞ ትምህርት በተመሳሳይ ወቅት ለማስጀመር መታቀዱም ተገልጿል።

ባሳለፍነው የትምህርት ዘመን የኮቪድ ወረርሽኝ ሥርጭትን ለመግታት በማሰብ ትምህርት ቤቶች በአንድ ክፍል ውስጥ መቀበል ያለባቸውን የተማሪዎች ቁጥር እንዲቀንሱ በመደረጉ ምክንያት ከሰኞ እስከ አርብ ይሰጥ የነበረው ትምህርት በቀናት ፈረቃ ሲሰጥ መቆየቱን አንስተው፣ በሚቀጥለው የትምህርት ዘመን ወደ መደበኛው ለመመለስ እየተሠራ መሆኑን ባለሙያው አስረድተዋል።

ትምህርት የሚሰጥባቸውን ቀናት ወደ መደበኛው ለመመለስ በተዘጋጀው ዕቅድ ላይ የጤና ሚኒስቴር ተሳትፎ ማድረጉን ያነሱት ባለሙያው፣ በሚከናወነው የትምህርት ቀናትን ወደ መደበኛ የመመለስ ሒደት ላይ ኮቪድን-19 ቫይረስን ከመካላከል አንጻር መከተል በሚገቡ ፕሮቶኮሎች ላይ ውይይት መደረጉንም አንስተዋል።

በተጨማሪም የ2014 የትምህርት ዓመትን በአገር ዐቀፍ ደረጃ መስከረም 25 ላይ ለማስጀመር በጊዜያዊነት ዕቅድ እንደተያዘ ባለሙያው ለአዲስ ማለዳ ጠቁመዋል።

በአገር ዐቀፍ ደረጃ መስከረም 25 ትምህርት ለማስጀመር ዕቅድ ይያዝ እንጂ፣ አሁን አገሪቱ ባለችበት ወቅታዊ ኹኔታ ምከንያት በተባለው ቀን ላይ ትምህርት ለማስጀመር ከባድ የሚሆኑባቸው አካባቢዎች መኖራቸውን ባለሙያው አንስተዋል። ዘግይተው የሚከፈቱ ትምህርት ቤቶችን በተለየ ኹኔታ ለማገዝ የሚያስችል ዕቅድ በመዘጋጀት ላይ መሆኑንም ጨምረው ገልጸዋል።

በሰሜኑ የአገሪቷ ክፍል እየተካሄደ ባለው ጦርነት ምክንያት ከሰባት ሺሕ በላይ ትምህርት ቤቶች ሙሉ በሙሉ እና በከፊል መውደማቸው ትምህርት ሚኒስቴር ባሳለፍነው ሳምንት መግለጹ የሚታወስ ሲሆን፣ በዚህም ምክንያት በርካታ ተማሪዎች ከትምህርት ገበታ ውጪ ሊሆኑ እንደሚችሉ ከፍተኛ ሥጋት አለ።

ግጭት ባለባቸው የአገሪቱ ክፍሎች ትምህርት ለማስጀመር ከፍተኛ ችግር እንዳለ የተጠቀሰ ሲሆን፣ ጦርነቱ መቼ ሊጠናቀቅ እንደሚችል በውል አለመታወቁ በትምህርት ማስጀመሩ ሒደት ላይ ዕንቅፋት መፍጠሩ የማይቀር እንደሆነ የሚያነሱት ባለሙያው፣ የወደሙትን ትምህርት ቤቶች መልሶ ለመገንባት እና የተማሪዎቹም ሆነ የአስተማሪዎቹ ለትምህርት ያላቸው የሥነ-ልቦና ዝግጁነት ትምህርትን መልሶ ለማስጀመር በሚደረገው ሒደት ላይ ተጽዕኖ እንደሚኖረውም ከተማ ቀውይ ለአዲስ ማለዳ ተናግረዋል።


ቅጽ 3 ቁጥር 148 ነሐሴ 29 2013

Comments: 0

Your email address will not be published. Required fields are marked with *

error: Content is protected !!