የእለት ዜና

“ለፀጥታው ስራ ሲባል ከበዓሉ ጋር በተያያዘ ርችት መተኮስ የተከለከለ ነው” የአዲስ አበባ ፖሊሰ

Views: 109

የተለያዩ አጋጣሚዎችን በመጠቀም የከተማችንን ሰላም ለማደፍረስ የሚንቀሳቀሱ የጥፋት ሃይሎችን መቆጣጠር እና ምቹ ሁኔታ ማሳጣት እንዲቻል ለፀጥታው ስራ ሲባል ከበዓሉ ጋር ተያይዞ ርችት መተኮስ በፍፁም የተከለከለ መሆኑን የአዲስ አበባ ፖሊስ ገለፀ፡፡

ህብረተሰቡ ይህን ተገንዝቦ ለጋራ ደህንነት ሲባል አስፈላጊውን ትብብር ሊያደርግ እንደሚገባም አሳስቧል።

የአዲስ አበባ ፖሊስ አያይዞም የ2014 የዘመን መለወጫ በዓል በሰላም እንዲከበር ለወንጀልና ትራፊክ አደጋ መከላከል ተግባሩ ልዩ ትኩረት በመስጠት በገበያ እና በመዝናኛ ስፍራዎች እንዲሁም ህዝብ በብዛት በሚንቀሳቀስባቸው ቦታዎች በርካታ አባላትን የተለያየ የጥበቃ ዘዴዎችን በመጠቀም ወደ ሥራ ማሰማራቱን ገልጿል፡፡

የሃገራችንን እና የከተማችንን ወቅታዊ የፀጥታ ሁኔታ ያገናዘበ ዕቅድ አውጥቶ ወደ ስራ መግባቱን የጠቀሰው የአዲስ አበባ ፖሊስ ከሀገር መከላከያ፣ ከብሔራዊ መረጃና ደህንነት አገልግሎት፣ ከፌደራል እና ከኦሮሚያ ፖሊስ እንዲሁም ከሌሎች የፀጥታ አካላት ጋር ተቀናጅቶ እየሰራ እንደሆነም አስታውቋል፡፡

በዓሉን ምክንያት አድርገው የገበያ አለመረጋጋትን ለመፍጠር ምርት በሚደብቁ እና ያልተገባ የዋጋ ጭማሪ በሚያደርጉ ነጋዴዎች ላይ ከሚመለከታቸው አካላት ጋር በመቀናጀት እርምጃ እየተወሰደ እንደሚገኝ የጠቀሰው የአዲስ አበባ ፖሊስ በበዓል ወቅት የግብይት መጠኑ የሚጨምር በመሆኑ ሀሰተኛ የገንዘብ ዝውውር ሊያጋጥም ስለሚችል ሰዎች ተገቢውን ጥንቃቄ ማድረግ አለባቸው ብሏል፡፡

ከመጠን በላይ አልኮል ጠጥቶና ከፍጥነት ወሰን በላይ ማሽከርከር ለትራፊክ አደጋ መንስኤ ከሆኑ ምክንያቶች መካከል ዋነኞቹ ስለሆኑ አሽከርካሪዎች ይህን ተገንዘበው እራሳቸውንም ሆነ ሌሎችን ከአደጋ ተከላክለው ሊያሽከረክሩ እንደሚገባም ፖሊስ አስገንዝቧል ፡፡

ከዚህ ቀደም የተከበሩ ሀይማኖታዊና ብሔራዊ በዓላት ካለምንም የፀጥታ ችግር በሰላም እንዲከበሩ ህብረተሰቡ ላበረከተው ከፍተኛ አስተዋፅኦ የአዲስ አበባ ፖሊስ ምስጋናውን እያቀረበ የ2014 የዘመን መለወጫ በዓልም በሰላም እንዲከበር ለፀጥታው ስራ ስኬታማነት እያደረገ ያለውን ድጋፍ አጠናክሮ እንዲቀጥል እና አካባቢውን በንቃት እንዲጠብቅም ጥሪውን አስተላልፏል፡፡

Comments: 0

Your email address will not be published. Required fields are marked with *

This site is protected by wp-copyrightpro.com