የእለት ዜና

አዲስ ዓመት አዲስ ተስፋ

እዮሃ አበባዬ………….መስከረም ጠባዬ
እዮሃ አበባዬ…………. መስከረም ጠባዬ
መስከረም ሲጠባ…………..አደይ ሲፈነዳ
እንኳን ሰው ዘመዱን………ይጠይቃል ባዳ

አሮጌው ዘመን በአዲሱ የመቀየሩን ብሥራት አብሣሪው የአዲስ ዓመት (ዕንቁጣጣሽ) በዓል፤ በእኛ በኢትዮጵያዊያን ዘንድ ልዩ ሥፍራ ከሚሰጣቸው በዓላት ውስጥ አንዱና ዋነኛው ነው። የጨለማ ተምሳሌት የሆነው ጭጋጋማው የክረምት ወቅት አልፎ፣ ቀን ከሌሊት ይዘንብ የነበረው ዝናብና አስገምጋሚው መብረቅ ጋብ የሚልበት፣ ምድር በዐደይ አበባ ተጥለቅልቃ በልምላሜ የምትታይበት፣ አሮጌው ዘመን ወደኋላ ተትቶ አዲሱ ሊተካ “እዮሃ አበባዬ” የሚባልበት በዓል በመሆኑ በብዙዎቻችን ዘንድ የተለየ ትርጓሜ ይሰጠዋል።

አዲስ ዓመት ሲመጣ በዓሉን በአዲስ መንፈስ እና ስሜት ለመቀበል የሚደረገው የቤት ጽዳትና ዕድሳቱ፣ ልብስ አጠባውና አሮጌውን በአዲስ ለመቀየር የሚከናወነው ግብይት፣ የሳር፣ የአደይ አበባ ጉዝጓዞ፣ የጠላው፣ የጠጁ፣ የዶሮው፣ የዳቦው ዝግጅት እና አጠቃላይ ሽር¬¬-ጉዱ፤ ዕለቱን በይበልጥ እንድንናፍቀውና ከአሁን አሁን ዐውደ ዓመቱ በደረሰ እያልን በጉጉት እንድንጠባበቀው የሚያደርግ ስሜት ይፈጥርብናል።

የልጃገረዶች ለአበባዮሽ ጨዋታ ዝግጅት፣ የሕፃናት ወንዶች የእንኳን አደረሳችሁ ሥዕል “ዲዛይን” ንድፍና የቀለም መረጣን ስንመለከት አዲስ ዓመት መቃረቡን እናስባለን። በትዝታ የኋሊትም ተስበን የልጅነት ጊዜያችን የምናስብና ትውስታችንንም የሚቀሰቀስብን ጥቂቶች አይደለንም።

ታዲያ አሮጌ ያልነው ዘመን አብቅቶ በአዲስ መተካቱን ከሚያበስሩን ከእነዚህ ማኅበራዊና ትውፊታዊ የዓውድ ዓመት ሥነ ሥርዓቶች በተጨማሪ፣ ተፈጥሮም እራሷን በውበት አሰማምራ የአዲስ ዓመትን መጥባት የምታመለክትባቸው ልዩ ልዩ መገለጫዎች አሏት።
አዲስ ዓመት ሲመጣ ሜዳው፣ ሸንተረሩ፣ ጋራና ሸለቆው በውብ የአበቦች ፍካት ይታጀባል፤ የአዋፋት ዝማሬ በየቦታው ይሰማል፤ ዐደይ አበባም ለእረጅም ወራቶች ሳትታይ ቆይታ ወቅቱን ተከትላ በየስፍራው ብቅ ማለቷን ትጀምራለች፡፡ የክረምቱን ማብቃትና የአዲሱን ዘመን መግባት የምታበስረው የመስቀል ወፍም በውብ ላባዋ ደምቃ ከተደበቀችበት በመውጣት የምትታይበት ወቅት ነው።

የዕንቁጣጣሽ በዓል ድባብ ገና የጳግሜ ወር ሲገባ ጀምሮ ነው የሚታየው። ቤተክርስቲያኖች አካባቢ የሚታዩ ሥርዓቶችም ልዩ ስሜትን ይፈጥራሉ። በተጨማሪም በከተሞች አካባቢ የተለያዩ የመልካም ምኞት ፖስት ካርዶችና ምስሎች በተለያዩ ካፌዎች እና የንግድ ቦታዎች ተሰቅለው የበዓሉን መድረስ ያመላክታሉ።

የዘንድሮው አዲስ ዓመት ድባብ
አሮጌው የ2013 ዓመት የተለያዩ መልካምና አስከፊ ኩነቶችን አስተናግዶ በማለፍ ተራውን ለተከታዩ አዲስ ዓመት አስረክቧል። የ2014 ዓመትን ‹ሀ› ብለን ልንጀምር ዛሬ የአዲስ ዘመን ማብሰሪያ የዕንቁጣጣሽ በዓልን ቀን ላይ እንገኛለን። በዓሉ በተለያዩ አካባቢዎች የተለያየ መልክና ይዘት ይዞ እየተከበረ የሚገኝ ሲሆን፣ ኹሉም አቅሙ በፈቀደ መጠን ቤት ያፈራውን አዘጋጅቶ በማቅረብ በደስታና በፍቅር ዐውደ ዓመቱን በማሳለፍ ላይ ነው።

ዶሮውን፣ በጉን፣ የቅርጫ ሥጋውን ኹሉም እንደየአቅሙ በቤቱ አዘጋጅቶ፣ ዘመድ አዝማድ፣ ጓደኛ ጎረቤቱ ተሰብስቦ አብሮ በመብላትና በመጠጣት በዓሉን በሳቅ በጨዋታ እያከበረውም ይገኛል። እርስ በእርስ እንኳን አደረሰህ (ሽ) መባባሉ ከጥንት የዘለቀውን ማኅበራዊ ትስስር የሚያጠክር በመሆኑ ለበዓሉ ልዩ ስሜትና ድምቀትንም ፈጥሮለታል።

የአገራችን አንዳንድ አካባቢዎች ላይ ግን የብዙዎችን ሕይወት እየቀጠፈ የሚገኘው የኮቪድ 19 ወረርሽኝና ወቅታዊው የአገራችን የሠላም ማጣት ኹኔታ ሥጋት የፈጠረና የበዓል አከባበሩ ላይ መቀዛቀዝን ያስከተለ ሆኗል። በወረርሽኙ ላይ በሚታየው መዘናጋትና በአንዳንድ የአገራችን አካባቢዎች በተነሳው ጦርነት ምክንያት የቤተሰብ አባላቸውን አጥተው በዓሉን በሐዘን እና በከፍተኛ ድብርት ውስጥ የሚያሳልፉትም ጥቂቶች እንዳልሆኑ ይታወቃል።

ለወትሮው የአዲስ ዓመት በዓል በመጣ ቁጥር አስቀድሞ በመዘጋጀት በዓሉን በልዩ ድምቀት ማሳለፍ እንደለመደ የሚናገረው ከአዲስ ማለዳ ጋር ቆይታ ያደረገው አበራ ነጋሽ ነው። አበራ የኮንስትራሽን ባለሙያ ሲሆን፣ አዲስ ዓመት በመጣ ቁጥር አንዳች ልዩ ስሜት እንደሚሰማው ያስረዳል።

“አዲስ ዓመት ደስ የሚል፣ ወደ ተስፋና ብርሃን የምንሄድበት በዓል በመሆኑ ለኹሉም ኢትዮጵያዊ ትልቅ በዓል ነው። ኹሉም በደስታ የሚያከብረውና ጓጉቶ የሚጠብቀው በዓልም ነው” ሲል ይናገራል። ምክንያቱም ሲያስረዳ የኹለት ወራት የክረምቱን ወቅት አሳልፈን ወደ ፀደይ እና ወደ ብርሃን የምንሻገርበት ወቅት በመሆኑ ካሉት በዓላት ሁሉ ትልቁን ድርሻ የሚይዝ እንደሆነም ይገልፃል።

“የዘንድሮ አዲስ ዓመት ትንሽ ከሌሎቹ ለየት የሚያደርገው፣ 2013 ከባድ ጊዜን ያሳለፍንበት ዓመት በመሆኑ ነው” የሚለው አበራ፣ አገራችን የገባችበት ጦርነት፣ ዓለም ዐቀፉ የኮሮና ወረርሽኝና ይበልጡንም በኑሮ ውድነት ምክንያት ኹሉም ነገር ጣራ መንካቱ በበዓሉ ላይ የተለየ ስሜት እንደፈጠረበት ይናገራል።

አክሎም፣ የእኛ ማህበረሰብ በዓላት ሲመጡ የለመደው አዳዲስ ዕቃዎችን መቀየር፣ ለበዓላት የሚሆኑና ብዙ ገንዘብ የሚያስወጡትን ነገሮች ማድረግ እንደሆነ በመግለፅ፣ የዘንድሮው በዓል ግን እነዚህን ነገሮች ለማድረግ የሚያስችል ነው ብሎ እንደማያስብ ይናገራል። “ምናልባት የማይቀሩ የምንላቸውን ዕርዶች ልናከናውን እንችላለን እንጂ፤ በዚህ በጣም በተጋነነ የዋጋ ውድነት አዳዲስ ዕቃዎችን ገዝተህ የምትቀይርበት ጊዜ ነው ብዬ አላስብም” ሲልም ምክንያቱን ያስረዳል።

“ነገር ግን የኢትዮጵያ ሕዝብ በዓላትን የሚያከብረው ዕርዶችን በማከናወን ስለሆነ እነሱ አይቀሩም። ምንም ያህል ቢወደዱና ነገሮች ጣራ ቢነኩም ሰዉ ያለውን አሟጦ፣ በባንክ ያስቀመጠውን አውጥቶም ቢሆን ዕርድ ያከናውናል። ያ ማለት ግን ሕብረተሰቡ አልተቸገረም ወይም ጤነኛ ገቢ አለው ማለት አይደለም። መንግሥትም ሆነ ነጋዴዎች የተለያየ ምክንያቶችን ሊያቀርቡ ይችላሉ፤ ግን በጣም የተጋነነ በሚባል ደረጃ የተፈጠረው የኑሮ ውድነት የቀድሞውን የበዓል ድባብ አጥፍቶታል። ይህ ደግሞ በተለይ ዝቅተኛ ገቢ አለው ተብሎ የሚታሰበው ማኅበረሰብ ላይ ትልቅ ፈተና ሆኖበታል” ሲልም ሐሳቡን ያጠናክራል።

“አዲስ ዓመትን ቀድሞ እንደማደርገው አይደለም የተቀበልኩት፤ ምክንያቱም የማገኘው ገቢና አጠቃላይ ለበዓሉ የሚያስፈልገኝ ወጪ የተመጣጠነ አልሆነም” የሚለው ደግሞ ማስረሻ ተረፈ ነው። ማስረሻ በዚህም ምክንያት የተለያዮ ወጪዎችን እንዲቀንስ እንደተገደደ ይናገራል። ነገር ግን ተስፋውና የአዲስ ዓመት ስሜቱ ድሮ ከሚያከብራቸው በዓላት የተለየ እንዳልሆነም ይናገራል።

“አዲስ ዓመት አሮጌው አልፎ አዲሱ የሚመጣበት፣ የክረምቱ ወቅት አብቅቶ የበጋውን ወራት የምንቀበልበት በመሆኑ የግዴታ የምፈልገው ወይንም የለመድኩት ነገር አልሞላልኝም ብዬ አዲሱ ዓመት ጥሩ አይደለም አልልም። አዲስ ዓመት ሲመጣ የራሱን አዲስ ነገር ይዞ ይመጣል የሚል ተስፋ አለኝ” ሲል ለአዲስ ማለዳ ያስረዳል።

እንደወጣት አሁን አሁን ነገሮች እየከበዱ እንደሄዱ የሚናገረው ማስረሻ፣ በዚህ ወቅት ውጪ ወጥቶ በጥቂቱ ተዝናንቶ ለመመለስ እንኳን አንድ ሺሕ እና ኹለት ሺሕ ብር የማይበቃበት ሁኔታ መፈጠሩን ይገልፃል። ይህ ደግሞ የወርሃዊ ደሞዙን እኩሌታ እንደሚወስድም ይናገራል።
“ኹሉ ነገር ከመጠን በላይ ጭማሪ አሳይቷል። እንደድሮው በደሞዝህ መልበስ ማጌጥ ይቅርና፤ ጠግበህ ለመብላትና በጥቁቱ ለመዝናናት እንኳን አይቻልም። ስለዚህ እኔ በበኩሌ ነገሮች እስኪስተካከሉልኝ ድረስ በዓሉን ለብቻዬ በቤቴ ለማሳለፍ ነው የወሰንኩት” በማለት በዓሉን ከወዳጆቹ ጋር ሰብሰብ ብሎ እንዳያሳልፍ የነገሮች መወደድ ትልቅ ተግዳሮት እንደሆነበት ይገልፃል።

ሌላዋ ከአዲስ ማለዳ ጋር ቆይታ ያደረገችው ደግሞ ወይንሸት ጌታቸው ነች። ወይንሸት በአንድ የግል ትምህርት ቤት ውስጥ በመምህርነት ተቀጥራ እያገለገለች ሲሆን፣ ባለትዳር እና የሦስት ልጆች እናት እንደሆነች ገልፃልናለች። እርሷም በበኩሏ የዘንድሮው አዲስ ዓመት እንደወትሮው የአዲስ ዓመት የአከባበር ሥርዓት ደማቅና አስደሳች እንዳልሆነላት በመግለፅ የዚህም ምክንያት ዓለም ዐቀፉ የኮቪድ 19 ወረርሽኝ እና በአገራችን የሚናፈሰው የጦርነት ዜና የፈጠረባት ተጽዕኖ መሆኑን ትናገራለች።

ነገር ግን ትላለች ወይንሸት፣ “ነገር ግን ነገሮች ምንም ያህል ቢያስከፉና የኮቪድ 19 የስርጭት ሁኔታ እጅግ አሳሳቢና አስጊ ደረጃ ላይ ቢደርስም፣ በተቻለ መጠን ጥንቃቄ በማድረግና ጥሩ ስሜትን በመፍጠር በዓሉን ከቤተሰቤ ጋር በደስታ መንፈስ ለማሳለፍ ጥረት እያደረኩ ነው” ትላለች።

አክላም የበዓሉን የገበያ ሁኔታ ስታነሳ “የቅቤ፣ የዘይት የዶሮና መሰል ለበዓሉ የሚያስፈልጉ ግብዓቶች ላይ ከሌላው ጊዜ የበለጠ ጭማሪን አስተውያለሁ። ሌላው ቢቀር ለአዲስ ዓመት ለኔም ሆነ ለልጆቼ እገዛው የነበረው የሐበሻ ልብስ እንኳን አሁን ላይ ዋጋው የማይደፈር ሆኖል። ነገር ግን፣ ዐቅሜ በፈቀደው መጠን ሁኔታዎችን እንደምንም እያብቃቃሁና ልጆቼ በተገኘው አልባሳት አምረው ሳይከፉ በዓሉን በድምቀት እንዲያከብሩ የተቻለኝን ጥረት እያደረኩ ነው” ስትል ምንም ያህል ነገሮች ቢከብዷትና ቢያስከፏትም አዲስ ዓመት እንደመሆኑ መጠን በዓሉን በጥሩ ስሜት ለማሳለፍ እያደረገች ያለውን ጥረት ታስረዳለች።

እንደ አጋጣሚ ሆኖ የዛሬ ዓመትም እንዲሁ የኮቪድ 19 ወረርሺኝ ሥጋት የበዓሉን ድባብ በጥቂቱም ቢሆን አቀዝቅዞት እንደነበር የምታስታውሰው ወይንሸት፣ አሁን ደግሞ በይበልጥ በአገራችን በተከሰተው የእርስ በእርስ ጦርነት ላይ የኑሮ ውድነቱ ተጨምሮ የበዓሉ ድባብ ላይ መቀዛቀዝን መፍጠሩን ትናገራለች። “ነገር ግን እነዚህ ኹላ ነገሮች ወደተሻለ ነገር እንደሚመጡ በማለም አሁንም በዓሉን በዐቅሜ በድምቀት ለማክበር ወደ ኋላ አላልኩም” ስትልም ትናገራለች።

ለወትሮው አዲስ ዓመት ሲመጣ የጳግሜ ወር የተለያዩ ሸመታዎችን በሚያከናውኑ ሰዎች ጎዳናዎች ይሞላሉ። ገበያዎች፣ የኤግዚብሽን ማዕከሎች የልብስና የጫማ ሱቆች በሰዎች ይጥለቀለቃሉ። ዘንድሮም ያን ያህል የተጋነነ ባይሆንም እንኳን እነዚህ ሸመታዎች አለመቅረታቸውን አዲስ ማለዳ በተለያዩ አካባቢዎች ዞር ዞር ብላ ለመታዘብ ችላለች።

ኹሉም ነገር ተወደደ፤ ኑሮ ጣራ ነካ ተብሎ መሸመቱን የሚተው ሰው የለም። ሁሉም የቻለውን ለማድረግ ይፍጨረጨራል። ለበዓሉ የሚሯሯጠው የሚሸጠው የሚሸምተውን ሁሉ ነገ ተስፋ እንዳለውና፣ ዛሬን ባለችኝ ነገር ተደስቼ በዓሉን አሳልፌ ነገ አገኛለሁ የሚል ዕምነት እንዳለው ያሳያል።

አዲስ አመት እና አዲስ ተስፋ
አገራችን ኢትዮጵያ ከሌሎች የዓለም አገራት በተለየ የራሷ የዘመን ስሌትና ቀመር ያላት አገር ናት። ብቸኛዋ የአስራ ሦስት ወር ፀጋ ባለቤት አገር መሆኗም ይታወቃል። ታዲያ አስራ ሦስተኛው የጳግሜ ወር አብቅቶ የአዲሱ ዓመት መባቻ የሆነው የመስከረም ወር ሲባጅ፣ ብዙዎቻችን አዳዲስ የሕይወት ዕቅዶችን ማውጣት ወይንም የጀመርነውን አጠናክረን በመቀጠል ውጤታማ ለመሆን እናስባለን። ዘመን ዕለቱን ጠብቆ ሲቀየር የእኛም የአስተሳሰብ፣ አመለካከትና አጠቃላይ የሕይወት ዘይቤና እሳቤ እንዲቀየርም እንተልማለን።
አዲስ ዓመት እንደተለመደው አዲስ ተስፋና ምኞትን የሚሰንቅበት በዓል እንደሆነ የሚናገረው አበራ፣ በአሁኑ ወቅት ለሚታየው የኢኮኖሚ ግሽበትም ይሁን የዋጋ ንረት አስተዋፆ ያደረጉ ብዙ አሉታዊ ምክንያቶች እንዳሉ ይናገራል።

ታዲያ እነዚህ አሉታዊ ተጽዕኖዎች ዳር ይዘው፣ ጦርነቱም አብቅቶ፣ የኮቪድ 19 ወረርሽኝም አስፈላጊው ጥንቃቄና የፈጣሪ ምህረትም ተጨምሮበት የሚቆምበት ሁኔታ ከመጣ፤ መስከረም በራሱ ለሰዎች ተስፋን ይዞ የሚመጣ ወር ነው ብሎ እንደሚያምን ይገልፃል።
“እኔ ብርሃን የለም ወይንም እንዲህ እንደጨለመ ይቀራል ብዬ የማምን ሰው አይደለሁም። ምክንያቱም ሁልጊዜ በነጋ ቁጥር አዲስ ተስፋን ይዞ ይመጣል ብዬ የማስብ ሰው ነኝ። የፈለገ ጫና ውስጥ ብሆን፣ ይህች ቀን አልፋ ሌላ የተሻለ ቀን ይመጣል ብዬ አምናለሁ” ሲልም ያለውን ተስፋና መልካም ምኞት ይገልፃል።

“በሥራ ጉዳይ የማያቸው የአገልግሎት አሰጣጦች፣ እንዲሁም መንግሥት ባስቀመጠው የለውጥ አቅጣጫ እየተሰሩ ያሉ የተለያዩ ፕሮጀክቶችን ስመለከት፣ ነገ ሰርቼ ነገሮችን ማሻሻል፣ የፕሮጀክቶቹም ተጠቃሚ መሆን እችላለሁ ብዬ ተስፋ አደርጋለሁ” የሚለው አበራ፣ አሁን እየታዩ ያሉት ችግሮች ጊዜያዊ ችግሮች እንደሆኑና እኛ ኢትዮጵያውያን የሚያጋጥሙንን መከራና ችግሮች ማለፍ የምንችል ማኅበረሰቦች እንደሆንን በማንሳት ነገ የተሻለ ተስፋ እንዳለ ዕምነት እንዳለው ያስረዳል።

“ያሳለፍነው ክረምት በጣም ከባድና ተንቀሳቅሶ ለመሥራት በጣም አስቸጋሪ የሆነ ጊዜ ነበር። መስከረም ደግሞ በራሱ ከወራቶች ኹሉ ከፍተኛ ወጪ የምታወጣበት ወር ነው” የሚለው ማስረሻ በበኩሉ፣ “ሥራዎች እንደማስባቸው ላይሳኩ ይችላሉ ወይንም ሰርቼ የማገኘው ገንዘብ የምፈልገውን ነገር አሁን ላይ ላይሸምትልኝ ይችላል። ነገር ግን፣ ነገ የተሻለ ሊሆን እንደሚችል አስባለሁ ለዚህም ደግሞ ተስፋ ባለመቁረጥ ከሕይወት ጋር እየታገልኩ ነው” ሲልም የኑሮ ውድነት እና የሥራ አለመሳካት እንደተግዳሮት ቢጋረጡበትም በቀጣዩ ዓመት የተሻለ ሥራ ለመጀመርና ሕይወቱን ለማሻሻል ዕቅድ እንዳለው ሐሳቡን ይገልፃል።

“አንድ ጥሩ ነገር ነው የምለው፣ በአሁኑ ሰዓት ሁሉም በሚያምንበት የዕምነት ተቋም ውስጥ መንፈሱን በማጠንከር ወደፈጣሪው በምልጃና በፀሎት እየቀረበ ነው። እኔም በራሴ እምነት ይሄን ነገር እያደረኩን ስለምገኝ፣ ነገ የተሻለ ኑሮና የተረጋጋ ሁኔታ እንደሚፈጠር ስለማስብ ባለኝ ተስፋ ደስተኛ ነኝ” የምትለው ወይንሸት፣ ባሳለፍነው አመት በነበረው አገራዊ አለመረጋጋትና የኮሮና ወረርሽኝ ምክንያት እምብዛም ያሰበቻቸውን ነገሮች እንዳላሳካች ትናገራለች።

ነገር ግን ትላለች ወይንሸት፣ “ነገር ግን እንደ እኔ ስኬት ብዬ የምለው ተስፋ አለመቁረጥና ነገ የተሻለ ነገር ይመጣል ብሎ በሙሉ ልብ ማመንን ነው” በማለት በቀጣይ ትላልቅ እቅዶች እንዳሏት ገልፃ፤ በያዘችው ዕምነት በመፅናትና አገሪቷን ሠላም እንዲያዲያደርግላት አምላኳን በመማፀን በቀጣዩ አመት ሐሳቦቿን ሁሉ ከግብ እንዲደርሱ የራሷን ጥረት ለማድረግ እንዳቀደች ተናግራለች።

አገራዊ የምልጃና የፀሎት መርሃ ግብሩ አገራዊ ለውጥን ለማምጣት ትልቅ ድርሻ እንዳለው የምትናገረው ወይንሸት፣ “እያንዳንዱ ሰው በየእምነቱ መፀለዩና ወደ ፈጣሪው መቅረቡ ነገን የተሻለና ብሩህ ተስፋን የሰነቀ ያደርገዋል ብዬ አስባሁ። ይህም ተጠናክሮ መቀጠል አለበት” ስትል ሐሳቧን አጋርታናለች።

መልካም ምኞት
እንደ አንድ ለአገሩም ሆነ ለወገኑ መልካም እንደሚመኝ ዜጋም ዓመቱ ለአገራችን አዲስ ተስፋን የሰነቀ የሠላም፣ የፍቅር እና የዕድገት እንዲሆን ሁላችንም እንመኛለን። እንኳን አደረሳችሁ! ዘመኑ የሠላም፣ የፍቅር፣ የደስታና የሐሴት ይሁንልህ/ሽ መባባሉ በራሱ አዲሱን ዓመት በአዲስ ተስፋ እንድንቀበለው የሚያስገድድ ልዩ ስሜትን ይፈጥራልና። አዲስ ማለዳም ያነጋገረቻቸውን ሰዎች መልካም ምኞት እና መልዕክታቸውን ያደርሱ ዘንድ ዕድሉን ሰጥታለች።

“የኔ ምኞት ለአገሬ ነው፤ አገር ሠላም እንዲሆን እፈልጋለሁ። አገር ሠላም ከሆነ ወጥተህ ገብተህ እንደፈለክ መሥራት ትችላለህ። ነገር ግን እንደዚህ ሞት በበዛበትና ሐዘን ባለበት ሁኔታ ምንም ነገር ማድረግ አይቻልም። አሁን እራሱ ከቤቴ ስወጣ ኹለት ሦስት ሰዎች በኮቪድ ምክንያት ሕይወታቸውን አጥተው ቀብሬያለሁ፡፡ ይሄ ደግሞ በጣም ስሜትን ይሰብራል። ታላላቅ ሰዎቻችንን በሽታው እየነጠቅን ነው። ወጣቶቻችን በጦርነቱ ምክንያት ሕይወታቸውን እያጡ ነው። ያ ያ ነገር ውስጤን ቢጎዳውም እንደ ዜጋ ለዚህች አገር የምመኘው እነዚህ ነገሮች ቆመውና ሠላም ወርዶ ኹሉም ማኅበረሰብ በየደረጃው በእኩል የሚጠቀምባት አገር እንድትሆን ምኞቴ ነው። ያም ይሆናል ብዬ ተስፋ አደርጋለሁ ሲል አበራ ነጋሽ መልካም ምኞቱን አስተላልፏል።

“እንደአገር በአሁኑ ሰዓት የተለያዩ ጫናዎች ውስጥ እንገኛለን። በዚህ በኩል የውስጥ ግጭት በሌላ በኩል ደግሞ በሕዳሴው ግድብ ዙሪያ የውጭ ጫናዎችና ግፊቶች እየበዙብን ነው። ነገር ግን በአሁኑ ሰዓት መንግስትና ሕዝባችን ያለውን አንድነት እና ጽኑ አቋም ስትመለከት፣ ኹሉንም ጫናዎች መቋቋምና አሸናፊዎች መሆን እንደምንችል ይሰማኛል። ለአገሬም የምመኘው ቀጣዩ አመት የሠላም፣ የፍቅርና የደስታ እንዲሆን ነው፡፡ የምንሰማቸው ክፉ ዜናዎች በሙሉ ተወግደው ዕድገታችን የሚፋጠንበት ዘመን ይሁንልን “ የሚለው ደግሞ ማስረሻ ነው።
ወይንሸት በበኩሏ እንዲህ ስትል የመልካም ምኞት መልዕክቷን ታስተላልፋለች፤ “ነገ የተሻለ ነገር ለማምጣት ዛሬ እራሳችንን በመጠበቅ በፀሎትና ለማኅበረሰብ በሚጠቅም መልካም ሥራ እራሳችንን ማሳደግ ይገባናል። ነገሮች ወደ ሠላማዊ የመረጋጋት መስመር ውስጥ እንዲገቡ የኹላችንም ኃላፊነት ነውና ነገ የተሻለ እንደሚሆን ተስፋ እያደረግን ዛሬ ያለንን ነገር በአግባቡ እንጠቀም። ሠላም፣ ፍቅርና ጤና ለአገራችን እና ለህዝቦቿ።”


ቅጽ 3 ቁጥር 149 መስከረም 1 2014

Comments: 0

Your email address will not be published. Required fields are marked with *

error: Content is protected !!