የእለት ዜና

አዲስ ዓመት እና የበዓል ገበያ

ዘመናት ዘመናትን እየወለዱ፣ ወራትና ቀናትን ቀንንና ወርን እየወለዱ አዲስ ዓመት ገብተናል። በኢትዮጵያ ዘመን አቆጣጠር የዘመን መለወጫ መስከረም አንድ ይከብራል። ይህ መስከረም አንድ የራሱ የሆነ መንፈሳዊ ሥያሜ ያለው ሲሆን፣ በዚህም መሠረት ዘመነ ማትዮስ፣ ዘመነ ማርቆስ፣ ዘመነ ሉቃስ እና ዘመነ ዮሐንስ ተብለው አመታት ይገለጻሉ። አሁን የሚከበረው 2014 አዲስ ዓመት ዘመነ ማርቆስ ይባላል። ኢትዮጵያውያን በዓል ሲመጣ የተለያዩ ለበዓሉ የሚያስፈልጉ ግብዓቶችን ለመገበያየት ይጣደፋሉ። ገበያውም የበዓል ድባብ ይኖረዋል።

በዓልን ያደምቃሉ ተብለው ከሚሸመቱት መካከል በሬ፣ በግ፣ ፍየል፣ ዶሮ፣ እንቁላል እና ቅቤ ይጠቀሳሉ። አዲስ ማለዳ በሾላ ገበያ ባሳለፍነው ዕሮብ ተገኝታ ባደረገችው ምልከታ ገበያው ገና ከአሁኑ ደርቷል። ከላይ የተጠቀሱትን ምርቶች ለመግዛት የመጣ ብዙ ሰው ባይኖርም፣ ቅድሚያ መገዛት ያለባቸውን የቤት ዕቃዎች ለመሸመት ሽር ጉድ የሚሉ በርካታ ሰዎች ነበሩ።

አበበች ደስታ ዘይት፣ ቡና እና በርካታ የቤት አስቤዛ ለመግዛት የመጡ በ30ዎቹ ዕድሜ ላይ የሚገኙ ናቸው። አዲስ ማለዳም ገበያው ላይ ያለው የኑሮ ውድነት እየተባባሰ በመጣበት ወቅት በዓል ሲደረብበት ምን አይነት ድባብ እንደሚኖረው ሐሳባቸውን ጠይቃለች።
‹‹የኑሮ ውድነት እና በዓል መደራረቡ ‹በቁስል ላይ እንጨት ሰደዱበት› ነው የሆነብን›› ሲሉ አበበች ይገልጻሉ። ከቤት ይዘው የወጡት የገንዘብ መጠን ያሰቡትን ሊያስገዛቸው ባለመቻሉ ከሚፈልጉት ኪሎ በታች በማድረግ እና አንዳንዶቹን በመተው መሸመታቸውንም ተናግረዋል።

‹‹ዘይት 650 ብር፣ ቡና 250፣ ዱቄት 60 ብር፣ ቅቤ 450 ብር በኪሎ ገዝቼ በተረፈኝ ገንዘብ አንዳንድ የቤት አስቤዛ ገዝቻለሁ›› ብለዋል።

ነጋዴዎች አብዛኛውን ጊዜ በዓል ሲደርስ ይጨምራሉ የሚሉት አበበች፣ አሁን ደግሞ በዓልም ሳይደርስ ኑሮ ከብዷል። ስለዚህ ምን ማድረግ እንዳለብን በማናውቅበት ኹኔታ ኑሮን እየገፋን፣ ባለችን ገንዘብ ደግሞ በዓልን ለማክበር አስበናል ብለዋል።
በኢትዮጵያ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ እየጨመረ የሚገኘው የሸቀጦች ዋጋ፣ የኑሮ ውድነት እንዲባባስ ምክንያት እየሆነ ይገኛል።

ያም ሆኖ ግን፣ የምርት ፍላጎት እና አቅርቦት አለመጣጣም፣ የሥራ አጥ ዜጎች መበራከት፣ የሕዝብ ቁጥር ዕድገት መጨመር እና የማምረቻ ግብዓቶች የዋጋ ንረት ለኑሮ ውድነት መባባሱ ምክንያት መሆናቸውን ምሁራን ያነሳሉ።
ዘይት፣ እህል፣ ጥራጥሬ፣ የታሸጉ እንደ ፓስታ ያሉና ሌሎችም መሠረታዊ ምግቦች ዋጋ መናር ከጀመረም ወራት ተቆጥረዋል። የዳቦ ዋጋን ጨምሮ እየናረ የሄደው የምግብ ዋጋ ሸማቹንም ሆድ ያስባሰ ሆኗል። ችግሩን ለመቅረፍ የተለያዩ ጥረቶች ተደርገዋል ቢባልም፣ አሁንም ችግሩ ሥር እንደሠደደ ይታያል።

የንግድና ኢንዱስትሪ ሚኒስቴርም ሆኑ የአዲስ አበባ ንግድ ቢሮ በንግዱ ላይ አሻጥር የሠሩ፣ ምርት የደበቁና ዋጋ ያናሩ እየቀጣሁ ነው ቢልም፣ ውጤቱ ገና አልታየም። በየጊዜው ኹሉም የኃላፊነቱን ይወጣ የሚል መልዕክት ከመንግሥት ባለሥልጣናት ቢሰማም ለሸማቹ የወረደ ነገር የለም።

የዋጋ ንረቱን ለማረጋጋት በተቋቋመው ግብረኃይል ውስጥ የሚገኘው የፌደራል ሸማቾች ባለሥልጣን፣ መጪው በዓልን መሠረት በማድረግ ሥራ እየሠራ እንደሚገኝ ለአዲስ ማለዳ ተናግሯል።
የአዲስ አበባ ንግድ ቢሮ በበኩሉ የበዓል ሸመታ በተመለከተ የሚደረጉ ያለአግባብ ጭማሪዎችን ለመቆጣጠር ዝግጅት እያደረገ መሆኑን በተቋሙ የሚገኙ ምንጮች ጠቅሰዋል።

ለኢትዮጵያውያን የበዓል አንድምታው ብዙ ነው። ዕለቱ ቤተሰብና ዘመድ አዝማድ ተሰባስቦ እየበላና እየጠጣ ባህሉን እና የእርስ በርስ ግንኙነቱን የሚያጠነክርበት ነው። ኢትዮጵያዊ የመረዳዳት ባህላችንን መሠረት በማድረግ ያለው ለሌለው የሚያካፍልበት እና በዓልን በአብሮነት የሚያከብርበት የራሱ መገለጫዎች አሉት።

በዓል ሲመጣ በአዘቦት ቀን የማንመገባቸው ምግቦች እንደ ዶሮ እና እንቁላል ያሉት የቀኑ ማድመቂያዎች ናቸው። ታዲያ አሁን ባለው የዶሮ እና እንቁላል ዋጋ መናር ምን ያህሉ ሰው እንደ ልቡ ገዝቶ ያከብራል የሚለው የኹሉም ሰው ጥያቄ ነው።
ሾላ ገበያ ሲሸጥ የነበረውም ቢሆን አንድ ዶሮ ከ300 ብር እስከ 800 ብር ድረስ ነበር። እንቁላል ከቦታ ቦታ ከ7ብር ከ50 እስከ 10 ብር ድረስ ሲሸጥ እንደነበር አዲስ ማለዳ ታዝባለች።
በተለይ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ የእንቁላል ዋጋ በፍጥነት መጨመሩ ያስደነገጣቸው የእንቁላል ነጋዴዎች ጉዳዩን እንዲህ ይገልጹታል።

ደበበ መኮንን በግቢው ውስጥ የሚያረባቸውን ዶሮዎች በመጠቀም እንቁላል የሚያከፋፍል 40ዎቹ ዕድሜ ላይ የሚገኑ ግለሰብ ሲሆኑ። “የዶሮዎቹ መኖ እህል መሆኑ ይታወቃል። እንደ በቆሎ እና ስንዴ ያሉ የእህል አይነቶች ደግሞ ዋጋቸው በፊት ከነበረው በእጥፍ ጨምሯል” ይላሉ። የዶሮዎቹ መኖ መጨመር ለእንቁላል ዋጋ መናር እንደምክንያት ያነሱት ደበበ በቀን ከ100 እስከ 300 የሚደርስ እንቁላል ለተለያዩ ንግድ ሱቆች እንደሚያከፋፍሉ ይጠቅሳሉ።

አንዱን እንቁላል በ7 ብር እንደሚያከፋፍሉ የጠቆሙት ደበበ፣ ይህ ደንበኞቹን ላለማጣት ያደረጉት አነስተኛ የዋጋ ጭማሪ መሆኑን ይገልጻሉ። “ከዚህ በበለጠ ዋጋ የምንሸጥ ከሆነ ገዢ አናገኝም”ይላሉ።
በዓል ሲመጣ ደግሞ ከፍተኛ ፍላጎት ስለሚኖር ለበዓል በብዛት ለማዳረስ እየሰሩ መሆኑን ገልጸዋል።

በሾላ ገበያ ከተመለከትናቸው የበዓል ግብይቶች መካከል ቅቤ እና ቡና ከፍተኛ የዋጋ ጭማሪ የታየባቸው ናቸው። በተለይ ቡና 150 ብር የነበረው በአሁኑ ሰዓት ከ250 እስከ 300 ብር እየተሸጠ ይገኛል።
የዓውድ ዓመት ሽታ አድማቂ ከሆኑት ውስጥ ቅቤ ተጠቃሽ ነው። ከባለፈው የፋሲካ በዓል በአንጻራዊነት የቅቤ ዋጋ መቀነስ ታይቶበታል።

አበራሽ ዘለቀ ለ7 ዓመት በቅቤ ንግድ ላይ ተሰማርተው የቆዩ ነጋዴ ናቸው። የቅቤ ዋጋ ባለፈው የፋሲካ በአል 600ብር ይሸጥ ከነበረው ዋጋ በተወሰነ የቀነሰ ሲሆን፣ መካከለኛ ቅቤ በ 480ብር፣ ለጋ 530ብር በኪሎ እንደሚሸጡ ነግረውናል።
አበራሽ ቅቤዎቹ ከተለያዩ የአማራ ክልል ከተሞች የሚመጡ በመሆናቸው አቅራቢዎቹ በትራንስፖርት ችግር ምክንያት እያዘገዩ እንደሚያመጡላቸው ይናገራሉ። አበራሽ ቅቤን ከገበያ ውጭ ወደ ተለያዩ ሠፈሮች፣ አልፎ አልፎም ወደ ተለያዩ ተቋማት እየሄዱ የሚሸጡ አቅራቢዎች ከ300 እስከ 350 ብር እንደሚሸጡ አስረድተውናል።

ይህ ደግሞ ሻጮች ጋር የቅቤ ምርት ተከማችቶ እንዲቆይ ያደርጋል ብለዋል። ምናልባት የዛ ተጽዕኖ ዋጋውን በትንሹ እንዲቀነስ አድርጎታል ብለዋል።
ሾላ ገበያ ከተለያየ አካባቢ ተሸምተው የሚመጡ በጎች በአማካይ እስከ ስድስት ሺሕ ብር እየተሸጡ ይገኛሉ። በገበያው ዝቅተኛው የበግ ዋጋ 3,000 ብር ሲሆን፣ ከፍተኛ የሚባለው እስከ 9,500 ብር እየተሸጠ ይገኛል።
በአዲስ አበባ ነዋሪ የሆኑት የ4 ቤተሰብ አስተዳዳሪ ሙሉ ደሳለኝ ኹሌም የሸቀጦች ዋጋ መጨመርን እንደለመዱት ይናገራሉ። በዓል ሲደርስ ደግሞ ይበልጥ እንደሚጨምር በመረዳት አንዳንዶቹን ቀድመው ለመግዛት አቅደው ነበር።
ሙሉ የወር ገቢያቸው 2300 ብር ሲሆን፣ ባለቤታቸው ከሞቱ በኋላ የሳቸውን ጡረታ 1350 ብር እንደተጨማሪ የገቢ ምንጭ ይጠቀሙበታል።

ሙሉ 3 ልጆች እና አንድ አካል ጉዳተኛ እህታቸውን የጽዳት ሥራ በመሥራት የሚያሥተዳደሩ ሲሆን፣ ኑሮ መወደዱ ቀስ በቀስ እየባሰበት ነው ይላሉ።
ከኹሉም ምርቶች በጣም ያስደነገጠኝ የዘይት ዋጋ ነው የሚሉት ሙሉ፣ ዘይት 650 ብር እገዛለሁ ብዬ አስቤም አላውቅም ይላሉ።

በርግጥ እስከ ቅርብ ጊዜ ድረስ 550 ብር ድረስ ገዝቼ ተጠቅሜያለሁ። አሁን ግን በአንድ ጊዜ 100 ብር ጨምሮ ሳገኘው በጣም ነው የደነገጥኩት ይላሉ።
“ዘይት የትኛውም የምግብ ዓይነት ውስጥ የሚጨመር ነው። ያለ ዘይት የሚሠራ ምንም ምግብ የለም። ስለዚህ ሳልወድ በግድ ገዝቻለሁ። በተለይ በዓል ሲመጣ የተለያየ ዓይነት ምግብ በዘይት እና በቅቤ ነው የሚሠሩት” ሲሉ ይገልጻሉ።
የዋጋ ንረቱን ያረጋጋል ተብሎ ንግድ እና ኢንዱስትሪ፣ሸማቾች ባለሥልጣንና የሚመለከታቸው አካላት በጋራ ያዋቀሩት ግብረ ኃይል የገበያውን መረጋጋት ለመፍጠር ይሠራል ተብሏል።

ለምግብ ዘይት ያለው የሕብረተሰቡ ፍላጎት እና የሚመረተው ምርት አለመጣጣሙን በንግድ እና ኢንዱስትሪ ሚኒስቴር የንግድ ዕቃዎች ዋጋ ጥናት ክትትልና ቁጥጥር ዳይሬክተር ካሳሁን ሙላት አንስተዋል።
የባለፈው አፈጻጻምን ያነሱት ካሳሁን 50በመቶ የሚሆን ፍላጎትን የሚያሟላ አቅርቦት መኖሩን ነው የገለጹት።

በቂ የሆነ የውጭ ምንዛሬ ባለመኖሩ የአቅርቦት መጠን መቀነሱን ያነሱት ካሳሁን፣ ኮቪድ-19 ወረርሸኝ ከተከሰተ በኋላ የመጣው የፍራንኮቫሉታ አሠራር በመቅረቱ የዘይት ዋጋ መናሩን አንስተዋል።
የፍራንኮቫሉታ አሠራር ከሰኔ መጨረሻ ጀምሮ እስከ ታኅሳስ 2013 ድረስ 16 ሚሊዮን ሊትር ከቀረጥ ነጻ ሆኖ ገብቶ ነበር።

በዚህ ጊዜ ኹሉም ሸማች እስከ 300 ብር ድረስ ይገበያይ ነበር። በፍራንኮቫሉታ የሚጠቀሙ ነጋዴዎች በጥቁር ገበያው ላይ ያለውን የዶላር ምንዛሬ ያለአግባብ በማባከናቸው ምክንያት ይህ አሠራር እንዲቀር ተደርጓል። በዚህ ጊዜ ከውጭ የሚገባው የዘይት መጠን በመቀነሱ ከጊዜ ወደ ጊዜ እየጨመረ አሁን ከ650 እስከ 700 ብር እየተሸጠ ይገኛል ብለዋል።

በዓል ላይ የሚኖረውን የዘይት ፍላጎት ታሳቢ በማድረግ ዘይት፣፣ስንዴና ስኳር መንግሥት ካለው ተቀማጭ ዶላር በመጠቀም ለማስገባት ታቅዷል።
አምራቾች የማምረት አቅማቸውን እንዲጨምሩ እየተደረገ መሆኑን ካሳሁን አንስተዋል።

አዲስ ዓመት ሲታሰብ አብዛኛውን ጊዜ የምናስተውለው ሰዎች ከመብላትና መጠጣት ባሻገር ያማረ ቤት መኖርን ማሰባቸው ነው። ቤትን ያስውባሉ የሚባሉ እንደ ምንጣፍ፣ ሶፋ፣ ቴሌቪዥን፣ መጋረጃ፣ የመመገቢያ ዕቃዎችና ጠረጴዛ ይገዛሉ።
በተለይ በአዲስ ዓመት ቤት ውስጥ አዲስ ነገር መግዛት ቀጣይ ዓመት አዲስ ተስፋ ይዞ ይመጣል ብለው የሚያስቡ በርካቶች ናቸው።

ከእነዚህ ውስጥ የሶፋ ግብይት ላይ ያገኘናቸው ተስፋዬ አበራ ናቸው። ከኦንላይን ገበያ እስከ እንጨት ቤቶች ድረስ የተለያዩ የዋጋ ዳሰሳዎችን ካደረጉ በኋላ ኮተቤ የሚገኝ እንጨት ቤት 40ሺ ብር የሚያወጣ ሶፋ መግዛታቸውን ይገልጻሉ።
“አዲስ ዓመት አዲስ ዕቃ መግዛት ያስደስተኛል። አሁን ቤተሰብ መሥርቼ አዲስ ዓመትን ሳከብር የመጀመሪያዬ ቢሆንም፣ እስከዛሬ ድረስ በአዲስ ዓመት አንድ ነገር ሳልገዛ አላልፍም ነበር” ሲሉ ትውስታቸውን አጋርተውናል።
በዚህ ዓመት ደግሞ ቤተሰቦቻቸውን ለማስደሰት የቤት ዕቃ ለማሟላት ዕቅድ ይዘው ነበር። ነገር ግን የገበያው ኹኔታ ያሰቡትን ያህል ለመግዛት እንዳላስቻላቸው ይናገራሉ።

ቴሌቪዥን ለመግዛት ከ15ሺሕ ብር እስከ 80 ሺሕ ብር መጠየቁን ነግሮናል። በተለያየ ብራንድ እና ኢንች መሠረት አድርጎ የተጠቀሰው ዋጋ ተስፋዬ ላለው የገቢ መጠን ከባድ እንደሆነበት ገልጿል።
ዘይት፣ ዶሮ፣ ሥጋና እንቁላል ሁሌም ለበዓል ከምንጠቀማቸው ዋነኞቹ የምግብ ዓይነቶች ናቸው የሚሉት ተስፋዬ፣ የቤት ዕቃ ለማሟላት ያሰብኩትን የተውኩት በዓል እየደረሰ በመምጣቱ ነው ይላሉ።
“አብዛኛውን ጊዜ ለበዓል ቅናሽ ይኖራል እየተባለ ቢገለጽም ለኔ ግን መቀነሱ አልታየኝም”፤ ስለዚህ ከበአል በኋላ ለመግዛት አቅጃለው ብለዋል።


ቅጽ 3 ቁጥር 149 መስከረም 1 2014

Comments: 0

Your email address will not be published. Required fields are marked with *

error: Content is protected !!