የእለት ዜና

የዕንቁጣጣሽ በዓል ሥዕል እና ልጅነት

Views: 96

የልጅነት ጊዜ ውብና በርካታ ትዝታወች የሞላበት ነው። በአንድ አካባቢ የሚኖሩ አንዳንዴም ከሌላ አካባቢ የሚመጡ ሕፃናት በጋራ እየተጫወቱ ውብ እና የማይረሳ የልጅነት ጊዜን ያሳልፉሉ። እንዳንድ ሰዎች ስለ ልጅነት ያሳለፉት ጊዜአቸውን ሲያወሩ፣ “ምነው ተመልሶ ቢመጣ፤ ልጅነትማ ገነት ነበር ምንም እንከን የሌለበት” የሚሉ ብዙ ናቸው።

አፈር ፈጭቶ፣ ጭቃ አቡክቶ፣ በጠጠር ተወራውሮ፣ አኩኩሉ (ድብብቆሽ)፣ ሩጫ፣ አባሮሽ፣ እንቆቅልሽ ተጠያይቆ እና ሌሎች የማይረሱ የልጅነት ጨዋታዎችን ተጫውቶ ማደግ የተለመደ ነው። ቤት ውስጥ አንዳንድ ጊዜ ልጆች ሲያስቸግሩ “ውጡና ተጫወቱ” ብለው ታላላቆች የራሳቸውን ሥራ ይሠራሉ፤ ለማውራት ፈልገውም ከሆነ ወሬያቸው ይቀጥላሉ።

ከልጅነት ውብ ገጽታዎች መካከል የበዓላት ሰሞን ትውስታዎች እንደ ጥሩ ትዝታ ይጠቀሳሉ። በዓላት ለሕፃናት እና ለታዳጊዎች ከአዋቂ በተለየ ልዩ ቦታ ይሰጣሉ። ብዙ የኢትዮጵያ በዓላትም ሕፃናት በዋናነት የሚሳተፉባቸው ናቸው። አዲስ ማለዳም የ2014 አዲስ ዓመት ዘመን መለወጫ በዓልን አስመልክቶ ሕፃናት ስለዕንቁጣጣሽ ሥዕል ያላቸውን ትኩረት ለመታዘብ ወደተለያዩ ቦታዎች ተጉዛ ከሕፃናት ጋር ቆይታ አድርጋለች።

ከአዲስ ማለዳ ጋር ቆይታ ያደረገው እንግዳችን ዳዊት ግደይ 14 ዓመቱ ነው። የአዲስ አበባ ከተማ ነዋሪ ሲሆን፣ የአምስተኛ ክፍል ተማሪ ነው። ከሰፈር ልጆች ጋር ቅዳሜ እና ዕሁድ እንዲሁም ከትምህርት ቤት መልስ መጫወት እና ማጥናት እንደሚወድ ይናገራል። አብደላ እና እዮብ እኩያ ጓደኞቹ ናቸው። በአካባቢያቸው ወደሚገኘው ትልቅ ሜዳ እየሄዱ ኹሌም ኳስ ይጫወታሉ። ዳዊት በሰባት አመቱ ለአዲስ ዓመት የወረቀት ሥዕል እየሣለ ለቤተሰቦቹ እና ጎረቤት መሥጠት መጀመሩን ያነሳል። ለበዓሉ ወረቀት እና ቀለሞች ቤተሰቦቹን አስገዝቶ ሥዕል መሣል እንደሚጀምር ይናገራል።

አዲስ ዓመት በዓልን ከሌሎቹ በዓሎች በተለየ መልኩ እንደሚወደው ይገልጻል። እንደ ምክንያት የሚያነሳው ለበዓሉ ከጓደኞቹ ጋር የሚያሳልፈውን ጊዜ ነው። በበዓሉ ሥዕል አዙሮ ከአምስት ብር እስከ አንድ መቶ ብር ድረስ ማግኘቱን ይጠቁማል። ዳዊት ከዚህ በፊት ለአዲስ ዘመን በዓል የእንኳን አደረሳችሁ ሥዕል ለማድረስ አንድ ቤተሰብ ጋር ሔዶ ሥዕሉን ሲሰጣቸው ዳቦ የሰጡትን ገጠመኝ እንደማይረሳው ይናገራል።

ዳግም ታደሰ ደግሞ የ12 ዓመት ታዳጊ ሲሆን፣ የአራተኛ ክፍል ተማሪ ነው። ለአዲስ ዓመት በዓል ሥዕል በየቤቱ እየሄደ ለመስጠት ዝግጅቱን የሚጀምረው ከበዓሉ ከአንድ ሳምንት እና ከዛ ቀደም ብሎ እንደሆነ ይናገራል። በአካባቢው ላይ ያሉ ሥዕል መሳል የሚችሉ ታዳጊዎች እና ወጣቶች ለራሳቸው እና ለሌሎችም ሥዕሎችን ያዘጋጃሉ። እሱ ሥዕል መሣል ስለማይችል በአካባቢው መሣል ከሚችሉ ልጆች እንደሚገዛ ይናገራል። “ሥዕሉን ገዝቼ እና በካርቦን ኮፒ አደርግና ለበዓሉ ማዘጋጀት እጀምራለሁ” ይላል። ኮፒ ያደረገውን ሥዕል ለማሳመር በአቅራቢያው የሚገኙ የተለያዩ የሚበጠበጡ ቀለሞችን ይገዛል፤ ካልተሳካለት ግን እስከ መርካቶ ድረስ በመሄድ ለበዓሉ እንደሚዘጋጅ ያስረዳል።

ዳንኤል የሚባለው ሌላው ታዳጊ በአብዛኛው የሚስለው የመላዕክት ሥዕሎችን እንዲሁም አበባና መስቀል እንደነበረ ይጠቁማል። በአሁኑ ሰዓት ግን ለበዓል የተለያዩ ሥዕሎች መሣል እንደጀመረ ይጠቅሳል። ለምሳሌ አምና ለአዲስ ዓመት በዓል ስጦታ ለመስጠት ከሰፈር ልጆች የገዛው ነበር። እንደ ዳንኤል ገለጻ፣ “ከምንም በላይ ግን ለበዓሉ ቀን በጠዋት ተነስቼ ለአዲስ አመት በዓል የሚገዛልኝን አዲስ ልብስ መልበስ ያጓጓኛል” ይላል።

ለበዓሉ የሳሏቸውን የወረቀት ሥዕሎች ከጓደኖቹ ጋር በመሆን ለቤተሰብ፣ ለጎረቤቶች፣ ለወዳጅ ዘመድ ለመስጠት በጠዋት ከእንቅልፋቸው እንደሚነሱ ይገልጻል። የበዓል ያዘጋጁትን ሥዕል ለአካባቢያቸው ሰዎች አንዳንዴም እርቀው በመሄድ ለሌሎች በመሥጠት ገንዘብ እንደሚያገኙም ያነሳል። በአገኘነው ገንዘብ ለበዓል ቀን ከረሜላ፣ ብስኩት እና ሌሎችም ጣፋጭ ነገሮችን እንገዛበታለን የሚለው ዳንኤል፣ አንዳንድ ጓደኞቹም የበዓል ሥዕል ስጦታ ሰጥተው የተሰጣቸውን ገንዘብ ለቤተሰብ ያስረክባሉ ብሏል። “መስከረም አንድ በጠዋት ቶሎ እነሳለሁ፤ ምክንያቱም ከዚህ በፊት ብዙ ብር የሰጡኝ ጎረቤታችን ጋር ጓደኞቼ ቀድመውኝ እንዳሄዱብኝ ነው” ይላል።

ወለል ላይ ቁጭ ብሎ በልሙጥ ወረቀት ላይ አበባ ለመሳል ሲታገል ያገኘነው የአምስት አመቱ ታዳጊ የአብ (ባባ) ይባላል። የለበሰውን ቁምጣ በትናንሽ እጆቹ ቀለም ለቅልቆታል። እናቱ ምግብ እንዲበላ ለማስነሳት ብትሞክርም፣ “ቆይ አንቴ” በማለት በኮልታፋ አንደበቱ መሞነጫጨሩን ይቀጥላል። ሐሳቡ የሚስለው ሥዕል ላይ ነው፤ የእናቱን ድምጽ አይሰማም። ትኩረቱ የጀመረውን ሥዕል ጨርሶ ማሳየት ላይ ነበር።

ከታላቅ እህቱ አርሴማ ጋር አብረው እየተጋገዙ ሥዕል እንደሚሰሉ፣ ጨዋታዎችን በጋራ ከትምህርት ቤት መልስ እንደሚጫወቱ ይናገራል። “ደሞ ለበዓል አመጪም” ብሎ ወሬውን ይጀምራል። እህቱ ሥዕል መሳል እና ግጥም መፃፍ ትወዳለች። እሱም ሁሌ እሷ የምትስላቸው ሥዕሎችን እያየ ይለማመዳል።በዓል ከመድረሱ ሁለት ሳምንት ቀደም ብሎ ከአርሴማ ጋር መሳል እንደሚጀምሩ ይናገራል። “ለበዓል ብዙ ጊዜ መሳል ምወደው መስቀል እና አበባ ነው” ይላል።

ሌላው አዲስ ማለዳ ያነጋገረችው ዮሴፍ ተካልኝ ይባላል። እድሜው አራት አመት ተኩል ነው። ትምህርት ባይጀምርም ለጠየቀው ሰው በሙሉ “አንደኛ ክፍል እኮ ነኝ” ይላል። ዮሴፍ ትምህርት ቤት ቀጣይ ዓመት ትገባለህ በመባሉ ብቻ ተማሪ ነኝ ብሎ ያስባል። ቀኑን ሙሉ ከእናቱ ጋር ሲጫወት አንዳንዴም ሲያለቅስ ይውላል። ትምህርት ቤት ለመሄድ ያለው ፍቅር እጅግ ከፍተኛ ነው።

በግቢያቸው ውስጥ ያሉት ሕፃናት ተማሪዎች ናቸው። በዚህም ምክንያት ከእናቱ ጋር ይውላል። ከሰሞኑ ዮሴፍ ትንሽ ለጨዋታ ጊዜ አጥቷል። በኢትዮጵያ የሚከበረውን የዘመን መለወጫ አዲስ አመትን አሰመልክቶ ብዙ ጊዜውን ወረቀት ላይ በሞነጫጨር ያሳልፋል። በዘንድሮ በዓል የተለያዩ ሥዕሎችን ስሎ ለቤተሰቡ ለመስጠት እንደሚፈልግ ለአዲስ ማለዳ ተናግሯል። “እኔ ለማዬ ወፍ ነው እምሰታት” አዲስ ማለዳም ለምን ብላ ጠየቀችው? “ወፍ በጣም ነው ምወድደው።” እሱ ለእናቱ በዘንድሮ አመት ለመጀመሪያ ጊዜ የሚወደውን እንደሚሰጣት ይናገራል።አዲስ ዓመትና ሥዕል በብዙ መንገድ ይገናኛሉ ያሉን ሰዓሊና ካርቶኒስት ሄኖክ ደምሴ ናቸው። ጨለማው እና አስፈሪው የክረምት ወቅት አልፎ ብርሃን የሚሆንበት ምድር በተለያዩ ቀለማት ባሸበረቁ አበቦች የምትዋጥበት በመሆኑ እንደሆነ ከአዲስ ማለዳ ጋር በነበራቸው ቆይታ ገልጸዋል። የአዲስ ዓመት መዳረሻ የጳጉሜን ቀናት በተለየ ሁኔታ ሥዕል ለመሣል እንደሚጠቀሙበት የሚናገሩት ሄኖክ፣ “የምስላቸው ሥዕሎች የራሴን ሐሳብ የሚገልጹልኝ ናቸው” ይላሉ።

ሥዕሎቹን ለመሸጥና ለማስቀመጥ እንደሚስሉ ይናገራሉ። አሁን ለሚሠሩት የሥዕል ሥራ እንደ አንድ መነሻ ምክንያት የሆናቸው በልጅነት ጊዜ አዲስ ዓመት ሲመጣ ለቤተሰብ ፣ጎረቤቶች እና ለወዳጅ ዘመድ ለስጦታ ይዘው ይሄዱ የነበረው ሥዕል እንደሆነም ይጠቅሳሉ። በጊዜው ጎረቤቱ ሥዕል የሚስልላቸው የነበረ ሲሆን፣ እያደር ፍላጎት ስለፈጠረባቸው መሣሉን በድፍረት እንደጀመሩት ያስታውሳሉ። ሥዕሉን ለበዓል ቀን በየቤቱ ማዞር ሲያቆሙ ለሌሎች ልጆች ይሥሉ ነበር። ለልጆቹ በሚሥሉ ወቅት ክህሎት እንዳላቸው ማመናቸውን ጠቅሰዋል።

ለአዲስ ዓመት በዓል ወቅት የመላዕክት ሥዕል ፣ አበባ፣ የተለያዩ ታዋቂ ሰዎች እና በዓሉ የዋለበትን ቀን እና ዓመተ ምህረት ይሳላሉ ብለዋል። አሁን አሁን የአዲስ አመት የበዓል ሥዕሎች ላይ የመላዕክት ሥዕል እየቀረ እንደሆነም ጠቅሰዋል። ሄኖክ በልጅነት ጊዜ የበዓል ሥዕሎችን በየቤቱ እየሄዱ ሲሰጡ ከገጠማቸውና ከማይረሱት ገጠመኝ መካከል ውኃ የሚደፉባቸውንና ውሻ የሚለቁባቸውን ሰዎች ነው። ብዙ ሕጻናት ለበዓሉ ሥዕል ይዘው በየቦታው ስለሚሄዱ፣ ሰዎቹ በር የሚያንኳኩ ሕፃናት ይደጋገሙባቸውና ይሰለቻሉ ሲሉ አስተያየታቸውን ይቋጫል።
በአዲስ ዓመት በዓል ቀን ብዙ ሰዎች በርካታ ትዝታዎች እንዳላቸው ይናገራሉ። ለበዓሉ ግብዓት የሚሆን ዕቃ ከመግዛት ጀምሮ፣ ቤተሰብን አዳዲስ ልብሶችን ማስገዛት እና በጠዋት ተነስቶ ሲደከምበት የከረመውን ሥዕል ተቦዳድኖ እየተሸቀዳደሙ ለማደል መሮጥ ዋናዋናዎቹ ናቸው። በር የማይከፍቱ እንዲሁም ውሻ የሚለቁ የመኖራቸውን ያህል በጉጉት የሚጠብቁ ቤተሰቦችም በየሠፈሩ አሉ። ከስጦታው የተገኘውን ከሰበሰቡ በኋላ ጣፋጭ በመብላት ቤተሰብ ለፍቶ ያዘጋጀውን መመገብ የሚያቅትበት ጊዜም ይፈጠራል።


ቅጽ 3 ቁጥር 149 መስከረም 1 2014

Comments: 0

Your email address will not be published. Required fields are marked with *

This site is protected by wp-copyrightpro.com