የእለት ዜና

በምስራቅ አፍሪካ አገራት ድርቅ ሊከሰት እንደሚችል ተተነበየ

ታንዛንያ፣ ቡሩንዲ፣ ሩዋንዳ፣ ኬንያ፣ ሶማልያ፣ ኢትዮጵያና ኤርትራ ከፍተኛ የሆነ የሙቀት ወቅት እንደሚያጋጥማቸው የምስራቅ አፍሪካ የልማት በይነ መንግስታት ድርጅት (ኢጋድ) ባወጣው ሪፖርት ገልጿል። ድርጅቱ አክሎም አሁን ኢትዮጵያ ያለችበት ወቅትም ለምርት እጅግ ወሳኝ መሆኑን በሪፖርቱ አመላክቷል።
አገራቱ የሚያጋጥማቸው የሙቀት መጠን ከዚህ በፊት ከነበረው ከፍተኛ መሆኑና በአንጻሩ የዝናብ መጠኑ ማነሱ የተገለጸ ሲሆን፣ ይህ ሁኔታ ከሚያጋጥማቸው አካባዎች መካከል ሰሜን ምዕራብ ሱማሊያ፣ ቡሩንዲ፣ ሩዋንዳ፣ የቀይ ባህር ሰሜናዊ ጫፍና በኢትዮጵያ ደግሞ የደቡብ ምስራቅ አካባቢዎች መሆናቸው ተነግሯል።
በማዕከላዊና በደቡብ የምስራቅ አፍሪካ አካባቢዎች የታየው የዝናብ ዕጥረት ደግሞ እስከ ታኅሳስ ድረስ እንደሚዘልቅ የተተነበየ ሲሆን፣ ሪፖርቱ የድርቅ ችግር የሚያሰጋቸው አካባቢዎች መኖራቸውን ጠቁሞ ይህም በአካባቢዎቹ እየዘነበ ባለው አነስተኛ የዝናብ መጠን መሆኑን አስታውቋል።
በመጨረሻም፣ ድርጅቱ በከፊል አነስተኛና እጅግ አነስተኛ የዝናብ መጠን በሚያገኙ አካባቢዎች ከፍተኛ መጠነ ሠፊ የሰብዓዊ ድጋፍ ሊደረግ እንደሚገባ በመግለጽ፣ በቀጠናው ሊከሰት በሚችለው ከፍተኛ ሙቀትና ድርቅ ከ30 ሚሊዮን በላይ ሰዎች ለርሃብ እንደሚጋለጡ በሪፖርቱ አመልክቷል።


ቅጽ 3 ቁጥር 149 መስከረም 1 2014

Comments: 0

Your email address will not be published. Required fields are marked with *

error: Content is protected !!